|
ሰማዕታተ ሊቢያ |
“ሰማዕት” የሚለው ቃል ከግዕዝ ቋንቋ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ምስክርነት ማለት ነው፡፡ እምነት አንለውጥም፣ ማተብ አንበጥስም፣ ከእግዘዚአብሔር ሌላ አምላክ የለም ብለው ስለሚያመልኩት አምላክ ታምነው አንገታቸውን ለስለት ደረታቸውን ለጦር የሰጡ ሰዎች ሁሉ ሰማዕታት ይባላሉ፡፡ እነዚህ ሰማዕታት ከራሳቸው ክብር ይልቅ የእግዚአብሔርን ክብር አብልጠው በቃል የሰሙትን በተግባር የቀየሩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በንባብ ብቻ ሳይሆን በተግባር የተረጎሙ ናቸው፡፡ ከሥጋ ሞት ይልቅ የነፍስን ሞት አብልጠው የሚፈሩ ለመሆናቸው ማረጋገጫው ይህ ቅዱስ ሰማዕትነት ነው፡፡ ዓለምን እየተፈታተናት ያለው በግፍ የሰውን ልጅ እንደ እንስሳት የማረድ (ለእንስሳት ከሚሰጥ ክብር በታች)፣ በጥይት የመደብደብ አስነዋሪ እና አስቀያሚ ተግባር ላይ የተሠማሩ የሰውን ልጅ ከመጤፍ የሚቆጥሩ “ሰው መሰል ሰው በላ” ፍጡራን ናቸው (አሸባሪ የሚለው ቃል የሚገልጻቸው ስላልመሰለኝ ነው)፡፡ እነዚህ “ሰው መሰል ሰው በላ” ፍጡራን በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስሞችን ለራሳቸው እየሰጡ ዘግናኝ ተግባራትን ሲፈጽሙ ተስተውለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተወሰኑ አገራት ብቻ ተወስነው ሲፈጽሙት የነበረውን አሰቃቂ ድርጊት አሁን ላይ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ በተለያዩ የዓለም አገራት ላይ ይህን ከሰብአዊ ፍጡር የማይጠበቀውን ክፉ ሥራ እንደ ተቀደሰ ሥራ አድርገው መፈጸማቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እያየነው እና እየሰማነው ያለው ነገር እጅግ የከፋ እየሆነ መምጣቱን ነው፡፡ የአገር መከላከያ ሰራዊቱን ልብስ የመሰለ ለብሰው ሰላም አስከባሪ መስለው በመንገድ የሚጓዘውን ሁሉ ክርስቲያን መሆን አለመሆኑን እያጣሩ ክርስቲያን ከሆነ ወደ አዘጋጁት “ኮንቴነር” አፍነው በማስገባት ወደ እንግልት ቦታቸው ይወስዷቸዋል፡፡ በዚያም የእንግልት ቦታ እምነታቸውን እንዲለውጡ፣ ማተባቸውን እንዲበጥሱ በብዙ ስቃይ ያንገላቷቸዋል፡፡ ይህን ስቃይ ሳይሰቀቁ እምነታቸውን እንደማክዱ፣ ማተባቸውን እንደማይበጥሱ ካሳወቁ ወደሚቀጥለው እጅግ ዘግናኝ ወደሆነው ጉዞ ይቀጥላሉ፡፡ ይኸውም የሰውን ልጅ ርኅራኄ በሌለበት ግፍ በስለት መቆራረጥ አልያም በጥይት በተደጋጋሚ መደብደብ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መከራ የሚደርስባቸው ስለእግዚአብሔር መንግስት፣ ስለመስቀል ክብር ስለክርስትና ነው፡፡ ክርስትና በተግባር ሲፈተሽ እንዲህ አይነት ስቃይ ውስጥ መግባትንም የሚጠይቅ መሆኑን ያረጋገጡልን ሁሉ ሰማዕታት ይባላሉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በሀሙስ ውዳሴ ማርያም እንዲህ ሲል ተናገረ፡-- “ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለእግዚአብሔር አፈሰሱ መራራ ሞትንም ታገሡ” የሰማዕትነት ሥራ ይህ ነው፡፡ 1. የዚችን ዓለም ከንቱነት መረዳትና መናቅ 2. ደምን ስለእግዚአብሔር ሲሉ ማፍሰስ (መታመን) 3. መራራ ሞትን መታገስ ሰማዕታት እነዚህ ታላላቅ ሀብታት አሏቸው፡፡ እኛ ዓለምን ለመናቅ የምንችልበት ደረጃ እና ቅድስና ላይ አልደረስንም ሰማዕታት ግን ደርሰውበታል ከዚያም በላይ አልፈውታል፡፡ እኛ ስለ እግዚአብሔር ብለን ስለእግዚአብሔር ምስክርነት አንገታችንን ለስለት ደረታችንን ለጦር አልሰጠንም፣ በእሳት አልተቃጠልንም፣ በፈላ ውኃ አልተቀቀልንም ሰማዕታት ግን የህንን ሁሉ በተግባር አረጋግጠውልናል፡፡ እኛ ሞትን እንጠላልን፡፡ ቤተሰቤን ማቄን ንብረቴን ለማን ሰጥቼ እያልን የሥጋን ሞት እንፈራለን፡፡ መከራ ለሚያጸኑብንም ከነፍስ ይልቅ የሥጋን ሞት ስለምንፈራ በመከራው እንሰቀቃለን፡፡ ሰማዕታት ግን “ሥጋን የሚገድሉትን አትፍሩ ይልቅስ ነፍስን የሚገድሉትን ፍሩ” የሚለውን የወንጌል ቃል በተግባር መራራ የሆነውን ሞት ታግሰው አሳይተውናል፡፡ ሰማዕትነት በብዙ መንገድ ሊፈጸም ይችላል፡፡ የሰማዕትነት መሠረት ግን አንድ ብቻ ነው እርሱም “አምላኬን አልክድም እምነቴን አልለውጥም ማለት ነው” ይህንን ስንል ድርጊት ፈጻሚዎች በስለት፣ በእሳት፣ በጦር፣ በውኃ፣ በተለያዩ ዘግናኝ ተግባራት ግድያ ሊፈጽሙብን ይችላሉ፡፡ እነዚህ የሚፈጸሙብን አስነዋሪ ተግባራት የተናገርነውን ቃል በተግባር የመግለጣችን፣ ለቃሉ መታመናችንን የምናሳይበት ማረጋገጫ ነው፡፡ ሰማዕትነት ድሮ በእነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በእነ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ በእነ ቅዱስ ቂርቆስ… ብቻ የቀረ አይደለም ዛሬ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ሰማዕትነት እየተፈጸመ ያለ ቅደስና ነው፡፡ ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ በተለያዩ አገራት እየተገደሉ ያሉ ወገኖቻችን ሰማዕታት ናቸው፡፡ ይህን የሰማዕትነት ክብር የተጎናጸፉ በርካታ የዓለም አገራት ዜጎች አሉ፡፡ በቅርቡ ሚያዝያ 11 /2007 ዓ.ም ደግሞ ይህ የሰማዕትነት ክብር ለቅድስቲቱ አገር ለኢትዮጵያ ደረሳት፡፡ በአፍሪካዊቱ አገር በሊቢያ ይኖሩ የነበሩ 30 ኢትዮጵያውያን ራሱን “እስላማዊ መንግሥት” በእንግሊዝኛ አጠራሩ “ISLAMIC STATE (IS)” ብሎ የሚጠራው የ “ሰው መሰል ሰው በላ” ስብስብ ሰብአዊነት በጎደለው ጭካኔ በስለት አርዶ በጥይት ደብድቦ በግፍ ገደላቸው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን በሃይማኖታቸው ላይ ለሚመጣ ነገር ድርድር የሌላቸው ናቸው፡፡ መራራ የሆነ ሞትን ለመታገስ የበቁት ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ የመጣ ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህ ሰማዕታት እምነታቸውን ቢለውጡ፣ ማተባቸውን ቢበጥሱ ኖሮ ለዚህ የሰማዕትነት ክብር ባልበቁ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ በንባብ የምንሰማውን የወንጌል ቃል እነርሱ እንዲህ ነው ብለው በተግባር ገለጡልን ለእኛም አሳዩን እኛም አየነው፡፡ ሰማዕትነትን እኛም ዛሬ አየነው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ገድል ሲነበብ “እንዴት ያን ያህል መከራ የሰው ልጅ ሊሸከም ይችላል” እያልን ልባችንን ለኑፋቄ ስንከፍት የነበርን ሰዎች እዩት እንግዲህ እንዲህ አይነቱን አሰቃቂ ተግባር ግፍ እና መከራ የእኛው ልጆች፣ የእኛው ወንድሞች በሚገባን ኢትዮጵያዊ ቋንቋ እና ለዛ ሲያስረዱን፡፡ እነዚህን ሰማዕታት የወለዱ እናቶች የተባረኩ የተመሰገኑ ናቸው፡፡ባለማዎቅ እነዚህን ሰማዕታት “ነፍስ ይማር” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ነፍስ ይማር የምንል እኮ ክርስተናቸውን በተግባር ስለእግዚአብሔር ምስክር ሆነው ስለሞቱ ሰማዕታት አይደለም፡፡ እርሱ የራሱ የሆነ ቦታ አለው እነዚህ ጋር ግር ቦታ የለውም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዐረፈ ጊዜ “ነፍስ ይማር” ያሉ ሰዎች ከነበሩ ተሳስተዋል፡፡ ከሰማዕታቱ ረድኤትና በረከት አምላካችን እግዚአብሔር ያካፍለን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment