Wednesday, November 18, 2015

አገሬ ኢትዮጵያ!!




© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 8/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አገርም ቢሏችሁ ከአገር በላይ ቅድስናን ከንጽሕና፣ ውበትን ከቁንጅና፣ ጀግንነትን ከፍልስፍና… ጋር አቆራኝታ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ዘርጋታ የኖረች፣ እየኖረች ያለች ወደፊትም የምትኖር ፈጣሪ ውብ አድርጎ የሠራት አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ይች አገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው ተመዝግቦ ከምናገኛቸው ቦታዎች መካከል አንዷ ናት፡፡ ገነትን ከሚያጠጧት አራት አፍላጋት መካከል አንዱ የኢትዮጵያው ግዮን ወይም አባይ እንደሆነ ዘፍጥረት ላይ እናነብባለን፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ለገነት ማጠጫ የሚሆን ትልቅ ወንዝ ለገነት የታጨ ቅዱስ ሕዝብ ያላት አገር ናት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ መሪዎቿ የተለያዩ ስሞችን ተቀብላለች፡፡ አቢሲኒያ፣ ኢትዮጵያ እየተባለች ተጠርታለች፡፡ በአቢስ አቢሲኒያ በኢትዮጲስ ኢትዮጵያ ተብላ የተጠራችው አገራችን ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ካገኘች በኋላ የመሯት መሪዎቿ “አዲሲቷ፣ አሮጊቷ” የሚል ቅጥያ ከመቀጠል ውጭ ስመ ተፋልሶ አላደረጉባትም፡፡ ኢትዮጵያ ስትነሣ ዓለምን የሚያስደንቀው የአኩስም ሐውልት፣ የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር ፋሲለደስ ቤተ መንግስት፣ በሐረር የጀጎል ግንብ፣ በጎጃም የጣና ሐይቅና በደሴቱ ያሉ ገዳማት፣ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን የሚመሰክረው የሉሲ ድንቅነሽ አጽም፣ የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች ተስማምተው የሚኖሩባት፣ ገነትን የሚያጠጣው የአባይ ወንዝ ወዘተ… ትዝ የሚላቸው ፈረንጆቹ ብቻ ናቸው፡፡ እኛ ግን “በቅርብ ያለ ጠበል …” እንዲሉ ከምንም አንቆጥራቸውም፡፡ እኛ የራሳችን ሃብትና ንብረት እንዴት ትዝ አላለንም? በእርግጥ በዚህ ዘመን በአሁኑ ሰዓት ስለብዙ ነገሮች እነዚህ ሁሉ ሃብቶቻችን ትዝ እንዳይሉን ከባድ ተጽእኖዎች አሉብን፡፡ ከእነዚህ ተጽእኖዎችም መካከል የመጀመሪያው የገዢው መንግሥት ተጽእኖ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከመሸለም ከማድነቅ ይልቅ መቅጣት የሚቀናው ማኅበረሰብ ማፍራታችን ነው፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን ያነገቡ አንዳንዶች ለራሳቸው ጥቅም ጥቂቶቹም ለአገራቸው ለወገናቸው ጥቅም ሲሉ የኖሩ መሪዎችን አይታለች ተቀብላም አስተናግዳለች፡፡ ማን ነው ለአገሩ የሞተው መሪ? ማን ነው በጠላት እጅ መሞትን የናቀው? ቴዎድሮስ አይደለም እንዴ? ነው፡፡
 “መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ” የተበላው ለማን ነው? የወንዶች ወንድ፣ የጀግኖች  ጀግና፣ ህዝቡን አሳልፎ ያልሰጠ፣ በጠላት እጅ በነጭ እጅ ላለመሞት ወስኖ የአገሩን የወደፊት ራእይ ሰንቆ፣ አደራውን ለቀሪው ትውልድ አስረክቦ በያዘው ሽጉጥ ራሱን ያሳለፈ የመቅደላው ጀግና የኢትዮጵያው ጀግና ቴዎድሮስ ዘ ኢትዮጵያ ፡፡ በአገራችን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያና የመጨረሻ የሆነውን መድፍ ነጮቹን ቀጥሮ ጋፋት ላይ ያሠራ ብቸኛው መሪ፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው አንዱ ጀግና የሞተለትን ጉዳይ አንዱ ፈሪ ቀበቶውን አላልቶ ሱሪውን አውልቆ ይቀበለዋል፡፡ በቴዎድሮስ የጀመረው ጀግንነትና የአገር ፍቅር በዚያው መጠን ቀጥሎ ዮሐንስ አራተኛ ለአገሩ ለወገኑ ሲል ባደረገው ጦርነት በሱዳኖች አንገቱን ተቆረጠ፡፡ የአገር ገዢዎች ለአገር መልማትም ሆነ መጥፋት ምክንያቶች ናቸው፡፡ እንግዲህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለአገር ፍቅር ለወገን ብሎ ራስን አሳልፎ በመስጠት  በኩል ቆራጥ መሪዎች እነዚህ እንደነበሩ ማሳያዎቼ  ናቸው፡፡ እነዚህ መሪዎች ጀግናዎቼ ናቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም ስማቸውን መስማት የምሻው የእነዚህን ምርጦች ነው፡፡ ምክንያቱም የሞቱለት ዓላማ ትልቅ ስለሆነ እና ለወደፊት ማስቀመጥ የፈለጉት ራእይ ምን እንደሆነ ሳስብ የሚገርም ስለሆነ ነው፡፡ በጠላት እጅ አልሞትም መሞቴ ካለቀረ ግን በራሴ እጅ ሞትን እመርጣለሁ ብሎ በባእድ መገዛትን ተጸይፎ መሞትን ያህል ወኔ የያዘ መሪ አይገርም ማን ይግረም ታዲያ፡፡  ምናልባት ልብ ልንለው የሚያስፈልገው ነገር  ከእነዚህ በፊት እና በኋላ ሌሎች ምርጦች የሉም ለማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለቱ ለአገራቸው ለወገናቸው ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ስለሰጡ በልጠውብኝ እንጅ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ስልጣኔ በር ከፋች የነበሩት ምኒልክም ለአገራችን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ አልዘነጋሁትም፡፡ የመጀመሪያው ተሽከርካሪ መኪና የኢትዮጵያን ምድር የረገጠው፣ ስልክ ተዘርግቶ መደዋወል የተጀመረው፣ የፖስታ አገልግሎት የተጀመረው ዘመናዊ ስልጣኔ ኢትዮጵያን የነካካት መቼ  ነው? በዘመነ ምኒልክ አይደለም እንዴ? አረ ነው ምን መዋሸት ያስፈልገዋል፡፡ ከአውስትራሊያ ጋር በመገናኘት አሁን ለአገራችን ህዝብ በተለይ ለገጠራማው ክፍል ዋስትና እየሆነ ያለውን ባህር ዛፍ ወደ አገራችን ያመጡት ማን ሆኑና፡፡ በዘመናዊ መሳሪያ ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ  ድረስ ተከናንቦ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣውን የኢጣሊያ ጦር በጀግንነትና በወኔ አድዋ ላይ ድራሹን ያጠፉት የአበሻ መሪ ማን ሆኑና፡፡ ጠላትን በመጣበት እግሩ አሳፍረው የመለሱ ድንቅ ኢትዮያዊ መሪ ምኒልክ ሁለተኛ፡፡ የዛሬዪቱን አንገቷን የተቆረጠችውን ሳይሆን ያችን ባለወደቧን ኢትዮጵያ ቅርጽና ግዛቷን እንድትይዝና በዚያ ካርታ እንድትታወቅ ያደረጉ መሪ ናቸው፡፡ በታሪካችን ውስጥ የሚገርመው ነገር ያለፈውን መሪ በበጎ ማንሣት አልተለመደም እንጅ ስንት በጎ ነገር ነበረን መሰላችሁ፡፡ ሃይለ ሥላሴን በብዛት የምናነሣቸው በበጎው አይደለም፡፡ ምንም እንኳ ከላይ ያየኛቸውን መሪዎች ያህል ለአገራችን ስልጣኔ አስተዋጽኦ ባያበረክቱም በተለያዩ ተጽእኖዎች ተነሣስተው የቻሉትን ያህል ግን አድርገዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን ከመመሥረት ባለፈ በመዲናችን አዲስ አበባ ጽ/ቤት እንዲኖረው ያደረጉ እሳቸው ናቸው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት የሰይጣን ትምህርት ነው በሚል አስተሳሰብ ታንቆ የነበረውን የአገራችን ሕዝብ አሳምነው ዘመናዊ ትምህርትን ወደ ኢትዮጵያ ያመጡ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው ዘመናዊ ትምህርትን ያስጀመሩ እሳቸው ናቸው፡፡ ምንም ያህል ብንተቸውም በበጎ ጎኑ ባናነሣውም  የመጀመሪያውን የተጻፈ ሕገ መንግሥት ለአገራችን ያስተዋወቁ ብቸኛ መሪ ናቸው፡፡ አገራችን አሁን ከአደጉት አገራት ተርታ ያለችውን ጀርመን ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ስንዴ የለገሰች በጃን ሆይ ዘመን ነው፡፡ ለአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የጽሕፈት መኪና ወደ አገራችን ያመጡ ጃንሆይ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን አገራዊ ስህተት አልሰሩም ማለት አይደለም፡፡ ማንም መሪ የሚሠራውን የአገር ስህተት ሰርተዋል፡፡ በተለይ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረ ጊዜ አገር ለቅቀው መሄዳቸውና ያም አልበቃቸው ብሎ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ አገር ውስጥ ተመልሰው አገርን በአርበኝነት ሲጠብቅ የነበረውን ጀግና በላይ ዘለቀን መስቀላቸው ዓበይት ስህተቶች ናቸው፡፡ ከጃን ሆይ ቀጥሎ የመጣው ወታደራዊ መንግሥትም አዲስ አስተሳሰብን “ሶሻሊዝም” የሚባለውን ለአገራችን አስተዋውቋል፡፡ እድገት የሚመጣው በኅብረት ነው የሚል አመለካከት ነበረው፡፡ መፈክሩም “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል ነበር በዚህ መፈክር ውስጥ የሚመጣብን ኢትዮጵያ በዓለም ስልጣኔ ላይ ቁንጮ ስትሆን ማየትን ነው፡፡ ዛሬ በቆረጠው ምትክ እንኳ የማይተክለው ደን ኢንተርፕራይዝ ብለን ያቋቋምነው ተቋም ሲቆርጠው የሚውለው ደን በማን ዘመን የተተከለ ነው እንላለን? በማይናወጥ መሠረት ላይ የታነጹት የቀበሌ ቢሮዎች እንዲሁም የቀበሌ ቤቶች በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች መቼ የታነጹ ናቸው? አሁን ከገነባናቸው ይልቅ በደርግ ዘመን የተሠሩት ናቸው ጥንካሬ ያላቸው፡፡ እንደ እድል ሆኖብን አንድ መንግሥት ሄዶ ሌላው ሲመጣ ያለፈው መንግሥት የሠራቸውን ነገሮች ሁሉ ማፍረስ እንወዳለን፡፡ መታሰቢያውን እንደመስሰዋለን፣ ይጠቀምባቸው የነበሩ ቢሮዎችን፣ መሥሪያ ቤቶችን እናፈርሳቸዋለን፣ ታሪክን ዜሮ ብለን እንደገና እንጀምራለን፡፡ አሁን ላይ በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች የተቀመጡ ሰዎች በማን ትምህርት ፖሊሲ እንደተማሩ ራሳቸው እኮ ያውቁታል፡፡ ነገር ግን ያለፈ ታሪክን በበጎ ስለማንመለከት ለዚህ ነው ደርግን በበጎው የማናነሣው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ አሁን እየመራን ወዳለው መንግሥት ደርሰናል፡፡ የአሁኑ መንግሥት ከክፋቱ ይልቅ በጎነቱ ጎልቶ እንዲታይ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ትልቅ ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ክረምት ላይ የተቀረጸውን አረንጓዴ ሰብል በበጋው እያሳዩ በመስኖ የተመረተ ምርት ነው ይሉናል፡፡ ስልጣኔውም እየመጠቀ ስለሆነ ይህንን ነገር ለአገራችን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለዓለም እንዲደርስ ስለተደረገ ውጮቹ ኢትዮጵያ አድጋለች ተመንድጋለች እያሉ ባላዩት ባልሰሙት ነገር ላይ ይመሰክራሉ፡፡ በጣም የሚገርመኝ የዚህ መንግሥት አገራዊ ስህተት ሁሉን አቀፍ የሆኑትን ብሄራዊ በዓላት እና የሃይማኖት በዓላትን ከማክበር ይልቅ ጥቃቅን የሚባሉ ነገሮችን ለወር ለሁለት ወር ከዛም ለረዘመ ጊዜ ሲያከብር ማየታችን ነው፡፡ በእውነት ኅሊና ላለው ሰው የአድዋን ጦርነት ያሸነፍንበትን የካቲት 23 ከማክበርና ብአዴን የተመሰረተበትን ህዳር 11፣ ኢህአዴግ ደርግን ያሸነፈበትን ግንቦት 20 ከምናከብር ትልቅ ስሜት ሊሰጠን የሚችለው የትኛው ነው? በየካቲት 23 ስም የተሰየመ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድ፣ አደባባይ የት አለ? ግንቦት 20 የሚለውን ስያሜ ግን ለብዙ ነገሮች ሰጥተነዋል፡፡ ግንቦት 20 የሚባል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በምሥራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ የካቲት 23 የሚባል ትምህርት ቤት ግን አላውቅም፡፡ የውጭን ጠላት አሸንፎ ዓለም አቀፋዊ እውቅናና ዝና ያጎናጸፈን የትኛው ነው? ሌላው የገዣችን ትልቅ ስህተት ካለፉት በጎ ነገሮችን መማር አለመቻሉ ነው፡፡ በእርግጥ ያን ጊዜ ድሮ የነበሩት መሪዎቻችን እንዲህ በቀላሉ ዓለምን መድረስ የሚችሉበት ሥልጣኔ የነበራቸው ስላልሆኑ እንጅ በጎ ስራ ስላልሰሩ አይደለም እውቅና ያላገኙት፡፡ አንድ ዛፍ ተክሎ ሺህ ጊዜ በሚዲያ መቅረብና ማቅረብ፣ አንድ ሽንኩርት አብቅሎ ሺህ ጊዜ ሚዲያ ላይ መውጣት እና ማውጣት የተጀመረው አሁን ቅርብ ጊዜ ነው፡፡ በእውነት ግን! ባህር ዛፍ ተከለ ተብሎ በሚዲያ ከመታየት ይልቅ ባሕር ዛፍን ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው ሰው ማን እንደሆነ ፎቶውን እንኳ ብናሳይ አይበልጥም ነበር? የዘመናዊ ትምህርትን ጥራትና ሽፋን፣ የትምህርት ቤቶቻችንን ቁጥር እያነጻጸርን ሺህ ጊዜ እስኪሰለቸን ከሚነግሩን ይልቅ ዘመናዊ ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ ማን እንዳስጀመረው? ሲጀመር የነበረው የህዝቡ አቀባብል ምን ይመስል እንደነበር ምነው በነገሩን፡፡ ባለፉት ዘመናት ለአገራቸው ለወገናቸው ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ጀግኖቻችን አድራሻቸው የት አለ? መታሰቢያ ሀውልታቸው የት ቆመ? በቅርቡ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ማለቴ ነው በየክልሉ የሰማዕታት ሃውልት እየተባለ ሲቆምላቸው (አይቁምላቸው ማለቴ አይደለም) ለቴዎድሮስ እና ለገብርዬ፣ለዮሐንስና ለምኒሊክና፣ ለበላይ ዘለቀ የትኛው ክልል ላይ ነው መታሰቢያ ሐውልት የቆመላቸው ምናልባት አሁን ካልፈረሰ በወረዳ ደረጃ ተሰርቶላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛው ትምህርት ቤት፣ የትኛው ሆስፒታል፣ የትኛው አደባባይ ነው በስማቸው የተጠራ? የሚገርመው ነገር አሁን በቅርቡ ላለፉት ባለራዕይ መሪ ስንት ትምህርት ቤት፣ ስንት መንገድ፣ ስንት አደባባይ፣ ስንት ስታዲየም፣ ስን ሆስፒታል፣ ስንት ፓርክ ነው በስማቸው የተሰየመ? ብቻ ታሪክ ይቀሰን! የእነ ቴዎድሮስ የእነ ዮሐንስ የእነ በላይ ዘለቀ ደም ይክሰሰን፡፡ ድሮ እነርሱ ደርግን የጣሉት በትጥቅ ትግል ነበር ምክንያቱም አስተሳሰቡና ርእዮቱ ለኢትዮጵያ ተገቢ ነው ብለው ስላላመኑ፡፡ ዛሬ ግን የትጥቅ ትግል የሚጀምርን ሰው አሸባሪና ኪራይ ሰብሳቢ ከማለት ውጭ ለአገሩ ለወገኑ ለሕዝቡ አስቦ ነው ብለን መቼ ተረዳን፡፡ አስተሳሰባችን አመለካከታችን ከጫካ አስተሳሰብና አመለካከት መቼ ተለየ? ለዛም እኮ ነው ከእኛ በላይ ፖሊሲ፣ ከኛ በላይ መሪ፣ ከኛ በላይ ካድሬ፣ ከኛ በላይ ሕገ መንግሥት የትም የለም ብለን የምንከራከረው፡፡ የተማረ ሰው መለያው “ይህ ስህተት ነው” ሲሉት ስህተቱን መመልከት መቻሉ ነበር የዚህኛው የኛ ገዢ ግን መማሩ ያልጠቀመው ይመስላል፡፡ አልተማረም እንዳንል ውጭ አገር ድረስ ሄደው ዲግሪ፣ ማስተርስ፣ ዶክትሬት ጭነው ተመልሰዋል ተማሩ እንዳንላቸው ደግሞ ዋይታችንን ችግራችንን ብሶታችንን አልተረዱልንም፣ አመለካከትና አስተሳሰባቸውን አልቀየሩልንም፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያን በነበረችበት ስልጣኔ ላይ ሳይሆን አፍርሰው እንደገና ወደ ስልጣኔ ጎዳና ስላመጧት በርካታ ጊዜያትን ሊወስድ እንደሚችል እናስባለን፡፡ ነገር ግን ሁል ጊዜ ጅማሬ የለም መጨረሻ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ከ83 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ጅማሬ ላይ ነን ሊባል አይገባውም ነበር፡፡ የጅማሬ ራዕያችን መቼ ነው አውን ሆኖ የምንመለከተው?
ሌላው የአገራችንን ታሪክ ከማድነቅ ይልቅ እንድንዘነጋውና እንድረሳው ትዝ እንዳይለን ያደረገን ጉዳይ ከመሸለም ይልቅ ለቅጣት የሚፈጥን ማኅበረሰብ ማፍራታችን ነው፡፡ በየቤታችን አስተዳደጋችን እንዲሁ ነው፡፡ ታሪክን እያስተማሩ ለአገር ፍቅር እንዲኖረን ከማድረግ ይልቅ “አንተ ወሬኛ” እየተባልን ታሪክን ለመማር እና ለመስማት ተሸማቀቅን አድገናል፡፡ ተረት ንገሩን ስንላቸውም የቀበሮና የበግ ተረት ነው የሚተርቱልን፡፡ እኛም እሱኑ ለመድነውና ቀበሮና በጎች ሆነን ቀረና፡፡ በጀመርነው የጥንቱ ስልጣኔ እና ትልቅነት ላይ አንዳች ነገር መጨመር ያልተቻለን ከማበረታታት ይልቅ ማሸማቀቅና ማስፈራራትን ባህላችን አድርገን በመኖራችን ነው፡፡ ለብዙ ዘመን በበጎ ስራህ ስትነሣ፣ ስትመሰገን፣ ስትወደስ፣ እንደ እርሱ አድርጋችሁ ሥሩ እየተባለ አርአያነትህ ሲጎላ፣ ህዝቡም አንተን ሲከተልህ ትኖራለህ መቼም ከሰው ልጅ ስህተት አይጠፋምና አንድ ቀን ታጠፋለህ ለብዙ ዘመን ይዘኸው የነበረው ስምና ዝናህ ከመ ቅጽበት ይለወጥና ትታሰራለህ ወይም ትቀጣለህ፡፡ አውሮፕላን ብትሠራ፣ መርከብ ብትገጣጥም፣ አዲስ ጥበብ ብታመጣ ማንም አያደንቅህም ሊቀጣህና ሊወግርህ የተዘጋጀው ግን አያሌ ነው፡፡ ሃይለ ሥላሴ በላይ ዘለቀን ለምን ሰቀሉት? ርስታቸውን ቀማቸው ወይስ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አደረገባቸው? አረ ምንም፡፡ ጀግንነቱ በህዝቡ ዘንድ ስለገነነ እና በርካቶች ስለተከተሉት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ምቀኝነታችን ያስቸግረናል፡፡ ምቀኛ መሪዎች ደግሞ ተፈራርቀውብናል፡፡ እነሱ የሚሰሩት ብቻ ትክክል ይመስላቸዋል፣ ያለፉት መሪዎች የሰሩት ሁሉ ደግሞ ስህተት ይመስላቸዋል ለዛ ነው ታሪካችን እንዲህ ዘቅጦ የቀረው፡፡ ስንት ሽህ ጊዜ በጎ ነገር ብትሠራ መልካም ነገር ቢኖርህ ለሎች ሁሉ አርአያ ብትሆንም ሽልማት አታገኝበትም እውቅናን አትጎናጸፍበትም፡፡ በአንጻሩ ግን ትንሽ ስህተት ብትሰራ ከሰምንት ሰዓት የሥራ ሰዓት ውስጥ 10 ደቂቃ ብትሸርፍ ሽራፊ ደመወዝ ይሰጥሃል፡፡ የጽሑፍና የቃል ማስጠንቀቂያ ማስፈራሪያና ዛቻ እንዲሁም አዲስ ስም ከኪራይ ሰብሳቢነት እስከ አሸባሪነት እና ትምክህተኛነት ድረስ ያሉት ስድቦች ይዘንቡብሃል፡፡ መሪዎችህም የሚደሰቱት በመሸለም ሳይሆን በመቅጣት ነው ምክንያቱም አስተዳደጋቸውና አስተሳሰባቸው ነዋ፡፡ ማበረታታት የሚባለው ነገር ተዘንግቷል፡፡ አዲስ ፈጠራ ፈጥረህ ስልክ በነጻ መደወል ብትጀምር ፈጠራህን የሚያበረታታ ፍርድ ቤት የለም 25 ዓመት ጽኑ እስራት የሚል እንጅ፡፡ ታዲያ በዚህ ሂደት ታሪክህን ማጥናት እንዴት ልትደሰት ትችላለህ?
አገራችንን አምላክ ይጠብቅልን፡፡


No comments:

Post a Comment