ማስመሰል ማለት መሆን ማለት እንዳይደለ ሁሉም ይስማማበታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ልዩ ስጦታ ያለው ሰው የተለያዩ እንስሳትን ድምጽ ያስመስላል ነገር ግን እነዚያን እንስሳት ሊሆን አይችልም፡፡ እንዴት ሆኖ አረ በፍጹም!!! ሰው የእንስሳ ድምጽን ከማስመሰል አልፎ እንስሳቱን ራሳቸውን ሊሆን የሚችልበት ተሰጥኦ የለውም፡፡ አንዳንዶች የሰውን ልጅ የማስመሰል ጥበብ የተረዱ አይመስለኝም፡፡ በርካታ የሚባሉ ወጣቶች በማስመሰል ጥበብ ውስጥ እጅግ የተካኑ ባለሙያዎች እየሆኑ መምጣታቸው የማይካድ እውነታ ነው፡፡ አንድ ወጣት አንዲትን ወጣት በዝሙት ለመጣል ከፈለገ የማስመሰል ጥበቡን ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ የማስመሰል ጥበብ የሚጀመረው ዝም ብሎ ከምድር ተነሥቶ አይደለም፡፡ ማስመሰል ከመጀመሩ በፊት በማስመሰል ስለሚጥሉት ሰው ወይም አገር ልዩ ባህሪ ማዎቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ወጣት በዝሙት ሊጥላት በልቡ ኃጢአትን ከጸነሰ በኋላ ያች ወጣት ምን ትወዳለች? ምንስ ትጠላለች? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይጠበቅበታል፡፡ የምትወደውንና የምትጠላውን ከተረዳ በኋላ ወደማስመሰል ጥበቡ ይጓዛል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ያች ወጣት ጥሩ መንፈሳዊ የቤተክርስቲያን ልጅ ከጾምና ጸሎት ውጭ ሌላ የማታውቅ ሆና ካገኛት እርሱም እንደዚያ ይመስላል፡፡ ጥሩ መንፈሳዊ ይመስላል፡፡ ነጠላውን መስቀለኛ ለብሶ ትልቅ የጸሎት መጽሐፍ ይዞ ያች ወጣት በምትገባበትና በምትወጣበት ሰዓት እየጠበቀ መታየትን ምርጫው ያደርጋል፡፡ ቀስ በቀስም ሰላምታ መለዋወጥን፣ መተዋወቅን፣ በአፉም ሰው ከሚመለከተው ማንነቱ ባለፈ እጅግ የበዙ ሥራዎችን እንደሠራ መንገር ይጀምራል፡፡ በዚህ የማስመሰል ጥበብ ውስጥ ትክክለኛውን ነገር የማትገነዘበው ወጣት በፍጹም መንፈሳዊ ፍቅር በወንድምነት እስከመኖሪያ ቤቱ ድረስ የምትሄድበትን እድል ሲያመቻችላት ትከተለዋለች፡፡ በስተመጨረሻም እርሱ ያን የማስመሰል ሰይጣናዊ ጥበቡን ተጠቅሞ የወደደውን ያደርጋል፡፡ ሴት እህቶቻችን እዚህ ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ልትወስዱ ያስፈልጋል፡፡ ነጠላ ለባሽ ሁሉ መንፈሳዊ፣ ቀዳሹ ሁሉ ዲያቆን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ሁሉ ሰባኪ፣ ድምጽ ማጉያውን የያዘው ሁሉ ዘማሪ፣ የጸሎት መጽሐፍ ያነገበው ሁሉ ጸሎተኛ አይደለም፡፡ የሰው ማንነቱ ከውስጡ የተደበቀ እንጅ ከላይ የምንመለከተው አይደለም፡፡
ማስመሰል ለምን ያገለግላል?
ሰዎች ማስመሰልን ለበርካታ ነገሮች ይጠቀሙበታል፡፡ ለተቀደሰ ዓላማ ማስመሰልን የተጠቀመው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ያላመኑትን ለማሳመን፣ ያልተጠመቁትን ለማስጠመቅ፣ ያልተማሩትን ለማስተማር ቅዱስ ጳውሎስ ሳይታመም የታመመ መስሎ ከታመሙት ጋር አብሮ ተኝቶ ብዙ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት መልሷል፡፡ አብዛኞቻችን ግን ማስመሰልን የምንጠቀመው ለኃጢአት ሥራ ብቻ ነው፡፡ ከላይ ከአገሪቱ መሪ እስከታች ተራው ሰው ድረስ ማስመሰልን የምንጠቀመው የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ብቻ ነው፡፡ በቅርበት የማያዩን ሰዎች እውነት እንደሆነ እንዲረዱን ስንሻ ማስመሰልን አማራጭ እናደርጋለን፡፡ ልማትን በማስመሰል፣ ምርጫን በማስመሰል፣ መንገድን በማስመሰል፣ ባቡርን በማስመሰል፣ ግድብን በማስመሰል፣ ትምህርትን በማስመሰል፣ ጤናን በማስመሰል አረ ስንቱን ብቻ ሁሉንም በማስመሰል የውጭ ብድር እና እርዳታ ማግኘትን የሚሻ መንግሥት አለ፡፡ ለምን ማስመሰልን መፍትሄው አደረገ? ካልን መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ለታይታ በማስመሰል የውጭ መንግስታትን ድጋፍ ለማግኘት ስለሚፈልግ ነው፡፡ እነዚያ ረጅ ድርጅቶች የሚመለከቱት በወረቀት የሰፈረውን እንጅ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ እውነታ አይደለም፡፡ ጸሎት ምን እንደሆነ የማያውቅ የኔቢጤ የሚፈልገውን ለማግኘት ሲል በማስመሰል ለምድ ተደብቆ ትልቁን የጸሎት መጽሐፍ ይዞ ቤተክርስቲያን ይሄዳል፡፡ የሚፈልገውን በዚህ መልኩ ማግኘት የለመደ ሰው ሁሌም ሲያስመስል እንጅ ሲሆን አናየውም፡፡ በለምድ ውስጥ ተደብቆ የራሱን የተደበቀ ሥራ ብቻ የሚሠራ ሰው ሁሌም አስመሳይ ነው፡፡
ሌላው ማስመሰልን ተከታይ ወይም ደጋፊ ለማፍራት የሚጠቀሙበትም አሉ፡፡ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ማስመሰልን ለዚህ ዓላማ የሚጠቀሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ ተሐድሶ መናፍቃን የቤተክርስቲያን ልጆች ሳይሆኑ እንደሆኑ አስመስለው የእግር ኳስ ደጋፊ የሚመስል “ክርስቲያን” ያፈራሉ፡፡ ሳይማሩ በማእረግ ስሞች ውስጥ ተደብቀው “ዲያቆን፣ መምህር፣ መጋቢ ሐዲስ …” በሚለው የማጭበርበሪያ ስልት ተጠቅመው ወገኖቻችንን ለመናፍቃን አዳራሽ ያዘጋጁ በርካታዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ነቅተን ራሳችንን፣ አገራችንን፣ ቤተክርስቲያናችንን፣ ወገናችንን ልንጠብቅ ያስፈልጋል፡፡ በማስመሰል ሥራ የተሰማራን ካለንም ከዚህ ድርጊታችን ልንቆጠብ ይገባናል፡፡
መልካሙ በየነ (ወልደ ማርያም)
No comments:
Post a Comment