የሰው ልጅ ያለው ከሌለው፣ የሌለው ካለው በመዋዋስ ይኖራል፡፡ ጎረቤት ከጎረቤት፣ መስሪያ ቤት ከመስሪያ ቤት፣ ተማሪ ከተማሪ፣ ነጋዴ ከነጋዴ ወዘተ መዋዋስ ልማድ ነው፡፡ አንዳንዱ መጽሐፍ አንዳንዱም የሚለበስ ነገር ይዋሳል፡፡ አሁን አሁን ግን የውሰቱ ጉዳይ ትንሽ ወጣ ሳይል አልቀረም፡፡ ባሕልም ማዋሻ መዝገብ ላይ መስፈር ከጀመረ ብዙ ጊዜያትን አስቆጥሯል፡፡ ሴቶች የወንዶችን ወንዶችም የሴቶችን፣ አፍሪካ የአውሮፓን አውሮፓም የአፍሪካን ወዘተ መዋዋስ ጀምረዋል፡፡ በውሰት ሕግ መሠረት መመለስ ግዴታ ነው፡፡ ማንም ሰው መዋስ ይችላል ነገር ግን በቀጠሮው ለመመለስ መዘግየት አመኔታን ያሳጣል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የተዋሱትን ነገር የራሳቸው አድርገው የሚያስቀሩ አሉ አንዳንዶቹ ደግሞ በአንጻሩ የተዋሱበትን ዓላማ እንደጨረሱ የሚመልሱ አሉ፡፡ የተዋሱት ነገር የራሳቸው የሚመስላቸው ሰዎች “ሲዋሱ የተጠቀሙበትን ትሕትና ሲመልሱም ይጠቀሙበት” የሚለው አባባል ላይ ቅሬታ አላቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ዓላማ የራሳቸው ያልሆነን ነገር በውሰት ሰበብ ማጠራቀም ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተዟዟሩ ካልሆነ በቀር አዋሽ አያገኙም፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ ነገር እንደ ግድግዳ ስልክ ውጦ ዝም ነዋ፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች በዓይናቸው ያዩትን፣ በጆሯቸው የሰሙትን ሁሉ ይዋሳሉ መመለስ ግን የለም፡፡ ፊደላትን፣ ቃላትን፣ አነጋገርን፣ አረማመድን፣ አለባበስን ወዘተ… ሁሉንም ነገር ይዋሳሉ መመለስ ግን የለም፡፡ ድሮ ድሮ ሰው የሚዋሰው ከሰው ነበር የአሁኑ ትውልድ ግን ከቴሌቪዥን፣ ከኮምፒዩተር፣ ከተንቀሳቃሽ ስልክ በቃ ከማንኛውም የቴክኖሎጅ መሣሪያ ሁሉ ከእንስሳቱ እንኳ ሳይቀር ጠቀመውም ጎዳውም ብቻ ይዋሳል፡፡ ይህን የተዋሰውን ነገር መመለስ የሚባለው ነገር ደግሞ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ወጣቱ ስማኝ አንተ የተዋስከው አነጋገር፣ አረማመድ፣ አለባበስ በእውነት እናት አገርህ የእነዚህ ሁሉ ድሃ ሆና ነው? አይደለም ድሃው አንተ ነህ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውን የምንታወቀው በባሕላችን፣ መላእክትን በሚያስመስለው አለባበሳችን ነው እኮ፡፡ ታሪክን መርሳት ባሕል መዋስን ማምጣት የለበትም፡፡ የአንተ የሆነውን ለምልክት እንኳ ሳታስቀር አውሰህ ጨረስከው፡፡ ታዲያ የአንተን ለሌላው የሌላውን ላንተ የምታደርግ ሌባ ቀማኛ ነህ ወይስ ዘራፊ? ዘመኑ የመረጃ ዘመን ነው ትላለህ ነገር ግን ምንም ጠቃሚ መረጃ የለህም፡፡ በሚጠቅመው በማይጠቅመው ጊዜህን በከንቱ ታሳልፋለህ፡፡ አናቶችህ እሳት ተጫጫሩ ልብስ ተዋዋሱ አንተ እሳቱን በኪስህ ከተትከው ሰውነትህ ደንዝዞ ሲያቃጥልህ እንኳ አይሰማህም፡፡ የሚጠቅም ነገር ተውሰህ ብታስቀር እንኳ ጥሩ ነበር፡፡ የሥራ ባህላቸውን መዋስ ስትችል 90 ደቂቃ እግር ኳስ ሲጫወቱ፣ሲታገሉ፣ ሲዳሙ ወዘተ ቁጭ ብለህ ትጮኸለህ፡፡ አስበው እስኪ በቀን ስንት ጨዋታ ትመለከታለህ? በቀላሉ ሦስት ጨዋታ ቢሆን እንኳ 270 ደቂቃ ወይም 4.5 ሰዓት ማለት ነው፡፡ በቀላሉ 8 ሰዓት ትተኛለህ፡፡ ለሌላው ጥቃቅን ነገር በድምሩ 2.5 ሰዓት ቢሆን ከ24 ሰዓት ምን ያህል ተረፈህ? በከንቱ የሚባክነው ሰዓት በቀላሉ 15 ሰዓት የቀኑን 62.5% የሚሸፍን ነው፡፡ አየኸው የተዋስከውን መጥፎ ነገር፡፡ ታዲያ ይህን አልመልስም ብለህ እስከመቼ ትከራከራለህ? ጸጉርህን አፍተልትለህ ሱሪህን ተልትለህ ሰው ፊቱን እየዞረ እብድ ነው ወይስ ጤነኛ እያለ ሲወራረድብህ የተዋስኩትን አልመልስም ትለላህ? ወንድ ነው ወይስ ሴት እየተባባለ ሰው ሲመጻደቅብህ የተዋስኩትን አልመልስም ትላለህ? ሁሉም በቦታው ሲደረግ ያምራል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በቦታችን ሳለን የሚያምርብን ራሳችንን ስንሆን ብቻ ነው፡፡ ልቅሶ ቤት ውስጥ የሚዘፍን፣ ሰርግ ቤት ውስጥ የሚያለቅስ ሰው ምን ያምርበታል፡፡ እኛ የተዋስነው ነገር እንደዚህ ያለ የማያምር ነገር ነው፡፡ስለዚህ የተዋስከውን ነገር በፍጥነት ልትመልስ ይገባሃል፡፡ የራስህ ያልሆነን ነገር ሞጭጨህ መገኘት በራሱ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስነቅፍ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌላው ሳንዋስ ያለን ነገር በራሱ በቂ ከበቂም በላይ ነው፡፡ አሁንም ደግሜ እላለሁ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌላው ሳንዋስ ያለን ነገር በራሱ በቂ ከበቂም በላይ ነው፡፡ ማዋስ ስንችል እንዴት የማይጠቅም ነገር ተውሰን እንገኛለን፡፡ ኩሩ እና ጀግና የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስደፈር አይሆንም እንዴ? ታሪካችንስ ቢሆን በደም የተጻፈውን ፍቀህ በውኃ ቀለም ትቀይረዋለህ እንዴ? ዓለም የሚያውቀን በጀግንነት፣ በሐይማኖት፣ በጥሩ ባሕላችን ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ በቴሌቪዥን መስኮት የተመለከትነውን ሁሉ እንሆናለን ስንል የነበረንን ሁሉ ትተን እንዳልነበረን ስንሆን ትንሽ አይሰማንም እንዴ? አንድ አይጥ ነበረች አሉ፡፡ ከምትኖርበት ጉድጓድ ውስጥ የምትበላው በየአይነቱ ተዘጋጅቶላት ያን እየተመገበች በደስታ ትኖራለች፡፡ በጉድጓዱ ውስጥ የተጠራቀመው ምግብ ሳያንሳት አንዳንድ ቀን ከጉድጓዱ ወጣ እያለች ሌሎች ይመገቡት የነበረውን ምግብ መመገብ ጀመረች፡፡ ይህች አይጥ መመገብ የጀመረችው የአንዱን ድሃ ጤፍ ነበር፡፡ አይጥ እንደበላችበት የተረዳው ያ ድሃ መርዝ ገዝቶ ከጤፉ አጠገብ አስቀመጠ፡፡ አይጧም እንደለመደች መብላት ጀመረች፡፡ ነገር ግን ያንን መርዝ አብራ በልታው ስለነበር ወዲውኑ ሞተች፡፡ የዚች የአይጥ ታሪክ አሁን ወደኛ ሕይወት ከገባ ውሎ አድሯል፡፡ ስለዚህ የማይገባውን የእኛ ያልሆነውን የተዋስነውን ነገር ልንመልስ ያስፈልጋል፡፡
No comments:
Post a Comment