፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

ቃለዓዋዲው ሰንበት ትምህርት ቤት እንዴት ለምን የት በማን ለማን ሊቋቋም እንደሚገባው የሚናገረውን
ያህል ስለገዳማትም እንደዚሁ በማብራራት ይናገራል፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ስለገዳማት ቃለ ዓዋዲው የሚለውን እንመልከትና በመቀጠልም
ስለሰንበት ትምህርት ቤት አደረጃጀት እንመለከታለን፡፡
ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ ፲፭ ገጽ ፳፯ ስለገዳማት አስተዳደር እና ሥርዓተ ምንኩስና በሚለው አንቀጹ
ንዑስ አንቀጽ ፩ መሠረት የገዳማት አስተዳደር እንደሚከተለው ተዘርዝሯል፡፡
ሀ. የአንድነት ገዳማት የሚተዳደሩበትእንደየገዳማቱ ሥርዓት በየአህጉረ ስብከቱ እየተጠና የሚፈቀድ
ደንብና መመሪያ ይኖራቸዋል፡፡ እንደአስፈላጊነቱ በሀገረ ስብከቱ አቅራቢነት በቅዱስ ሲኖዶስ ሊወጣላቸው ይችላል፡፡
ለ. ሥርዓተ ገዳም በሚፈቅደው መሠረት በየገዳማቱ ውስጥ ጽ/ቤቶችና ልዩ ልዩ የአመራር አካላት
ይቋቋማሉ፡፡
ሐ. በገዳሙ አስተዳደር መሠረት የጾም የጸሎት ሥርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ መነኮሳት የሚማሩበት
ቦታና በልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰማሩበት የሥራ መስኮች ይኖሩታል፡፡ በዚህ መልኩ ይዘረዝርና በመጨረሻ
ነ. የገዳሙ ተጠሪነት ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ይሆናል፡፡ ብሎ
ይህን ንዑስ አንቀጽ ይደመድማል፡፡
ንዑስ አንቀጽ ፪ ስለገዳማት አስተዳዳሪዎች ስለ አበምኔቱ እና ስለእመ ምኔቷ ይናገራል፡፡
ንዑስ አንቀጽ ፫ ስለምንኩስና መመዘኛዎች ይናገራል፡፡
ሙሉውን ለመጻፍ ብዙ ስለሆነ አልቻልሁም ስለሆነም ቃለ ዓዋዲውን እንድትመለከቱት እጋብዛለሁ፡፡
ከዚህ ቀጥሎ በሚመጣው አንቀጽ ደግሞ ሰንበት ትምህርት ቤት እንዴት መደራጀት እንዳለበት አንቀጽ ፳፩ ላይ በሚገባ ይናገራል፡፡ አንቀጹ
ገና ሲጀምር ስለሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የሚወጣውን ደንብና መመሪያ እየተከታተለ የሰበካው የሰንበት
ትምህርት ቤት ክፍል ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ተግባራት ያከናውናል ይልና ተግባራቱን ይዘረዝራል፡፡ ይህ ክፍል መመሪያን ከቅዱስ ሲኖዶስ
እየተቀበለ ወጣቶችን ዕድሜያቸው ከ፴፭ ዓመት በታች እና ከ፬ ዓመት በላይ ያሉ ህጻናትን ያደራጃል፡፡ ዲያቆናት እና ቀሳውስትም በመማርና
በማስተማር እንዲያገለግሉ ያዝዛል፡፡ ሙሉውን አንብቡት፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤትን ለመዝጋት “ይህ ቦታ ገዳም ነው” ማለት ይቻላልን አይቻልም፡፡ ገዳማት
ከከተማ የራቁ በበረሃ ያሉ የጸጥታ ቦታዎች የጸሎት ቦታዎች ዓለምን የናቁ ገዳማውያን መኖሪያ ቦታ ነው፡፡ ይህ ቦታ የጽሙና የተመስጦ
ቦታ እንደመሆኑ መጠን ጸሎትን ሊስታጉል የሚችል ተመስጦን ሊቀማ የሚችል ጽሙናን ሊያጠፋ የሚችል ነገር ሊደረግበት አይገባም፡፡ ወጣቶች
መዝሙር ሲያጠኑ ትምህርት ሲማሩ ገዳማውያንን ስለሚረብሹ በገዳማት ዘንድ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አይደራጁም መልካም ነው፡፡ ለዚህም
ገዳመ አስቄጥስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወክርስቶስ ሰምራ አንድነት ገዳም ላይ ሰንበት ትምህርት ቤት መቋቋም የለበትም ይበሉ ገዳማውያኑን
ሊረብሽ የሚችል ሆኖ ከተገኘ፡፡ ገዳመ ሕያዋን ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል ላይ ግን ሊረበሽ የሚችል አንድም መነኮስ የለም አንድም፡፡ እስኪ
ገዳሙን የገደመው ማነው? አበምኔቱ ወይም እመምኔቷ ማናቸው? ስንት መነኮሳት ናቸው የሚኖሩበት? የገዳሙ ሥርዓትስ ምን ይመስላል?
እስኪ ገዳም መሆኑን የሚያስረዳ ነገር አብራሩላቸው፡፡ ልማር ብሎ የሚመጣን ሰው ማባረር ምን የሚሉት አረመኔነት ነው? ምን ዓይነት
ሰይጣናዊነት ነው? ገዳማት ምን መምሰል እንዳለባቸው ቃለ ዓዋዲው ላይ መመሪያ ተቀምጦላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቀደሙ ገዳማውያን
አባቶችን እና እናቶችን ህይወት መመልከት ይቻላል፡፡
ነገም እኮ ሰንበት ትምህርት ቤት እንዳይኖር ለማድረግ የምሥራቅ ጎጃም አጥቢያዎችን በሙሉ ገዳማት
ናቸው ልትሉን ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል፡፡ ሥርዓተ ገዳም በየገዳማቱ እንደገዳሙ ገዳሚ ይለያያል አንድ ዓላማ ያለው ቢሆንም፡፡
ለምሳሌ ደብረ ሊባኖስ ላይ ለምግብነት የሚውለው ዳቤ እና ንፍሮ እንደሆነ ሁሉ በዋልድባ ደግሞ ቋርፍ ነው፡፡ ሴቶች ለብቻቸው ወንዶችም
ለብቻቸው ሆነው እንደሚኖሩ ሁሉ በአንድነትም የሚኖሩባቸው ገዳማትም አሉ፡፡ በዚህም መሠረት ማንም እንደፈለገው ተነሥቶ የሚዘልባቸው
ቦታዎች አይደሉም፡፡ በመሆኑም ሰንበት ትምህርት ቤቶች አይቋቋሙባቸውም ማለት ነው፡፡ ይህን ተገን አድርጎ ግን ሰንበት ትምህርት
ቤቶችን ለማፍረስ መንቀሳቀስ አይቻልም፡፡


፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥር ፳፬
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment