Saturday, May 30, 2015

ባል ማነው?

እባካችሁ ሼር በማድረግ ወገኖቻችንን እንታደግ!!!!

ሁለት “ፍቅረኛሞች” ነበሩ፤ አብዝተው “ይዋደዳሉ”፡፡ ዘመኑ ዛሬ አልነበረም እጅግ ብዙ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ “ታሪክ ራሱን ይደግማል” አለ አሉ አንድ ፈላስፋ፡፡ ማለቴ ዛሬም ያ ከብዙ ዘመን በፊት የነበረው ዘመን ዛሬ ዘመን ሆኖ እየዘመነ ነው ማለቴ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ “ፍቅረኛሞችንም” ከዛሬው ዘመን ጋር አብረን እናዘምናቸው እና ዘመኑን አብረውን ይዘምኑ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- እነዚያ ሁለቱ “ፍቅረኛሞች” ፍቅራቸውን ወደ ትዳር ደረጃ ከፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ጋብቻቸውን ልዩ በሆነ ሁኔታ ማስረግ ጉጉታቸውና ምኞታቸው ነው፡፡ የመኪና ዘር የሚባል አልቀራቸውም፣ አርቲስት የሚባል ከዘፋኝ እስከ ኮሜዲያን ድረስ ሁሉም ተጠርተዋል፤ የካሜራ ባለሙያ በሙሉ  የስዕል ባለሙያዎችም ሳይቀሩ ተጋብዘዋል፤ የአካባቢው ሰው በሙሉ አደራ ልጆቻችንን እንድተመርቋቸው ተብለዋል፤ የሚታረዱት  ፍሪዳዎች  ከመድለባቸው የተነሣ ጫንቃና ሻኛቸው የማይታወቅ ለቁጥር የሚያስቸግሩ እጅግ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ የሚጠጣው መጠጥ ለባላገሩ ጠጅ፣ ጠላ፣ አረቄ ለከተሜውም ቢራው፣ ለስላሳው ተዘጋቷል፡፡ የሙሽሮቹ ልብስ ታዋቂ በሆኑ “ዲዛይነሮች” የተሠራ በርካታ ጥበብ የፈሰሰበት ነው፡፡ በወርቅ እና በዕንቁ የተጌጠ ካባ ሊደርቡ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡
እናም ይህንን ሁሉ አድርገው የጋብቻቸውን ቀን ቆረጡ፤ ሁሉም በጉጉት ጠበቀ፡፡ ከሙሽሮቹ ይበልጥ የተጠራው ሰው ቋመጠ፡፡ “ሙሽራን ሊሞቀው ሰርገኛን ልብ ወደቀው” የሚባለው አባባል ባይኖር ኖሮ እነዚህን ሰዎች ሊገልጥ የሚችል አቻ ቃል ባልተገኘ ነበር፡፡ የሆነው ሆነና መቼም ቀኑ መሄዱን ውኃም መፍሰሱን አያቆምምና የሰርጉ ቀን ደረሰ፡፡ ሙሽሮቹ የናፈቁት፣ የተጠሩ ሰዎች በጉጉት የጠበቁት ልዩ ትእይንት የሚታይበት ቀን ደረሰ፡፡ እልል ተባለ፣ ተጨበጨበ፣ ሰርገኛንም ልብ ወደቀው፤ ሙሽራንም ሞቀው፣ ዘለለ ሁሉም በየፊናው የየራሱን ደስታ ገለጸ፡፡ ሁሉም በየቋንቋው ደስታውን ገለጸ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚባለውን “ለሙሽሮች ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እያሉ እንደ ሚዳቋ ይዘሉ ገቡ፡፡
እየተጨበጨበ፣ እየተዘለለ፣ ሆ ቀን ወጥቶላት ሁሉም እያላት  ጉዞ ወደ ማዘጋጃቤት፡፡ መዘጋጃ ቤቱ እንዲህ አይነት ሰርግ ሲያስተናግድ የመጀመሪያው አይደለም ለካ፡፡ እኔ በጣም ተገርሜያሁ፤ ከመገረሜም የተነሣ እጄን አፌ ላይ ጭኜ ለብዙ ሰዓታት ራሴን ብቻ እያነጋገርሁ ነበር፡፡ ሙሽሮቹ ወደ መዘጋጃ ቤት ኃላፊው በሚዜዎቻቸው ታጅበው ሄዱ፤ ከባለጉዳዮች መቀመጫ ላይ ተቀምጠውም ቃለ መጠይቁን በሚገባ አድርገው መለሱ፡፡
ኃላፊው ፡ “ሥም” አለ
ሙሽሮቹ፡ “እገሌ እና እገሌ”
ኃላፊው፡  “ዕድሜ”
ሙሽሮቹ “25 እና 27 ዓመት”
ኃላፊው “ጾታ”
ሙሽሮቹ፡ “ወንድ”
ኃላፊው፡ “ባል ማነው?”
ሙሽሮቹ፡ “እኔ ባል፤ እርሱ  ደግሞ ሚስት”
ኃላፊው “መጠይቁን ጨርሻለሁ፤ የጋብቻ የምሥክር ወረቀታችሁን እስከማዘጋጅላችሁ ድረስ ትንሽ ጠብቁኝ” አላቸውና የምሥክር ወረቀታቸውን አዘጋጅቶ ሲሰጣቸው ርችቱ ተተኮሰ፣ መኪኖች ሁሉ አክላሉ፣ ሰው ሁሉ አጨበጨበ፣ በእልልታ አቀለጠው፡፡

ዘመናችን ለካ ዘመነ ሰዶም ነው፡፡ ዛሬ ገና ገባኝ ዓለም ዳግም በንፍር ውኃ እንደማትጠፋ ለኖኅ ቃል ኪዳን የተገባለት ቢሆንም እንኳ ነገ በሌላ መቅሰፍት ምድራችን ሙት ባሕር ልትሆን እንደምትችል  ዛሬ ተረዳሁ፡፡ ዓለም ልትጠፋ ትንሽ የቀራት የመሰለኝ ሁለት ወንዶች ሊጋቡ ሄደው ባል ማነው? ሁለት ሴቶችም ሊጋቡ ሄደው ሚስት ማናት? ተብሎ ከሚጠየቅበት ዘመን መድረሴን ሳስታውስ ነው፡፡ ሴት እና ሴት፤ ወንድና ወንድ ሊጋባ ሄዶ ባል ማነው? ሚስት ማናት? መባል እንዴት ያለ ውርደት ነው? 

Monday, May 25, 2015

“ትናንት አልባው ዛሬ”

አንድ ውሻ ነበር አሉ፡፡ ይህ ውሻ እንደማንኛውም ውሻ ያው ውሻ ነው፤ እርሱን ከሌላው ልዩ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ እናም ይህ ውሻ ጠገብኩ በቃኝን ሳይሆን ራበኝ አብሉኝን ከዚያ ውጭ ግን እበላችኋለሁ በማለት የሚያስፈራራ ነው፡፡ የሰጡትን ሁሉ በቃኝ ሳይል ንጹሁን ከቆሻሻ ሳይለይ የሚያግበሰብስ በቃኝ የሚለው ቃል የተዘነጋው ነው፡፡ ሲፈልግ ጌታውን አስፈቅዶ ሲፈልግ የጌታውን ጓዳ በርብሮ ያግበሰብሳል፡፡ አንድ ቀን ጌታው ተገረመ እና “አንተ ግን ለምን በቃኝ አትልም” አለው፡፡ ውሻም መለሰ “እንዴ ጌታዬ ከማን የተማርኩትን” ብሎ አረፈው፡፡ ጌታውም እርሱን የሰደበው ስለመሰለው በጣም ተበሳጨና “ውሻ መቼም ውሻ ነው ከማን ተማርኩት ልትል ነው ደግሞ!” አለው፡፡ “ከአባቴ፣ ከአያቴ፣ ከቅድመ አያቴ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልዩ ስጦታዬ ነው” በማለት የዘሩ እንደሆነ ገለጸ፡፡ ጌታም “እኔ እኮ ከአንተ ነው የተማርኩት ልትለኝ መስሎኝ በጣም ተናድጄብህ ነበር” አለው፡፡ “እርስዎንስ አይደለም” ብሎ መለሰ፡፡ “በነገራችን ላይ ግን  እምብርት የሚባል ነገር አልፈጠረብህም እንዴ” አለው ጌታው፡፡ “ጌታዬ እርስዎ እኮ የእኔን ልዩ ባህሪ አልተረዱም ማለት ነው” አለ ውሻ፡፡ “ምን አይነት ባህሪ አለህ መቼም ያው ማግበስበስ ብቻ!” አለው፡፡ “እርስዎ የሚመለከቱ ማግበስበሴን እንጅ የት እንደማጠራቅመው አያውቁም፡፡ በእናንተ በሰዎች ዘንድስ ይህ አይነት ነገር አለ አይደለም እንዴ? የአገር ሃብትን በቃኝ ሳይሉ የሚያግበሰብሱ ሙሰኞች ሞልተው የለም እንዴ? እነዚህ ሰዎች እኮ ከእኔ አባቶችና አያቶች በሚገባ የተማሩ የሰው ውሾች ናቸው፡፡ እነዚህ እኮ ሲያግበሰብሱ እንጅ በቃኝ ሲሉ፣ ሲያጠራቅሙ አይታዩም፡፡ ዛሬ ያገኙትን ሁሉ ያግበሰብሳሉ፤ ትናንት ምን እንዳግበሰበሱ እንኳ አያውቁም ምክንያቱም የሚያግበሰብሱት እጅግ በጣም ብዙ ስለሆነ፡፡ እኔ ያገኘሁትን ሁሉ እበላለሁ በቃኝን አላውቅም ሆዴ በጣም ሲሞላ እኔ ብቻ ከማውቃት ቦታ ሄጄ አስወጣዋለሁ(እመልሰዋለሁ)፡፡ ነገ ሌላ የምመገበው ካላገኘው ያንን ትናንት የመለስኩትን እመገባለሁ፡፡ እነዚህ የናንተ ሰዎች ግን ትናንት ያጠራቀሙትን ነገር ዛሬ አይጠቀሙበትም ምክንያቱም በየቀኑ የሚበሉት አያጡማ፡፡ የሚበሉትን ማግኘት እኮ ለእኛ የሚከብደንን ያህል ለእነርሱ እጅግ በጣም ሲበዛ ቀላል ነው፡፡ ሥራ አጡን ሥራ ላስይዝህ ይሉና ይበላሉ፣ አገር ለቆ መሰደድ የሚፈልገውን ከደላላ ላገናኝህ ይሉና ይበላሉ፣ መታወቂያ ፈላጊውን ቶሎ እንድሰጥህ ክፈል ይሉና ይበላሉ፣ ባለመኖሪያ ቤቱን ቤትህ እንዳይፈርስ ይሉና ይበላሉ፣ ተማሪውን ውጤት እንድሰጥህ ይሉና ይበላሉ፣ ገበሬውን ማዳበሪያ እንድሰጥህ ይሉና ይበላሉ፣ ነጋዴውን ግብር እንድቀንስልህ ይሉና ይበላሉ አረ ስንቱ!!! የሚበሉበት መንገድ እንደ ትልቅ ከተማ ባጃጅ እጅግ በጣም የበዛ ነው፡፡ እነርሱ ግን እንደእኔ ሲያስመልሳቸው አይታዩም፡፡ እምብርት አልባ የሚባሉት እንደነዚያ ያሉት ናቸው፡፡ ስልጣናቸውን መከታ አድርገው ደሃን የሚበድሉ ፍርድ የሚያጓድሉ ያገኙትን የሚውጡ የሰው ዘንዶዎች ናቸው እኮ ጌታዬ፡፡ እርስዎስ ግብር በዝቶብዎ የፍትህ ያለህ እያሉ ሲንከራተቱ አልነበረም እንዴ? ፍትህ ማግኘት አልችል ብለው አይደል እንዴ ያን ያህል ገንዘብ ለበላተኛ የሰጡት፡፡ አሁን አርስዎ ይህንን ረስተውት ነው?” አለ ውሻው፡፡ ጌታውም ገረመው፤ የበላተኞች ሲሳይ የሆነባቸውን አጋጣሚዎችም ዞር ብሎ አስታወሳቸው፡፡ በተለይ ግብር ለማስቀነስ ብሎ ከግብሩ በላይ እቀንስልሃለሁ ላለው ሁሉ የዘራውን ገንዘብ አስታወሰ፡፡ “እሽ ሌላስ ምን አለሀ?” አለ ጌታው ውሻውን እያሻሸ፡፡ ውሻውም ቀጠለ “ጌታዬ የሰው ውሻ እኮ ይከብዳል ምክንያቱም ከሰው ጋር እንደሰው ከውሻ ጋርም እንደ ውሻ ነውና፡፡ እንዴ አኔ እኮ ውሻነቴን ጠንቅቄ አውቃለሁ ውሻ ብቻ ነኝ እነርሱ ግን የውሻና የሰው ባህሪ የተደባለቀባቸው ናቸው፡፡ እነርሱ ዛሬን እንጅ ትናንትን የማያውቁ ናቸው፡፡ እነርሱ ዛሬ መጥገባቸውን እንጅ ትናንት መራባቸውን፣ ዛሬ መበደላቸውን( በ ይላላል) እንጅ ትናንት መበደላቸውን (በ ይጠብቃል) ፣ ዛሬ መንደላቀቃቸውን እንጅ ትናንት መኮሳመናቸውን አያውቁም፡፡ ባጠቃላይ ትናንት አልባዎች ናቸው፡፡ ዛሬን እንጅ ትናንትን ዞር ብለው ማሰብ የማይፈልጉ ናቸው፡፡ አገር ወዳድ ሲባል የትናንቱን ቴዎድሮስ ሳይሆን የዛሬውን መሪ ነው የሚያስቀድሙ፡፡ የአገሩን ድንበር ያስከበረ ሲባል የትናንቱን ሚኒሊክን ሳይሆን የዛሬውን ቆርሶ ሰጥ ነው የሚያሞግሱ፡፡ አገሩን ከጠላት የጠበቀ ሲባል የሚኒልክን ጦር ጣልያንን ያሳፈረውን ሳይሆን የአገሩ ክፍል የነበረችውን ኤርትራን ተዋግቶ የተሸነፈውን የዛሬውን ወታደር ነው  የሚያደንቁ፡፡ ከኃይለ ሥላሴ ይልቅ የሞሶሎኒን ሐውልት ማቆም ነው የሚቀናቸው ፡፡ ብቻ ትናንትን ሳይሆን ዛሬን ብቻ ነው የሚያሞግሱ፡፡ ስልጣኔ የጀመረ ዛሬ እንጅ ትናንት በአክሱም ዘመነ መንግስት አይመስላቸውም፡፡ ዘመናዊ ትምህርት የተጀመረ ዛሬ እንጅ በኃይለሥላሴ ዘመን አይመስላቸውም፡፡ ታዲያ እነዚህ እኮ ታሪክ የማያውቁ ሆነው ሳይሆን የትናንትን ታሪክ መደፍጠጥ ስለሚቀናቸው ነው፡፡ አረ እኔው እውነተኛው ውሻ እሻላለሁ፡፡ ወቼው ጉድ፡፡ በሰው ባህሪ ገብቼ እዘባርቃለሁ እንዴ? እኔ እኮ ማግበስበስንም ከአባቴ፣ ከአያቴ፣ ከቅድመአያቴ የወረስኩት ነው ብያለሁ፡፡ የትናንት ማንነቴን አልዘነጋሁትም እናንተ ሰዎች ግን የትመጣችሁን ዘንግታችኋል፡፡ ማግበስበስ ቢያመሳስለንም ታሪክ ጥበቃ ግን ያለያየናል፡፡ ዛሬን ያለትናንት የሚተርከው እኮ የሰው ልጅ ነው፡፡ መቼ እንደተማሩ፣ መቼ እንደተወለዱ፣ እንዴት እንዳደጉ እኮ የዘነጉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ትናንትን ዞር ብለው ማሰብ ስለማይሹ አለቀ!!!” ሰውዬውም ማንነቱን ወደኋላ ለማዬት የሞከረው ዛሬ ከውሻው ምክር በኋላ ነበር፡፡ አስተዳደጉ ትዝ አለው፡፡ ዛሬን ትቶ ትናንትን አስታወሰ ልዩ ክስተቶችንም አስታወሰ፡፡ “እውነትም የሰው ልጅ ትናንት አልባ ዛሬን ነው ሲላዝን የሚውለው” በማለት ራሱን መከረ፡፡

Wednesday, May 20, 2015

አማርኛችን ወዴት እየሔደ ነው?

ቋንቋ መግባቢያ ነው፡፡ ከመግባቢያነቱ ባለፈ  ቋንቋ የራሱ የሆነ  የአነጋገርና የአጻጻፍ ሥርዓት አለው፡፡ አንድ ቋንቋ በራሱ ለተናጋሪው ምሉዕ (የተሟላ) እንዲሆን ዘመኑን የሚዋጁ (ዘመኑ የሚወልዳቸው) ቃላት ሊኖሩት ይገባል፡፡ እኔ ምንም እንኳ የቋንቋ ተመራማሪ ባልሆንም አንድ ቋንቋ ምን ማሟላት እንዳለበት ግን እረዳለሁ፡፡ የሰው ልጅ በበርካታ ነገሮች ሊግባባ ይችላል፡፡ የሚግባባበት ሁሉ ግን ቋንቋ አይደለም፡፡ ወፎችም፣ እንስሳትም ሁሉም ይግባባሉ (የራሳቸው የሆነ መግባቢያ አላቸው) ነገር ግን ቋንቋ የላቸውም፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ሥልጣኔ ውስጥ አብራ የሰለጠነች በዘመናት መካከልም አብራ የዘመነች እንደሆነች በርካታ ማስረጃዎችን ማንሣት እንችላለን፡፡ አክሱም ሐውልትን የመሰለ ልዩ ምህንድስና ያለበት፣ ላሊበላን የመሰለ ልዩ ጥበብ የፈለቀበት፣ ልዩ የሆነውን 13 ወራት የሚይዘው የቀን አቆጣጠር ሃብታችን፣ የራሳችን የሆነው የፊደል ገበታችን ስልጣኔያችን ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር በቂ ማሳያዎቻችን ናቸው፡፡ በርካታ አገራት ፊደላትን ከሌሎች እየተዋሱ ሲጠቀሙ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያ ይህንን የመሰለውን የራሷ የሆነውን ብርቅየ ቋንቋ ከነፊደሉ ማዘጋጀቷ ትልቅ እና የጥበብ መፍለቂያ አገር እንደነበረች ያስረዳናል፡፡
የግዕዝ ፊደላት አማርኛ ቋንቋ ውስጥ የምንጠቀምባቸው ብቸኛ ፊደላት ናቸው፡፡ ቃላት እንደዘመናት መፈራረቅ ሁሉ ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይሞታሉ፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ የቃላት ዑደት በማንኛውም ቋንቋ ዘንድ እንደሚኖር አልጠራጠርም፤ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ግን አለ፡፡ አሁን አሁን ግን እየተወለዱ ያሉት ቃላት አማርኛ አማርኛ የማይሸቱ እየሆኑ በመምጣታቸው ለአማርኛ ቋንቋችን ከፍተኛ ተጽእኖን እያሳደሩ ናቸው፡፡ በቋንቋችን አፍረን ለሌላ ቋንቋ ልባችንን ከፍተን የማንነታችን መታወቂያ የሆነውን ቋንቋ በርዘነዋል፡፡ የተወሰነውን የቋንቋ ባህሪ ለሌላው በማውረስ ቃላትን የምንፈጥር አለን፡፡ ለምሳሌ እንመልከት፡- ኮምፒዩተር የሚለው ቃል እንግሊዝኛ ነው እኛ እንደአማርኛ ኮምፒዩተሮች እያልን አናረባዋለን፡፡ አበበ የኮምፒዩተርኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር ብለንም ማስታወቂያ እንሰራለን፡፡ የእንግሊዝኛ ቃላትን ከአማርኛ ቃላት ጋር በማጣመርም ቃል የፈጠርን የሚመስላቸው ሞኞች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡ መስከረም ባርሬስቶራንትፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ሳይንስቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ፣ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ሬጅስትራር ጽ/ቤት፣ አርቲስት እገሌ፣ ኢንጅነር እገሌ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የፋይናንስ አስተዳደር፣ የኮምፒዩተርኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር  አረ ስንቱ፡፡ በአማርኛ ፊደል  መጻፉ ብቻ አማርኛ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ይኼ ደግሞ በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ባህሪ የጎደለው ግድየለሽነት ነው፡፡ በዚህ የምንቀጥል ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ፊደላችን ብቻ ሊቀር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እንግሊዝኛን ከአማርኛ ጋር ቀላቅሎ  መናገር ትልቅነት የሚመስላቸው በርካታዎች ናቸው፡፡ እንግሊዝኛ ማለት አማርኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ጣልያንኛ ወዘተ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ቋንቋዎች፣ መግባቢያዎች ስለሆኑ፡፡ አለቀ፡፡ ማግባባት ከቻለ የእኛው አማርኛ ምኑ ላይ ነው ድክመት ያለበት? የተለያዩ ቋንቋዎችን መቻል በጣም ጥሩ ነው ደስም ይላል፡፡ ምክንያቱም ብዙ እውቀት ልናገኝበት የምንችልበትን እድል ስለሚከፍቱ፡፡ ነገር ግን አንዱን ከአንዱ ጋር እየቀላቀሉ መናገርም ሆነ መጻፍ አላዋቂነት ነው፡፡
በተለያዩ ቦታዎች የተጻፉ ማስታወቂያዎችን ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? አንድ ከተማ ውስጥ ግቡ እና ማስታወቂያዎችን ተመልከቱ ሙሉ አማርኛ አታገኙም፡፡ እኔ ባለሁበት አካባቢ ጥቂቶችን ልግለጽላችሁ፡፡ ጎዛምን ሆቴልኤፍ. ኤም ኢንተርናሽናል ሆቴልስታር ቢዝነስ ግሩፕፎቶ ስታርፓራዳይዝ ሕንጻ፣ አበበ የኮምፒዩተርኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር፣ማርታ ጁስ መሸጫ ወዘተ ዘርዝሬ መግለጽ አልችልም በእርግጥ፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም የዚህ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ፋይናንስና ግዥ አስተዳደር፣  የታክስኦዲት ባለስልጣን፣ የፌዴራል ኦዲተር፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትዳይሬክተርዲፓርትመንት ሄድ፣ ምርጫ ቦርድ፣ የገንዘብና  ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ወዘተ … እነዚህ ሁሉ በአማርኛ የተጻፉ በአማርኛ የቃላት እርባታ እንደአስፈላጊነቱ እየረቡ ያሉ ናቸው፡፡ ለነገው ትውልድ ምንድን ነው የምናወርሰው? ይህን የተበረዘ አማርኛችንን ነው? የመንግስት ተቋማትስ ምን እየሰሩ ነው? የአማርኛ ትምህርት ክፍልስ ምን አይነት መምህራንና ተማሪዎችን እያፈራ ነው? መቼ ይሆን በራሳችን ፊደል የራሳችንን ቋንቋ ብቻ የምንጽፍበት? ሁኔታው አሳሳቢ ነው፡፡ አንድ ደብዳቤ ምን ያህል የእንግሊዝኛ ቃላትን በአማርኛ ፊደላት እንደተጠቀመ በየአጋጣሚው  የሚጻፉ ደብዳቤዎችን ተመልከቱ፡፡ በውኑ የአማርኛ ቋንቋ መግለጽ የማይችለው ነገር አለን? ካለስ የአማርኛ ምሁራን ሰብሰብ ብለው ለዚያ ነገር አዲስ የአማርኛ ቃልን መውለድ (መፍጠር) እንዴት ተሳናቸው? በዚህ ችግር እስከመቼ እንቆይ ይሆን?
ታዲያ መፍትሔው ምን ሊሆን ይችላል? በመጀመሪያ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ተናጋሪው በራሱ ትክክለኛውን አማርኛ መናገር አለበት፡፡ ሁለተኛም የአማርኛ ምሁራን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በመጨረሻ መንግሥትም ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል፡፡ ከራሱ መሥሪያ ቤቶች ስያሜ በመጀመር፡፡ የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን የወሰነ መንግስት የመገናኛ ብዙኃኑን (EBC) ማለቱ በጣም የሚያናድድና የሚያበሳጭ ነው፡፡ ኢብኮ- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ‹‹ብሮድካስቲንግ - ኮርፖሬሽን›› የትኛው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ ነው እነዚህ ቃላት የሚገኙት? ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ትልቁን ድርሻ ሊወስድ ይገባዋል፡፡ ማደግ የምንችለው በራሳችን ሃብት መጠቀም ስንችል ብቻ ነው፡፡  ቋንቋችን ደግሞ ትልቁ ሃብታችን ነው፡፡ ቻይና ለማደጓ ምሥጢሩ የራሷን ቋንቋ መጠቀሟ ነው፡፡ እኛም ማደግ የምንችለው በራሳችን ቋንቋ መጠቀም ስንችል ብቻ ነው፡፡


Monday, May 18, 2015

የማስመሰል አባዜ

ማስመሰል ማለት መሆን ማለት እንዳይደለ ሁሉም ይስማማበታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ልዩ ስጦታ ያለው ሰው የተለያዩ እንስሳትን ድምጽ ያስመስላል ነገር ግን እነዚያን እንስሳት ሊሆን አይችልም፡፡ እንዴት ሆኖ አረ በፍጹም!!! ሰው የእንስሳ ድምጽን ከማስመሰል አልፎ እንስሳቱን ራሳቸውን ሊሆን የሚችልበት ተሰጥኦ የለውም፡፡ አንዳንዶች የሰውን ልጅ የማስመሰል ጥበብ የተረዱ አይመስለኝም፡፡ በርካታ የሚባሉ ወጣቶች በማስመሰል ጥበብ ውስጥ እጅግ የተካኑ ባለሙያዎች እየሆኑ መምጣታቸው የማይካድ እውነታ ነው፡፡ አንድ ወጣት አንዲትን ወጣት በዝሙት ለመጣል ከፈለገ የማስመሰል ጥበቡን ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ የማስመሰል ጥበብ የሚጀመረው ዝም ብሎ ከምድር ተነሥቶ አይደለም፡፡ ማስመሰል ከመጀመሩ በፊት በማስመሰል ስለሚጥሉት ሰው ወይም አገር ልዩ ባህሪ ማዎቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ወጣት በዝሙት ሊጥላት በልቡ ኃጢአትን ከጸነሰ በኋላ ያች ወጣት ምን ትወዳለች? ምንስ ትጠላለች? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይጠበቅበታል፡፡ የምትወደውንና የምትጠላውን ከተረዳ በኋላ ወደማስመሰል ጥበቡ ይጓዛል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ያች ወጣት ጥሩ መንፈሳዊ የቤተክርስቲያን ልጅ ከጾምና ጸሎት ውጭ ሌላ የማታውቅ ሆና ካገኛት እርሱም እንደዚያ ይመስላል፡፡ ጥሩ መንፈሳዊ ይመስላል፡፡ ነጠላውን መስቀለኛ ለብሶ ትልቅ የጸሎት መጽሐፍ ይዞ ያች ወጣት በምትገባበትና በምትወጣበት ሰዓት እየጠበቀ መታየትን ምርጫው ያደርጋል፡፡ ቀስ በቀስም ሰላምታ መለዋወጥን፣ መተዋወቅን፣ በአፉም ሰው ከሚመለከተው ማንነቱ ባለፈ እጅግ የበዙ ሥራዎችን እንደሠራ መንገር ይጀምራል፡፡ በዚህ የማስመሰል ጥበብ ውስጥ ትክክለኛውን ነገር የማትገነዘበው ወጣት በፍጹም መንፈሳዊ ፍቅር በወንድምነት እስከመኖሪያ ቤቱ ድረስ የምትሄድበትን እድል ሲያመቻችላት ትከተለዋለች፡፡ በስተመጨረሻም እርሱ ያን የማስመሰል ሰይጣናዊ ጥበቡን ተጠቅሞ የወደደውን ያደርጋል፡፡ ሴት እህቶቻችን እዚህ ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ልትወስዱ ያስፈልጋል፡፡ ነጠላ ለባሽ ሁሉ መንፈሳዊ፣ ቀዳሹ ሁሉ ዲያቆን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ሁሉ ሰባኪ፣ ድምጽ ማጉያውን የያዘው ሁሉ ዘማሪ፣ የጸሎት መጽሐፍ ያነገበው ሁሉ ጸሎተኛ አይደለም፡፡ የሰው ማንነቱ ከውስጡ የተደበቀ እንጅ ከላይ የምንመለከተው አይደለም፡፡
ማስመሰል ለምን ያገለግላል?
ሰዎች ማስመሰልን ለበርካታ ነገሮች ይጠቀሙበታል፡፡ ለተቀደሰ ዓላማ ማስመሰልን የተጠቀመው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ያላመኑትን ለማሳመን፣ ያልተጠመቁትን ለማስጠመቅ፣ ያልተማሩትን ለማስተማር ቅዱስ ጳውሎስ ሳይታመም የታመመ መስሎ ከታመሙት ጋር አብሮ ተኝቶ ብዙ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት መልሷል፡፡ አብዛኞቻችን ግን ማስመሰልን የምንጠቀመው ለኃጢአት ሥራ ብቻ ነው፡፡ ከላይ ከአገሪቱ መሪ እስከታች ተራው ሰው ድረስ ማስመሰልን የምንጠቀመው የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ብቻ ነው፡፡ በቅርበት የማያዩን ሰዎች እውነት እንደሆነ እንዲረዱን ስንሻ ማስመሰልን አማራጭ እናደርጋለን፡፡ ልማትን በማስመሰል፣ ምርጫን በማስመሰል፣ መንገድን በማስመሰል፣ ባቡርን በማስመሰል፣ ግድብን በማስመሰል፣ ትምህርትን በማስመሰል፣ ጤናን በማስመሰል አረ  ስንቱን ብቻ ሁሉንም በማስመሰል የውጭ ብድር እና እርዳታ ማግኘትን የሚሻ መንግሥት አለ፡፡ ለምን ማስመሰልን መፍትሄው አደረገ? ካልን መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ለታይታ በማስመሰል የውጭ መንግስታትን ድጋፍ ለማግኘት ስለሚፈልግ ነው፡፡ እነዚያ ረጅ ድርጅቶች የሚመለከቱት በወረቀት የሰፈረውን እንጅ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ እውነታ አይደለም፡፡ ጸሎት ምን እንደሆነ የማያውቅ የኔቢጤ የሚፈልገውን ለማግኘት ሲል በማስመሰል ለምድ ተደብቆ ትልቁን የጸሎት መጽሐፍ ይዞ ቤተክርስቲያን ይሄዳል፡፡ የሚፈልገውን በዚህ መልኩ ማግኘት የለመደ ሰው ሁሌም ሲያስመስል እንጅ ሲሆን አናየውም፡፡ በለምድ ውስጥ ተደብቆ የራሱን የተደበቀ ሥራ ብቻ የሚሠራ ሰው ሁሌም አስመሳይ ነው፡፡
ሌላው ማስመሰልን ተከታይ ወይም ደጋፊ ለማፍራት የሚጠቀሙበትም አሉ፡፡ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ማስመሰልን ለዚህ ዓላማ የሚጠቀሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ ተሐድሶ መናፍቃን የቤተክርስቲያን ልጆች ሳይሆኑ እንደሆኑ አስመስለው የእግር ኳስ ደጋፊ የሚመስል “ክርስቲያን” ያፈራሉ፡፡ ሳይማሩ በማእረግ ስሞች ውስጥ ተደብቀው “ዲያቆን፣ መምህር፣ መጋቢ ሐዲስ …” በሚለው የማጭበርበሪያ ስልት ተጠቅመው ወገኖቻችንን ለመናፍቃን አዳራሽ ያዘጋጁ በርካታዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ነቅተን ራሳችንን፣ አገራችንን፣ ቤተክርስቲያናችንን፣ ወገናችንን ልንጠብቅ ያስፈልጋል፡፡ በማስመሰል ሥራ የተሰማራን ካለንም ከዚህ ድርጊታችን ልንቆጠብ ይገባናል፡፡
                                                                                                  መልካሙ በየነ (ወልደ ማርያም)

Friday, May 15, 2015

“ለካ ጊዜው ኖሯል”

አንድ ስሙን ለጊዜው የማላስታውሰው ሰው እንዲህ የሚል አባባል አለው “ALL COLOURS WILL AGREE IN THE DARK”. ይህን አባባሉን ሳነበው ትልቅ መልእክት እንዳለሁ ልቤ ተረዳ፡፡ የተረዳው ልቤም መላ አካላቴን አነቃቃው እና አጆቼን ወደ መጻፊያ ሰሌዳው ወሰዳቸው፡፡ በዚያም የሚንኳኳውን የመጻፊያ ሰሌዳ በእኛው በአገራችን በለመድነው ቋንቋ እንዲጽፍ የመጻፊያ ስልቱን ቃኘሁት (ቀየርኩት)፡፡ ከዚያም ይህንን ቁም ነገር በኢትዮጵያዊ ለዛው ተናዘዝሁ፡፡
“ፀሐይኒ አእመረ ምዕራቢሁ፣ ታመጽእ ጽልመተ ወይከውን ሌሊተ” መዝ 103÷20 እንዳለው ነቢዩ  ቅዱስ ዳዊት፡፡ “ፀሐይም መግቢያውን አወቀ፣ ጨለማን ታመጣለህ ሌሊትም ይሆናል” በሚለው ግርድፍ አማርኛ እንቀይረውና በምንግባባበት መጠን እንግባባ፡፡ ለማንኛውም ግእዙን በቀጥታ የመፍታት አቅሜ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ የምትረዱት እንደሆነ ባውቅም ከዋናው የቅዱስ ዳዊት ሃሳብ ግን እምብዛም የራቅሁ አይመስለኝም፡፡ ይህንን ጥቅስ የመረጥኩት ሌሊት የሚባለው የጊዜ ቀመር ፀሐይ የምትጠልቅበት ጊዜ እንደሆነ እንረዳ ዘንድ ነው፡፡ ነገርን ነገር ያመጣዋልና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 3 ቀናት እና 3 ሌሊት በከርሰ መቃብር ማደሩን የምንቆጥረው አንዱ በዚህ አቆጣጠር ዘዴ ነው፡፡ አርብ ከቀኑ 11 ሰዓት ወደ መቃብር ወረደ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሌሊት 6 ሰዓት ተነሣ በጠቅላላው 31 ሰዓታት ማለት ነው፡፡ ይህን ነገር በምንም አይነት ቀመር 3 ቀን እና 3 ሌሊት ማለት አይቻልም፡፡ 1 ቀን እኩል ይሆናል 24 ሰዓት ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ 3 ቀናት 36 ሰዓታት 3 ሌሊት 36 ሰዓታት በጠቅላላው  72 ሰአታትን በከርሰ መቃብር ማደር ነበረበት፡፡ ነገር ግን ቀመሩ እንዲህ አይደለም፡፡ አቆጣጠሩ ፀሐይ ስትኖር ቀን፤ ስትጠልቅ ደግሞ ሌሊት በሚል ቀመር ነው፡፡ አርብ ከተያዘበት እስከተሰቀለበት 6 ሰዓት ድረስ( 1ኛቀን)፣ ከ 6- 9 ሰዓት ጨለማ ሆነ (1ኛሌሊት)፣ ከ9-11 ሰዓት ብርሃን ሆነ(2ኛቀን)፣ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ(2ኛ ሌሊት)፣ ቅዳሜ ሙሉ ቀን(3ኛ ቀን)፣ ቅዳሜ ለእሁድ እስከተነሣበት ድረስ(3ኛ ሌሊት)፡፡ በእርግጥ ሌላ አቆጣጠርም አለው ነገር ግን ከዚህ ሃሳብ ጋር የሚመሳሰለው ይኼኛው አቆጣጠር ስለሆነ ብቻ በዚህ እናብቃ፡፡ በአጠቃላይ ሌሊት ማለት ጨለማ የሚሆንበት  ወይም ፀሐይ የምትጠልቅበት ጊዜ ማለት ነው፡፡
ሌሊት ምን እንደሆነ ከተረዳን ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡ የዚያ የማላውቀው ሰውዬ አባባል ከሞላ ጎደል በግርድፉ እኔ በተረዳሁበት አገላለጽ  እንዲህ አልኩት ፡- “በጨለማ ሁሉም ቀለሞች ይስማማሉ”፡፡ ቀይ ቀይ የሚሆነው ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ አረንጓዴም አረንጓዴ የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ቢጫም ቢጫ የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ሰማያዊም ሰማያዊ  የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ነጭም ነጭ የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ  ቀለም ቀለም  የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ለካ ቀይ የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ለካ አረንጓዴም  የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ ለካ ቢጫም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ለካ ሰማያዊም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ለካ ነጭም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለካ የቀለም አይነቶችን የምንዘረዝረው  በፀሐይ ነው፡፡ ቀለምን ቀለም የሚያሰኘው ለካ ጊዜው ኖሯል፡፡ ለካ ቀለሞች ያልተስማሙት አንድ ያልሆኑት ፀሐይ ስላለች ነው፡፡
አሁን ምልከታዬ ሰፋ እያለ መጣ፡፡ ለካ ሃብታም ሃብታም የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ደሃም ደሃ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ለካ ባለሥልጣንም  ባለሥልጣን  የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ አልቃሽም አልቃሻ  የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ የራበውም ረሃብተኛ  የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ካገሩ የወጣም ስደተኛ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ የተቸገረ ሰውም ችግረኛ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ የታመመ ሰውም በሽተኛ  የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ያልተማረ ሰውም ማይም የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ጊዜ የማይለውጠው ዘመን የማይሽረው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ ለካ ሁሉም በጊዜ ይለወጣል፣ በዘመንም ይሻራል፡፡
እኔ ደሃ ነኝ አንድ ቀን ግን ከሃብታሙ ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ ረሃብተኛ ነኝ አንድ ቀን ግን ከጠገቡት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ አልቃሻ ነኝ አንድ ቀን ግን ከሚስቁት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡  እኔ ችግረኛ  ነኝ አንድ ቀን ግን ካልተቸገሩት  ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ በሽተኛ ነኝ አንድ ቀን ግን ከጤነኞች ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ ያልተማረኩ ማይም ነኝ አንድ ቀን ግን ከተማሩት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ ይህ አንድ የሚያደርገኝ  ቀን ሩቅ አይደለም ቅርብ ነው፡፡ ቀለሞችን ሁሉ አንድ ያደረጋቸው ጨለማ እኔ ጋርም አለ፡፡ እርሱ አንድ ቀን ከሌሎች ጋር አንድ ያደርገኛል፡፡ ትልልቅ መሪዎች፣ አስፈሪ ወታደሮች፣ የተከበሩ ምሑራን፣ ሁሉ የሞላቸው ባለጠጎች፣ ሕዝብን በግፍ ያንገላቱ ጨካኞች፣ ፀሐይ ስትወጣላቸው የምንፈራቸው፣ በሥልጣን ኮርቻ ሲቀመጡ የበደሉን ሁሉ ነገ አንድ እንሆናለን፡፡ ቀይ፣ አረንጓዴ ፣ቢጫ፣ ሰማያዊ፣ ነጭ በጨለማ ሁሉም ተስማምተው ጥቁር እንደሚሆኑ ሁሉ እኛም እነደዚሁ  የማንረታው፣ ጥበባችን የማያርቀው፣ መቼ እንደሚመጣ የማናውቀው ፣ ባለሥልጣን፣ ሃብታም፣ ደሃ የማይለየው ለሁሉም እኩል የሚፈርደው ሞት ሲመጣ ያኔ እኩል እንሆናለን፡፡ የተበደለው ከበደለው ጋር፣ የተገደለው ከገደለው ጋር፣ ያለቀሰው ካስለቀሰው ጋር፣ በግፍ የተንገላታው ከአንገላታው ጋር፣ የተንቋሸሸው ከአንቋሸሸው ጋር፣ የተደበደበው ከደበደበው ጋር፣ የተሰደደው ከአሳደደው ጋር፣ የተገረፈው ከገረፈው ጋር፣ የተሰረቀው ከሰረቀው ጋር፣ የተደፈረው ከደፈረው ጋር፣ የተሸማቀቀው ካሸማቀቀው ጋር፣ የተመራው ከመሪው ጋር፣ የተቀለደበት ከቀለደበት ጋር… ፩ ቀን ፩ እንሆናለን፡፡ ሕይወት አላስማማን ቢልም  ቅሉ ፩ ቀን ግን ሞት ያስማማናልና በዚህ እንጽናናለን፡፡ ለካ አላስማማን ያለ ጊዜው ነው፡፡ የፀሐይ መኖር አላስማማቸው ያሉ ቀለሞች በጨለማ ሁሉም ጥቁር ሆነው እንደሚስማሙ ሁሉ ጊዜው ሲደርስ በሕይወት አልስማማ ያልን ሁሉ በሞታችን እንስማማለን፡፡