Thursday, November 12, 2015

እውነተኛ ሰላም

© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 2/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

…ይህ ሰላም ዘላለማዊ ዕረፍትን የሚያጎናጽፍ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ልዩ ሃብት ነው፡፡ በቅዳሴው ጸሎት ካህኑ “ሰላም ለሁላችሁ” ብሎ የሚጸልይልን ይህን ሰላም ነው፡፡ ለዚህም ነው “ከመንፈስህ ጋራ” ብለን ያንን እውነተኛ ሰላም እናገኝ ዘንድ የምንማጸነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 28÷ 11 ላይ “እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል” የሚለውን መዝሙር ይዘን እኛም በቅዳሴ ጸሎታችን ውስጥ “የሰላም ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሰላምን ስጠን ሰላምንም አጽናልን” እያልን እውነተኛ ሰላማችን እንድትጸናልን ሰላማዊ የሆነውን የሰላም ንጉሥ በየዕለቱ እንለምነዋለን፡፡ ይህ ሰላም ለአገር፣ ለወገን፣ ለፍጡራን ሁሉ የሚያስፈልግ መሆኑን በመረዳት በቅዳሴ ጸሎታችን ላይ በተደጋጋሚ እናነሣዋለን፡፡ ይህ በተደጋጋሚ የምንማጸነው ሰላም ከዲያብሎስ፣ ከፍርሃት፣ ከጭንቀት፣ ከመከራና ከሃዘን ጠብቆ ሙሉ ደስታን የሚያጎናጽፍ ልዩ መሣሪያ ነው፡፡ ብዙዎች ልባቸው በጭንቀትና በፍርሃት በሚሸበርበት ጊዜ የአንተ ውስጣዊ ሰላምህ አይናጋም፡፡ በጦርነት መካከል ተሰልፈህ የመሸነፍ ስሜት ጠፍቶ የማሸነፍ ወኔ ትጎናጸፋለህ፡፡ በዚህም የተነሣ ውስጣዊ መረበሽ፣ መጨነቅ ብን ብሎ ይጠፋልህና እውነተኛ ሰላም በፊትህ ትፈስሳለች፡፡ በከባድ አደጋዎች መካከል የብዙዎች  ልብ በፍርሃትና በጭንቀት ቀልጦ ዋይታ ሲበዛባቸው አንተ ግን ምንም እንደማያውቅ ሕጻን ንጹሕ ሰላምን ተሸፋፍነህ በደስታ ትቦርቃለህ፡፡ በከንቱ በመጨነቅ እና በማልቀስ አንዳች ነገር መፍጠር እንደማትችል እውነተኛ ሰላምን የሠጠህ አምላክ ያስተማረህ ወንጌል በሕይወትህ ትርጉም እያገኘ ፍሬ ሲያፈራ አንተም ፍሬውን ስትመገብ ይበልጥ ደስታህ ይጨምራል፡፡ ብዙዎች እንቅልፍ በማጣት ሲባዝኑ አንተ በንጹሕ እረፍት መካከል ትሰማራለህ፡፡ “እግዚአብሔር እረኛየ ነው የሚያሳጣኝም የለም በለመለመ መስክ ያሰማራኛል በእረፍት ውኃ ዘንድም ይመራኛል” /መዝ22÷1/ የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ዝማሬ በእውነተኛ ሰላም መካከል ትዘምራለህ፡፡ የአገሬን ጥፋት አታሳየኝ እያለ ይለምን የነበረው በእግዚአብሔር ጥበብ ለድውያን የሚሆን ዐጽቀ በለስን ቆርጦ እንዲያመጣ የተላከውና ዐጽቀ በለሷን ይዞ መጥቶ ከዛፍ ሥር እንዳረፈ በዚያው ለ66 ዓመት ያህል በእንቅልፍ አሳልፎ የአገሩን ጥፋት ከማየት የሰወረውን አቤሜሌክ ወደ አንተ ያመጣዋል፡፡ እርሱም እውነተኛ ሰላምን በሚገባ በተግባር ያረጋግጥልሃል ይተረጉምልሃልም፡፡ ያ እውነተኛ ሰላም ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ኃይል አለው፡፡ “ስለዚህ ኤልሳቤጥ የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ጽንሱ በማኅጸን ዘለለ” /ሉቃ 1÷41/ እውነተኛ ሰላም እንዲህ በማኅጸን ያለውን ጽንስ ሳይቀር ደስ የሚያሰኝና የሚያዘልል ነው፡፡  ያ ሰላም በየዋህነትና በንጽሕና ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን የሚገኝ ነው፡፡ ያን ሰላም ዮሐንስ እንዲህ ገልጾታል “ ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም”/ዮሐ14÷27/ እውነተኛ ሰላም ከእግዚአብሔር የሚገኝ  ዓለምም ከምትሰጠው ሰላም እጅጉን የተለየ ለመሆኑ ይህ ቃል ምስክር ነው፡፡ ዓለም የምትሰጠው ሰላም የሐሰት ነው፡፡ የጠፋው ልጅ ታሪክ ይህንን በሚገባ ያስረዳናል፡፡ በአባቱ ቤት የነበረው እውነተኛ ሰላም ሆኖ ሳለ ወደ ዓለም ገባ፤ ዓለምም ገንዘቡን በሚገባ ከጨረሰች በኋላ ሰላም ነፈገችው፡፡ በዚህም የተነሣ እንደገና ተመልሶ ወደ ቀድሞው ሰላም ወደ አባቱ ቤት ገባ፡፡/ሉቃ15÷11-24/ ይህ ልጅ እውነተኛ ሰላም የሚገኘው በአባቱ ቤት ብቻ መሆኑን ተረዳ፡፡ ከእግዚአብሔር ስትርቅ የምታጣው ይህንን ዓይነት ሰላም ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን ሰላም እንድታጣ ከተወህ ወጥተህ መግባት አትችልም፤ ለሴኮንዶች ያህል እንኳ እረፍት አታገኝም፡፡ ድምጽ በሰማህ ኳ ባለ ቁጥር ትሸበራለህ፡፡ ያ እውነተኛ ሰላም በገበያ መካከል ገብተህ ድምጽ ሳትሰማ የምትወጣበት ነበርና አሁን ግን እርሱን በማጣትህ ትጨነቃለህ፣ ፍርሃት ይበዛብሃል፣ ተቅበዝባዥ ትሆናለህ፡፡ ስለዚህ ወደ እውነተኛው ሰላም ወደ አባትህ ቤት ልትመለስ ያስፈልጋል፡፡ በኃጢአት የቆሸሸ ማንነትህን በንስሓ አጥበህ ወደ አባትህ ቤት ልትመለስ የምትችልበት ዕለት ዛሬ ብቻ ስለሆነ እውነተኛ ሰላምን ወደሚሰጠው አባትህ ቤት ተመለስ፡፡ እውነተኛ ሰላም ለእግዚአብሔር ክብር እንድትመሰክር ሊወግሩህ ድንጋይን በያዙ ሰዎች መካከል ወይም ሊፈጩህ በተዘጋጁ ወፍጮዎች መካከል ቆመህ እውነቱን እንድትገልጥ ትረዳሃለች፡፡ የፍርሃት ካባን ታወልቅልህና የቅዱስ ጊዮርጊስንና የቅዱስ እስጢፋኖስን ሰማእትነት እስክትቀበል ድረስ ታጸናሃለች፡፡ ለሚወግሩህም ሰዎች “ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” የሚል ፍጹም ፍቅር የተሞላበት ልመና እንድታቀርብ ውስጥህን በንጹሕ ፍቅር ታትምሃለች፡፡ /የሐዋ 7÷60/ ስለዚህ ያንን እውነተኛ ሰላም ገንዘብህ ልታደርገው ይገባል፡፡ ከኃጢአትህ ተመልሰህ በንጽሕናና በቅድስና በየዋህነትም ሆነህ ብትገኝ እውነተኛ ሰላም ወደ አንተ ትመጣለች፡፡ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ትእዛዙን ጠብቀህ ብትጓዝ እውነተኛ ሰላም ከአንተ ጋር ትጓዛለች፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ እንደእርሱ መልካም ፈቃድ በመጓዝ ከቤቱ ሳትርቅ በእውነተኛ ሰላም ልትኖር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ይህን የማታደርግ ከሆነ እውነተኛ ሰላም እጅጉን ትርቅሃለች፡፡

No comments:

Post a Comment