አንድ ውሻ ነበር አሉ፡፡ ይህ ውሻ እንደማንኛውም
ውሻ ያው ውሻ ነው፤ እርሱን ከሌላው ልዩ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ እናም ይህ ውሻ ጠገብኩ በቃኝን ሳይሆን ራበኝ አብሉኝን ከዚያ
ውጭ ግን እበላችኋለሁ በማለት የሚያስፈራራ ነው፡፡ የሰጡትን ሁሉ በቃኝ ሳይል ንጹሁን ከቆሻሻ ሳይለይ የሚያግበሰብስ በቃኝ የሚለው
ቃል የተዘነጋው ነው፡፡ ሲፈልግ ጌታውን አስፈቅዶ ሲፈልግ የጌታውን ጓዳ በርብሮ ያግበሰብሳል፡፡ አንድ ቀን ጌታው ተገረመ እና
“አንተ ግን ለምን በቃኝ አትልም” አለው፡፡ ውሻም መለሰ “እንዴ ጌታዬ ከማን የተማርኩትን” ብሎ አረፈው፡፡ ጌታውም እርሱን የሰደበው
ስለመሰለው በጣም ተበሳጨና “ውሻ መቼም ውሻ ነው ከማን ተማርኩት ልትል ነው ደግሞ!” አለው፡፡ “ከአባቴ፣ ከአያቴ፣ ከቅድመ አያቴ
ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልዩ ስጦታዬ ነው” በማለት የዘሩ እንደሆነ ገለጸ፡፡ ጌታም “እኔ እኮ ከአንተ ነው የተማርኩት ልትለኝ መስሎኝ
በጣም ተናድጄብህ ነበር” አለው፡፡ “እርስዎንስ አይደለም” ብሎ መለሰ፡፡ “በነገራችን ላይ ግን እምብርት የሚባል ነገር አልፈጠረብህም እንዴ” አለው ጌታው፡፡ “ጌታዬ እርስዎ
እኮ የእኔን ልዩ ባህሪ አልተረዱም ማለት ነው” አለ ውሻ፡፡ “ምን አይነት ባህሪ አለህ መቼም ያው ማግበስበስ ብቻ!” አለው፡፡
“እርስዎ የሚመለከቱ ማግበስበሴን እንጅ የት እንደማጠራቅመው አያውቁም፡፡ በእናንተ በሰዎች ዘንድስ ይህ አይነት ነገር አለ አይደለም
እንዴ? የአገር ሃብትን በቃኝ ሳይሉ የሚያግበሰብሱ ሙሰኞች ሞልተው የለም እንዴ? እነዚህ ሰዎች እኮ ከእኔ አባቶችና አያቶች በሚገባ
የተማሩ የሰው ውሾች ናቸው፡፡ እነዚህ እኮ ሲያግበሰብሱ እንጅ በቃኝ ሲሉ፣ ሲያጠራቅሙ አይታዩም፡፡ ዛሬ ያገኙትን ሁሉ ያግበሰብሳሉ፤
ትናንት ምን እንዳግበሰበሱ እንኳ አያውቁም ምክንያቱም የሚያግበሰብሱት እጅግ በጣም ብዙ ስለሆነ፡፡ እኔ ያገኘሁትን ሁሉ እበላለሁ
በቃኝን አላውቅም ሆዴ በጣም ሲሞላ እኔ ብቻ ከማውቃት ቦታ ሄጄ አስወጣዋለሁ(እመልሰዋለሁ)፡፡ ነገ ሌላ የምመገበው ካላገኘው ያንን
ትናንት የመለስኩትን እመገባለሁ፡፡ እነዚህ የናንተ ሰዎች ግን ትናንት ያጠራቀሙትን ነገር ዛሬ አይጠቀሙበትም ምክንያቱም በየቀኑ
የሚበሉት አያጡማ፡፡ የሚበሉትን ማግኘት እኮ ለእኛ የሚከብደንን ያህል ለእነርሱ እጅግ በጣም ሲበዛ ቀላል ነው፡፡ ሥራ አጡን ሥራ
ላስይዝህ ይሉና ይበላሉ፣ አገር ለቆ መሰደድ የሚፈልገውን ከደላላ ላገናኝህ ይሉና ይበላሉ፣ መታወቂያ ፈላጊውን ቶሎ እንድሰጥህ ክፈል
ይሉና ይበላሉ፣ ባለመኖሪያ ቤቱን ቤትህ እንዳይፈርስ ይሉና ይበላሉ፣ ተማሪውን ውጤት እንድሰጥህ ይሉና ይበላሉ፣ ገበሬውን ማዳበሪያ
እንድሰጥህ ይሉና ይበላሉ፣ ነጋዴውን ግብር እንድቀንስልህ ይሉና ይበላሉ አረ ስንቱ!!! የሚበሉበት መንገድ እንደ ትልቅ ከተማ ባጃጅ
እጅግ በጣም የበዛ ነው፡፡ እነርሱ ግን እንደእኔ ሲያስመልሳቸው አይታዩም፡፡ እምብርት አልባ የሚባሉት እንደነዚያ ያሉት ናቸው፡፡
ስልጣናቸውን መከታ አድርገው ደሃን የሚበድሉ ፍርድ የሚያጓድሉ ያገኙትን የሚውጡ የሰው ዘንዶዎች ናቸው እኮ ጌታዬ፡፡ እርስዎስ ግብር
በዝቶብዎ የፍትህ ያለህ እያሉ ሲንከራተቱ አልነበረም እንዴ? ፍትህ ማግኘት አልችል ብለው አይደል እንዴ ያን ያህል ገንዘብ ለበላተኛ
የሰጡት፡፡ አሁን አርስዎ ይህንን ረስተውት ነው?” አለ ውሻው፡፡ ጌታውም ገረመው፤ የበላተኞች ሲሳይ የሆነባቸውን አጋጣሚዎችም ዞር
ብሎ አስታወሳቸው፡፡ በተለይ ግብር ለማስቀነስ ብሎ ከግብሩ በላይ እቀንስልሃለሁ ላለው ሁሉ የዘራውን ገንዘብ አስታወሰ፡፡ “እሽ
ሌላስ ምን አለሀ?” አለ ጌታው ውሻውን እያሻሸ፡፡ ውሻውም ቀጠለ “ጌታዬ የሰው ውሻ እኮ ይከብዳል ምክንያቱም ከሰው ጋር እንደሰው
ከውሻ ጋርም እንደ ውሻ ነውና፡፡ እንዴ አኔ እኮ ውሻነቴን ጠንቅቄ አውቃለሁ ውሻ ብቻ ነኝ እነርሱ ግን የውሻና የሰው ባህሪ የተደባለቀባቸው
ናቸው፡፡ እነርሱ ዛሬን እንጅ ትናንትን የማያውቁ ናቸው፡፡ እነርሱ ዛሬ መጥገባቸውን እንጅ ትናንት መራባቸውን፣ ዛሬ መበደላቸውን(
በ ይላላል) እንጅ ትናንት መበደላቸውን (በ ይጠብቃል) ፣ ዛሬ መንደላቀቃቸውን እንጅ ትናንት መኮሳመናቸውን አያውቁም፡፡ ባጠቃላይ
ትናንት አልባዎች ናቸው፡፡ ዛሬን እንጅ ትናንትን ዞር ብለው ማሰብ የማይፈልጉ ናቸው፡፡ አገር ወዳድ ሲባል የትናንቱን ቴዎድሮስ
ሳይሆን የዛሬውን መሪ ነው የሚያስቀድሙ፡፡ የአገሩን ድንበር ያስከበረ ሲባል የትናንቱን ሚኒሊክን ሳይሆን የዛሬውን ቆርሶ ሰጥ ነው
የሚያሞግሱ፡፡ አገሩን ከጠላት የጠበቀ ሲባል የሚኒልክን ጦር ጣልያንን ያሳፈረውን ሳይሆን የአገሩ ክፍል የነበረችውን ኤርትራን ተዋግቶ
የተሸነፈውን የዛሬውን ወታደር ነው የሚያደንቁ፡፡ ከኃይለ ሥላሴ ይልቅ
የሞሶሎኒን ሐውልት ማቆም ነው የሚቀናቸው ፡፡ ብቻ ትናንትን ሳይሆን ዛሬን ብቻ ነው የሚያሞግሱ፡፡ ስልጣኔ የጀመረ ዛሬ እንጅ ትናንት
በአክሱም ዘመነ መንግስት አይመስላቸውም፡፡ ዘመናዊ ትምህርት የተጀመረ ዛሬ እንጅ በኃይለሥላሴ ዘመን አይመስላቸውም፡፡ ታዲያ እነዚህ
እኮ ታሪክ የማያውቁ ሆነው ሳይሆን የትናንትን ታሪክ መደፍጠጥ ስለሚቀናቸው ነው፡፡ አረ እኔው እውነተኛው ውሻ እሻላለሁ፡፡ ወቼው
ጉድ፡፡ በሰው ባህሪ ገብቼ እዘባርቃለሁ እንዴ? እኔ እኮ ማግበስበስንም ከአባቴ፣ ከአያቴ፣ ከቅድመአያቴ የወረስኩት ነው ብያለሁ፡፡
የትናንት ማንነቴን አልዘነጋሁትም እናንተ ሰዎች ግን የትመጣችሁን ዘንግታችኋል፡፡ ማግበስበስ ቢያመሳስለንም ታሪክ ጥበቃ ግን ያለያየናል፡፡
ዛሬን ያለትናንት የሚተርከው እኮ የሰው ልጅ ነው፡፡ መቼ እንደተማሩ፣ መቼ እንደተወለዱ፣ እንዴት እንዳደጉ እኮ የዘነጉ ናቸው፡፡
ምክንያቱም ትናንትን ዞር ብለው ማሰብ ስለማይሹ አለቀ!!!” ሰውዬውም ማንነቱን ወደኋላ ለማዬት የሞከረው ዛሬ ከውሻው ምክር በኋላ
ነበር፡፡ አስተዳደጉ ትዝ አለው፡፡ ዛሬን ትቶ ትናንትን አስታወሰ ልዩ ክስተቶችንም አስታወሰ፡፡ “እውነትም የሰው ልጅ ትናንት አልባ
ዛሬን ነው ሲላዝን የሚውለው” በማለት ራሱን መከረ፡፡
No comments:
Post a Comment