Tuesday, April 28, 2015

በጣም አልበዛም ግን?

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ችግሮች ይገጥሟታል፡፡ አንዱ ችግር ሌላውን ተከትሎ ስለሚመጣ አንዱን አዝነን ሳንጨርሰው ሌላው አሳዛኝ ችግር ይተካል፡፡ የአንዱ ችግር ተከትሎ መምጣትም ያለፈውን ያስረሳናል፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ጉዳይ ይህ ነው፡፡ በአገሪቱ አለመረጋጋት ሳቢያ በየመን ይኖሩ የነበሩ ወገኖቻችን እጅግ አስጨናቂ መከራ ላይ መውደቃቸውን እያሰብን ሳለን ከወደ ደቡብ አፍሪካ የሰማነው ጉዳይ እነርሱን እንድንዘነጋቸው አደረገን፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወገኖቻችን በእሳት ተቃጠሉ በአደባባይ በስለት ተቆረጡ እጅግ አለቀስን፡፡ ለነጻነታቸው ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራት አገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ያንን ነጻነታቸውን ከተጎናጸፉ በኋላ ግን ይህንን ክፉ ሥራ ፈጸሙብን፡፡ ስለ እነርሱ ስናለቅስ ስናነባ 30 ወንድሞቻችን በሊብያ በረሃ ደማቸው ከውኃ ጋር  ጎረፈ፡፡ አሰቃቂ ዘግናኝ የተባለውን መከራ ተቀበልን፡፡ አብዝተን በምሬት አለቀስን እንባችንን አፈሰስን በአደባባይም በሰላማዊ ሰልፍ ሀዘናችንን ገለጽን ሆኖም ግን ሀዘናችን ሃዘናቸው ያልሆኑ ፖሊሶች በአገራችንን በዱላ ቀጠቀጡን፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አምላክን ከመለመን ውጭ ምንም ማለት ስለማንችል “አንመካም በጉልበታችን፣ እግዚአብሔር ነው የእኛ ኃይላችን” እያልን ዘመርን፡፡ ያም ሆኖ በዚያ አለፈ፡፡ ሲኖዶሱ በ 7 ቀናት ጸሎተ ፍትሐት ረሳቸው፣ መንግሥትም በ 3 ቀናት ብሄራዊ ሀዘን ዘነጋቸው እኛ ቤተሰቦቻቸው ግን እስከመቼም ድረስ አንዘነጋቸውም አንረሳቸውም፡፡
በጣም የሚሳዝነውና የሚገርመው ጉዳይ ግን እስከዛሬ ድረስ በመገናኛ ብዙኃኑ የሚነገረው ዜና መሰል ትርኪ ምርኪ ንግግር ነው፡፡ “እስልምናን አይወክልም” ከሚለው በሻገር እኛ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ከእስላም ለብዙ ዘመናት በፍቅር አብረን የኖርን ነን፤ እንዲያውም መስጊድ ሲሰራ ክርስቲያኑ፤ ቤተ ክርስቲያን ሲሰራም እስላሙ ማህበረሰብ ይደጋገፋሉ ተባለ፡፡ ትክክል ነው ለብዙ ዘመናት አብሮነታችን ዘልቋል፡፡ አንድ በጣም የበዛው ጉዳይ ግን “በጋብቻም ተሳስረናል” ተብሎ የሚገለጸው የመገናኛ ብዙኃኑ ግዴለሻዊ ዘገባ ነው፡፡ ፍቅራችን ምን ወደር ባይኖረው፣ እጅግ ብንረዳዳ፣ በለቅሶ በደስታ ብንጠያየቅ፣ አብረን በጉርብትና ብንኖር በጋብቻ ግን ልንተሳሰር እንዴት እንችላለን? ፖለቲካው ምን ያህል ጫና እየፈጠረብን እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል፡፡ የሃይማኖት መሪዎች በአንድ ወንበር ተቀምጠው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ፎቶ ቢነሱ፣ ቪዲዮ ቢቀረጹ ከፊት የነበራቸውን ፍቅር የሚያሳይ ነው እንጅ ሌላ መልእክት ያለው አይመስለኝም፡፡ አሁን አሁን  ግን ድሮ ከነበራቸው አንድነት የተለየ ሌላ አንድነት የፈጠሩ ይመስል ለታይታ በአደባባይ እጅ ለእጅ መያያዝን የፍቅር መገለጫ አድርገውታል፡፡ ቤተክርስቲያን እንዲገቡም ሳይፈቀድላቸው አልቀረም፡፡ በጣም በዛ “ፍቅራችን” ከልኩ አለፈ ሥርዓት እየተጣሰ እንዲህ ያለ ነገር መሠራቱ አስፈላጊ መስሎ አይታየኝም፡፡ እስላሙ ያረደውን ክርስቲያኑ፤ ክርስቲያኑ ያረደውን ሙስሊሙ አለመመገብን እንደልዩነት የሚመለከተው መንግሥት አንዱ ያረደውን ሌላው እንዲመገብ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ በጋብቻ ተሳስረናል ላለ አካል ይህን ማድረግ እጅግ ቀላል ነዋ!!!

No comments:

Post a Comment