=============================
‹‹ደብረ አሚን-የሃይማኖት ተራራ›› የተሰኘችው ባለ 328 ገጽ መጽሐፍ ‹‹መሰረተ ሃይማኖት›› ለምትል
ባለ 55 ገጽ መጽሐፍ ምላሽ የያዘች ናት፡፡ እስከ ምእራፍ 4 ድረስ መሠረታዊውን የተዋሕዶ ትምህርት ከሊቃውንት መጻሕፍት እና ከሰማንያ
አሐዱ መጻሕፍት እያመሳከረች ታብራራለች፡፡ የቅብዐትን ትርጉም እና እንደ ሃይማኖት ቅባት ወደ ሀገራችን መቸ እንደገባም በተለይ
ምእራፍ 4 ላይ ታብራራለች፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስለምስጢረ ጥምቀትም መጽሐፎቻችን የጻፏቸውን ምስክሮች በማቅረብ ታብራራለች፡፡
እዚህ ላይ የልጅነት እና የቄደር ጥምቀትን ልዩነትና መቼ የትኛው ጥምቀት እንደሚፈጸም በምሳሌ ታስረዳናለች፡፡
ምእራፍ አምስት ላይ ‹‹መሰረተ ሃይማኖት›› የተሰኘችው መጽሐፍ የያዘውን ክህደት እየነቀሰች መጻሕፍትን
ምስክር እያቀረበች መለስ ትሰጣለች፡፡ በመጨረሻው ምእራፍ ላይ ቅብዐቶች የዋሐን ምእመናንን ለማደናገር የሚጠቅሷቸውን አንዳንድ ጥቅሶች
ቤተክርስቲያናችን ከምትገለገልባቸው የአንድምታ ትርጓሜ መጻሕፍት በቀጥታ ሳይቀነስ ሳይጨመር ጽፋለች፡፡
ይችን መጽሐፍ ከማሳተም እስከ ማሰራጨት ድረስ ሙሉ ኃላፊነቱን የተሸከምኩት ራሴ ነኝ፡፡ በርግጥ ይህን መጽሐፍ
በዚህ መልኩ ለዚህ ጊዜ እንዲበቃ ያደረጉት በርካቶች ከጎኔ መኖራቸው እሙን ነው፡፡ በተለይ ከማተሚያ ቤቶች ጋር ውል በመያዝ በማሳተም
መጽሐፉን ተረክቦ አስጭኖ ይዞ በመምጣት አሁንም ለሚፈልጉ ሰዎች በማሰራጨት ላይ ያለውን አንድ ወንድሜን ውለታውን የመክፈል አቅም
የለኝም፡፡
ይች መጽሐፍ መጸነስ ምክንያቷ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ የምጽፈውን ጽሑፍ
እየተመለከቱ በስልክም በአካልም መልእክት በመላክምዳ መጽሐፍ እንድለውጠው በርካቶች ወተወቱኝ፡፡ እኔ ግን መጽሐፍ የመጻፍ አቅም
ይኖረኛልን በሚለው ትልቅ ሃሳብ ውስጥ ራሴን ስመረምረው ጭንቀት ይይዘኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በርካታ ሊቃውንት እያሉ እነርሱ ዝም
ሲሉ ሳይ ውስጤን ሀዘን ተሰማውና የሚሻክር የሚጎራብጥ ያልቀና ቢሆንም እንኳ የተሻለ እንጽፋለን ብለው ሊቃውንቱ እንዲነሣሡ ለማድረግ
ያህል ወደ ሥራው ገባሁበት፡፡ ወደ ሥራ ስገባ በኮምፒዩተር የመጻፉን ነገር ራሴ ሁሉን ነገር መሥራት ስለምችል ለማንም አሳልፌ ሳልሰጥ
ራሴ ሁሉን ነገር ሠራሁት፡፡ መጽሐፍ ሲጻፍ ራስጌ ግርጌ ግራና ቀኝ ሁሉም ነገር ምን ያህል መተው እንዳለበት ማወቅ ተገቢ ነው፡፡
በዚያ ላይ ገጾቹን መቀነስ መጨመር ያስፈልጋል የፊደላት ቁምፊ ቅርጽ እና መጠንም እንዲሁ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡
አንባቢ እንዳይሰለች ለማድረግ ደግሞ ልዩ ልዩ ምልክቶችን እንዲሁም ወጣ ገባ በማድረግ መጻፍን እና ፊደላቱ
ለእይታ ማራኪ መሆን ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህንን ሁሉ በአግባቡ ሠርቼ አጠናቀቅሁና መጋቢት 2010 ዓ.ም ሁሉን ነገር አጠናቅቄ ለሊቃውንተ
ቤተክርስቲያን ለግምገማ ተላከች፡፡ ብዙዎች አዩልኝ ተመለከቱልኝ ስህተቴን አረሙኝ፡፡ እኔም ያንን የማሰተካከል ሥራውን እየሠራሁ
በጎን የማተሚያ ቤቶችን መነጋር ጀመርሁ፡፡ ዋጋው ለአንድ ግለሰብ ያውም ለእንደኔ ላለው የሚነካ አልሆነም፡፡ በዚህ የተነሣ የሃይማኖት
ነገር ቢሆን ውስጤ እያፈረ ውስጤ እያረረ ሳላፍርና ሳልፈራ በአደባባይ ላይ ለማታውቁኝ ለሁላችሁ መጽሐፍ ላሳትም ነውና እርዱኝ አልኳችሁ፡፡
እናንተም እግዚአብሔር ያክብርልኝና ሳታሳፍሩ ያላችሁን ላካችሁልኝ፡፡ ገንዘብ በመላክ ውስጥ በጣም የማልረሳው አንድ የዩኒቨርሲቲ
ተማሪ (አሳየ በላይ) የላካትን 100 ብር እና አንዲት እህታችን ሙሉውን የወር ደመወዟን ምንም ሳታስቀር የላከችልኝን ነው፡፡ ብዙዎች እስከ 7000 ብር ድረስ የላኩልኝ ወንድሞችና እህቶችም አሉ፡፡
ይህን ሲያደርጉ ግን እኔ ማን እንደሆንኩ አያውቁም፡፡ በጣምም ይደንቀኝ የነበረው ይኼው ነው፡፡ በዚህ መልኩ ወደ 30 ሺህ ብር
አካባቢ አገኘሁ፡፡ ከዚያም ወደ ማተሚያ ቤት አመራሁና ውል ያዝኩ፡፡ ከዚያ ወደ ሥራ ሲገባ ‹‹ማርጂኑን አስፋው›› ይላል፡፡ እሽ
ብየ አሰፋዋለሁ ገጹ ግን በጣም ይጨምርብኛል፡፡ ‹‹ፎንቱን ከፍ አድርገው›› ይለኛል እርሱ ባለኝ መሠረት ሳደርገው ከ600 ገጽ
በላይ ይሆናል፡፡ ዋጋ ስጠይቅ እስከ 133 ብር ለ1 መጽሐፍ ያደርሰዋል፡፡
በዚህ ጊዜ የእኔ ህልም እንዳልተሳካ አወቅሁ ነገር ግን ተስፋ አልቆረጥሁም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሳያውቁኝ
ገንዘባቸውን የሰጡኝ እህቶችና ወንድሞችን ምን እላቸዋለሁ? ምን አደረስከው ሲሉኝ ምን እመልስላቸዋለሁ፡፡ ከዚያ ባለሰባት ምእራፍ
የነበረችውን መጽሐፍ ሰባተኛውን ምእራፍ ማስወገድ ግድ ሆነብኝ፡፡ ሰባተኛውን ምእራፍ ሳስወግደው የገጹ መጠን በተወሰነ መልኩ ቀነሰልኝ፡፡
ለዚህ ዋጋ ስጠይቀው አሁንም የሚነካ አልሆነም፡፡ በዚህ ዋጋ መስማማት አቃተኝ ምክንያቱም ከ300 ሺህ ብር በላይ ሊያስወጣኝ ነውና፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን 3 ወራት አልፈዋል፡፡ ይህ ማተሚያ ቤት እንደማይሠራው ሳረጋግጥ አሁን ወደታተመችበት ቦታ ደወልኩና የገጹን ብዛት
ነገርኳቸው ዋጋ ሠርተው አሳወቁኝ፡፡ የመጀመሪያው ከተመነለት ዋጋ በግማሽ ያህል ቀነሱልኝ፡፡ እኔም አይኔን ወደ ‹‹ፋር ኢስት››
አደረግሁ፡፡ ውል እንዲይዝ አንድ ወንድሜን ላኩት በወር ውስጥ እንደሚደርስ የሚገልጥ ውል መስከረ፣ 22/2011 ዓ.ም ይዞ መጣ፡፡
ጥቅምት 22/2011 ዓ.ም ደብረ አሚን በእጃችን እንደምትገባ አድርገን ስንጠብቅ ማተሚያ ቤቱ የተወሰኑ
ቀናትን አዘገየን፡፡ በዚያ ላይ እኔም ሙሉ የሕትመት ወጭውን የሆነ ተአምር ካልተፈጠረ በቀር ስለማልችል ገንዘብ የሚረዱኝን ሰዎች
ማፈላለግ ጀመርሁ፡፡ ከዚያም የሚመለስ 30 ሺህ አንድ እህታችን 50 ሺህ አንድ ወንድማችን ረዱኝና ክፍያ ፈጽሜ ከአዲስ አበባ ወደ
ጎጃም አመጣሁት፡፡ ጠቅላላ የቅጂው ብዛት 3000 ነው፡፡ ከእነዚህ ቅጂዎች መካከል እስካሁን ድረስ ከ50 ያላነሱ በስጦታ ለተለያዩ
ሰዎች የተሰጡ ናቸው፡፡
ይች መጽሐፍ በዚህ መልኩ እጅ ላይ ስትያዝ ቀላል ትመስላለች እንጂ በጣም ከባድና አድካሚ ውጣ ውረዶችን
ያለፈች ናት፡፡ በዚህ መልኩ በአጭሩ ልገልጠው ወደድሁ እንጂ በርካታ ፈተናዎች ነበሩ፡፡
መጽሐፏ የታተመችው ለትርፍ አይደለም፡፡ የኅትመትና የትራንስፖርትን ወጭ ጨምሮ በአጠቃላይ በአማካኝ ለ1
ደብረ አሚን ከ60 ብር ያላነሠ ወጭ አድርገናል፡፡ የመጽሐፏ ዋጋ 100 ብር ነው፡፡ ውል ስንይዝ ዋጋውን በ85 ብር ነበር እንዲሠራ
የተነጋገርን፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ መጻሕፍት በስጦታ መልክ መሰጠት ስላለባቸው እና አንዳንድ የኅትመት ችግር ያለባቸውን መጻሕፍት
ለመቀየር ሲባል ኪሳራ እንዳይኖር ቢያንስ 100 ብር ዋጋ ይሁንና አስተያየት እያደረግን እናደርሳለን በሚል ነው ወደ 100 ብር
ከፍ ያለችው፡፡ በዋናነት ዋጋውን ያስጨመረኝ ግን አንድ መጽሐፍ 306 ገጾች ያሉት (ማተሚያ ቤቱ ለኅትመት ያስከፈለው) በዚሁ ማተሚያ
ቤት የታተመ ዋጋው 130 ብር ነው፡፡ እኔ ደግሞ ለኅትመት የከፈልኩበት ገጽ ብዛት 334 ነው፡፡ 306ቱ በ130 ከተሸጠ እኔም
334ቱን በ100 ብር ዋጋ ባወጣለት በጣም ቅናሽ እንደሆነ ስረዳ ዋጋውን 100 ብር ማድረግን መረጥኩ፡፡
መጽሐፏ ገጽ ለመቀነስ ሲባል ብዙ ነገር የተደከመባት ናት፡፡ በዚህ መልኩ ነው እንግዲህ ወደ እጃችን የደረሰች፡፡
ብዙዎች እንድናደርሳቸው በስልክም በመልክትም ይጠይቁናል፡፡ ተፈላጊነቷ በጣም እየጨመረ መጣ፡፡ እኔ እና በማሰራጨት በኩል የሚያግዙኝ
ወንድሞቼ ደግሞ ለእያንዳንዱ ሰው በተፈለገው ልክ መድረስ አልቻልንም፡፡ ብዙዎች የገና በዓልን ለማክበር እንደመጡ በየሰዓቱ እየደወሉ
እንድናደርሳቸው ጠይቀውናል እኛ ግን መድረስ ሳንችል ቀርተን አሳዝነናቸዋል፡፡ ለተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎ በፖስታ አድራሻቸው
እየተሰበሰቡ ጠይቀውን አድርሰናል፡፡ ሆኖም ግን አቅርቦታችን አናሳ ነው፡፡ መጻሕፍት መደብሮች ውስጥ ግን እንደሌሎች መጻሕፍት በብዛት
አትገኝም፡፡ ይህ ብዙ ምክንያቶች አሉት፡-
1ኛ. መጻሕፍት መደብሮች ዋና ዓላማቸው ትርፍ እንጂ ምእመናንን የመታደግ ሥራ አይደለም፡፡ ዋጋውን እንዳያችሁት
ለአከፋፋዮች ተብሎ የተጨመረ የተጋነነ ነገር የለውም፡፡ እነርሱ የሚፈልጉት 40 እና 35 ፐርሰንት ቅናሽ ነው፡፡ በዚህ ቅናሽ እንድንሰጣቸው
ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ዋጋ ስንሰጣቸውም መጽሐፉ ከተሸጠ በኋላ ክፍያ ሊፈጽሙልን ነው፡፡ መጽሐፉን በብዙ ውጣ ውረድ ደክሜ ጽፌ 40
ብር ነጋዴዎች ያተርፋሉ እኔ ግን ኪሳራ ውስጥ እወድቃለሁ ማለት ነው፡፡ በዚህ መካከል እኔ የጻፍኩትም አምስት ሳንቲም አላገኝም
እናንተ የምትገዙትም አምስት ሳንቲም ቅናሽ አይደረግላችሁም፡፡ ሙሉውን ትርፍ ጠቅልሎ የሚወስደው ነጋዴው ብቻ ነው ማለት ነው፡፡
ቤተክርስቲያናችን እንኳ ስንት ችግር እያለባት ከትርፉ በሚገኝ ገንዘብ ተጠቃሚ አትሆንም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ እኔም በስጦታ የምሰጠውን
እንዲሸፍንልኝ ገዥውም ከነጋዴ 100 ብር ከሚገዛው እዚሁ ቅናሽ እያደረግን እንድናደርስ ከወንድሞቼ ጋር ተስማማን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ
30 ፐርሰንት ቅናሽ አድርገን ለነጋዴ ከምናስረክብ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ባሉ መጻሕፍት መሸጫ ሱቆች ላይ ብንሰጣቸው የተሻለ
እንደሆነ በማሰብ ታላቁ ዲማ ገዳም ውስጥ አንድ ብለን በማስረከብ ሥራ ጀመርን፡፡
2ኛ. መጻሕፍት መደብሮች ለሚገዛቻ ሁሉ መስጠት እንጂ ችግሩ ወዳለበት አካባቢ የማድረስ ችሎታውም አቅሙም
አይኖራቸውም በሚል በግል ማከፋፈልን መርጠናል፡፡ ችግሩ ባለበት አካባቢ ያሉ አከፋፋዮች ግን ፍርኃታቸውም ጉድ ነው፡፡ መጽሐፉን
ለማከፋፈል በጣም የሚፈሩ አሉ፡፡ እኔ የጻፍኩት እያለሁ ለማከፋፈል ምኑ ያስፈራል?
3ኛ. የመጽሐፉ የቅጂ ብዛት በየቦታው ተከፋፍሎ የሚዳረስ አይደለም፡፡ በዚህ ኅትመት 3000 ቅጂዎችን ብቻ
ነው ያሳተምን፡፡ ከእነዚህ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነውን አከፋፍለነዋል፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች ማከፋፈሉን በግለሰብ ደረጃ አድርገነዋል፡፡ ይህንን ችግር ተረድታችሁ እስካሁን ድረስ
እየጠየቃችሁን ሳናደርሳችሁ የቀረን ሁሉ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ በአቅራቢያችሁ ያሉ መጻሕፍት አከፋፋዮች ከተባበሩን እነርሱን እያናገራችሁ
ብትጠቁሙን እና በቀላሉ ብናደርሳችሁ ደስ ይለናል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ያለን አማራጭ ፡-
1ኛ. ፖስታ ቤትን መጠቀም ነው፡፡
2ኛ. የመጽሐፉን ዋጋ በባንክ ታስገቡና መክፈላችሁን አረጋግጠን መጽሐፉን በሰው መላክ ነው፡፡
3ኛ. ሰው እየላካችሁ ከደብረ ማርቆስ መውሰድ፡፡
4ኛ. ሁለት ሦስት እየሆናችሁ እየደወላችሁ እንድንልክላችሁ መጠየቅ፡፡
5ኛ. በመኪና ሹፌሮች በኩል ማድረስ ነው፡፡
በዚህ መልኩ ልናደርሳችሁ እንችላለን፡፡ ብዙ መጻሕፍትን በዚህ መልኩ ነው እያደረስን ያለነው፡፡ ስለዚህ
በተለይ መጻሕፍት አከፋፋዮች ቢተባበሩን መልካም ነው፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት፤ በግቢ ጉባዔ፣ በሰበካ ጉባዔ፤ በሕንጻ አሠሪ ኮሚቴነት
ወይም በሌሎች መልኩ ቤተክርስቲያንን እያገለገሉ ላሉ ትርፉ ለቤተክርስቲያኒቱ እንዲሆን ለሚሩ ሁሉ 30 በመቶ ቅናሽ እናደርግላቸዋለን፡፡
ስለዚህ መጽሐፉን እየወሰዳችሁ መጠቀም ትችላላችሁ፡፡ እስካሁን ባለው ሱቅ ላይ የምታገኟት ዲማ ገዳም እና ብቸና ወረዳ ማዕከል ሱቅ
ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የጁቤ፣ ደጀን፣ የትኖራ፣ ወጀል፣ጉንደ ወይን፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ፣ ቢቡኝ፣ መካነ ሰላም፣
ሞጣ፣ መርጡለ ማርያም በትእዛዝ አድርሰናል፡፡ አዲስ አበባም ለተወሰኑት በጣም በጥቂቱ ቢሆንም ለማድረስ ሞክረናል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ
አዲስ አበባ የሚገኙ አከፋፋዮችን መጽሐፏን ይዞ እየሄደ የጠየቀልኝን ዮሴፍ ፍስሐን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ እናንተም በአቅራቢያችሁ
ያሉትን የማኅበረ ቅዱሳን ማእከላት ሱቆችን አነጋግሩ እንልክላቸዋለን፡፡ በዋናው ማእከል በኩል በ40 በመቶ ቅናሽ ግን ማድረስ የምችለው
አይደለም፡፡
በመጻሕፍት መደብሮች ስለማታገኟት ከዚህ በታች በተያያዘው ፎቶ ላይ ያሉ ስልኮችን በመጠቀም መልእክት አድርሱን
መጽሐፏን እንልክላችኋለን፡፡ ከዚህ የተሻለ አማራጭ ካለ እስኪ እናንተም ጠቁሙኝ፡፡ መጻሕፍት አከፋፋዮችን ግን እናንተም እስኪ አስተዋውቋቸው
እንደዚህ የምትባል መጽሐፍ ነበረች አምጡልን በሏቸው እኛ እናደርሳቸዋለን፡፡ ግን ለትርፍ ሳይሆን ነፍሳትን ለማዳን ለሚሠሩ ሰዎች
ብቻ ነው፡፡ አናሳ በሆነው አቅርቦታችን ለተማረራችሁ፣ ቅርም ላላችሁ፣ በውስጥ መስመርም ቅሬታችሁን ለጠቆማችሁኝ ሁሉ ይቅርታ እየጠየቅሁ
ምክንያቴ ግን ይህ እንደሆነ እንድታውቁልኝ አሳስባለሁ፡፡
==================
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
ጥር 17/2011 ዓ.ም (ዲቁና የተቀበልኩባት ቀኔ ናት፡፡ ጥር 2000 ዓ.ም)
====================