Wednesday, July 30, 2014

የእውቀት መጨረሻው


እውቀት መጻሕፍትን በማንበብ፣ ከሌሎች በመስማት፣ በማየትና በሌሎችም ልዩ ልዩ መንገዶች የሚገኝ ሃብት ነው፡፡ ይሁን እንጅ በዚህ መልኩ የምናገኘውና በአእምሯችን ስልቻ የምናጠራቅመው ሁሉ በራሱ አውቀት ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ምክንያቱም እውቀት እውቀትነቱ የሚረጋገጠው በሥራ ሲተረጎም በተግባር ሲገለጽ ነውና፡፡ እምነት ያለሥራ የሞተ እንደሆነ ሁሉ እውቀትም ያለ ተግባር የሞተ ነው፡፡ ያዕ2፥17 መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራእየ ዮሐንስ ድረስ አንብበን እውቀት ብንይዝና የእግዚአብሔርን ሕግጋት የማንጠብቅ ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር የሌለን ከሆነ አዋቂነታችን ወዴት አለ? “ከመቶ ሃምሳ ዳዊት የልብ የዋሕነት ይሻላል” የሚሉ ይህንኑ ለማጠናከር ነው፡፡ እንደ አምላክ ልብ የሆነ ዳዊት የጻፈውን መቶ ሃምሳ መዝሙራት በቃላችን እስከመያዝ ብናውቅ ነገር ግን የማይራራ ፣ ጨካኝና ፍቅር የሌለበት ልብ ያለን ከሆነ አዋቂዎች ሳንሆን መቶ ሃምሳ ዕዳዎችን የተሸከምን ባዕዳዎች ነን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያው ቆሮንቶስ መልዕክቱ ላይ በሚገባ አብራርቶ እንዲህ በማለት ጽፏል “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡ ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና አውቀትን ሁሉ ባውቅ ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ድሆችን ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳለፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡” 1ኛ ቆሮ 14፥1-7 አዋቂ ሰው የሚናገረውን የሚሠራ፣ ያወቀውን ተግባራዊ ማድረግ የሚችል ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ለታይታ በሰዎች ፊት አዋቂነታችን እንዲታወቅልን የሆነ ያልሆነውን እየቀባጠርን በተግባራችን ስንመዘን የተናገርነውን እንኳ በሥራ መተርጎም የማንችል ሆነን ከተገኘን የእኛ አዋቂነት ከንቱ ነው፡፡ አዋቂዎች መሆን የምንችለው ደግሞ የምናነበውንና የምንሰማውን ለምን? እንዴት? ምን ማለት ነው? ወዘተ… የሚሉትን ጥያቄዎች እየመለስን የምንሄድ ከሆነ እና ለሕይወታችን አስፈላጊ የሆኑትን በመሥራት ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ አንድ ተማሪ ውዳሴ ማርያምን በቃሉ ለመያዝ የቃሉን ትርጉም ሳይረዳ ብዙ ጊዜ እየደጋገመ ይጮኸል፡፡ ይህን የሰማ አንድ መናፍቅ “ በዕለተ ረቡዕ ኩሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ” ይላልና ረቡዕን መጾም አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም “ኩሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ” ተብሏልና፡፡ ታዲያ የሰማይ ሠራዊት መላእክት ሲበሉ እኛ ለምን እንጾማለን? ከእነርሱ እንበልጣለን እንዴ? ሲለው ተሜ የሸመደዳትን ማመላለስ ጀመረ፡፡ ከረቡዕ ውዳሴ ማርያም ሲደርስ እንዲህ አለ “ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ረቡዕ፡፡ ኩሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ብጽእት አንቲ…” ለካ በዕለተ ረቡዕ ኩሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ተብሏል በማለት ረቡዕን ሻረ ይባላል፡፡ ይህ ተማሪ የቃሉን ትርጉም በሚገባ ሳይረዳ በቃሉ ለመያዝ ብቻ ይደክም ስለነበር መናፍቁ ከምንባቡ መካከል ቆራርጦ ባገናኛቸው ቃላት ለመታለል ተገደደ፡፡ ስለዚህ ለምን? ምን ማለት ነው? ወዘተ… የሚሉትን ጥያቄዎች በሥራችን መካከል እየመለስናቸው ማለፍ አለብን፡፡ የአንዲትን ቃል ትርጉም በሚገባ ሳንረዳ ወደ ሌላኛዋ የምንሸጋገር ከሆነ ትርጉም አልባ በሆነ ነገር አእምሯችንን ለጭንቀት እንዳርገዋለን፡፡ በሥራ መተርጎም ከቻልን ለጠቢብ አንዲት ቃል ትበቃዋለች” የሚለው በራሱ በቂ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በ 1ኛቆሮ 14፥1-7 በጻፈው መልእክቱ በርካታ የቅድስና ሥራዎችን ዘርዝሮ ማሰሪያ ያደረገው አንዲትን ቃል ፍቅርን ነው፡፡ ስለንስሓ አስፈላጊነት፣ በንስሓ ስለተጠቀሙ ሰዎች ወዘተ… ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን ብንሰጥ፣ ብዙ መጻሕፍትን ብንጽፍ፣ ለሰዎች ብናስተምር እኛ ራሳችን ንስሓ የማንገባ ከሆነ ምን ይጠቅመናል? “ንስሓ ግቡ” ለማለትማ ቴፑስ መቼ አነሰን? እርሱ ንስሓ ገብቶ አላሳየንም እንጅ፡፡ ስለዚህ ያወቅነውን አውቀት ወደ ተግባር በመቀየር እና በእውቀታችን ተጠቃሚ በመሆን መቶ፣ ስድሳ እና ሠላሳ ያማሩ ፍሬዎችን ልናፈራ ይገባናል፡፡ ማቴ 13፥8 በአእምሯችን ውስጥ የሚንጫጫውን የእውቀት ተልባ በአንድ የተግባር ሙቀጫ ውስጥ በማስገባት ልንወቅጠው ያስፈልጋል፡፡ “የእውቀት መጨረሻው እውቀትን በተግባር ማዋል ነው፡፡” ብጹእ አቡነ በርናባስ የምዕራብ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ የነበሩ፡፡

No comments:

Post a Comment