1. የሥጋ ፈውስ
2. የነፍስ ፈውስ
የሥጋ ፈውስ ማለት ከሰውነት አካላት በሽታዎች መዳን ነው፡፡ የእጅ የእግር የዓይን የጆሮ ወዘተ የነፍስ ፈውስ ስንል ግን የነፍስ ከኃጢአት፣ ከበደል፣ ከአጋንንት ቁራኝነት መዳን ነው፡፡
ፈውስ ከማን ይገኛልያልን እንደሆነ ከእግዚአብሔር በባሕርይው ከቅዱሳን በጸጋ ይገኛል፡፡ መላእክት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ አበው መነኮሳት ነቢያ ካሕናት ይፈውሳሉ፡፡
ፈውስ የት ይገኛል ስንል
1 በቤተ ክርስቲያን /ሐዋ3፡1-10/
2 በመጠመቂያ ቦታዎች /ዮሐ5፡1-18;
3 እግዚአብሔርን በመከተል /ማር 5፡25-34/
ፈውስ እውነተኛ እና ሐሰተኛ ተብሎም ይከፈላል፡፡ እውነተኛው ፈውስ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ስንል እግዚአብሔር በባሕርይው የሚሰጠን ፈውስ ወይም በቅዱሳኑ አድሮ በጸጋ የሚገኘውን ፈውስ ማለታችን ነው፡፡ ያ ፈውስ ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅም ሊሆን ይገባዋል፡፡ የመጠመቂያ ቦታዎች ላይ እግዚአብሔር አጋንንትን አሥሮ ያሰቃያቸዋል ለጥቂት ጊዜያት እንኳ ለመቆየት አይችሉምና ከሰዎች ዘንድ ይወጣሉ፡፡ ዳግም ላይመለሱም ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ በማርቆስ ወንጌል ምእራፍ 5፡25-34 የተጠቀሰችው ሴት 12 ዓመት ያህል ደም ይፈሳት ነበር የክርስቶስን ልብስ ነክታ ዳነች ዳግም ያ ደዌ አልመጣባትም፡፡ ዮሐ5፡1-18 የምናየው የ38 ዓመት በሽተኛው መጻጉእ ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ ተፈውሶ አላጋውን ተሸክሞ ሄዷል፡፡ ሐዋ3፡1-10 የተገለጠው ሽባ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥ ብለው ፈውሰውታል ዳግም ወደ ሽባነት አልተመለሰም፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያላስገረመው ሰው አሁን ይሠራል በሚሉት ነገር ሲደነቁ ልዩ ተአምር ተደረገ እያሉ ሲታለሉ በጣም ያሳዝናል፡፡ ትውልዱ ሆይ አትደናገር በሽታ መፈወስ ብቻ አይደለም ቅዱሳኑ ሙት አንሥተዋል እኮ፡፡ ኤልያስ አንድ ሙት ኤልሳዕ 2 ሙት አንሥተዋል፡፡ /መጽሐፈ ነገሥትን ተመልከቱ፡፡/የሰው ልጅ በባሕርዩ ድንቅ በሚባል ተአምር ይታለላል፡፡ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስን እነዲሁም ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተአምራት የምናቃልል ሰዎች ዛሬ ተአምር እንደርጋለን በሚሉ ተኩላዎች አፋቸውን ከፍተው ጉድ ተሠራ እያሉ ሲከተሉ ማዬት አይቶም ዝም ማለት ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ጅልነትም ነው፡፡ አጋንንትን የማውጣት ጸጋ የተሰጣቸው ቅዱሳን ጸጋቸው እንዳይገለጥባቸው ያደርጉ ነበር እግዚአብሔር ያስተማራቸው ያንን ነበርና፡፡ እግዚአብሔር በወንጌሉ በርካታ ቦታዎች ላይ ፈውስ ካደረገላቸው በኋላ ይህንን ተአምር ለማንም እንዳትናገሩ ይላቸው ነበር፡፡/ማር7፤36-37//ዮሐ5፡15/ ቅዱሳን ፈውስን የሚያደርጉት በነጻ ያለምንም ክፍያ ነበር፡፡ ክርስቶስ ሐብተ ፈውስን ለሐዋርያት ከሰጣቸው በኋላ እንዲህ አላቸው ለእናንተ ለእጀጠባባችሁ ኪስ አይኑራችሁ እኔ በነጻ የሰጠኋችሁን እናንተም እንዲሁ በነጻ ስጡ፡፡/ማቴ10፡9/ ለዚህም ነው ወርቅና ብር የለንም ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣ እያሉ በነጻ ሽባዎችን እየተረተሩ ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ያደርጉ የነበረው፡፡ ሐሰተኛ ፈውስ የምንለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ ፈውስ ጊዜያ ነው፡፡ በዓይናችን ስናየው እንደነቃለን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ተአምር ይመስለናል፡፡ አሁን ያልገባን ነገር አለ አጋንንት ደረጃ ደረጃ አላቸው፡፡ ተራ አጋንንት ወይም በደረጃቸው ዝቅ ያሉ አጋንንት በአለቃቸው ወይም ከእነርሱ በበለጡ አጋንንት ይወጣሉ፡፡ የቡዳ መንፈስ፣ መተት፣ ድግምት ወዘተ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ አጋንንት ናቸው እነዚህን በአለቃቸው በብዔል ዜቡል ማውጣት ተአምር አይደለም፡፡ እነዚህ መናፍስት አኮ በነጭ ሽንኩርት ማንም ሰው የሚያባርራቸው ተራ አጋንንት ናቸው፡፡ ተራ አጋንንት በአለቃቸው ለምን ይወጣሉ ቢሉ አለቃቸው ነፍስን ተቆራኝቶ በገሐነመ እሳት ለዘላለም መያዝ ስለሚፈልግ ነው፡፡ የሰይጣንን ጥበብ ብዙዎቻችን አልተረዳነውም ለዚህም ነው አባታችን እንዲህ አድርገው ይፈውሳሉ እያልን አምላክ እስከሚመስሉን ድረስ ያመንነው፡፡ ሰው የሚደነቀው በሥጋው መፈወሱን ብቻ ነው ከፈውስ ባሻገር ነፍሱ ምን እንደምትሆን አይረዳም፡፡ ሥጋህ ለምን አይታመም ዋናው እኮ የነፍስ በሽታ ነው፡፡ የስጋ በሽታ እኮ ይፈውሱ የነበሩት እነ ቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ጴጥሮስም ነበረባቸው፡፡ ነፍስህን አስብ ትውልዱ!!!!!
በዚህ ዘመን አጋንንትን እናወጣለን የሚሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ነው የሚያወጡ እንላለን፡፡ እውነት ነው የእግዚአብሔር ስም ሲጠራ እንሰማለን ከእግዚአብሔር ስም በስተጀርባ ምን ይደረጋል እርሱ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ ገና ብዙ ነገር ይቀረናል እኮ ምንም አልገባንም ክርስትናው፡፡ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ስንቱ መጫኛ ያቆማል፣ ድውይ ይፈውሳል፣ የግሉን ገንዘብ ያካብታል መሰላችሁ፡፡ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ ውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፡፡/ማቴ7፡15-16/ የበግ ለምድ የተባለው የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር ስም፣ ጥምጣሙ፣ ካባው፣ አስኬማው ነው፡፡ ይህ ከላይ የምናየው ለምድ ነው በግ የሚያስመስለው፡፡ ውስጡ ግን እምነቱ፣ ምግባሩ፣ ቅድስናው ወዘተ ተኩላዎች ነጣቂዎች ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ የሚያፈሩት ትውልድ ለእግዚአብሔር የሆነ አይደለም ለራሳቸው መመጻደቂያ፣ ቡና የሚያፈላላቸውን፣ ጫማ የሚያስርላቸውን፣ በየሔዱበት አባቴ አባቴ የሚሏቸውን ነው፡፡ ትውልዱ በዚህ አትደነቅ በመጨረሻው ዘመን ከዚህ የበለጠ ተአምር እንደሚሠራ መጽሐፋችን ይነግረናል፡፡ በምትሀት ፀሐይን እና ጨረቃን ይዞ የሚመጣ ትውልድ የሚነሣበት ዘመን ይመጣል ያን ጊዜ የተመረጡ የሚባሉት እንኳ እስኪስቱ ድረስ ብዙ ተአምራትን ያደርጋሉ፡፡ አስቡት እንግዲህ የምጡን መጀመሪያ ዛሬ በዚህ ተራ በሆነ ቀላል ነገር ሕዝቡ እንዲህ ካመነ ያን ጊዜ ማን ይሆን ጸንቶ የሚቆመው? ማንም ሰው እንዲህ አድርግ እንዲህ አታድርግ ተብሎ የሚመለስበት ጊዜ ላይ አይደለንም ነጻ ፈቃድ የራሳችን ነው፡፡ የፈለግነውን የመከተል መብታችን የራሳችን ነው፡፡ አመጸኛ ትውልድ ምልክትን ይሻል እንዲል መጽሐፉ ተአምራትን ቤተክርስቲያን ገብታችሁ ተመልከቱ፡፡ ጸበል ቦታዎች ሄደን መጽናት ሲደክመን በቀላሉ የተገላገልን እየመሰለን ሰው አንከተል፡፡ አጋንንት የሚወጡት በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ሐዋርያት በአንድ ወቅት አጋንንት ያደረበትን ሰው መፈወስ አልችል አሉ፡፡ ኢየሱስም መጣ እና ያንን አጋንንት አስወጣው፡፡ ሐዋርያቱም እኛ ለምን አላወጣነውም ብለው ጠየቁት እርሱም መልሶ እንዲህ አይነቱ መንፈስ በጾምና በጸሎት ካልሆነ በቀር አይወጣም አላቸው ይላል፡፡ ለዚህም ነው በጸበል ቦታ አጋንንት የሚቃጠሉት እዚያ ላይ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት አለ፡፡ በአጠቃላይ እውነተኛ ፈዋሽ እንዴት እናውቃለን ለሚለው የሚከተሉትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ መሟላት አለበት፡፡
1. ጸጋ እግዚአብሔር ያደረበት
2. የሚጾም፣ የሚጸልይ፣ የሚሰግድ፣ በእምነት የጸና
3. ለፈወሰበት ጸጋ ገንዘብ የማይቀበል
4. ጸጋው በአደባባይ እንዳይገለጥ የሚያደርግ
5. ቃለ እግዚአብሔርን ብቻ የሚናገር
ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ የተባልነው ያንን የሚሠሩትን ሥራ እንድንገመግም ነው፡፡ በበለጠ ገዳማት ሔዳችሁ እውነተኛ ፈውስ ምን እንደሆነ አረጋግጡ፡፡ በእምነት አትጎስቁሉ፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የዋሃንን ከሚያታልሉ ተኩላዎች ራስህን ጠብቅ መልእክቴ ይህ ነው
No comments:
Post a Comment