Wednesday, November 11, 2015

“አይምሰላችሁ!!!”

© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 2/2008 ዓ.ም
ደብረማረቆስ፣ ኢትዮጵያ
ወገኖቻችን መጠንቀቅ እንዲገባቸው ልንጠነቀቅና ልናስተውል የሚገባንን ነገር ለመንገር ብዕሬን አነሣሁ፡፡ የሚቀበል ይቀበላል የማይቀበል ደግሞ አይቀበልም አለመቀበሉንም ሆነ መቀበሉን ግን በነጻነት አስተያየት መስጫው ላይ መተው ይቻላል፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ ወደ መልእክቴ እገባለሁ፡፡
ዘመኑ ቀርቧልና ንስሐ ግቡ እያለች ልጆቿን በምግባርና በትሩፋት የምትጠብቅ እናት ቅድስት ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰአት ባስተማረቻቸው ልጆቿ እና ምንም በማያውቋት ጥላቻ ከባድ ፈተና ላይ ናት፡፡ ነገር ግን እስካሁን ካሳለፈቻቸው በርካታ ፈተናዎች የበለጠ ስላልሆነ በጥበብና በማስተዋል እንደምታልፍ ጥርጥር የለኝም፡፡ ነፋስ በነፈሰ ቁጥር ባለማስተዋል የምንነፍስ፣ በበረሩበት የምንበር፣ በሄዱበት የምንሄድ፣ በገቡበት የምንገባ፣ በወጡበት የምንወጣ እግዚአብሔርን ከመደገፍ ይልቅ የሰው ምርኩዝ የምንመረኮዝ በርካታዎች ነን፡፡ ከንቱ ሰማዕትነት ለመክፈልም የምንጣደፍ የሆነ ያልሆነውን የምንዘባርቅ መረጃዎችን ከማገላበጥ መጻሕፍትን ከማንበብ ይልቅ የሰዎችን አባባልና ወሬ የምናመላልስ “አባ እገሌ እንዲህ ብለው” ፣ “እማ እገሊት እንዲህ ብለው”፣ “እዚህ ገዳም እንዲህ ተብዬ”፣ “አባ እገሌ ራዕይ አይተውልኝ” ወዘተ አያልን ባለማስተዋል የተበላን በርካታዎች እንደሆንን ልንዘነጋው አይገባም፡፡ “የአባ እገሌ” ሃሳብ ከመጽሐፉ ጋር አልገጥም ይላል “የእማ እገሊት”ም ራዕይ እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱሱን ይጋጨዋል ነገር ግን የምንወዳቸው የምናከብራቸው “አባ አባ፣ እማ እማ” የምንላቸው ዝቅ ብለን ጉልበታቸውን የምንስማቸው ናቸውና የተናገሩት እነርሱን ለሚቃወም ሁሉ ዘብ እንቆምላቸዋለን፡፡ አንድ ሰው የሆነ ውለታ ሊውልልህ ይችላል ያ ውለታው ግን እምነትህን እንድትለውጥ የሚያደርስ ተጽእኖ ሊኖረው አይገባም፡፡ ውለታ የዋለልህ በመሆኑም ብቻ “በዚህ ምድር  እንደእርሱ ያለ ሰው ፈጽሞ አይገኝም”፣ “አረ በፍጹም እርሱ እንዲህ አይነት ነገር አያደርግም” ወዘተ እያልክ ልትሞግትለት ጥፋቱን እራሱ አምኖ እንኳ “በፍጹም ይህን ያደርጋል ብዬ አልገምትም ዝም ብሎ አምኖ ይሆናል እንጅ” እያልክ ልትከራከር ሁሉ ትችላለህ፡፡ ግን አይደለም…
አይምሰላችሁ! አትሞኙ! የጠመጠመ ሁሉ ካህን አይደለም፤ ድምጽ ያለው ሁሉ ዘማሪ አይደለም፤ ጥቅስ የጠቀሰ ሁሉ ሰባኪ አይደለም፣ ደብተር የያዘ ሁሉ ተማሪ አይደለም፣ ቾክ የያዘ ሁሉ መምህር አይደለም፣ ጋወን የለበሰ ሁሉ ሃኪም አይደለም፣ በተሸከርካሪ ወንበር የተቀመጠ ሁሉ ኃላፊ አይደለም፡፡ በቃ! ይህንን ደፍረን እንናገረዋለን! እየሆነ ያለው ነገር እሱ ስለሆነ፡፡ ተሐድሶ መናፍቃን አይደለም ይህንን ማድረግ ቀርቶ ሌላም ሌላም ለማድረግ እቅዱ ስላላቸው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በግልሰቦች ደረጃ ወርደን ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ሳይለያቸው ድሮ እንመጻደቅባቸው እንዳልነበር ሁሉ አሁን አብዛኛው ሰው ንቆ ሲተዋቸው “ፓስተር እገሌ” ለማለት መቅደማችን በራሳችን የመተማመኑ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ በመኪና የሄደ ሁሉ ሹፌር ሊሆን አይችልም፤ በአውሮፕላን የበረረ ሁሉ ፓይለት ሊሆን አይችልም፣ ትምህርት ቤት የገባ ሁሉ ተማሪ ሊሆን አይችልም፣ ዩኒቨርሲቲ የተማረ ሁሉ ሊመረቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን ያደገ ሁሉም እንዲሁ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ሊሆን አይችልም፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል ይገባናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ጊዜ እንዲቆይ በዚያ እንዲያድግ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? እናትነቷን ፈልጎ ነው ወይስ ሌላ ጥቅም ፈልጎ? የሚለው መመለስ አለበት፡፡ በርካታ አርቲስቶችን መመልከት ትችላላችሁ፡፡ ኮፒ ራይትን ማስቆም ባለመቻሉ ዛሬ ያወጡት ዘፈን ነገ በዓለም ሁሉ ይደመጣል አንድ ካሴት እንደሸጡ ሁሉም ሰምቶ ይሰለቸዋል ይህ በመሆኑ ምንም ህይወታቸውን የሚለውጥ ገንዘብ ማግኘት አልተቻላቸውም፡፡ በዚህ የተነሣ አብዛኞቹ ወደ ሃይማኖቱ ገብተው እምነታቸውን እንደሽፋን ተጠቅመው “ዘፋኝነተን አቁሜ ዘማሪ ሆኛለሁ” እያሉ “አርቲስት ዘማሪ እገሌ” እየተባለ መዝሙር አይሉት ዘፈን ቅጡን ያጣ አድርገው እያሳተሙ ሲቸበችቡት ይውላሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ነገ ያ የኮፒ ራይት መብት ቢጠበቅላቸው ወደ ዘፈናቸው ላለመመለሳቸው ምን ዋስትና አለ? ምንም፡፡
እግዚአብሔር ያደረገልንን ውለታ ለግለሰቦች አሳልፈን የምንሰጥ ግለሰቦች አሳልፈን የምንሸጥ የአምላካችንን ስም ከማመስገን ይልቅ የግለሰቦችን ስም እየጠራን ያኑርልን የምንል ከንቱዎች፡፡ ምንም ያህል ነገር ከሰው ቢደረግልን ያን እንዲያደርግልን የረዳንን አምላክ ወዴት እንዘነገዋለን? አምላካችን ሲሰደብ ኢየሱስ አማላጅ ሲባል ቅዱሳኑ ሲሰደቡ አያማልዱም ሲባሉ ስናጨበጭብ የነበርን ሰዎች ዛሬ አንድ ግለሰብ እንዲህ ሆነ እንዲህ ተደረገ ሲባል አካኪ ዘራፍ እንላለን፡፡ ለመሆኑ መቅደም የነበረበት ለማን ነው? ለአምላካችን ወይስ ለግለሰቦች? እኔ በጣም ይገርመኛል ምን ዓይነት አዚም እንደተጫነን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ የውስጣቸው ቅድስና ለልብሳቸው ብሎም ለጥላቸው ሲሆን በጥላቸው ድውይ ሲፈውሱ አላነበብንም እንዴ?ሺህ ጊዜ  አንብበነዋል፡፡ ታዲያ በሮም አደባባይ ቁልቁል ሲሰቀሉ ምን ተነፈስን? ምንም፡፡ ምክንያቱም የአምላክ ፈቃድ ነዋ!!! ታዲያ ዛሬስ??????????

No comments:

Post a Comment