© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 16/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ቤት የለኝ አልሠራሁ መሬቱ የመንግሥት፣
መኖር ደግሞ አለብኝ ተጠልየ በቤት፣
ታዲያ የት ልኑረው ወዴት ብየ
ልግባ፣
የራሴ ማስገቢያ ስለሌለኝ ታዛ
ሆዴ እጅጉን ባባ፣
ዓይኔ ራሰ በእንባ፡፡
እንባዬን ጠርጌ ቀና ስል በድንገት፣
“ይከራያል” የሚል
አየሁኝ ከርቀት፣
ችግር ያበሰለኝ ማደሪያ አጥቼ፣
እየተንሰፈሰፍኩ ቤቱን ተጠግቼ፡፡
የሚከራየውን አሳዩኝ አልኳቸው፣
አሳዩኝ ዶርሚቱን ከነመመሪያቸው፣
መመሪያ ቁጥር አንድ…
አምሽቶ መግባት መስከር መወላገድ፣
ቆሻሻ መጣል እንጀራ መጋገር ማድቤትን
ማቆሸሽ ሴት ልጅን ማሳደድ፣
አምጥቶ ማሳደር ጓደኛና ዘመድ፣
ሳያንኳኩ መግባት ሳልፈቅድ ወጥቶ
መሄድ፣
ከዶርም ያባርራል ሳትወድ በግድ፡፡
መመሪያ ቁጥር ሁለት…
ሽንት ቤት ውስጥ ገብቶ ደቂቃን
ማባከን፣
ሳልፈቅድ መጠቀም መብራት እና
ውኃን፣
ያስወጣል ከግቢ ካልጠበቅህ ይህንን፡፡
… እናም መመሪያውን ተጋበዝኩትና
፣
ዶርሚቱን አየኋት ፈቀዱልኝና፡፡
ዶርሚቱ እንዲህ ናት…
የግድግዳ ቀለም ምንም ያልነካካት፣
ክፍተቱ የበዛ መስኮትና በር የተገጠመላት፣
አንድ አልጋን መዘርጋት የማይቻልባት፣
ኮርኒስ የሚባለው ያልተሰበከባት፣
ምንም ምን የሌላት፣
ፈጣሪ የሰጠን ጭቃ እንኳ በአግባቡ ያልተለጠፈባት፣
መመሪያ እና ደንብ ክልከላ እና
ዛቻ የተንሰራፋባት፣
ለአቅመ ኪራይ የማትበቃ ባዶ ሆና
አገኘኋት፡፡
እ ኔ-- ም… ውስጤ ተክኖ ልቤ
አዝኖ ተክዞ፣
ዋጋዋ ስንት ነው? ብየ ጠየቅኋቸው
ዓይኔ በእንባ ፈዞ፡፡
“ሶስት መቶ ነው ለአንድ ከሆነ፣
ስድስት መቶ ነው ለሁለት ከሆነ፣
ዘጠኝ መቶ ነው ለሦስት ከሆነ፣”
እያሉ ሲጠሩት የብሩን ጋጋታ፣
በጣም ተገርሜ “ኪራይ ነው ወይስ
ሽያጭ” አልኳቸው በእርጋታ፡፡
ምን ይላል! ይሄ ሰው፣
በሦስት መቶ ነው ቤቴን የምሸጠው?
ይልቅስ ከያዝከው፣
“ይከራያል” የሚለውን ጽሑፍ አሁን
ልገንጥለው፣
አሉኝ ቀና ብለው::
እኔም ተገርሜ እጅግ ተደምሜ፣
በቤት አልባነቴ እኔን ተቀይሜ፣
እከራይ ነበር ዶርምስ ቢኖርዎ፣
አሁን ያሳዩኝ ግን ዶርም አይደለም ከቶ ቅር ካላልዎ፡፡
እናም! ያኔ ዶርም ሰርተው “ይከራያል” ሲሉ፣
መጥቼ እይዛለሁ መመሪያን ሲያቀሉ፡፡
አሁን ግን! ዶርም የሎት ምኑን ልከራየው???
ያው ቤት አልባነቴን ይዤው እኖራለሁ፡፡
(ማስታወሻነቱ፡ በዶርም አጥረት ሳይሆን
በዶርም ውጥረት፤ በዶርም ማጣት ሳይሆን በዶርም ቅጣት ላለሁት ለእኔ እና ለመሰሎቼ ይሁን)