Monday, April 27, 2015

የ ISIS ዳግም ግድያ በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች የተባለላት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም  የአስራት የበኩራት አገር ናት፡፡ ታዲያ ይች አገር በተለያዩ ዘመናት ክርስትናን የሚቃወሙ አረመኔዎች እጅግ በርካታ ፈተናዎችን ሲያደርሱባት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ አረመኔው ግራኝ መሀመድ ጨካኟ ዮዲት ጉዲት እንዲሁም በቅርቡ ፋሽስት ኢጣሊያ ከዚያም በኋላ በኢትዮጵያ የተመሠረተው የደርግ መንግሥት በቤተክርስቲያናችን ላይ ጦራቸውን ሲያዘምቱ ምእመናንን ለሞት ሲዳርጉ ክርስትናዊ የሆኑ ትውፊቶችን ሲያጠፉ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲበርዙ መቆየታቸው የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ እነዚህ አረመኔዎች በተነሡባቸው ጊዜያት ሁሉ በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ምእመናን  እና ካሕናት ጳጳሳት ሳይቀሩ ለሞት ተዳርገዋል፡፡ እነዚያ ለሞት የተዳረጉት ወገኖቻችን በተቀደሰው የሰማዕትነት (የምስክርነት) ሥራቸው ስናወሳቸው ነበር ወደፊትም እናወሳቸዋለን እንማርባቸዋለን፡፡ ማንም ቢሆን ስለእምነቱ የመጣበትን ጠላት በትእግሥት ሊያሸንፍ ይገባዋል፡፡ የጥላቻ ማጥፊያ ብቸኛው መሳሪያ ፍቅር ነውና፡፡ ለዚያም ነው እኛ ኢትዮጵያውያን በፍቅር መኖራችን ለዓለም ሁሉ ተምሳሌት ሆነን እንድንዘልቅ የረዳን፡፡
በቅርብ ቀናት ክርስትናን ለማጥፋት (ለዚያውም ጠላቴ ናት ያላትን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን) የሚንቀሳቀሰው ጨካኙ ሃይማኖታዊ ቡድን ራሱን  ISIS ብሎ የሚጠራው እስላማዊ መንግሥት በ 30 ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን ዘግናኝ ተግባር አይተናል ተመልክተናል አዝነናል አልቅሰናልም፡፡ ከሃዘኑ ባሻገር ምን ተደረገ ለሚለው ግን ጥያቄው ጥያቄ ውስጥ እንደሆነ የሚቀጥል ለመሆኑ እየተመለከትን ነው፡፡ እጅግ እስኪሰለቸን የምንሰማው የመገናኛ ብዙኃኑ የጋዜጠኞች ንግግር የሚያስረዳን ግን የሞቱት ኢትዮጵያውያን ህገ ወጥ ስደተኞች ናቸው በሚል ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ለይ ብቻ የተመሠረተ ነው፡፡ እሽ ሕገወጥ  ስደተኞች ናቸው እንበል ISIS የሚገድለው  ሕገወጥ ስደተኛ ማነው ብሎ ነው እንዴ ከሆነ ጥሩ፡፡ እንደዚህ ከሆነ ከዚህ የምገነዘበው ነገር አለ እርሱም ISISን ያደራጀው የኢትዮጵያ መንግሥት  እንደሆነ፡፡ ለምን አደራጀው ስንል ሕገወጥ ስደተኞችን ከሕጋዊ ስደተኞች እንዲለይለት፡፡ በቃ፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኞችም ሆኑ የመንግሥት አካላት የሐይማኖት መሪዎችም ሆኑ ተራው ምእመን ሕገወጥ እና ህጋዊ ስደት የሚለውን ከአእምሯችን ፍቀን ልናወጣው ይገባል፡፡የኢትዮጵያኑ ሞት ከስደት ጋር የተያያዘ ነገር ስላልሆነ፡፡ ስንቱ ሰው ነው ዛሬ በስደት የሚኖረው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ ከአንታርክቲካ በስተቀር ሰው በሚኖርባቸው አረገራት ሁሉ ተበትኖ የሚኖር ነው፡፡ ታዲያ ያ ሁሉ ሰው ተገደለ እንዴ፡፡ አልተገደለም፡፡ ለእነዚህ ሞት ዋናው ምክንያት ክርስትናቸው መስቀላቸው ብቻ ነው፡፡ አለቀ፡፡ በዚህ ልንወናበድ አይገባም፡፡ ሰማዕትነታቸውን አጉልተን ልናወጣው ይገባል እንጅ ስደታቸውን ልናጎላው የፖለቲካ ፍጆታ ልናደርገው አይገባም፡፡
ሌላው ከሃይማኖት አባቶች የሰማነው መግለጫ መሰል ንግግር ዳግም ግድያን ለመፈጸማቸው ማስረጃ ነው፡፡ ISIS ን እናወግዛለን የሚል መፈክር ይዞ መዞር ብቻውን ISISን ያጠፋል ማለት ከሆነ አምላክ ይፋረደናል፡፡ ከሃይማኖት መሪ ነን ባዮች ይልቅ የተሻሉ መምህራንን የተመለከትነው በሊብያ በረሃ ከዚያ ከውኃማው አካባቢ ነው፡፡ ስለእውነት መራራ ሞትን የታገሱት እነዚህ ቅዱሳን ሰማእታት ስለክርስትናቸው ታረዱ በጥይት ተደበደቡ ጳጳሱን ተቀድመውት መንግሥተ ሰማያትን ወረሱ፡፡ እኛ እዚህ ስለክርስትናችን ባልተፈተንበት ቦታ ሳለን የምንቀልድበትን ክርስትና እነርሱ እስከሞት ድረስ ታምነው በደማቸው ኢትዮጵያን ቀደሷት፡፡ ሲኖዶሱ ምን አለ ምን መግለጫ ሰጠ፡፡ ሊባል ይገባው የነበረው ነገር ተባለ ወይ ስንለ አልተባለም ነው መልሱ፡፡ ክርስትና ሰይፍ ለሚያነሱባችሁ ሰይፍ አንሱ አይልም እንዲያውም ቀኝ ፊትህን ለሚመታህ ግራ ፊትህን ደገሞ ስጠው ይላል፡፡ በአጠቃላይ ክርስትና ስለእምነታችሁ ስለመንግሥተ ሰማያት ተሰደዱ ሙቱ ይላል እንጅ አሳድዱ ግደሉ አይልም፡፡ ለዚህም ነው ከነማተባቸው አንገታቸውን ለስለት የሰጡት፡፡ ይህን የተቀደሰውን ሰማዕትነት ከምንም ባለመቁጠር መንግሥት ከሚዘበዝበን ፖለቲካ የበለጠ ፖለቲካዊ ዝብዘባ ከሃይማኖት መሪዎች አንፈልግም፡፡ የትኛው የሃይማኖት መሪ ነው በሊብያ የተሠዉት ኢትዮጵያውያን ስለሃይማኖታቸው ፍቅር ነው እና ሰማዕታት ናቸው ብሎ ባለማፈር የተናገረው፡፡ ይህን ብል እንዲህ እደረጋለሁ በሚል ፍርሃት ተሸብበን ወገናችን እስከመቼ አገሩን ትቶ ሲኮበልል ይኖራል፡፡ እኛ ለማንም መሬታችንን እየሰጠን በሃገራችን መኖር እንደ እሳት እየፈጀን  እስከመቼ እንቀጥላለን፡፡ አባቶች መስቀሉን ከፍ አድርገው የሚመሩትን ሕዝብ ሃዘን ካልተረዱ በጣም አሰቃቂ ግድያ ማለት እርሱ ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስን ዛሬ ላይ ምነው ባገኘናቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለፋሽስት ኢጣሊያ እንድትገዛ ከፋሽስቱ የመጣላቸውን የመኪና፣ የቤት፣ የገንዘብ እና የተለያዩ የማግባቢያ ሽልማቶች ከምንም ባለመቁጠር ኢትዮጵያ ለፋሽስቱ እንዳትገዛ በተቀደሰ መስቀላቸው በተከበረው ስልጣናቸው መላ ኢትዮጵያን አወገዙ፡፡ ይህንን ውግዘት የሰማው ፋሽስትም በጥይት ደብድቦ ገደላቸው፡፡ አያችሁ የአገር ፍቅር ማለት፡፡ በአፍ ከመናገር ባለፈ በተግባር የተረጋገጠ የአቡነ ጴጥሮስ የአገር ፍቅር፡፡ ታዲያ ዛሬ ምነው ይሄ የአገር ፍቅር ጠፋ፡፡ ምእመናን በሚከፍሉት ገንዘብ የምንተዳደር አባቶች ትንሽ ቆም ብለን  የምናስብበት ወቀት ላይ ነን፡፡
እጅግ የሰለቸኝ ሌላው ነገር ISIS የማንንም እምነት አይወክልም የሚለው የቂልነት ንግግር ነው፡፡ እስላማዊ ነኝ እያለ፣ ቁራንን ካልተቀበላችሁ ብሎ እያስገደደ፣ የሸሪአ ሕግን ተቀበሉ ብሎ እያስፈራራ የማንንም እምነት አይወክልም የሚለው አባባል ጅልነትን የሚያሳይ ነው፡፡ “ሃይማኖት አንዲት ናት የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ክርስቲያኖች አሉ” ስንባል በዝምታ አለፍነው፡፡ አወ አሉ ብለን በራሳችን ላይ ፈረድን፡፡ የመጽሐፉን ቃል ዘንግተን መንግሥት የሚቀባጥረውን ፖለቲካ አብረን ተናገርነው፡፡ በክርስትናችን ላይ አፈርን፡፡ ቃሉ መጽሐፍ ውስጥ መኖሩንም ተጠራጠርን፡፡ ያ የመጽሐፍ  ውዱስ ቃል እንደ አንድ ተራ መፈክር ተቆጥሮ “መፈክር አንግበው” ስንባል ይህንን ለማስረዳት የሞከረ ማነው አረ ማንም፡፡ ያ የያዝነው የመጽሐፍ ቃል ሰው አልገደለም እኮ ነገር ግን ክርስቲያኖች እንዲህ አደረጉ ተባልንበት፡፡ ዛሬ 30 ንጹሃንን የገደለው እስላም የማንንም እምነት አይወክልም ማለት ምን ማለት ነው? ሙስሊሙ ማህበረሰብስ ይበል መንግስትም ይበል ሲኖዶሱ እንዴት እንዲህ ይላል፡፡ ግጭት ይቀሰቅሳል ተብሎ ታስቦ ከሆነ እኛ ክርስቲያኖች በማረድ ደም በማፍሰስ ላይ አልተመሰረትንምና አናደርገውም፡፡ እኛ ብንሆን ኖሮ እኮ አስተምረን እንመልሳቸዋለን ብለዋል ተብለን ነበር እኮ፡፡ እስላም ነን ባዮች ናቸው ያረዱን ታዲያ እነዚህ እስልምናን የማይወክሉ ከሆነ ሙስሊሙ ማህበረሰብ አስተምሮ ሊመልሳቸው ይገባል፡፡ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ  የዐረቡ ክፍል ባሳደዳቸው ጊዜ እስልምና እምነትን የሚከተሉ ሰዎችን ከነእምነታቸው ተቀብላ ያስተናገደች እንጀራዋን ቆርሳ ያበላች ብቸኛ አገር እንደሆነች ማንም የሚመሰክረው ሃቅ ነው፡፡ ክርስቲያኑ ከእስላሙ ጋር በፍቅር እና በመተባበር በመረዳዳት እና በመተዛዘን እንኖራለን፡፡ በዚህ መዋደዳችንም ብዙ ዘመናትን አስቆጥረናል ወደፊትም እንደዚሁ እንዘልቃለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ እስላሞች ይህንን አረመኔያዊ ተግባር ላይፈጽሙት ይችላሉ ISIS የተባሉት እስላሞች ግን አድርገውታል፡፡ አባቶቻችን ደፍረው ያልተናገሩት ጉዳይ ይኼ ነው፡፡ እስላም የሆኑት ISIS ክርስቲያን የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ገድለዋል፡፡ እኛ ግን እነርሱን ለመግደል አናስብም ምክንያቱም ክርስቲያኖች ስለሆንን ማለት ነበረባቸው አላሉንምና እናዝናለን፡፡የ ISIS ዳግም ግድያ በኢትዮጵያ ተፈጽሟል የሚያሰኘን ቅሉ ይኸው ነው፡፡ ከዐረፉት ወንድሞቻችን ረድኤት በረከቱን አምላካችን ይክፈለን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment