Wednesday, January 23, 2019

"እንትንን አትሁን"


እንትን ከሆንክ ጤንነትህ በራሱ ያጠራጥራል። እንትን ቅመም አይደለችም ዝም ብላ ሁሉንም እተካለሁ ባይ የወተት ዝንብ እንጅ። እንትን ያወቀ ሰው አማርኛ ለመናገር አይቸገርም። እንድትነግሩኝ የምፈልገው በእንግሊዝኛ እና በሌሎች ቋንቋዎች ውስጥ እንትን ምን እንደምትባል ነው። አረ መኖሯንም እስኪ አረጋግጡልኝ።

እንትን ሰውንም እንስሳንም ቁስ አካልንም ቃልንም የሚዳሰሰውንም የማይዳሰሰውንም የሚጨበጠውንም የማይጨበጠውንም ብቻ ሁሉንም እወክላለሁ ባይ ናት። ከቃላት ሁሉ ያለቦታዋ የምትገባ የጥፋት መሸፈኛ ቃል እንደ እንትን ያለ ቃል አላገኘሁም። ስናዝዝ እንት አምጣ፤ ስንጠይቅ እንትን ልስጥህ? ስናስረዳ እንትን ለማለት ፈልጌ ነው፤ ሐኪም ሲጠይቀን እንትን ሆነን፤ መልስ ስንመልስ እንትን ይሆናል ወዘተ እያልን ነው። እና ሁሌ ግርም የምትለኝ ቃል ብትኖር እንትን ናት።
እንትን ብቻ እንግባባለን እኮ። እንትና እንትን ፈልጎ መጥቶ እንትን አለ ወይ ብሎኝ የለም አልኩት። ይች እንትን በዚህ ሁሉ ውስጥ ምን ምን እንደተካች እግዚአብሔር ይወቀው።

ስህተትን እና አለማወቅን እንትን እንሸፍናለን። በጋዜጠኞች የሚጠየቁ ሰዎችን ልብ ብላችሁ አዳምጧቸውማ እንትን ሳይሉ አይቀሩም። የወሬ ማጣፈጫ ቅመም ናት እንዳንል ስህተታችንን እና አለማወቃችንን ነው እየሸፈንባት ያለን። ታዲያ አንተ እንደ እንትን አትሁን። ሁሉን እተካለሁ አትበል። ዲያቆኑን፣ ካህኑን፣ ጳጳሱን ወዘተ እንደ እንትን እተካለሁ አትበል።

መምህሩን፣ ፖሊሱን፣ ባለሙያውን፣ ሐኪሙን፣ አካውንታቱን እኔ ብቻ እንደ እንትን እተካለሁ አትበል። ያለቦታህ እየገባህ የሌሎችን ሥራ ብቻህን አትቀማ።
ከምር "እንትን" ማን ናት? ሃሳቤን ካገኛችሁት አስተያየት መስጫው ላይ ስለ እንትን ጻፉ።

"እንትን አድርጌ መጣሁ" ይላል ምን አድርገህ? ይለዋል "ወጥ ሰርቸ እንትን አሳንሸው" ይላል። ምን አሳነስኸው ይለዋል "ሃሳቤን እንትን ወስዶት ጨው አሳነስኩት" .....ወይ እንትን ስንቱን ተካችው።

እኔ በተለይ የሚገርሙኝ የመንግስት ባለሥልጣናት ጥያቄ እንፈታለን ብለው መጥተው መዓት የሆነ ጥያቄ ይቀበሉና ሲመልሱ በቀጣይ ዓመት እንትን እናደርጋለን ብለው ሲናገሩ ነው። እንትን ምንድን ነው?


ተናጋሪው ብቻ የሚያውቃት ቃል ነገር ግን በሁሉ ቦታ ሁሉን እተካለሁ ባይ ቃል እንትን ብቻ ናት። ወይ እንትን!

No comments:

Post a Comment