በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰበካ እና ሰበቃ የተባሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ የእነዚህ ሁለት ሰዎች የሁልጊዜ ተግባር ጭቅጭቅና ንትርክ ነው፡፡ በጠረንጴዛ ዙሪያ ተወያይተው በሦስተኛ አካል ተሸምግለው እንኳ ሥምምነት ላይ መድረስ ቀርቶ የሥምምነቱን ጉዞ መጀመር አይችሉም፡፡ አንድ ቀን እጅግ በጣም የተፋፋመ ጠብ ጀመሩ፡፡ ጎረቤት ሰማ፡፡ ሊያስማሟቸው በጠረንጴዛ ዙሪያ ተሰበሰቡ፡፡ “ልማደኛ” አለ ሰበካ፡፡ ሰበቃ ሊደባደብ ተነሣ ተገለገለ፡፡ “ግሩም ነው! ይህን ያህል ዘመን አብራችሁ ስትኖሩ እንዲህ ያለ ነገር አይታዎቅባችሁም ነበር፡፡ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የምናየው ነገር ተለውጧል፡፡ ለጎረቤት ሳይቀር አስቸገራችሁ እኮ!” አሉ አንድ የጎረቤት ሽማግሌ፡፡ “እስከ አሁንማ ከጊዜ ጊዜ ይሻሻላል በሚል በትዕግሥት ነበር የቆየሁት፡፡ ነገር ግን ሊሻሻል አልቻለም፡፡ ከወንበርህ ውረድ እኔ ያንተን ቦታ ልቀመጥበት አለኝ ጭራሽ፡፡ አንተ ሥራህን አቁም እኔ አዲስ አሠራር አለኝ ብሎ ጮኸብኝ፡፡ የቤታችን አሠራር እና የአኗኗር ሥርዓት በአዲስ መልኩ በዘመናዊ አኗኗር ዘይቤ ሊቀየር ይገባዋል አለኝ፡፡ በአሮጌ ሕግና ሥርዓት በአሮጌ ትምህርት እስከመቼ እንኖራለን? ከሥር ከመሠረቱ ጀምሮ ለቤታችን አዲስ ለውጥ ሊኖረው ይገባል፡፡ እያለ ብዙ ጊዜ ይጠይቀኛል፡፡ እኔ ግን አባታችን በሠራልን ቤት የሠራልንን ሥርዓት አክብረን እርሱ በሄደበት መንገድ ሄደን በወጣበት ወጥተን በገባበት ገብተን መኖር እንደሚገባን መከርኩት ሊመለስ ግን አልቻለም፡፡” አለ ሰበካ፡፡ “ከየት ወደ የት ነው የምመለሰው አሁንም ቢሆን አቋሜ ያው ነው፡፡ አባታችን የሠራልን ቤት እና ሥርዓት እንደእኛ የአኗኗር ዘይቤ ሙሉ በሙሉ መለወጥ ያስፈልገዋል፡፡ የእርሱ ሥርዓት ለዘመናዊነት የተመቸ በፈለግሁት ወጥቼ በፈለግሁት የምገባበት አይነት አይደለም፡፡ ስለዚህ ልንቀይረው ያስፈልጋል፡፡ ቆዩ ግን እስከመቼ ድረስ ነው ባረጀ እና ባፈጀ ቤት ያረጀ እና ያፈጀውን ሥርዓት፣ ሕግና ትምህርት እየተከተልን የምንኖረው?” አለ ሰበቃ፡፡ “ኧረ ተው ልጅ ሰበቃ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ንግግር አትናገር” አሉ የጎረቤቱ ሽማግሌ፡፡ “ምኑ ነው ለጆሮ የሚሰቀጥጠው? አንድ በድሮ ጊዜ የተፈጠረ ሰው በሠራው አሠራር ዛሬ ላይ ሆኜ ልኖርበት እንዴት እችላለሁ፡፡ ትናንት ሌላ ቀን ነበር ሥርዓቱም ሌላ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከትናንት የተለየ ቀን እንደሆነ ሁሉ ልዩ ሥርዓት ያስፈልገናል፡፡ ልተዳደር ልመራ የሚያስፈልገውም ዛሬ ላይ በሚሠራ በተስማማሁበት ሥርዓት፣ ሕግና ትምህርት እንጅ አንድ አካል ባስቀመጠው ሥርዓት፣ ሕግና ትምህርት ሊሆን አይችልም፡፡” አለ ሰበቃ፡፡ “ይቅር ይበልህ፡፡ አባታችን የሠራው ሥርዓት እኮ ልጆቹ እንድንኖርለት እንጅ እንድንጠፋበት አይደለም፡፡ ትናንት ሌላ ቀን ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ቢሆንም እንኳ የቤታችን መተዳደሪያ ሥርዓት፣ ሕግና ትምህርት ግን ቅንጣት ታህል እንዲሻር እንዲለወጥ አልሻም፡፡ ሥርዓት፣ሕግና ትምህርት አልባ በመሆን ቤታችንን ማንም ሲቀልድበትና ሲፈነጭበት ማዬት አልፈልግም፡፡ እንዲህ ከሚሆን ለቤታችን መሞትን እመርጣለሁ፡፡” አለ ሰበካ፡፡ ሽማግሌው ከሃሳብ ባሕር ወጥተው ጉሮሯቸውን ሞረድ ሞረድ አድርገው ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ “ልጅ ሰበካ ጥሩ ብለሃል፡፡ የአባታችሁ ቤት የወንበዴ ዋሻ ሲሆን ማዬት እንዴት ያስችላል? ሥርዓቱ፣ ህጉና ትምህርቱ ተቀይሮና ተበርዞ ማንም ቤቱን ሲፈነጭበት መመልከት ልጅ የሚለውን ሥም ያሳጣል፡፡ አባታችሁ ሕግና ሥርዓቱን ከትምህርት ጋር የሰጣችሁ እኮ ቤቱንና የቤቱን ኗሪዎች ለመጠበቅ እንጅ ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት አይደለም፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ እየኖራችሁ ሕግና ሥርዓቱን እናፍርስ ማለት ያሳፍራል፡፡ በቤቱ ለመኖር የቤቱን ሕግና ሥርዓት መከተል የግዴታዎች ሁሉ ግዴታ ነው እኮ፡፡ አባታችሁ ቤታችሁን ያጠረው ጠላት እንዳይነጥቃችሁ፣ ማንም ቤታችሁ ውስጥ እየገባ ቤታችሁን እንዳያቆሽሽባችሁ እንጅ እናንተ ቤታችሁን እንድትጠሉ ለማድረግ አይደለም፡፡” አሉ ሽማግሌው፡፡ “ምን እያሉ ነው! በቤቱ ለመኖር የቤቱን ሕግና ሥርዓት ማክበር ሳይሆን የየግላችንን ሕግና ሥርዓት ልንከተል ያስፈልጋል፡፡ የቤቱ ሥርዓት እኮ ዛሬን ያላገናዘበ ለትናንት ብቻ የወጣ ነው፡፡ መብላትና መጠጣት በፈለግሁ ጊዜ ካልበላሁና ካልጠጣሁ የእኔ መኖር ምኑ ጋር ነው? እንዳልበላና እንዳልጠጣ ጹም የሚል የቤቱ መመሪያ አለ፡፡ እኔ የምፈልገው ማድረግ የሚገባኝን ሁሉ እየሠራሁ መኖር ብቻ ነው፡፡ ምንም አይነት አጥር እንዲኖርብኝ አልፈልግም፡፡ የቤቱ ሕግና ሥርዓት በጣም ይከብዳል፡፡ አሁንም ቢሆን ሊቀየር ይገባዋል፡፡ በየግላችን ሕግና ሥርዓት እየተመራን በአንድ ቤት መኖር አንችልም እንዴ?” አለ ሰበቃ፡፡ “የቤታችን ሕግና ሥርዓት ሰበካ ወይም ሰበቃ ስላልተመቻቸው የሚቀይሩት ተራ ሕግ አይደለም፡፡ ይህ ሕግና ሥርዓት ስንፈልግ ሆ ብለን ወጥተን የምንሽረው ወይም በእጅ ብልጫ የምናሻሽለው ሳይሆን ለመኖር የምናከብረው ነው፡፡ የቤቱም አባል ሆኖ ለመቀጠል በቤቱም ለመኖር የግድ የምንጠብቀው ነው፡፡ ይህን ሕግና ሥርዓት ከበደኝ የሚል ሰው ቤቱን መልቀቅ እንጅ በቤቱ ተቀምጦ የመኖሪያ ሕግና ሥርዓቱን መጣስ እንደፈለገው መለወጥ ማሻሻል መብት የለውም፡፡ አባታችን አውጥቶ አውርዶ ከእግዚአብሔር ጋር ተመካክሮ ያወጣው ደገኛ ሕግ ነው እኮ ሰበቃ! ትናንትን ብቻ አስቦ ሳይሆን ዛሬን ነገን ጭምር አስቦ ነው ሕግና ሥርዓቱን የሠራልን፡፡ ለአንተ እንዲከብድ ለሌላው እንዲቀል ሆኖ የተዘጋጀ አይደለም ለሁሉም የቤቱ ኗሪ እኩል የተሰጠ ነው እንጅ፡፡ ታዲያ አንተ ሕግና ሥርዓቱ የከበደህ ላንተ ምን የተለየ ነገር ኖሮ ነው? የቤታችንን ሕንጻ ብንቀይረው እንኳ ሕግና ሥርዓቱ ግን አይቀየርም፡፡ ወደድንም ጠላንም በቤቱ እስከኖርን ድረስ የቤቱን ሕግና ሥርዓት መጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ የቤቱ ሕግና ሥርዓት የከበደው ቤቱን መልቀቅ እንጅ በቤቱ እየኖረ ሌላ አዲስ ሕግና ሥርዓት አውጥቶ አብሮ ሊኖር አይችልም፡፡ በአንድ ቤት እያለን የተለያየ ሕግና ሥርዓት ይኑረን ማለት የማይታሰብ ነው፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ ሁለት የተለያዩ ህጎች ኖሩን ማለት እኮ አንዱ ሲዘጋ ሌላው ይከፍታል፤ አንዱ ሲከፍት ሌላው ይዘጋል፡፡ እንዱ ሲያጸዳ ሌላው ያቆሽሻል፤ አንዱ ሲያቆሽሽ ሌላው ያጸዳል፡፡ አንዱ ሲጠግን ሌላው ያፈርሳል፤ አንዱ ሲያፈርስ ሌላው ይጠግናል፡፡ አንዱ ሲያጥር ሌላው ይጥሳል፤ አንዱ ሲጥስ ሌላው ያጥራል፡፡ አንዱ ሲበላ ሌላው ይጾማል፤ አንዱ ሲጾም ሌላው ይበላል፡፡ አንዱ ሲተኛ ሌላው ይነሣል፤ አንዱ ሲነሣ ሌላው ይተኛል፡፡ አንዱ ሲቀመጥ ሌላው ይቆማል፤ አንዱ ሲቆም ሌላው ይቀመጣል፡፡ አንዱ ሲያበራ ሌላው ያጠፋል፤ አንዱ ሲያጠፋ ሌላው ያበራል፡፡ አንዱ ሲስቅ ሌላው ያለቅሳል፤ አንዱ ሲያለቅስ ሌላው ይስቃል፡፡ አንዱ ሲጎዳ ሌላው ይጠቀማል፤ አንዱ ሲጠቀም ሌላው ይጎዳል፡፡ አንዱ ሲሠራ ሌላው ይቀመጣል፤ አንዱ ሲቀመጥ ሌላው ይሠራል፡፡ ማለት ነው እኮ፡፡ ስለዚህ ሁለት የሚቃረኑ ህጎች አንድ ቤት ውስጥ ሊኖሩ አይገባቸውም፡፡ አንድ ቤት ውስጥ እንዲህ የማይስማሙ ህጎችና ሥርዓቶች ሊኖሩ እንዴት ይቻላል? አንድ ቤት ስንት ሕግና ሥርዓት ሊኖረው እንሻለን? አንድ ቤት አንድ ሕግና ሥርዓት ብቻ ነው ሊኖረው የሚገባ፡፡ የዚያ ቤት ሕግና ሥርዓት የማይስማማው ደግሞ ያን ቤት መልቀቅ እንጅ ሌላ ሕግና ሥርዓት መፈለግ የለበትም፡፡ በአባታችን ሕግ እመራለሁ ያለ ብቻ በዚህ ቤት ይኖራል፡፡ ከዚያ ውጭ የራሴን ሕግ በዚህ ቤት ውስጥ አራምዳለሁ ማለት ግን ደም እስከመፋሰስ የሚያደርስ ከባድ ጉዳይ ነው፡፡ ቤቱን መልቀቅ ያልፈለገ የቤቱን ሕግና ሥርዓት መከተል ግዴታው ነው፡፡” አለ ሰበካ ቆጣ ባለ ንግግር፡፡ ሽማግሌው በደስታ ተሞልተው “ያሳድግህ! ለቁምነገር ያድርስህ! በዚህ ቤት እስከ ፍጻሜህ ለመኖር ያብቃህ! ልክ ነው ምድር ጠብ የማይል ቁም ነገር ነው ልጅ ሰበካ የተናገረው፡፡ ሁለት የተለያዩ ህጎችና ሥርዓቶች በአንድ ቤት ውስጥ በፍጹም መስማማት አይችሉም፡፡ ጨለማና ብርሃን፣ ጣዖትና ታቦት፣ ኃጢአትና ጽድቅ፣ ሐሰትና እውነት አንድ ላይ እንዴት ተባብረው መኖር ይቻላቸዋል? ጨለማ ከሆንን ብርሃን ልንሆን አንችልም፡፡ ሌላውንም እንደዚሁ፡፡ ስለዚህ ትክክለኛው መፍትሔ በቤቱ ሕግና ሥርዓት የማይመራ ሰው ሁሉ ቤቱን ለቅቆ የራሱን ቤት መሥራት ብቻ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓቱ ሳይመቸው ማንም ቢሆን በግድ በዚህ ቤት ውስጥ መኖር አለብህ የሚል አካል የለም ሊኖርም አይገባው፡፡” አሉ ሽማግሌው፡፡ ሰበቃ ልቡ ተረበሸ፡፡ በቀላሉ ይቀበሉኛል የሚል አመለካከት ነበረው ሊሆን ግን አልቻለም፡፡ አሁን የወሰነ ይመስላል፡፡ “በቃ ተቀብያችኋለሁ፡፡ የምትሉት ሁሉ ልክ ነው፡፡ አሁን የሕግና የሥርዓቱ ጉዳይ በትክክል ገብቶኛል፡፡ ባለማዎቅ የቤታችን ሕግና ሥርዓት ይታደስ ማለቴ ጥፋት ነበር፡፡ ስለዚህ በቤቱ ሕግና ሥርዓት እየተመራሁ በዚሁ ቤት መኖርን መርጫለሁ፡፡” አለ ሰበቃ፡፡ “ተባረክ! እግዚአብሔር ያሳድግህ! ለቁም ነገር ያብቃህ!” አሉ ሽማግሌው በሰበቃ መመለስ ተደስተው፡፡ ሰበቃ ግን ይህን ያለበት የራሱ ዓላማ ነበረው፡፡ ቤቱን ለቅቆ ሌላ ቤት ከሠራ በኋላ ወደዚህ ቤት ቢመለስ እንደፈለገው በቤቱ ላይ የማዘዝ ሥልጣን የለውም፡፡ ስለዚህ በዚሁ ተቀምጦ የቤቱን ሕግ ያከበረ መስሎ በራሱ ሕግ መኖርን መርጦ ነው የተመለሰ የመሰለው፡፡ የተመለሰ ስለመሰላቸው በቤቱ እንዲኖር ፈቀዱለት፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሰበቃ የአባቱን ቤት ንብረቶች ቀስ በቀስ አውጥቶ መሸጥ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰበካ “ከቤቱ ውጣ! አንተን እሹሩሩ እያልኩ የአባቴን ንብረት የቤቱን ልዩ ሃብቶች አውጥተህ ስትጨርሳቸው ማዬት አልፈልግም፡፡ የተመለስክ የመሰልከው ለዚህ ነው አይደል?” አለ ሰበካ የመጨረሻ ውሳኔ መሆኑን ለማሳዬት፡፡ ሰበቃ እንደተነቃበት ስላወቀ የአባቱን ቤት ሕግና ሥርዓት ትቶ የራሱን ቤት መሥርቶ ለመኖር ከቤቱ ኮበለለ፡፡ ነገር ግን ያሰበው ሳይሳካ ከአባቱ ቤት በወጣ በዓመቱ በከፋ አደጋ ሞተ፡፡
No comments:
Post a Comment