አዳምና ሔዋን ትዕዛዝ አፍርሰው ሕግ ጥሰው ከጸጋ ልብሳቸው ከተራቆቱ በኋላ ስቃይና ፍዳ ወደበዛባት ምድር እንዲወርዱ ተፈርዶባቸው ፈተና ወደበዛባት ዓለም ቢመጡም በልቡናቸው የሚቀጣጠለው የእግዚአብሔር ፍቅርና የገነት ሰላማዊ ኑሮ ህሊናቸውን ስለነሣ ው "አጥፍተናል በድለናል ይቅር በለን ማረን ራራልን " እያሉ በትሕትና ሆነው በጸሎት ቢተጉም የበጎ ሥራ ጠላት የሆነ ዲያብሎስ በእባብ ተሰውሮ እንዳሳታቸው የብርሃን መልአክ መስሎ "ቅዱስ ገብርኤል ነኝ እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ሰምቷል " በማለት ጸሎታቸውን እንዲያቋርጡ አድርጓቸዋል፡፡ አዳም የብርሃን መልአክ መስሎት ሲከተለው መልኩን ቀይሮ ከመንገድ ላይ በድንጋይ ፈንክቶ ያፈሰሰውን ደም ወደ እግዚአብሔር ቢረጭም የእርሱ ደም ለዓለም ሁሉ መድኃኒት ስለማይሆን ለሰው ልዩ ፍቅር ያለው አምላክ ከ5500 ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በመስቀል ተሰቅዬ፣ ደሜን አፍስሼ፣ ሥጋዬን ቆርሼ፣ ሞቼ፣ ተነሥቼ አድንሃለሁ የሚለውን የተስፋ ቃል ስለሰጠው ይህን ተስፋ በትዕግሥት ሲጠብቅ ኖሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሥጋን ለብሶ መድኃኒት መስቀል ቀራንዮ በተተከለ ጊዜ ተፈጽሞለታል፡፡ለመግቢያነት ይህን ያህል ካልን ወደ ዋናው ርእሳችን እንግባ፡፡ በዓለም ባሕር ውስጥ ሰይጣን ጥቁር ብቻ ስለሚመስለን የብርሃን መልአክ መስሎ ሲመጣ እንታለላለን፡፡ የዲያብሎስ መገለጫ የሆኑ መልኮችን በዓለም ባሕር ውስጥ ከሰው ልጅ ኑሮ ጋር ያለውን ቁርኝት እንመልከት፡፡
ዲያብሎስ በአንድ ወቅት በሰው አምሳል ተገለጠልኝ አብረን ስንጫወት ከቆየን በኋላ "አቤት ሙቀት" ሲለኝ እኔም እንደእርሱ እንዴ ! እንዴት ይሞቃል ባክህ አልኩ፡፡ እርሱም በአቅራቢያችን ካለ ትልቅ ባሕር ሄደን መዋኘት እንዳለብን ስለገፋፋኝ በሐሳቡ ተስማምቼ ወሬዬንና ወጌን እየቀጨሁ አብሬው መክነፍ ጀመርሁ፡፡ ከባሕሩ እንደደረስን የነካኝን ሳላውቀው ፈጥኜ ልብሴን አውልቄ ከባሕሩ ዘልዬ ስገባ እርሱ ግን ቆሞ በፌዝ ዓይን ይመለከተኝ ነበር፡፡ ዘለህ ግባና አብረን እንዋኝ ስለው "ዋና ስለማልችል ሌላ ዋና የሚችል አመጣልሃለሁ አንተ ግን እንዳትወጣ ስትዋኝ ቆይ" ብሎኝ ሄደ መጀመሪያ ዋና የሚችል መስሎ የመዋኘትን ሃሳብ ያቀረበ እርሱ መሆኑን ዘንግቶ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ከባሕሩ ሳለሁ በርካታ ዋናተኞችን አምጥቶ ባሕሩን አጨናነቀው፡፡ በመዋኘት ላይ ሳለሁ ዋና ያስጀመረኝን ከዋናተኞች መካከል ፈልጌ በጭራሽ ላገኘው ባለመቻሌ አዲስ የመጡ ዋናተኞችን የት እንደሄደ ብጠይቃቸው እነርሱም የሄደበትን እንዳላወቁ መለሱልኝ፡፡ በዓለም ባሕር እየዋኜን ሳለ ቅጠሏ የለመለመች "ጫት" የምትባል ዛፍ ለእንስሳት የተፈጠረች መሆኗን ብናውቅም እኛም እንደ እንስሳት ልናላምጣት ዋናተኞች በሙሉ ድምጽ ስላጸደቅነው ቅጠሏን እንደ ፍየል ማላመጥ ጀመርን፡፡ አረንጓዴ ልብስ የለበሰ እርሱ ሳይበላ "ብሉ" እያለ ቅጠሏን ለዓይን የምትማርክ አድርጎ የሚያቀርብልን ሰው በመካከላችን አለ፡፡ ቅጠል መብላቴን ባላቆምም ሳይበላ የሚያበላን ዋና ያስጀመረን ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ፡፡ ያ አረንጓዴ ልብስ የለበሰ ሰው ወዲያውኑ "የወረቀት ጥቅል ለምን አንጨምርበትም? ቅጠል ብቻውን እኮ ዋጋ የለውም" አለን፡፡ እኛም አዲስ የሆነውን "ሲጋራ" የተባለ የወረቀት ጥቅል ለመጠቀም በመስማማታችን አጠቃቀሙን እንዲያስረዳን በጠየቅነው ጊዜ ክብሪት አምጥቶ በእሳት ለኩሶ ጢሱን ወደ ውስጥ ከማገ በኋላ በአፍንጫው የፋብሪካ ጢስ ሲያስመስለው ያንን ለመፈጸም በመጓጓት ሲጋራ የተባለውን የወረቀት ጥቅል ሁላችንም በእሳት አያይዘን በከንፈራችን መካከል ይዘን በጋራ የደመራ ጢስ እስኪመስል ድረስ አትጎለጎልነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከጫት ጋር የሁልጊዜ ሥራችን አድርገን አፋችንን ምድጃ አፍንጫችንን የጢስ መውጫ በማድረግ አብሪ ትል መስሎ መኖርን ተያያዝነው፡፡ ሳያደርግ የሚያስደርገን ልማደኛ ዛሬ ደግሞ ጫቱን በእጃችን ሲጋራውን በኪሳችን አስይዞ ራቁታቸውን የሚደንሱ ሴቶች ካሉበት ደብዛዛ ክፍል መርቶ አስገባን፡፡ በዚህ ክፍል ልክ የሌለው ሳቅ፣ ጫጫታ፣ መዳራት ወዘተ… የበዛበት ከመሆኑም በላይ በመጠጥ ብዛት አእምሯቸውን የሳቱት በዝሙት አልጋ የሚጋደሙበት ልዩ ትዕይንት የሚስተናገድበት ነው፡፡ በዓለም ባሕር ውስጥ ዋና ያስጀመረን ሰው የክፍሉ መጠሪያ "ጭፈራ ቤት" ይባላል ካለን በኋላ ልዩ ነው ያለውን "ቢራ" የሚባል መጠጥ በተቀመጥንበት ወንበር ደርድሮ "ጠጡ!" በማለት ራሳችንን እስክንስት ካጠጣ በኋላ ከሴቶች ጋር በዝሙት አልጋ ላይ አጋደመን፡፡ ይህን ሥራ ከጫትና ሲጋራ ጋር በማስተባበር ለብዙ ዘመናት ሥሙ በውል በማይታወቅ ማኅበር ተደራጅተን ቀን በጫትና በሲጋራ ማታ በቢራ፣በጭፈራና በዝሙት ቀናትን ልናሳልፍ በሙሉ ድምጽ ተስማምተን ለዚህ ሥራ ማስፈጸሚያ በጀት አስፈላጊ በመሆኑ "ስርቆት" የሚባል አዲስ ሥራ መፍጠር እንዳለብን የማኅበራችን ሊቀ መንበር ስላስጠነቀቀን በጀት በሚገኝበት ዙሪያ ለመምከር የስብሰባ ቀን ወስነን ተለያየን፡፡ በቀጠሯችን ተገናኝተን ስንወያይ ከመካከላችን አንዱ "አቶ ከበደ ተሰማ የተባለ ብዙ ገንዘብ ያለው ነጋዴ በከተማችን ስላለ ዛሬ ሰው ሁሉ በሚተኛበት ሌሊት 9፡00 የቤቱን ቁልፍ ሰብረን በመግባት ስርቆት የተባለ ሥራችንን መጀመር አለብን፡፡" ሲል ሁላችንም በጭብጨባ ድጋፋችንን ስንገልጽለት ሊቀመንበራችን በእንቅልፍ እንዳንሸነፍ ቀን ተኝተን ውለን አስፈላጊ መሣሪያዎችን ይዘን ከምሽቱ 3፡00 እንድንገናኝ ማሳሰቢያ ሰጥቶን በሰዓቱ ለመገኜት ወስነን ተለያየን፡፡ በሥምምነታችን መሠረት ከምሽቱ 3፡00 ተገናኝተን ሲጋራችንን እያጤስን በሊቀመንበራችን መሪነት ወደ አንድ መጠጥ ቤት ገብተን መጠጣት ጀመርን፡፡ ልክ 6፡00 ሲሆን መጠጥ ቤቱ ሊዘጋ በመሆኑ "ውጡ!" ተብለን ወደ አንድ ጨለማ ቦታ ተቀምጠን ስለ 9፡00 ሥራችን በጥልቀት እየተወያየን ሳለ አንድ ነጭ ልብስ የለበሰ ወፍራም ሰው በአጠገባችን ሲያልፍ ገንዘብ የያዘ ስለመሰለን ስብሰባ አቋርጠን ለቁልፍ መስበሪያ በያዝነው መዶሻ አናቱን ብለን ከገደልን በኋላ ብንፈትሽ ምንም ገንዘብ ባለማግኜታችን እየተሳሳቅን ወደ ስብሰባችን ተመልሰን የሥራ ክፍፍል በማድረግ ሰዓቱ 8፡45 ሲሆን ጉዟችን ወደ አቶ ከበደ ተሰማ ሱቅ አደረግን፡፡ ከሱቁ እንደደረስን ቁልፉን ለመስበር የተመደቡ አባላት ቁልፉን ሰብረው ገንዘብ በርባሪነት ላይ የተመደቡት ገንዘብ በመፈለግ ላይ ሳሉ አቶ ከበደ ተሰማ ስለነቃ ለመጮኽ ሲሞክር በያዝነው ሽጉጥ አናቱን ብለን ገደልነው፡፡ መሸከም እስኪሳነን ድረስ ብዙ ንብረት ይዘን ወደ ቤታችን ከተመለስን በኋላ ለመካፈል በመስማማታችን ለአባላቱ በሙሉ እኩል ተካፍለን እንደጨረስን ከአቶ ከበደ ተሰማ ቀብር ሄደን የአዞ እንባችንን ስናፈስ ውለን ባለቤቱን ያጽናሽ ብለን ተሰናብተን ተመለስን፡፡ ለተወሰኑ ቀናት እንደጨፈርንበት ገንዘቡ በማለቁ ከሊቀ መንበራችን አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ ደረሰን ሁሉም የማኅበሩ አባላት ተሰበስብን ሳለ ሊቀመንበራችን "ሽብር የሚባል ገንዘብ ማግኛ ዘዴ ስላለ በገንዘብ ማጣት አትዘኑ" ብሎ ሲያጽናናን በጣም ተደሰትን፡፡ እኛም "ሽብር" የተባለውን እንዴት መፈጸም እንደምንችል ከሊቀመንበራችን ዝርዝር ገለጻ ከተቀበልን በኋላ ከትልቅ ገበያ ሄደን በተለያዩ በርካታ ቦታዎች ላይ ቦንብ በመጣል "ሽብሩን" ጀመርን፡፡ ልክ ቦንቡን እንደጣልነው ገበሬ ማሩን፣ ቅቤውን፣ እንቁላሉን ፣ እህሉን ወዘተ… ነጋዴም ብሩን እናትም ልጇን እየጣሉ ነፍሴን አውጭኝ እግራቸው ወደመራቸው ሲሯሯጡ በትዕይንቱ እየተደሰትን በየተመደብንበት ቦታ ገንዘብ ለቀማችንን ተያያዝነው፡፡ በጣም በርካታ ገንዘብ ከሰበሰብን በኋላ ገንዘብ ወደምንካፈልባት ቦታ በኅብረት እየሮጥን ሄደን ያገኘነውን ገንዘብ እኩል ተካፍለን በጫት በሲጋራ በመጠጥ ወዘተ… መከስከሳችንን በቀጠልንበት ወቅት ሊቀመንበራችን ሌሎችን ያልተጠናከሩ ማኅበራት ለማጠናከር ትቶን ሄደ፡፡ ለብዙ ቀናት በቀደመ ግብራችን ጸንተን ብንጠብቀውም ሊመለስ ባለመቻሉ በተለያዩ ሃሳቦች ልንከፋፈል ተገደድን፡፡የእኔ ሃሳብ ከሌሎች እጅጉን ልዩ ስለነበር ከማኅበሩ ተለይቼ እኔ ማነኝ? ሥራዬ ምን ነበር? የት ነበርሁ? ወዘተ… የሚሉትን የማንነት ጥያቄዎች እያወጣሁና እያወረድኩ ፊቴን በእንባ እያጠብኩ እግሬ ወደ መራኝ በረሐ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ ሌሎች የማኅበሩ አባላት በርካታ በሆኑ ፖሊሶች ተይዘው ወደ እሥር ቤት እንደወረዱ በሰማሁ ጊዜ የበረሐ ጉዞዬን አፈጠንኩት፡፡ በጉዞዬ ወቅት ምድር ተከፍታ የምትውጠኝ ሰማይ ተሰብሮ የሚጫነኝ ፀሐይ የምትጨልምብኝ ወዘተ… ይመስለኝ ስለነበር ወዮልኝ፣ ወዮ ለእኔ እያልሁ መሪር በሆነ እንባ ፊቴ ይቃጠል ነበር፡፡ በሳቅ ያሳለፍኩትን በልቅሶ፣ በደስታ ያሳለፍኩትን በኃዘን ቀይሬ ጫት ፣ሲጋራ ፣ስርቆት፣ ሽብር ፣መዳራት፣ስካር ወዘተ… ለእኔ አንዳልሆኑ ዳግምም ላልመለስባቸው ለራሴ ቃል እየገባሁ ስጓዝ አንድ ጽሕማቸው የረዘመ በግራ እጃቸው መቋሚያ በቀኝ እጃቸው መስቀል በራሳቸው የምንኩስና ቆብ የደፉ ቢጫ ልብስ የለበሱ መነኩሴ ከርቀት ስላየሁ ልደርስባቸው ፈጠንኩ፡፡ እንደደረስኩባቸው አባቴ ጤና ይስጥልኝ አልኳቸው፡፡ እርሳቸውም "አብሮ ይስጥልን ልጄ" ብለው በመስቀላቸው ባርከው "እግዚአብሔር ይፍታህ" ካሉኝ በኋላ "ምነው ልጄ በዚህ ፀሐይ እዚህ በረሐ ውስጥ ትቅበዘበዛለህ? " አሉኝ፡፡ እኔም የሆነውን ሁሉ አንዲት ሳላስቀር እየነገርኳቸው የበረሐውን ጉዞ ከአባ ጋር ተያያዝኩት፡፡ መድረሻዬን ባላውቅም አባ ከደረሱበት ደርሼ ለማረፍ ስለወሰንኩ ድካሜን በብርታት አድሼ በእያንዳንዲቱ እርምጃቸው እየተከተልኩ አባ ከሚኖሩባት መቃብር ቤት ስንደርስ ለዛ ባለው አንደበታቸው "የእኔ መኖሪያ እዚህ ገዳም ውስጥ ሲሆን የጸሎት ቤቴ ደግሞ ይህች ናት" ብለው በያዙት መቋሚያ ጠቆሙኝ፡፡ ከዚያም "ቤተክርስቲያን ገብቼ ጸሎት አድርሼ እስክመጣ ድረስ በዚህ ቆየኝ " ብለውኝ ሲሔዱ የአባን ቤት ዙሪያዋን ስቃኛት ቀልቤን የሳበ አንድ ጽሑፍ ከበሩ አጠገብ አነበብኩ፡፡ "ወጣት አያሌው እጅጉ ባልታሰበ ድንገተኛ አደጋ በ21 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡" የሚል ጽሑፍ ነው፡፡ ቀጣዩ የሞት ዕጣ ለእኔ እንደሆነ በማሰብ አለቀስኩ፡፡ ዓለም ለምኔ በሞት ሳልጠራ አሁኑ መመለስ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ አባ ጸሎታቸውን ጨርሰው የጸሎት ቤታቸውን ከፍተው ካስገቡኝ በኋላ "ነፍስ ያለ ሥጋ አትቆምምና ለድካምህ መጠገኛ ይህን ተመገብ" ብለው ኮቸሮ አቀረቡልኝ፡፡ እኔም የቀረበልኝን ኮቸሮ በልቼ እንደጨረስኩ አባቴ እደነገርኩዎት የእኔ ሕይወት የተበላሸ ነው፡፡ በኃጢአት የቆሸሸ የተጨማለቀ ታሪክ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ታዲያ አሁን ምን ባደርግ አምላኬ ይታረቀኛል? አልኳቸው እንባዬን እያፈሰስኩ፡፡ አባም "አይዞህ ልጄ አንተ ያን የኃጢአት ዓለም ንቀህ ስትመጣ አምላክ ታርቆሃል፡፡ ብዙዎች አሁንም በዓለም ባሕር የሚዋኙ ሆነው ሳለ አንተን ግን እግዚአብሔር ለቤቱ የመረጠህ ምርጥ ሰው ሆነሃል፡፡ ሰይጣን ከጥንት ጀምሮ የሰውን ልጅ በማሳት ወደ ሲዖል ያጋዘ የሐሰት አባት ነው፡፡ ሔዋንን ዕፀ በለስን ያበላ፣ አቤልን ያስገደለ፣ 14 ሽህ ከ 400 የቤተ ልሔም ሕጻናትን በአንድ ቀን ያስገደለ! ኧረ ስንቱን እነግርሃለሁ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊፈትንም እኮ የቀረበ ደፋር ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰይጣን የበጎ ሥራ ጠላት በመሆኑ በሰው፣ በእንስሳት፣ በዕፅዋት እያደረ መልኩን እየቀያየረ ይፈታተነናል፡፡ እስስት አታውቅም? ልክ እንደዚያ ነው፤ ዛሬ ጥቁር፣ ነገ ቀይ ፣ ከነገ ወዲያ ነጭ፣ ከዚያ ወዲያ ደግሞ ሌላ ሆኖ ማንነቱን እየቀያየረ ነው የሰውን ልጅ የሚያጠቃው፡፡ አንተ ደግሞ ልጄ ይህን ሁሉ አሻፈረኝ ብለህ ከዚያ የኃጢአት ባሕር በመውጣትህ የተመረጥክ ሆነሃል፡፡ " አሉኝ፡፡ እኔም እና እግዚአብሔር ይቅር ይለኛል? አልኳቸው፡፡ አባም "ልጄ የእግዚአብሔርን ይቅር ባይነት ትጠራጠራለህ እንዴ? አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በልቶ የነበረ አዳምን በመስቀል ተሰቅሎ ይቅር ያለ፤ ወንበዴ ሽፍታ የነበረ ጥጦስን ገነት ያገባ ይቅር ባይ አምላክ ይቅር ይልሃል፡፡ የእኔ አና የአንተ አምላክ አኮ ኃጢአትን እንጅ ኃጢአተኛን የሚጠላ አምላክ አይደለም፡፡ " አሉኝ፡፡ እኔም አባቴ ከዚህ በኋላ ዳግም ወደ ዓለም ላልመለስ ከእርስዎ ጋር ልኖር ወስኛለሁ ብዬ ከእግራቸው በታች ተደፋሁ፡፡አባም "አይዞህ ልጄ ተነሣ በጾም በጸሎት በስግደት ተወስነህ የምትኖርባት ትሕትና የተባለች ቤት በዚህ ገዳም ውስጥ ስላለች ቤትህን ላሳይህ የሚከብድህ እና የሚያስቸግርህ ነገር ሲገጥምህ እኔ ዘንድ እየመጣህ ትጠይቀኛለህ፡፡ እኔም ካንተ አልለይም አይዞህ ጽና ዳግም እንዳትበድል ተጠንቀቅ " ብለው ወደ ቤቷ ወሰዱኝ፡፡ እኔም፡-
አቤቱ በቁጣህ አትቅሰፈኝ፣
በመዓትህም አትገስጸኝ፣
የበደሌን ብዛት አይተህ፣
አትቅጣኝ ጌታ በመቅሰፍትህ፣
ተመልሻለሁ ወደ ቤትህ፣
የዓለምን ባሕር ትቼዋለሁ፣
ላልመለስ ወስኛለሁ፣
በ “ትሕትና” ቤቴ እኖራለሁ፣
ተቀበለኝ መጥቻለሁ፡፡ የሚለውን መዝሙር እየዘመርኩ "ትሕትና" ወደ ተባለች ቤቴ በንስሓ ገባሁ፡፡
I am regular visitor, how are you everybody? This article posted at this web site is actually pleasant.
ReplyDelete