አጋንንትን መቼ ማሸነፍ ይቻላል?
የሳጥናኤል ሠራዊት አጋንንት ሰይጣናት ሰውንና እንስሳትን የሚያስቱ ረቂቃን የሆኑ ከደመና በላይ የሚኖሩ ተፈጥሯቸው እንደ ብርሃን መላእክት ከእሳትና ከነፋስ የሆኑ ነፍስና ሥጋ የሌላቸው ከበደሉ በኋላ እንደጢስ የሆኑ እውራን ከጌትነት ብርሃኑ የተራቆቱ አሉ፡፡ ዳግመኛም በባሕርና በየብስ የሚኖሩ ሥጋ የለበሱ፣ የሚጋቡ፣ የሚዋለዱ፣የሚሞቱ መልካቸው እንደ ሰው፣ እንደ እባብ የሆኑ ሌላም ልዩ ልዩ መልክ ያላቸው ማንንም የማያስቱ በሽታ፣ደዌ የሚሆኑ የሚያሳምሙ የእግዚአብሔር ትዕዛዝና ፈቃድ ካልተጨመረ ነፍስን ከሥጋ መለየት የማይቻላቸው አሉ፡፡ እነዚህ በማሳትና ደዌ በመሆን የተሰማሩ አእምሮ የጎደላቸው የሰውን ልጅ ከጥንት ጀምረው በማሳትና ደዌ በመሆን ለራሳቸው አድርገው በገሐነመ እሳት ሊጥሉ ዝግጁዎች ናቸው፡፡ ሔዋንን ያሳተ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን በጲላጦስ አደባባይ ለፍርድ ያቆመ ደፋር ዛሬም ድረስ የቀደመ ተንኮሉን ባለመተው “በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ” ዘፍ3፥15 ተብሎ እንደተጻፈ ጠላታችን በመሆን ሊውጠን ያገሳል፡፡ ዳግመኛም አስተዋይ አእምሮ የላቸውምና በእግዚአብሔር አምነው ይንቀጥቀጡ እንጅ በጎ ሥራን ለመሥራት ዝንጉአን ናቸው፡፡ ያዕ2፥19 በምጽአት ጊዜ አእምሯቸው ሲመለስ የማይጠቅም ንስሓ ቢገቡም ለዘላለም ገሐነመ እሳት ይገባሉ እንጅ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ አይቻላቸውም፡፡ እነዚህን ለማሸነፍ ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ለኑሯቸው ምቹ ሆኖ አለመገኘት ብቻ ነው፡፡ ለዝንብ የሚስማማት ቆሻሻ ቦታ ነው፤ ለጅብ የሚስማማው የሞቱ እንስሳት የወደቁበት ቦታ ነው፤ እንደዚሁም ለአጋንንት የሚስማማቸው ልቡናው የቆሸሸ በቁሙ የሞተ ሰው ነው፡፡ በልቡና መቆሸሽ፣ በቁም መሞት ማለት በኃጢአት መዘፈቅ ፣ ከእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው፡፡ በቆሸሸ ፊታችንና ልብሳችን ላይ ያረፉ ዝንቦችን ለጊዜው በጭራ ማባረር ቢቻልም ተመልሰው መምጣታቸው አይቀርም፡፡ የሞተ እንስሳ ከወደቀበት ቦታ የተሰበሰቡ ጅቦችን ለጊዜው ድንጋይ ወርውረን ልናባርራቸው ብንችልም ተመልሰው መምጣታቸው አያጠራጥርም፡፡ ዝንብን እስከ መጨረሻው ማባረር የምንችለው ፊታችንንና ልብሳችንን ስናጸዳ ብቻ ነው፤ ጅብን ደግሞ የሞተውን እንስሳ በመቅበር አልያም በጣም አርቀን በመጣል ነው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ዝንብንም ሆነ ጅብን እስከመጨረሻው ማባረር የሚቻለው ለማረፍ የሚስማማቸውን ነገር ይዞ ባለመገኘት ብቻ ነው፡፡ አጋንንትን በኃጢአት ሳለን ለጊዜው በጸሎት፣ በጾም ፣በስግደት ልናባርራቸው ብንችል ተመልሰው መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእነርሱ ተስማሚ የሆነ ያልጸዳ ነገር በውስጣችን ተደብቋልና፡፡ እስከመጨረሻው ማባረር የምንችለው አጋንንት የሚወዱትን ነገር ይዞ ባለመገኘት ብቻ ነው፡፡ አዲስ እንግዳ ሰው አብሯችሁ ተቀምጦ ሳለ አይዞህ አይዞህ ባትሉት ጭራሽ ባታነጋግሩት ጭንቅ ጭንቅ ስለሚለው የሚሄድበት ሳይኖረው “እዚህ ቦታ ደርሼ ልምጣ” ብሎ ታቷችሁ እንደሚሄድ ሁሉ አጋንትም እንዲሁ ናቸው፡፡ ስለዚህ አጋንንትን ለማባረር በዝሙት፣ በርኩሰት፣ በመዳራት፣ ጣዖትን በማምለክ፣ በምዋርት፣ በጥል፣ በክርክር፣ በቅንዓት፣ በቁጣ፣ በአድመኛነት፣ በመለያየት፣ በመናፍቅነት፣ በምቀኝነት፣ በመግደል፣ በስካር፣ በዘፋኝነት ወዘተ… ቋንቋዎች ልናነጋግራቸው አይገባም፡፡ እነዚህን ቋንቋዎች በሚገባ የሚያውቋቸውና የሚወዷቸው የሁልጊዜ መግባቢያዎቻቸው ስለሆኑ እነርሱ ያልተማሯቸውን፣ የማያውቋቸውን ሲነገሩም ጆሯቸውን የሚያሳክኳቸውን ቋንቋዎች መርጠን ልናናግራቸው ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የዋሃት፣ ራስን መግዛት ወዘተ… የመሳሰሉት መግባያዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ መግባቢያዎች የሚግባቡ ሰዎችን መግባባት የማይችሉ አጋንንት ለሰዎች ባዕድ ሲሆኑ መባረራቸው የግድ ነው፡፡ ይሁን እንጅ አጋንንት ሁል ጊዜ “ምን አዲስ ነገር አለ” ብለው ሊፈትሹን ስለሚመጡ ለቅጽበትም ቢሆን ከመግባቢያ ቋንቋችን ውጭ ማውራት ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በዚያች ቅጽበት ውስጥ ለሲኦል አደጋ የሚጥሉበትን ምቹ ጊዜ የሚያመቻቹበት ሊሆን ቢችልስ ምን ማረጋገጫ አለን? አጋንንትን እስከመጨረሻው ለዘላለም ለማባረር እስከሞታችን ድረስ በውስጣችን ልናሰርጸው የሚገባው ቋንቋ የመንፈስ ፍሬ የሚባለውን ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚያ ውጭ በእኛ ውስጥ የገባ ርኩስ መንፈስ ሌሎችንም ርኩሳን መናፍስት ስቦ በማምጣት ለሚያጨናንቅ አደጋ አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ማቴ12፥43-45 በመሆኑም በአጋንንት ላይ ድልን ልንቀዳጅባቸው የምንችልባቸውን ሥራዎች መሥራት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት ወዘተ… ባለበት አጋንንት እንዴት ሊቀርቡ ይችላሉ? እሳት በላያቸው ላይ እየነደደ እንዴት ሊታገሱ ይችላሉ? በርግጥ ለተወሰነ ጊዜ የሚነድባቸውን እሳት ሊታገሱ ይችሉ ይሆናል ሁልጊዜ የሚነድባቸውን እሳት ግን የሚታገሱበት ኃይል ከቶ አያገኙም፡፡ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከስግደት፣ ከበጎ ሥራ፣ ከንስሓ ወዘተ… የማንርቅ ከሆነ ከእነዚህ ሥራዎች ወደራቁት ይሄዳሉ እንጅ ከእኛ ጋር የሚታገሉበት ጦራቸው መሰበሩ አይቀርም፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ የመንፈስ ፍሬ በማፍራት የሥጋ ሥራን በማስወገድ የቆሸሸ ልቡናችንን በንስሓ በማጽዳት ከአጋንንት ጦር የምናመልጥበትን ጋሻ ስንይዝ የአጋንንትን ሠራዊት ልናብረከርካቸው የምንችልበትን ኃይል ከኃያሉ እግዚአብሔር እንቀዳጃለን፡፡ በሥራችን ገነት መግባት ባንችል ሰይጣን ደስ እንዳይለው ኃጢአትን መሥራት የለብንም፡፡ አጋንንት ድል የምናደርግበትን ኃይል እገዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም ያድለን፡፡ አሜን፡፡ ማቴ 17፥19-21
No comments:
Post a Comment