ኢትዮጵያውያን ለምን ይሰደዳሉ? የሚለውን ከባድ ጥያቄ መጠየቅ ግድ ከሚልበት ሰዓት ላይ እንደደረስን የተረዳሁት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያኑ አገር ለቅቆ በባእድ አገር መበተን ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? በውኑ ይችን ቅድስት አገር ጠልተው ይሆን የተሰደዱት? እስኪ የገባኝን የተረዳሁትን ትንሽ ነገር ልበላችሁ፡፡ ብዙዎች በችግር ወድቀው መድረሻ ባጡበት በዚህ ጊዜ ወደ ሊብያ፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ወደ የመን ወደ ሌሎችም አገራት ለመጓዝ (ለመሰደድ) የሞከሩ እንዳሉ በመገናኛ ብዙኃን ሲነገር ሰምተናል፡፡ እርሱማ አበውስ “ከረሃብ ጦር ይሻላል” ብለው የለም እንዴ? ትክክል ነው መከራ ያስጨንቃል፣ ረሃብ ክፉ ነው ለስደት ይዳርጋል፣ ነገ ተስፋ የምናደርገውን እንጅ ስንጓዝ የሚደርስብንን መከራ ከምንም አንቆጥረውም ምክንያቱም እዚህ ብንቀመጥም በአእምሮ ከመቁሰል፣ በረሃብ አለንጋ ከመገረፍ የዘለለ ምንም ነገር ላናተርፍ እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያውያን የማይገኙበት ቦታ አንታርክቲካ ብቻ ነው፡፡ በሌላው የዓለም ክፍል ነፋስ እንደበተነው እህል እንደዚያው ተበትነዋል፡፡ ወገኖቻችን ለእኛ ሲሉ፣ ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ፣ ለአገራቸው ሲሉ ተበትነዋል፡፡
ስደት የቅድስና መንገድ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ እነ ቅዱስ አትናቴዎስን፣ እነ ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅን ለአብነት ያህል መጥቀስ እንችላለን፡፡ ዓላውያን ነገሥታት በተነሡባቸው ወቅት ከተከበረው መንበራቸው ወርደው ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ለምን ተሰደዱ? የሚለውን ጥያቄ ስንመለከት እንጀራ ፍለጋ ወይም የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለመቀየር ነው ብለን አንመልስም፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ እጅግ አብዝቶ የሚወዳቸው የተቀደሱ የዓለም ብርሃን የነበሩ ጳጳሳት ናቸውና፡፡ ወንጌል “የሚያሳድዷችሁን መርቁ” ስለሚል ያንን የወንጌል ቃል ይፈጽሙ ዘንድ ተሰደዱ፡፡ ዓለም አልተገባቻቸውምና በምድረ በዳ ተንከራተቱ፣ ተራቡ፣ ተጠሙ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስደትም እንዲሁ ለቅድስና ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ እንጀራ ፍለጋም ይሁን ለፖለቲካ ነጻነት አገርን ለቅቆ መሰደድ የወንጌልን ቃል መፈጸም ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሰላሙን ለማግኘት ነጻነቱን ለማስከበር ብቸኛው መንገድ ስደት ሆኖ ያገኘው ሰው ቢሰደድ ኃጢአት የለበትም፡፡ ከተማረ ሰው ይልቅ ለአበባ ምርት ቅድሚያ በምትሰጥ አገር ውስጥ መኖር ከመረረው ያ ሰው ብቸኛው ምርጫው ስደት ነው፡፡ በአገሩ ላይ ከሁለተኛ ዜጋ በሚያንስ ክብር እየኖረ ያለ ሰው ቢሰደድ ፍርዱ በተሰደደው ሕዝብ ሳይሆን ባሰደደው ወገን ላይ ነው፡፡ ለስኳር መሰለፍ፣ ለውኃ መሰለፍ፣ ለዱቄት መሰለፍ፣ ለመብራት መሰለፍ፣ ለታክሲ መሰለፍ፣ ለዘይት መሰለፍ ወዘተ ክንዱን ያዛለው ህዝብ ቢሰደድ ማነው ሊጠየቅ የሚገባው ህዝቡ ወይስ አስተዳዳሪው? ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ ዲፕሎማውን፣ ዲግሪውን፣ ማስተርሱን፣ ዶክትሬቱን ወዘተ ያጠናቀቀ ሰው የሥራ እድል ለማግኘት ሲሞክር ቀድመው በሥራው ላይ በተቀመጡ 8ኛ ክፍልን እንኳ ባግባቡ ባላጠናቀቁ ሰዎች ሲሰደብ ሲንቋሸሽ ሲሸማቀቅ መሰደድ ሲያንሰው ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ሥም ለውጭ ኢንቨስተር ከ100,000 ሄክታር መሬት በላይ በነጻ በሚሰጥባት አገር ውስጥ እኛ ዜጎቿ 1 ካ.ሜ ከ 1000 ብር ባላነሰ ዋጋ በምንገዛበት ሁኔታ መኖር ሲያቅተን ብንሰደድ ማነው ተወቃሹ? የፖለቲካ መሪዎቹ እስከውጭ ድረስ እየሄዱ በሚማሩበት፣ በሚታከሙበት እና በሚዝናኑበት ገንዘብ ላይ ማዘዝ የማይችለው ሕዝብ በረሃብ አለንጋ ሲገረፍ፣ ነጻነቱ ሲገፈፍ፣ ቴክኒክ ለመማር እንኳ ክፍያ ሲጠየቅ፣ ሙያውን በአግባቡ ባልተማረ ሃኪም በማይገባ መድኃኒት በበሽታው ላይ ሌላ በሽታ ሲጨምር መታገስ ያልቻለ ህዝብ ቢሰደድ ነውሩ ምኑ ጋር ነው? የወገኖቻችን ሞት አብዝቶ አሳዝኖናል እና በአደባባይ ማልቀስ አለብን ብሎ የወጣ ሰላማዊ ህዝብ ላይ ዱላ የሚሰነዝር፣ አስለቃሽ ጋዝ የሚረጭ ፖሊስ በተሰማራባት አገር ውስጥ መኖር ሲሰለቸው ሰው ቢሰደድ ማው የሚጠየቀው? በሃይማኖቱ ያበረቱኛል ያላቸው አባቶች የፖለቲካ መሪዎች ሲሆኑበት ህዝቡ ቢሰደድ ምን በደል አለበት?
ኢትዮጵያውያን በእውነት ቅዱስ ነን፡፡ ስለራሳችን ቅድስና መመስከር የተገባ ባይሆንም እኔ ግን እመሰክራለሁ፡፡ እኔ ቅዱስ አይደለሁም ህዝቡ ግን ሲበዛ ቅዱስ ነው፡፡ ለምን? በአገሩ ሰርቶ በአገሩ መኖርን የሚጠላ ለዚያውም ኢትዮጵያዊ ሰው ይገኛል ብየ አላምንም፡፡ ነገር ግን በአገሩ የሚያሰራው ሲያጣ እንዳይሰራ ያደረገውን አካል ከመቃወም፣ ረብሻ ከመፍጠር ይልቅ ስደትን ይመርጣል፡፡ ክፉን በክፉ የሚቃወም ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ማሳያው ይኸው ነው፡፡ ከግብጽ የጀመረው አብዮት ወደ ሊብያ ብሎም ወደ የመንና ሶሪያ ሲዘልቅ ተረኛ አገር ትሆናለች ተብላ ብዙዎች ይጠብቋት የነበረ ኢትዮጵያን ነው፡፡ ነገር ግን የህዝቡ ጨዋነት፣ ቅዱስነት እዚህ ላይ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃውሞ ያልተነሣው ህዝቡ ፈሪ ስለሆነ፣ የተደራጀ ፖሊስ ስላለ፣ ህዝቡ 1 ለ 5 ስለተደራጀ፣ ችግር ስላልገጠመው፣ በሰላም ስለሚኖር፣ መንግሥት እንደሚለው 11 በመቶ ስለተመነደግን፣ መሰረተ ልማት ስለተሟላልን፣ ሥራ አጥ ስለቀነሰ ወዘተ አይደለም ህዝቡ ጨዋና ቅዱስ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ በአገሩ መኖር የቸገረው ሰው ይሰደዳል፡፡ ቢሮ ክራሲ ያዛለው ሰው ይሰደዳል፡፡ ህጋዊ ሆኖ ለመሄድ ዓመት ደጅ መጥናት የሰለቸው ሰው በኮንቴነር ታፍኖ በበረሃ በጥምና በረሃብ እየተገረፈ ይሰደዳል፡፡ በቃ ምርጫ የለውማ! እዚህም ሞት እዚያም ሞት ብሎ ወስኗላ! ለሌላው የሚያስብ ህዝብ ማለት ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው፡፡ አገሬን አልለቅም በአገሬ መብቴን አስከብራለሁ፣ ነጻነቴን እጎናጸፋለሁ የሚል ሰው የግብጹን ተቃውሞ ኢትዮጵያ ውስጥም መፍጠር አይሳነውም ነበር፡፡ ነገር ግን ርኅራኄ በማይሰማው ፖሊስ የሚገደለውን የወገኑን ሞት፣ እልቂት ያስባል፣ የሚወድመውን ሃብትና ንብረት፣ ቅርስ እና ታሪክ ከግምት ውስጥ ያስገባል ስለዚህ ብቸኛው አማራጭ ራሱን ይዞ መሰደድ ብቻ ነው፡፡ ለሌላው መጨነቅ፣ ክፉን በክፉ አለመመለስ (አለመቃወም) ማለት ይህ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች የተባለውም ለዚህ ነው እኮ፡፡ ህዝበ ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን እንጅ መሪውን ፈርቶ አያውቅም፡፡ በዚህ ልንተማመን ይገባል፡፡ ስንቱ ገንዘብ የሞላው፣ ሁሉ የተረፈው ባለሃብት አገሩን ለቅቆ ወጥቷል? ስንቱ የተማረው የተመራመረው ከከርሰ ምድር እስከ ጠፈር አበጥሮ የሚያውቀው ምሁር ነው የተሰደደው? ታዲያ ኢትዮጵያኑ የተሰደዱት ለእንጀራ ፍለጋ ብቻ ነው ማለትን እንዴት እንደፍራለን፡፡ መንግሥት ራሱን መፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ኢትዮጵያኑ ለምን ተሰደዱ የሚለውን ጉዳይ ነው፡፡ ህዝቡ ሁሉ ተሰድዶ አልቆ ዛፍና ውኃውን ገደል ተራራውን ሸለቆ ኮረብታውን የሚወስዳቸው ያጡ እንስሳትን ብቻ የሚመራ ብቸኛው መንግሥት ተብሎ እንዳይነገር እፈራለሁ፡፡ ህዝቡ ያልፈለገው ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ስለዲሞክራሲ ሲል ሲለቅ እንጅ የሙጥኝ ብሎ ሲቀመጥ ያየሁት የእኛውን ልማታዊ መንግሥት ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ከውጭ በሚያገኘው ምንዛሬ ቤቱን የሚገነባ የፖለቲካ መሪ ስላለን በዚህ ላንገረም እንችል ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ ለወገኖቻችን ስደት ዋናው ተጠያቂው በመምራት ላይ ያለው መንግሥት ብቻ ነው፡፡ አየነው እኮ የሆነውን ሁሉ ዛሬ እንደድሮው ሊደልለን የሚችልበት ምንም ወኔ የለውም፡፡ ይችን የመሰለች ቅድስት አገር ትቶ በባእድ አገር መንገላታት ያ ክፉ ስደት ግን ለምን? አኔን የሚናፍቀኝ ያ እውቀቱ ለዓለም መብራት የሆነው የተማረው ወገናችን ሁሉ ተመልሶ በእውቀቱ አገሩን ገንብቶ ድሮ የነበራትን ኃያልነት የሚመልስበት ቀን ብቻ ነው፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃት፡፡
ታናሽ ወንድማችሁ የምሆን መልካሙ ነኝ፡፡