Monday, January 21, 2019

"በተዋሕዶ ከበረ" ላይ የተነሡ ጥያቄዎችና መልሶች!


===================================
"በተዋሕዶ ከበረ" በሚል ርእስ አጭር ጽሑፍ መጻፌ ይታወቃል። በዚህ ጽሑፍ ላይ አስተያየት የሰጡ በርካታ ሰዎች አሉ። አስተያየት ሰጭዎችን ሥራየ ብየ በየቀኑ ስለማልከታተል በጊዜው መልስ ለመስጠት አልችልም። አስተያየት ሰጭዎችን ከአንድ ቀን በላይ አላያቸውም። በዚህ የተነሣ አንድ ጓደኛዬ በውስጥ መስመር ይህን መልእክት ይልክልኛል። እኔም ቅባት አማኞች በራሳቸው ገጽ የጻፉት ስለሚሆን መልስ ልስጥበት እያልኩ ስጠባበቅ "በተዋሕዶ ከበረ" በሚለው ጽሑፌ ላይ የተሰጠ አስተያየት ሆኖ አገኘሁት። በአጋጣሚ ጽሑፉን ስጽፈው በወንድ አንቀጽ አድርጌ ጽፌው (ጀምሬው) ስለነበር በአስተየየት ሰጭዋ samrawit belete ጾታ የተገለጠ አይደለም። ለዚህ ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ጽሁፉ የጠያቂዋን ጥያቄ ከዚያም የእኔን መልስ የያዘ ነውና በጥሞና ተመልከቱት። በዚህ ጽሑፍ ላይ የተሳሳተ አነጋገር ቢገኝ ስህተቱ የራሴ እንጂ የቤተ ክርስቲያኔ አይደለም። እኔ አላዋቂ ሆኘ ብሳሳትም ቤተ ክርስቲያናችን ግን ባሕረ ጥበባት፣ መዝገበ ምሥጢራት በምድር የተሰራች ሰማያዊት ናት።
=============================
ጥያቄ፡- ‹‹ለመልካሙ በየነ እና በተዋሕዶ ከበረ ብላችሁ ለምታምኑ በሙሉ››
መልስ፡- መልካሙ በየነ "በተዋሕዶ ከበረ" ብሎ የሚያምን አንድ ክርስቲያን ነው። ስለዚህ በዚህ እምነት ውስጥ መልካሙ በየነ ገባበት እንጂ ይህን እምነት መልካሙ በየነ አልፈጠረውም። ስለዚህም "ለመልካሙ በየነ እና በተዋሕዶ ከበረ ብላችሁ ለምታምኑ በሙሉ" ሲል "በተዋሕዶ ከበረ" ብሎ ከሚያምኑ ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ስለሆንኩ ስሜ መጠቀሱ ትርጉም የለውም። "በተዋሕዶ ከበረ" ብሎ ከሚያምኑ ውጭ አይደለሁምና ያ እኔንም ያጠቃልል ነበር።
ጥያቄ፡- “በተዋሕዶ ከበረ” ብለህ የተናገርከው የክብር መገኛው ተዋሕዶ ነውን? (መልስ ከነማስረጃው)
መልስ፡- የክብሩ መገኛ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ማለት ደግሞ የሦስቱም አካላት መጠሪያ ስማቸው ነው። በማክበር ሦስቱም አካላት አንድ ናቸው። ማክበር አካላዊ ሳይኾን አምላካዊ ግብር ነው። ስለዚህ አብ ያከብራል፣ ወልድም ያከብራል፣ መንፈስ ቅዱስም ያከብራል። አብ ፈጠረ፣ ወልድ ፈጠረ፣ መንፈስ ቅዱስ ፈጠረ ብንል ሌሎች በስም ስላልተጠሩ ከመፍጠር በአፍአ ናቸው አንልም። እንደዚህም ሁሉ በማክበር ጊዜ ሦስቱም አካላት ያከብራሉ። ስለዚህ በተለየ አካሉ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ የተዋሐደውን ሥጋ አክብሮታል። ተዋሕዶ የምንለው ከኹለት አካላት አንድ አካል፣ ከኹለት ባሕርያት አንድ ባሕርይ የኾነበት፤ የቃል ገንዘብ ለሥጋ፣ የሥጋ ገንዘብም ለቃል ከኃጢአት በቀር ገንዘቡ የኾነበት፤ የወልድ ክብር ለሥጋ ገንዘብ የኾነበትን ምሥጢር ነው። ተዋሕዶ ምስጢር ነው። ይህን መመርመርና ማወቅ ከባድ ነው። ድንቅ ምስጢር ረቂቅ ነገር ነውና። በሰው አእምሮ ከመመርመር በጣም የራቀ ነው። የጠየቁትን ማስረጃ ወደታች ያገኙታል።
ጥያቄ፡- አንዱን አካል አክባሪ አንዱን አካል ከባሪ አድርጋችሁ ስትናገሩ መለኮት የመለኮትን ሥራ ይሰራል ሥጋም የሥጋን ሥራ ይሰራል ከሚሉት መለካዊያን በምን ትለያላችሁ?
መልስ፡- እኛ አንዱን አካል አክባሪ አንዱን አካል ከባሪ አድርገን አንተ እንደምትለው ያለ ፍልስፍና ላይ አልተሰማራንም። ከበረ፣ አከበረ የምንለው በጊዜ ተዋሕዶ ላይ ያለን ጊዜ ብቻ ናት። መክበር ይሻ የነበረን ሥጋ አካላዊ ቃል በአምላክነት ክብሩ አከበረው ይች እመቤታችን "ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ" ባለችው ጊዜ የተፈጸመች ድንቅ ምስጢር ናት። ከዚህ ጊዜ በኋላ መለኮትና ትስብእት አንድ ስለኾኑ ከባሪና አክባሪ የለም። ወልድ አምላክ ነውና በአምላክነት ክብሩ ያከብራል ስንል ወልድ ማክበር አይችልም ካላችሁን "በመንፈስ ቅዱስ ከበረ" ስትሉ መንፈስ ቅዱስስ ማክበር የብቻው ግብሩ ነው ብላችሁ ነውን? አዎ ካላችሁ ለመንፈስ ቅዱስ ከመሥረጽ ውጭ ሌላ አካላዊ ግብር እንዳለው ከየት ተማራችሁት? ማስረጃስ ማቅረብ ትችላላችሁ ወይ?
አንዱ አካል አክባሪ ያልከው ቃልን አንዱ አካል ከባሪ ያልከው ትስብእትን ለማለት ፈልገህ ነው። እናንተ "በመንፈስ ቅዱስ ከበረ" የምትሉት ሥግው ቃልን ነው። ሥግው ቃል አምላክ ነው ወይስ አይደለም? ሥግው ቃል እስከሚከብር ድረስ የአብ የመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ማን ነበር? ትስብእት አምላክ የኾነው በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከኾነ ሥግው ቃል እስኪከብር ድረስ አብና መንፈስ ቅዱስ ዲዳ ነበሩ (ሎቱ ስብሐት)?
ጥያቄ፡- ሥጋ በተዋሕዶ ከብሮ እንኳንስ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ መሆን ይቅርና የጸጋ ልጅነትንስ ያገኛል ወይ?
መልስ፡- ይህን ለማወቅ ወደ አካላዊ ቃል የባሕርይ ልጅነት መሄድ ይጠይቃል። አካላዊ ቃል የአብ የባሕርይ ልጁ ነው ወይስ አይደለም? ነው ካልክ የባሕርይ ልጁ ቃል የተዋሐደው ሥጋ የአብ የባሕርይ ልጁ ለመኾን የማይችልበት ምን ነገር አለ? በቅብዐት የባሕርይ ልጅ ኾነ ብንል ኖሮ እንደ ነቢያት እንደ ነገሥታት እንደ ካህናት የጸጋ ነው እንለው ነበር። ይህ እኮ ቃል የባሕርይ አምላክ እንደኾነ ኹሉ የተዋሐደውንም ሥጋ የባሕርይ ልጁ አድርጎታል ነው። አብ "ወአነ ዮም ወለድኩከ" ያለው ማንን ነው? ዛሬ ወለድሁህ ማለት እኮ አንተ ሥጋ አካላዊ ቃል የባሕርይ ልጄ እንደኾነ አንተም ከልጀ ጋር ተዋሕደሃልና ልጄ ነህ ሲለው ነው። አንድምታውን ተመልከተው እስኪ ከተቀበልከው። በተዋሕዶ ከብሮ የባሕርይ እንጂ የጸጋ ልጅ ሊኾን አይችልም። የጸጋ ልጅ ይኾን የነበረው "በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ" ብንል ነበር። በቅብዐት ከብሮ የባሕርይ ልጅ የተባለ አናውቅምና። 
ጥያቄ፡- ልጅነት የሚገኘው በተዋሕዶ ወይንስ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ?
መልስ፡- ልጅነት የሚገኘው በኹለቱም ነው። በተዋሕዶ የሚገኘው ልጅነት የባሕርይ ልጅነት ነው። በቅብዐት የሚገኘው ግን የጸጋ ልጅነት ነው። እኛ ሁላችን ክርስቲያኖች ስንባል ልጅነትን ያገኘንበት ቅብዐ ሜሮን ሁላችንንም የእግዚአብሔር ልጆች አስብሎናል። ይህ ቅባት የባሕርይ ልጅ የሚያደርግ ቢሆን ኖሮ ሁላችንም እኮ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጆች እንባል ነበር። ትስብእት የባሕርይ ልጅ የኾነው በተዋሕዶ ነው።
ጥያቄ፡- ክርስቶስ በተዋሕዶ ከብሮ እንዴት ካህን ሊቀ ካህን፣ ንጉሠ ነገስት፣ ርዕሰ ነቢያት፣ በኩረ ምዕመናን፣ ሐዲስ አምላክ ይባል ዘንድ ይቻላል?
መልስ፡- በመጀመሪያ ሐዲስ አሮጌ የሚባል አምላክ አናውቅም። ሐዲስ አምላክ ኾነ ብለንም ተብለንም አናውቅም። ቃል ሥጋን የተዋሐደ አርጅቶ፣ አፍጅቶ ሐዲስ ለመኾን አይደለም። በመዠመሪያ የጌታን ሰው መኾን ድንቅ ምስጢር እና ጥበብ መረዳት ያስፈልጋል። ይኸውም ምስጢረ ሥጋዌ ነው። በየትኛውም የሥጋዌ ትምህርት ላይ «ሐዲስ አምላክ ሆነ» የሚል ንባብ አናገኝም። መለኮቱ አያረጅም አያፈጅም ታዲያ «ሐዲስ» ልንለው እንዴት እንደፍራለን? እርሱ እኮ ከዘመናት በፊት የነበረ አልፋ ዘመናትን አሳልፎ የሚኖር ኦሜጋ ነው። እርሱ እኮ ዘመናትን አስረጅቶ የሚኖር እንጂ ዘመናት የሚያስረጁት አምላክ አይደለም። እርሱ እኮ ዘመናትን የሚያድስ እንጂ ዘመናት የሚያድሱት አይደለም። ታዲያ ሰው አምላክ ቢኾን አምላክ ሰው ቢኾን ዕፁብ ዕፁብ ዕፁብ ይባላል ይደነቃል ይመሰገናል እንጂ «ሐዲስ አምላክ» ሊባል እንዴት ይቻላል?
«ሐዲስ አምላክ ሆነ» ማለትን ሊቃውንት መምህራን አውግዘውታል። ይህንንም መዝገበ ሃይማኖት በተሰኘው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ፫÷፵፩ ላይ እንዲህ ተጽፏል፡-
«እመቦ ዘይብል አምላክ ሐዲስ ወአምላክ ብሉይ ውጉዝ ውእቱ - አዲስ አምላክና አሮጌ አምላክ የሚል ቢኖር የተወገዘ ነው» ይላል።
በዚህም መሠረት «ሐዲስ አምላክ ሆነ» ብሎ መናገር፣ ማመን፣ ማስተማር ከአንዲት ቤተክርስቲያናችን በራሱ ፈቃድ የተለየ የተወገዘ፣ የተረገመ ነው ማለት ነው። እግዚአብሔርን «ሐዲስ» ብለን ዘመናት እንደሚያድሱት፤ «አሮጌ»ም ብለን ዘመናት እንደሚያስረጁት አንናገርም። ዘመናትን የሚያስረጃቸው እና ዘመናትን የሚያድሳቸው አምላክ እንለዋለን እንጂ።
«ቃልም ሥጋን ስለተዋሐደ በኲረ ምእመናን ተባለ» ድርሳነ ቄርሎስ ፳፰÷፪-፫። ይላል እስኪ ይህን ተመልከተው።  ካህን፣ ሊቀ ካህን፣ ንጉሠ ነገሥት ሆነ በተዋሕዶ ነው የሚለው እኮ መጽሐፍ ነው። መዝሙረ ዳዊት ላይ "እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም" አይልም ይላል? ይላል ካልክ እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው የተባለው በተዋሕዶ ነው ወይስ በቅብዐት ነው? ታዲያ እግዚአብሔር ካህን ለመባል ንጉሥ ለመባል በኩረ ምእመናን ለመባል የግድ "በመንፈስ ቅዱስ ከበረ" ማለት ያስፈልጋል ትላለህ?
ጥያቄ፡- “እራሱ(አብ) አክብሮ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድኩህ አለው” ዮሐንስ አፈ ወርቅ ድር 8፥69 ብሎ አብ ወልድን እንዳከበረው እየተናገረ ለምን እራሱን በራሱ አከበረ ለማለት ደፈራችሁ? ምን ምስክርስ አላችሁ?
መልስ፡- አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድኩህ የሚለው ቃል መነሻው ዳዊት ነው። ይህን የጻፈው ዳዊት ነው። ስለዚህ በዚያ ያለውን አንድምታ ትርጓሜ ተመልከተው። ማክበር አምላካዊ ግብር እንደመኾኑ መጠን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሊነገር ይችላል። ይህ ችግር ነው ብለን አናውቅም። ሰለዚህ ማክበር የማን ግብር ነው ብለህ ታስባለህ? ግብርነቱስ የአካል ነው ወይስ የአምላክነት?
ምስክራችን
«ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጂ ሰው ቢኾንም በባሕርይ ክብሩ ከበረ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው ሥጋ ትሁት ሕጹጽ ነዳይ ስለኾነ ተለዐለ ተብሎ ተነገረለት ከኹሉ በላይ የኾነ ስምንም እርሱ ራሱ ሰጠው ተባለ ይህም የኾነ በባሕርይ ተዋሕዶ ነው አምላክ እንደኾነ እኛንም እርሱ ወደ አለበት ያቀርበን ዘንድ» ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ በሃይማኖተ አበው ስምዐት ፻፳፬÷፴፬ ላይ ይላል።
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በሃይማኖተ አበው ፷፮÷፲፰-፲፱ ላይ አካላዊ ቃል የተዋሐደውን የእኛን ሥጋ እንዳከበረው በመደነቅ እንዲህ ይላል፡-
«ክብሩ ተለይቶ የነበረ ሥጋን ክቡር አምላክ ሊያደርገው የጸጋ ገዥነትን አጥቶ የነበረ ሥጋንም የባሕርይ ገዥ ሊያደርገው ወደደ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ኾነ ያለውንም ሰው በመኾን ሊገልጠው ወደደ። ስለዚህ ሥጋዬን ተዋሐደ። ወንጌልን ሲያስተምር እሰማው ዘንድ ሥጋዬን በተዋሕዶ ገንዘብ አደረገ፤ መንፈስ ቅዱስን ሰጠኝ ሰጠሁ ተቀበልኩ ለእኔም ፍጹም ሕይወትን ገንዘብ አደረግሁ። እርሱ ያከብረው ዘንድ ሥጋዬን ተዋሐደው። የሚያድነኝ መንፈስ ቅዱስን ሰጠኝ»
በዚህ አነጋገር መሠረት እርሱ የተባለው አካላዊ ቃል ነው። አንዳንድ የቅብዐት እምነት ተከታዮች ግን እርሱ የሚለውን ለመንፈስ ቅዱስ ቀጽለው በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ለሚለው ኑፋቄያቸው ደጋፊ ጥቅስ አድርገው ይጠቅሱታል። እርሱ የሚለውን ለመንፈስ ቅዱስ ከቀጸሉት ሥጋዬን የተዋሐደው መንፈስ ቅዱስ ነው ያሰኛልና ፍጹም ክህደት ነው። መንፈስ ቅዱስ ሥጋዬን ተዋሕዶ ሰው ኾነ የሚያሰኝ ክፉ መንገድ ነው። በተዋሕዶ ከበረ ብለው ላለማመን ወደ ሌላ ስህተት ሲያመሩ ይታያሉ። ሊቁ እንደጻፈው ግን እርሱ የሚለው ለአካላዊ ቃል የተነገረ ነው። ስለዚህም እርሱ መንፈስ ቅዱስን ሰጠኝ ሲል አካላዊ ቃል ለተዋሐደው ሥጋ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን መስጠቱንና ሥጋ የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ገንዘቡ ማድረጉን መናገር ነው። ይህ የተደረገው ደግሞ በተዋሕዶ ብቻ ነው። የሊቁን ትምህርት በማስተዋል ተመልከቱና ከሰፊው የምስጢር ባሕር ውስጥ ገብታችሁ የምስጢሩን ጥልቀት የትምህርቱን ርቀት ( ይጠብቃል) አድንቁ።
ሃይማኖተ አበው ስምዓት ፻፳፬÷፲፬ ላይ «ወከመዝ ነአምሮ ለሊሁ ተቀብዐ ከመ ሥርዓተ ትስብእት ወዳእሙ ውእቱ ዘይቀብዕ ርእሶ በመንፈሱ ባሕቲቱ - በተዋሕዶ እንደከበረ እናውቃለን ግን በገዛ ሥልጣኑ ራሱን የሚያከብር እርሱ ነው» ይላል።
ወንጌላዊው ዮሐንስም በወንጌሉ ዮሐ ፲፯÷፲፱ ላይ «አነ እቄድስ ርእስየ - እኔ ራሴን አከብራለሁ» ብሎ ጌታ የተናገረውን ጽፎት እናገኛለን። እኔ ራሴን አከብራለሁ ሲል በተዋሕዶ ማለቱ ነው። እኔ ሲልም በቃል ርስት ኾኖ ነው በሥጋ ርስትማ ይህን አይናገርም። ሥጋ ስንኳንስ ሊያከብር የጸጋ ልጅነትን እንኳ ያጣ ነበርና። ቃል ሲዋሐደው ግን ክቡር አምላክ ኾነ ይባላል። እኔ ብሎ አምላክነቱን (አክባሪነቱን) ራሴን ብሎ ሰውነቱን (ከባሪነቱን) ይናገራል። እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እርሱ ራሱም ከባሪ ነው።
ሌሎችን ማስረጃዎች ደብረ አሚን የተሰኘችውን መጽሐፌን እንድታነብ እጋብዝሃለሁ። እርሷን ማንበብ ካልቻልህ ፕሌይ ስቶር ላይ ገብተህ "ፍኖተ ጽድቅ ዘተዋሕዶ" የምትለዋን መተግበሪያ አውርደህ በ20 ብር ገዝተህ አንብባት።
አካላዊ ቃል ማክበር ይችላል አይችልም? ማክበር የአብ የብቻው ግብር ነውን? ከላይ ማክበር የመንፈስ ቅዱስ ግብር ነው ስትል አልነበረምን?
ጥያቄ፡- “ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሊሆን እራሱን ያከበረ አይደለም አንተ ልጄ ነህ ያለው እሱ ነው እንጅ” ዕብ 5፥5 በማለት አብ ሊቀ ካህናት፣ ንገሠ ነገስት እንዳደረገው እየተናገረ እናንተ ለምን እራሱን በራሱ ሾመ፣ አከበረ ለማለት ፈለጋችሁ?
መልስ፡- ዕብ 5፥5 ላይ ያለውን ቃል ለመረዳት የምትፈልግ ከኾነ ቃሉን ሳትቆራርጥ ከቁጥር 4 ጀምረህ አንብበው። ቁጥር 5 ላይ "ከማሁ" "እንደዚህም ሁሉ" ብሎ ነው የሚጀምር። "ከማሁ" የሚለው ቃል ከላይ እንደተገለጠው ማለት ስለኾነ ወደድህም ጠላህም ከቁጥር 5 በፊት ያለውን አንብበህ መምጣት አለብህ። ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የኾነው ወይም ራሱን ሊቀ ካህናት አድርጎ የሾመ ነቃሁ በቃሁ ብሎ አይደለም የሚል ነው። "ቅዱስ ጳውሎስ ክህደትን ሊያስተምር መምህር አልኾነም" ቢባል ቅዱስ ጳውሎስ መምህር አይደለም ተብሎ የሚተረጎምበት አማርኛ የለም። ዕብ 5፥5 ን ለመረዳት ከፈለግህ ከላይ ያለውን በሙሉ አንብብ። በቀጣይ ደግሞ ያ አልረዳህ ካለ አንድምታውን ተመልከት። መጽሐፍ አንባቢ ያለ መጽሐፍ ተርጓሚ መጽሐፍ ቢያነብ ይስታል እንጂ እምነቱን አያጸናም። አንድምታ ትርጓሜው ከሌለህ ልልክልህ እችላለሁ።
ራሱን በራሱ አከበረ ለማለት የቻልን እኮ ማክበር የሁላቸው ግብር እንደኾነ ስለተረዳንና መጻሕፍትም ስለተናገሩት ነው። ከላይ የሰጠሁህን ማስረጃዎች ተመልከት የጠቆምሁህንም መጻሕፍት ተመልከታቸው። "አብ ሊቀ ካህናት፣ ንገሠ ነገስት እንዳደረገው እየተናገረ እናንተ ለምን እራሱን በራሱ ሾመ፣ አከበረ ለማለት ፈለጋችሁ?" ላልከው ደግሞ በፊት ጥያቄ 4ን ስመልስ የመለስኩትን ደግመህ አንብብ። መሾም፣ ማክበር አምላካዊ ግብር ነውና ኹሉም ያከብራሉ ኹሉም ይሾማሉ።
ጥያቄ፡- “እኔ እራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው” ዮሐ 8፥54 እያለ እናንተ ለምን እራሱን በራሱ በተዋሕዶ ያከብራል አላችሁ?
መልስ፡- ይህን የተናገረው ለማን ነው? መጽሐፍ እኮ ዝም ብሎ አላነጋገሩ አይፈታም። ቃሉ የተነገራቸው እነዚህ ሰዎች እኮ አብን አምላክ ነው ብለው የተቀበሉ ወልድን በሥጋ ሲገለጥ ቢያዩት እሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ ያሉ ሰዎች ናቸው። ታዲያ ለእነዚህ ሰዎች ምን ቢላቸው ነበር አምላክነቱን የሚቀበሉ? ወንጌል ላይ ከገባን እስኪ "ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁ" የሚለውን ተርጉመው? አምላክ አለው ልትለን ነው?
ወንጌላዊው ዮሐንስም በወንጌሉ ዮሐ ፲፯÷፲፱ ላይ «አነ እቄድስ ርእስየ - እኔ ራሴን አከብራለሁ» ይላል ራሱ ዮሐንስ ወንጌል ላይ። እስኪ አስታርቀው።
መጻሕፍትን እንደ አነጋገራቸው መተርጎም ካልተቻለ ኑፋቄ እንጂ እምነት አይገኝበትም። ለምሳሌ "አብ ከእኔ ይበልጣል" ሲል ታገኘውና "እኔና አብ አንድ ነን" ሲል ደግሞ ታገኘዋለህ። ዳዊትም በመዝሙሩ "ሕቀ አሕጸጽኮ እመላእክቲከ - ከመላእክት በጥቂት አሳነስከው" ብሎ ተናግሮለታል።  አሁን ይህን ማለቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት የሚያንስ ኾኖ ይመስልሃልን?
ጥያቄ፡- ክርስቶስ እራሱ “እኔንም ያከብረኛል(መንፈስ ቅዱስን)”መ/ምስጢር ምዕ 1 ብሎ እየተናገረ እናንተ ለምን አያከብርህም ብላችሁ ትከራከራላችሁ?
መልስ፡- ማክበር የማን ግብር ነው? አንተ ራስህ እኮ እየዘበራረቅህ ነው ያለኸው። ከላይ የሚያከብር አብ ነው እያልክ መጥተህ እዚህ ላይ ስትደርስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ያከብረዋል ትላለህ። አብና መንፈስ ቅዱስ ያከብሩታል ብለህ የምታስብ ከኾነ ወልድስ ማክበር አይችልም ብለህ ታስባለህ ወይ? አብና መንፈስ ቅዱስ ማክበር የሚችሉትን ነገር ወልድ ማክበር አይችልምን? ለዚህ ቁርጥ መልስ ስጥ እስኪ። አብና መንፈስ ቅዱስ እንደሚያከብሩት አምነህ ስለመጣህ ነው ይህን የምጠይቅህ።
መጽሐፈ ምስጢር ላይ ስንሄድ እኔንም ያከብረኛል በሚለው ውስጥ በውስጠ ታዋቂ የተገለጠው መንፈስ ቅዱስ ነው ብለህ በቅንፍ ጽፈሐል። ይህን በድፍረት ለመጻፍ ምን ምስክር አገኘህ? እኔንም ያከብረኛል የሚልስ ገጸ ንባብ ከወዴት አገኘህ? ምእራፍ 1 ላይ መጽሐፉ ስለሚያነሣቸው ነገሮች ይዘረዝራል እንጂ ራሱን ችሎ የሚናገርበት አንቀጽ አይደለም። ቃሉ ካለ እስኪ ቁጥሩን አምጣው።
ጥያቄ፡- ቅዱስ ቄርሎስም “የተዋሐደው ሥጋ ክብርን ስለሚሻ ክብርን ከአብ ገንዘብ ያደርጋል(ይቀበላል)” ሃይ/አበው 79፥74 ብሎ ተናገረ እንጅ ክብርን ሥጋ ከቃል ይቀበላል/ ክብርን ቃል ለሥጋ ይሰጠዋል መቼ አለ?
መልስ፡- ቅዱስ ቄርሎስ እንደዚህ ብሎ አልጻፈም። ‹‹ከአብ በክብር እንደተገለጠ የተነገረውም የክብር ባለቤት ሲሆን በምን ነገር ከአብ ተገለጠ ይባላል፤ ይህ ነገር ፍጡር የሚል እንደሚመስል ነገሩ ግልጥ ነው። ይህም ሰው ስለመኾኑ እንጂ ለሌላ አልተነገረም። እርሱ የባሕርይ አምላክ ሲሆን ሰው በመሆኑ ከአብ ክብርን ገንዘብ ያደርጋል›› ሃይ. አበ 79፥74 ላይ። አንተ የጻፍከው እና መጽሐፉ ላይ ያለውን ልዩነት ተመልከተው። ምናልባት አንተ የያዝከው መጽሐፍ ሌላ እንደሆነ ግን ንገረን። "ገንዘብ ያደርጋል" ማለት እና "ይቀበላል" ማለት አንድ ነው እንዴ ያልተጻፈ ነገር በቅንፍ እያስገባህ የምትጽፍ? መቀበል የምትለው እኮ አካላዊ ቃል የሌለው ነገር ሲሆን እና ሥጋን ሲዋሐድ ያ ነገር አስፈላጊ ቢሆን ለሥጋ የሚሰጠው ነው። ሥጋም ቃልም ያ ስለሌላቸው አንዱ ያንዱን ገንዘብ ገንዘባቸው ሲያደርጉ እነርሱ ላይ የሌለ ገንዘብ ቢገኝ ተቀበለ ይባላል። ገንዘብ አደረገ ማለት ግን ለቃል ወይም ለሥጋ ገንዘባቸው ሆኖ የነበረውን በተዋሐዱ ጊዜ አንዱ የሌላውን ገንዘብ ገንዘባቸው አደረጉት ማለት ነው። የተቀበለ እና የገንዘብ አደረገ ልዩነት የሰማይና የምድርን ያህል ርቀት ያለው የምስጢር ተፋልሶ የሚያመጣ ነው።
ቅዱስ ቄርሎስ “የተዋሐደው ሥጋ ክብርን ስለሚሻ ክብርን ከአብ ገንዘብ ያደርጋል(ይቀበላል)” ብሎ አልጻፈም። ይህን ደግሞ ማንም ሃይማኖተ አበው 79፥74 ላይ ሄዶ ማረጋገጥ ይችላል። ሰውን ለመተቸት ስትሉ የአሸናፊነትና የተሸናፊነትን ነገር ለማምጣት ስትሉ ለምን ያልተባለ ትላላችሁ? ይህ የሁላችሁ ቅብዐት ነን የምትሉ ሰዎች ፀባይእ ነው። ምናልባት አንድ ሰው ጽፎ የሰጣችሁን ነገር ስለምትገለብጡ ይሁን አይሁን ግን አላወቅሁም።
ጥያቄ፡- “በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክ ያደረገው እሱ ነው” ሃይ/አበው 2፥5 ብሎ ሕይወት በሆነው በመንፈስ ቅዱስ የአዳምን ሥጋ ሕያው ዘላለማዊ እንዳደረገው እየተናገረ እናንተ ለምን መንፈስ ቅዱስን ሥጋ ከቃል ተቀበለ ብላችሁ ወልድን አስራፂ በማድረግ ግብር አፋለሳችሁ?
መልስ፡- ሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ፪÷፭ ላይ «ዘአንገሦ ለሥጋ አዳም በመንፈስ ቅዱስ ወረሰዮ ቅዱሰ ወማሕየዌ - በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክ ያደረገው እርሱ ነው» ይላል። እርሱ የተባለው አካላዊ ቃል እንደኾነ በሚገባ እንረዳለን። ይኸውም ይህን የመጽሐፍ ክፍል ከመዠመሪያው ጀምረን ስንመለከት «ለኵነተ ሥጋ የመጣው» የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን። «እርሱ» የተባለው አብ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ነው እንዳንል ለኵነተ ሥጋ አልመጡም። በተለየ አካሉ በተለየ አካላዊ ግብሩ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይጎድል ሳይለይ ለኵነተ ሥጋ የመጣው አካላዊ ቃል ብቻ ነውና በዚህ እንረዳለን። ስለዚህ ሥጋን ክቡር አምላክ ያደረገው የቃል ከሥጋ ጋር መዋሐድ ብቻ እንደኾነ በዚህ እንረዳለን።
የአብ እና የወልድ የባሕርይ ሕይወታቸው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ የታወቀ ነው። ይህ ሕይወት የሆነው መንፈስ ቅዱስ በአብና በወልድ እንደሚኖር ለማንም የታወቀ ነው። አብ ወልድ ሕያው ሆነው የሚኖሩት በሕልውናቸው ጸንቶ ባለው በመንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ በአብና በወልድ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ለሥጋ ገንዘቡ የሆነው በተዋሕዶ ነው። ይህ እኮ ግልጥ ነው። ሕይወትነት የወልድ ገንዘቡ ነው። ለእኛ ለፍጡራን እኮ አብም ሕይወታችን ነው። ወልድም ሕይወታችን ነው። መንፈስ ቅዱስም ሕይወታችን ነው። ሕይወት በመኾን ለእኛ ለፍጡራን እግዚአብሔር አንድ ነው። ሕይወትነታቸው አንዲት ናት። ታዲያ አካላዊ ቃል ሥጋን ሲዋሐድ በህልውናው ያለውን የመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት በተዋሕዶ ለሥጋ ገንዘቡ ያደርጋል እንጂ ሌላ ሕይወትን ከየት ሊቀበል ይችላል? እግዚአብሔር ስንት ሕይወት አለው ብለህ ታስባለህ? አንድ ሕይወት ነው ካልክ ታዲያ በየጊዜው ሊታደስ የሚችል ሕይወት አላቸው ወይ? ሕይወታቸው የባሕርይ እንጂ የጸጋ ይመስል በየጊዜው ተቀበለ ይባል አንድ እንዴት ይገባል?
"የግብር ተፋልሶ አለ" ስለምትለው ግን ምንም የገባህ አልመሰለኝም። የግብር ተፋልሶ የሚኖረው ምኑ ላይ ነው? የአብ ግብሩ ወላዲ አስራጺ፣ የወልድ ግብሩ ተወላዲ፣ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ ሰራጺ ነው ከዚህ ውጭ ምን ግብር አላቸውና ነው ሕይወትነትን ከመስረጽ ጋር የምታያይዘው? ከዊን ወይም ኩነት የሚባል ከግብር እና ከስም ሦስትነት የተለየ ሦስትነት አለ። አብ ልብ፣ ወልድ ቃል፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ወይም ሕይወት ይባላል። ይህ በተፈልጦ በተከፍሎ ሳይሆን በተጋብዖ በተዋሕዶ ነው። ምሥጢረ ሥላሴ ላይ ያለውን ተዋሕዶ እዚህ ላይ ታገኘዋለህ። አብ ለራሱ ለባዊ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አለባዊ፣ ወልድ ለራሱ ነባቢ ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ፣ መንፈስ ቅዱስ ለራሱ ሕያው ለአብ ለወልድ ማኅየዊ ነው። ይህ ድንቅ ምስጢር በፀሐይ በእሳት በውኃ በሰው ልትረዳው ብትወድ ተፈጥሯቸውን ተመልከተው። ይህን የከዊን ሦስትነት ከአካላት ግብር ጋር ስትቀላቅለው ስመለከት ምስጢረ ሥለሴ ላይ ችግር እንዳለብህ ተረዳሁ። የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መስረጽ ብቻ ነው።
ጥያቄ፡- “ተዋሕዶ ከኹለት አካላት አንድ አካል ከኹለት ባሕርያት አንድ ባሕርይ ከኹለት ፈቃዳት አንድ ፈቃድ የኾነበት ምስጢር ብቻ (መንታነትን ያጠፋ ብቻ) ሳይኾን ክብርንም ያሳለፈ ነው” ብለሃልና ተዋሕዶ ክብርን እንደሚያስተላልፍ ምን ማስረጃ አለህ? በተዋሕዶ የቃል ክብር ለሥጋ ከሆነ የክብር አጸፋው ንዴት ነውና የሥጋ ንዴት የት ሄደ?
መልስ፡- ተዋሕዶ የተፈጸመው አጸፋ ለመመለስ ለመወራረስ ነው ብለህ ለምን ታስባለህ? የፊዚክስን ሕግ እንዲህ ያለው ድንቅ ምስጢር ላይ ከወዴት ፈልገህ ነሰነስከው? በተዋሕዶ ከበረ የሚለውን ርእስ ደብረ አሚን በተሰኘችው መጽሐፌ ላይ በሰፊው ተመልከተው። ማስረጃየ በዚያ ተቀምጦልሃል። ተዋሕዶን የሚሻ ማን ይመስልሃል? እስኪ ንገረኝ አካላዊ ቃል ነው ወይስ ሥጋ? ተዋሕዶው የጠቀመውስ ለማን ነው ለሥጋ ነው ለመለኮት? ከተዋሕዶ በፊት እስከ ጊዜ ተዋሕዶ ድረስ ባለው ጊዜ ይህን መልስልኝ እስኪ ከተዋሕዶ በኋላ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኗልና ይህን ልጠይቅህ አልችልም።
ጥያቄ፡- መዋቲ፣ ነዳይ፣ መሬታዊ የነበረ ሥጋ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት የማይሞት ዘላለማዊ ካልሆነ በምን ሕያው ሆኖ ይኖራል?
መልስ፡-  ችግራችሁ እኮ በሕልውና መገናዘብ ላይ ያላችሁ ስህተት ነው። የአብና የወልድ ሕይወታቸው መንፈስ ቅዱስ ነው ብለናል። ለእኛ ግን ሕይወታችን ሥላሴ ናቸው። ለምሳሌ «ወበከመ አብ ያነሥኦሙ ለምውታን ወያሐይዎሙ። ከማሁ ወልድኒ ለዘፈቀደ ያሐዩ - አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወት ይሰጣቸዋል» የሚል ነው ዮሐ ፭÷፳፩ ሲል ሕይወት የተባለው ማን ይመስልሃል?
ዳግመኛም «በወልድ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው። በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር የቊጣ መቅሠፍት በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም» ይላል ወንጌል ዮሐ ÷፴፮ ላይ።
ወልድ የራሱ ሕይወት ባይኖረው ኖሮ በእርሱ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት እንደሚኖረው ባልተናገረም ነበር። በወልድ ያመነ ሕይወትን ከመንፈስ ቅዱስ ያገኛል ብሎ ባስተማረንም ነበር።
መዝገበ ሃይማኖት ፩÷፯ ላይ ሲናገር፡-
«አብ አባት እንደኾነ ሕይወትም እንደኾነ ገዥም እንደኾነ ወላጅም እንደኾነ ላኪም እንደኾነ በቃሉና በመንፈሱ አምላክ ሠሪና ፈጣሪ እንደኾነ እናምናለን» ይላል።
ሃይማኖተ አበው ዘአርክዎስ ፱÷፬፡- «እንግዲህ ወዲህ አይሞትም ከመለኮት ጋር በተዋሐደ ጊዜ የማያልፍ የማይለወጥ አድርጐታልና» ይላል። በተዋሐደ ጊዜ አለህ እኮ የተዋሐደ መንፈስ ቅዱስ ነው ትለኝ ይሆን?
ታዲያ ከዚህ ወዴት ትሸሻለህ? «ከመለኮት ጋር በተዋሐደ ጊዜ የማያልፍ የማይለወጥ አድርጐታል» ማለቱን አስተውል። በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ የግድ የማይታመም የማይሞት ሆነ ብሎ ሊቁ አላስተማረንም «በተዋሐደ ጊዜ የማያልፍ የማይለወጥ አድርጐታል» በማለት ነገረን እንጂ።
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በተዋሕዶተ መለኮት፤ ሥጋ የማይሞት የማይጠፋ የማይለወጥ እንዳደረገው ሲናገር እንዲህ ይላል፡- «ይህ ሕያው የማይሞት የሚሞት ሥጋን ለበሰ። ያንን የሚሞት ሥጋ የማይሞት ሕያው አደረገው። ይህ የማይጠፋ ኃይል የሚጠፋ ሥጋን ለበሰ። ያንን የሚጠፋ ሥጋ የማይጠፋና የሚናገር አደረገው» ይላል መጽሐፈ ምስጢር ፫÷፴፭ ላይ።
አባ ጊዮርጊስ ዳግመኛ በዚሁ መጽሐፉ ፳÷፲፰ ላይ እንዲህ ይላል፡-
«የሚጠፋ ሥጋን ለበሰ ያንንም የሚጠፋ ሥጋ የማይጠፋ አደረገው። የሚሞት ሥጋን ለበሰ ያንንም የሚሞት ሥጋ ከማይለወጥ አኗኗሩ ሥጋ የተካከለ እንዲኾን የማይሞት አደረገው። ምድራዊ ሥጋን ለበሰ ያንንም ምድራዊ ሥጋ የእርሱ ከኾነ ልዕልና ጋራ የተካከለ እንዲኾን ሰማያዊ አደረገው። ጎስቋላ ሥጋ የእርሱ ከኾነ ኃይል ጋራ የተካከለ ይኾን ዘንድ ለክብርና ለብርሃን አደለው። የሚታመም ሥጋን ለበሰ ያንንም የሚታመም ሥጋ ከማይታመም አኗኗሩ ጋራ የተካከለ እንዲኾን የማይታመም አደረገው። የተለየ እንዳይኾን በአንድነት አዋሐደው። እንዳይቀላቀል በመጠበቅ አኖረው። የተዋሐደውን ባሕርይ በማስወገድ ግን አይደለም። ሰው የኾነ መለኮትንም በመለወጥ አይደለም» ይላል።
ይህን ስንናገር ግን ጌታ በሥጋው ሕማምን መቀበሉን ዘንግተን አይደለም። ሕማሙን የተቀበለው በግድ ሳይኾን በፈቃዱ ነውና ሥጋን በግድ የማይታመም አድርጐታል። አንድም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምን መቀበሉ የተዋሐደው ሥጋ ምትሐት ነው እንዳይሉ ነው። ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ ይናገራል፡- «እኛ ግን ባለመለየት አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደኾነ እናምናለን ግን በፈቃዱ ሥጋውን መከራ እንዲቀበል አደረገ። ሰዎች የተዋሐደው ሥጋ ምትሐት ነው እውነተኛ ሥጋ አይደለም እንዳይሉ ስለዚህ እንዲታመም አደረገው» ይላል ሃይማኖተ አበው ፸፩÷፲፭።
ጥያቄ፡- አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ እንደሆኑ የታወቀና የተረዳ ነው:: እናንተ ግን አካላዊ ቃል ለተወሐደው አካላዊ ሥጋ የአብን ልብነትና የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ከራሱ (በሕልውናው ካለው) ሰጠው ብላችሁ የአብን የልብነት ከዊን ለወልድ (ለቃል)ና የመንፈስ ቅዱስን የሕይወትነት ከዊን ለወልድ (ለቃል) በመስጠት ሥላሴን አንድ ገጽ፣ አንድ መልክ እንዳለው እንደሰባልዮስ ለማድረግ ለምን ፈለጋችሁ? የግብር ውላጤንስ አያስከትልም ወይ?
መልስ፡- አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሕልው ነው አይደለም? ወልድስ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ሕልው ነው አይደለም? መንፈስ ቅዱስስ በአብና በወልድ ሕልው ነው አይደለም? አብና መንፈስ ቅዱስ በወልድ ሕልው ናቸው። ይህ ማለት አንድ ገጽ ናቸው ማለት አይደለም። አብ በመላው ዓለም ከዓለም ውጭም መልቶ ይኖራል። አብ መልቶ ከኖረበት ወልድና መንፈስ ቅዱስ በየት ይኖራሉ? እስኪ ይህን መልስልኝ። አንዱ በሌላው ሕልው መኾናቸውን ካላመንህ ወልድ በዓለም ከዓለም ውጭም መልቶ ይኖርበታል። ታዲያ አብና መንፈስ ቅዱስ በየት ይኖራሉ ብለህ ታስባለህ?
አየህ ሕልውና ማለት እንደፀሐይ ነው። ፀሐይ ብርሃኗ በመጣበት መልቶ በኖረበት በዚያው በሕልውና ያለው ሙቀት ይመጣበታል ይመላበታል። የፀሐይ ብርሃኗ ሙቀቷን፤ ሙቀቷም ብርሃኗን እንደማይከልለው አንዱ በአንዱ ህልው እንደሆነ ሁሉ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም አንዱ በአንዱ ሕልዋን ናቸው። አንዱ በመላበት ዓለምም ሌላው ይመላበታል። አካለ ሥላሴ እንዲህ ነው ሕልውናቸው።
ይህን ሕልውና ከተቀበልከኝ አንተ ያልከው ጥያቄ መልሱ ይኸው ይኾናል። ለዚህም ማስረጃ አለን ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ፪÷፻፶፭ ላይ እንዲህ ይላል፡- «…አብን በልብነት መንፈስ ቅዱስን በእስትንፋስነት ገንዘብ ለማድረግ ሥጋ ቃልን ተዋሐደ» ይላል። ትስብእት በተዋሕዶ የአብን ልብነት የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ገንዘቡ አድርጓል ይላል። ምክንያቱም አብና መንፈስ ቅዱስ በአብ ሕልው ናቸውና ነው። በቅብዐት ሕይወትነትን ገንዘብ አደረገ ካልክ ልብነትን ገንዘብ ለማድረግ ምን አደረገ ልትለን ነው? የግብር ውላጤን የሚያመጣ እኮ አብን ተወላዲ ወይም ሰራጺ ብንል ወልድንም ወላዲ አሥራጺ ወይም ሰራጺ ነው ብንል ወይም ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ወላዲ አስራጺ ተወላዲ ነው ብለን ቢሆን ነበር እኛ እኮ ይህን አላልንም። ለሥላሴ ከዚህ የተለየ ምን የአካል ግብር አላቸው? የሥላሴ ከዊን ወይም ኩነት ላይ ችግር ያለብህ ትመስላለህና እባክህ አንብብ።
ጥያቄ፡- ቃል ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ግብር ምን ነበር?
መልስ፡- የጠየከው ምን አይነት ግብርን ነው? በአምላካዊነታቸው የሠሩትን ወይስ በአካላቸው ለየብቻቸው የተሠራውን ሥራ ነው የምትጠይቅ?
አብ ለአጽንኦ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ ለተሰብኦ በድንግል እንዳደሩ ታውቃለህ መቼም። ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ፪÷፻፶፬ ላይ «ለአጽንዖተ ክልዔሆሙ - አብን መንፈስ ቅዱስን በጥንተ ስማቸው ለማስጠራት በጥንተ ግብራቸው ለማጽናት» የሚለው ትምህርት ተቀባይነትን የሚያጣው አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ያሉ እንደኾነ ነው። የጥንት ስማቸው  አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ መባል ነው የጥንት ግብራቸውም ወላዲ አሥራጺ፣ ተወላዲ፣ ሠራጺ መባል ነው። ወልድ (ወልደ አብ) ከድንግል ማርያም በመወለዱ ድጋሜ ወልድ (ወልደ ማርያም) ተባለ አብ እና መንፈስ ቅዱስ ግን ምን ይባላሉ? ቢሉ አብ ልጀ ብሎ ሥግው ቃልን በመጥራቱ ለሥግው ቃል አባቱ (አብ) ተብሎ የቀደመ ስሙ ወላዲ ተብሎ የቀደመ ግብሩ ጸና። መንፈስ ቅዱስም ከአብ ሠርጾ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነውና ይህ ሕይወት (እስትንፋስ) መኾን ለሥግው ቃልም ነውና የቀደመ ስሙ የቀደመ ግብሩ ጸና ይባላል።
እዚህ ላይ እንዲያው ይገባችሁ ዘንድ ለመናገር እንጂ የአብ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ ግብራቸው በየጊዜው የሚቀያየር አይደለም። የአብ ግብሩ ማስረጽ መውለድ የወልድ ግብሩ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው አለቀ። አካላዊ ቃል ሥጋን ስለተዋሐደ የአብ እና የመንፈስ ቅዱስ ግብራቸው ምንም ሊቀየር አይችልም። አካላቸው እና ግብራቸው አንድ ጊዜ የተገኘ ነው። ታዲያ አካላቸው የተቀየረ ይመስል ግብራቸው ምን ነበር? ብሎ መጠየቅ የጤንነት ነውን? አካላዊ ቃል ሥጋን ስለተዋሐደ የአብ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ አካላቸው ተቀይሯልን? አልተቀየረም ካላችሁ ግብራቸውስ በምን ሊቀየር ይችላል። ግብራቸው እኮ አካላዊ ግብር ነው።
መለኮታዊ ግብርን የምታነሱ ከሆነ ግን መለኮታቸው ባሕርያዊ እንጂ የጸጋ አይደለምና በየጊዜው የሚለዋወጥ አይደለም። ስለዚህ በአካልም ብንል በመለኮት ግብራቸው አልተቀያየረም። የአብና የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ግብራቸው ከተዋሕዶ በፊትም በተዋሕዶ ጊዜም ከተዋሕዶ በኋላም ያው ነው። መቀየር መለወጥ የለበትም።
ጥያቄ፡- “ይኸውም የወልድ ክብሩ ለሥጋ ክብር የኾነው ቃል ከሥጋ ጋር ባደረገው ተዋሕዶ ብቻ ነው። ቃል ሥጋን ክቡር አምላክ፣ ፈጣሪ፣ የኹሉ አስገኝ፣ የኹሉ ገዥ ያደርገው ዘንድ ሌላ አክባሪን አይሻም እርሱ ራሱ አክባሪ አምላክ ነውና” ብለህ ያለ አንዳች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ለመናገር ያስደፈረህ ምንድን ይሆን?
መልስ፡- በተዋሕዶ ስለመክበሩ ከላይ ጥቂት ማስረጃዎችን ሰጥቸኸለሁ። ሁሉንም እዚህ ላይ ልገልብጠው ብል የቱን ጽፌ የቱን እተወዋለሁ። መጻሕፍት በሙሉ የሚመሰክሩት ነውና መጻሕፍትን በማስተዋል ሆነህ አንብብ። በተረፈ ደብረ አሚንን አንብብ ብየ ጠቁሜሃለሁ። መጽሐፉ ካለህ እንድታጣቅሰው በተዋሕዶ ከበረ የሚሉ ጥቅሶችን ብሰጥህ ግን መልካም ይመስለኛል።
ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ በሃይማኖተ አበው ስምዐት ፻፳፬÷፴፬
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በሃይማኖተ አበው ፷፮÷፲፰-፲፱
ሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግአያ ፪÷፭
ሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ፬÷፲፩
ሃይማኖተ አበው ስምዓት ፻፳፬÷፲፬
ወንጌላዊው ዮሐንስም በወንጌሉ ዮሐ ፲፯÷፲፱
ቅዱስ ቄርሎስ ድርሳነ ቄርሎስ ፵፯÷፱-፲
ቅዱስ ቄርሎስ አሁንም ድርሳነ ቄርሎስ ፶፮÷፬
ድርሳነ ቄርሎስ ፶፮÷፲፭
ድርሳነ ቄርሎስ ፶፯÷፲፬
ድርሳነ ቄርሎስ ፸፭÷፲፫
ድርሳነ ቄርሎስ ፸፮÷፩
ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ፴፫÷፳፱
ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ ፷፰÷፵፬
ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ፸÷፳
ሃይማኖተ አበው ዘአርክዎስ ፱÷፬
 መጽሐፈ ምስጢር ፲፯÷፳
የሐሙስ ውዳሴ ማርያም አንድምታ «ብዕለ ጸጋ ጥበቡ ዘኢይትዓወቅ - ብዑለ ጸጋ አንድም በተዋሕዶ የከበረ»
እነዚህን ማስረጃዎች መጽሐፍ አገላብጣችሁ ተመልከቷቸው። ብዙ ጊዜ ደጋግሜ ደጋግሜ ጽፌያቸዋለሁ።
ጥያቄ፡- አካላዊ ቃል ሥጋን ክቡር አምላክ፣ ፈጣሪ፣የሁሉ አስገኝ፣ የሁሉ ገዢ ሲያደርገው ተዋሕዶ አገናዛቢ ነውና ቃል አካላዊ ሥጋን በመዋሐዱ ምን ሆነ?
መልስ፡- የማይዳሰሰው ተዳሰሰ። የማይጨበጠው ተጨበጠ። የማይወሰነው ተወሰነ። ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ተቆጠረለት። የማይራበው ተራበ። የማይጠማው ተጠማ። የማይሞተው ሞተ። የማይቸነከረው ተቸነከረ። በአጠቃላይ ሰው ሆነ።
ተዋሕዶ አገናዛቢ ነው የምትለዋን አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያመጣችኋት እውነታ ናት። ከዚህ በፊት አገናዛቢው ቅባት እንጂ ተዋሕዶ አይደለም ስትሉን ነበር። አገናዛቢው ተዋሕዶ መኾኑን በእውነት ካመናችሁ የቃል ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብም ለቃል ከኃጢአት በቀር የሆነው በተዋሕዶ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ ማለት ነው። ታዲያ በተዋሕዶ የቃል አምላክነት ለሥጋ ገንዘቡ ሆኖ ሥጋ ቃል ስለተዋሐደው የባሕርይ አምላክ መኾንን ገንዘብ ካደረገ ቅባቱ ምንድን ነው ጥቅሙ? በቃ ተዋሕዶ አገናዛቢ ነው ካላችሁ በተዋሕዶ ከበረ ማለት ይህ ነው እኮ። ሌላ ምንም ተረት ተረት መጨመር አያስፈልግም። ተዋሕዶ አገናዛቢ ነው ብላችሁ ካመናችሁ ሌላው ጥያቄያችሁ ሁሉ በዚህ ይመለሳል። የተምታታባችሁ ምኑ ላይ እንደሆነ ግን ግልጥ አይደለም።
ጥያቄ፡- ከዚህ በታች ያሉት ምሳሌዎች ደግሞ እጅጉን ያሳዝናሉ!
ሀ/ “ውኃ እድፍን ለማንጻት ሌላ ውኃን አይሻም እርሱ ራሱ ንጹሕ ስለኾነ ያነጻል እንጂ” ብለህ ለመናገር የደፈርከው አሁን ይሄ ምሳሌ ለቃልና ለሥጋ የሚመሰል ነውን? እንዲህ ካልክማ ወልድ አምላክ ሲሆን ለምን ሞተ፣ ተነሳ፣ በላ፣ ጠጣ፣ዐረገ፣ ደገመ፣ተራበ........ ተብሎ ይነገርለታል? ምክንያቱም እሱ አምላክ ስለሆነ ምን ጎሎበት ነው እንዲህ ሊሆን የቻለው? ክርስቶስ የሕይወት ውኃ ሲሆን ለምን ተጠማሁ አለ? ከሳምራዊቷ ሴትስ ውኃን ታጠጣው ዘንድ ለምን ለመነ? ወልድ እንደ አብ እንደ ወልድ አለምን ፈጥሮ የሚገዛ ሲሆን ከሥጋ ጋር ሳይዋሐደ እኛን ማዳን አይችልም ነበርን?
መልስ፡- የዚህ ቅኔ ደራሲ ብሆን ዕድሜ ልኬን ትልቅ ሐውልት ያቆምሁ ያህል በተሰማኝ ነበር። ቅኔው ከታች ተቀምጧል። የቅኔው ሃሳብ በገባኝ መጠን ለማብራራት ሞከርሁ እንጂ ሃሳቡ ከቅኔው ላይ የተወሰደ ነው። ምሳሌ ዘየሐጽጽ ነው። የተዋሕዶን ነገር ምንም ምሳሌ አይገልጠውም። ለማይገባው ሰው በቀላሉ እንዲረዳ ግን በተፈጥሮ ያሉትን ምሳሌዎች እንማርባቸው ዘንድ እንመስላለን። የዚህ  እኔ ያመጣሁት ምሳሌ ሰሙም ወርቁም ስላልገባህ እንጂ ይህ ነገር የሚያልቀው ጊዜ ተዋሕዶ ላይ ነው። ከጊዜ ተዋሕዶም በፊት ሆነ ከዚያ በኋላ ላለው ይህ ምሳሌ አልተጠቀሰም። የእናንተ ችግር የሆነው ግን በተዋሕዶ ጊዜ የተደርገችዋን ምስጢር ከዚያ በኋላ ላለውም እናስተላልፍ ማለታችሁ ነው።
ውኃ እድፍን ለማንጻት ሌላ ውኃን አይሻም ማለት ምን ማለት ነው? አካላዊ ቃል ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ የሥጋ ንዴት ተወግዷል ማለት ነው። የሥጋ ንዴትን ለማስወገድ ቅብዐተ መንፈስ ቅዱስን አይሻም። ምክንያቱም አካላዊ ቃል የሥጋን ንዴት ማስወገድ የሚችል ባዕለጸጋ ነውና። ይህ እኮ ሌላ ምርምርን የሚጠይቅ አይደለም። ይህ ደግሞ የተደረገው በጊዜ ተዋሕዶ ነውና ሞተ፣ ተራበ፣ ተጠማ ለሚለው ነገር የሚዘልቅ አይደለም። በተዋሕዶ ከበረ የምንለው የተዋሕዶ ምስጢር እኮ ማኅፀነ ማርያም ላይ የተደረገ ነው። እስኪ እናንተ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ የምትሉት መቼ ነው? ሞተ ለማለትም ለመሞትም ሌላ ቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ፣ ሲጠማም ለመጠማት ሌላ ቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ፣ ተራበ ለማለት ለመራቡ ሌላ ቅብዐተ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሏል እያላችሁ ነውን?
የምንነጋገረው እኮ ጊዜ ተዋሕዶ ላይ ስለተደረገ ረቂቅ ምስጢር እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ ስላለው አይደለም። ይህ ቅኔ የሚናገረው በተዋሕዶ ስለመክበሩ እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ ስላለው አይደለም። የሞተ የተራበ የተጠማ በግድ ሳይሆን በፈቃዱ ነው። በተዋሕዶ ስለከበረ እነዚህ ሁሉ መጥፋት አለባቸው ካላችሁን ግን ተዋሕዶ አገናዛቢ ነው የሚለውን ልትክዱ ነው ማለት ነው። ተዋሕዶ አገናዛቢ ስለሆነ እነዚህ ሁሉ ለመለኮት ተነገሩ። ውኃ እድፍን ለማንጻት ሌላ ውኃን አይሻም የሚለው ግን ጊዜ ተዋሕዶ ላይ ስላለው ብቻ የተነገረ ነውና በዚያ ተረዳው።
ጥያቄ፡- “ብርሃን ጨለማን ለማስወገድ ሌላ ብርሃንን አይሻም እርሱ ራሱ ብርሃን በመኾን ጨለማን ያስወግዳል (ያርቃል) እንጂ” ብለህ ለመናገር የደፈርከው እሱ የብርሃን ባለቤት ሲሆን ለምን ሥጋውን በመቃብር(በጨለማ) ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳደረው?
መልስ፡- ከላይ እንዳለው ነው። እኔ የተናገርሁት ጊዜ ተዋሕዶ ላይ ስላለ ድንቅ ምስጢር ነው እናንተ እየጠየቃችሁ ያላችሁት ስለመቃብሩ ነው። ብርሃን ጨለማን ለማስወገድ ሌላ ብርሃንን እንደማይሻ ሁሉ አካላዊ ቃልም ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ሥጋን የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ ለማድረግ ሌላ አክባሪን አይሻም ነው ዋናው ምስጢሩ። ይህንን ምስጢር ከዚህ ውጭ መጠቀም ጽሑፉን ሰሙንም ወርቁንም ካለማወቅ የተነሣ ነው።
ጥያቄ፡- ሌሎችም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የግለሰቡ ምሳሌዎች በሙሉ ሁሎችም የሚያስረዱት አምላክ ሲሆን ሁሉን ማድረግ ይችላል ምን ይሳነዋልና በማለት የተነገሩ እንጅ ቃል ሥጋን በመልበሱ ገንዘብ ያደረጋቸውን ኩነታት የሚናገር አንዳችም ስለሌለ ግለሰቡ የተናገረው ስለ ቃል አምላክነት እንጅ ስለ ቃል ሰውነት(ቃል ሰው ስለመሆኑ) የተነገረ አንዳችም ነገር የለምና አንባቢያን ሆይ ልናስተውል ይገባናል እንጅ በየዋሀን የፈጠራ ጽሁፎች ልንወናበድ አይገባንም::
ንግግሮቹም እኒህን ይመስላሉ:-
“እሳት ቅዝቃዜን ለማስወገድ ሌላ እሳትን አይሻም እርሱ ራሱ ሙቀት በመኾን ቅዝቃዜን ያርቃል እንጂ።
ቀለም ልጻፍ ባለ ጊዜ ሌላ ቀለምን አይሻም እርሱ ራሱ በቀለምነቱ ይጽፋል እንጂ።
ሽቱ ልሽተት ባለ ጊዜ ሌላ ሽቱን አይሻም እርሱ ራሱ ይሸታል እንጂ። ወርቅ ላክብር ባለ ጊዜ ሌላ ወርቅን አይሻም እርሱ ራሱ ያከብራል እንጂ።
ዐየር እስትንፋስ ለመኾን ሌላ ዐየርን አይሻም እርሱ ራሱ በዐየርነቱ እስትንፋስ ይኾናል እንጂ።
መድኃኒት ላድን ባለ ጊዜ ሌላ መድኃኒትን አይሻም እርሱ ራሱ ያድናል እንጂ” በማለት ይህን ሁሉ ፍልስፍና በከንቱ ይናገራል::
መልስ፡- ሌሎችም ምሳሌዎች የተዘረዘሩት ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነው። አካላዊ ቃል የተዋሐደውን ሥጋ ማክበር ስለሚችል ሌላ አክባሪን አይሻም የሚል ነው ዋናው ምስጢሩ። ምሳሌዎችም ያንን የሚገልጡ ቅኔውም ያንን የሚናገር እንጂ ከጊዜ ተዋሕዶ በኋላ ስላለው ነገር የሚናገር አይደለም። እንዴት እንዳነበባችሁት እንዴት እንደተረዳችሁት ባላውቅም የመረዳትና የማንበብ ወሰናችሁ ዝቅተኛ መሆኑን አልያም ደግሞ ላለመረታት የጻፋችሑት ይመስለኛል።
ይህ ምንም ፍልስፍና የለበትም። ምን ይሣነዋል በሚል መልኩም የተነገሩ አይደሉም የሚሳነው ነገር ባይኖርም። የጻፍሑት ምስጢር ከገባችሁ ያ የተነገረ ጊዜ ተዋሕዶ ላይ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ የሚዘልቅ አይደለም። ምክንያቱም ከጊዜ ተዋሕዶ በኋላ አንድ አካል አንድ ፈቃድ አንድ ባህርይ ሆኗልና። ይህ ምስጢር አሁንም እደግመዋለሁ ጊዜ ተዋሕዶ ላይ የተደረገ ነውና ከዚያች ጊዜ በፊትም በኋላም ሳትሄዱ ተረዱት። እዚህ ላይ መጠማትን መሞትን መራብን መቸንከርን በከርሰ መቃብር ማደርን ምን አመጣው?
ጥያቄ፡- ለመሆኑ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ስለሆነ ከድንግል ተወለደ፣ እንደ ሕጻናት በየ ጥቂቱ አደገ፣ ጾመ፣ ሰገደ፣ ፀለየ፣ተራበ፣ተጠማ፣ተወጋ፣ ተደፋ፣ተገፋ፣ምራቅ ተተፋበት፣ ሆምጣጤ አጠጡት፣ሞተ፣ተነሳ፣ ዐረገ፣ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ ብሎ ለመነ፣ አባት ሆይ ነፍሴን አደራ ብሎ ተናገረ፣ ዳዊትም ከመላእክት ጥቂት አሳነስከው ብሎ ተናገረ፣ ወንጌላዊው ዮሐንስም “እኔ እራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፣ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው” ዮሐ 8፥54 ብሎ ስለ ክርስቶስ ሲናገርለት ይህንንና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ሁሉ ሲሆን ወልድ ይሄን ሁሉ ነገር እንዲሆን ያደረገው ምን ስለሆነ ነው? በእውኑ አምላክ ስላልሆነ ይመስልሃልን? ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ስለሚያንስ ነውን? ወልድስ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ አለምን ፈጥሮ የሚገዛ ሲሆን ለምን ይራባል፣ ይጠማል፣ ይሞታል?
መልሱ ግን ደካማ፣ ነዳይ፣ትሑት፣ ፍጡር፣ መዋቲ የሆነ ሥጋን በመዋሐዱ ተቀበለ፣ከበረ፣ሞተ፣ ተነሳ ተብሎ የተነገረለት ዓቢይ ምስጢሩ ይህ ስለሆነ ነው::
መልስ፡- ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ማለት ይህን ጊዜ ነው። የእኔ ጽሑፍም ሆነ የቅኔው መንፈስ የሚናገረው ጊዜ ተዋሕዶ ላይ ስላለ ምስጢር ብቻ ነው። ይህ የተዘረዘረው የሥጋ ገንዘብ ሁሉ የመለኮት ገንዘቡ የሆነ እኮ በጊዜ ተዋሕዶ ነው። ይህን ሁሉ የሥጋ ገንዘብ ቃል ገንዘቡ ያደረገው በተዋሕዶ ነው። ስለዚህ ይህን የሥጋ ገንዘብ ቃል ገንዘቡ ለማድረግ ሌላ አካልን አይሻም። ሥጋም የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ ለማድረግ ሌላ አካልን አይሻም። ቃል ሥጋን ሲዋሐድ የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ እንዳደረገ ሁሉ ሥጋም ቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጓል። አምላክነት የሥጋ ገንዘብ ሲሆን ሰውነት ደግሞ የቃል ገንዘብ ሆነ አለቀ። ይህን የአንዱን ገንዘብ ሌላኛው ገንዘቡ ለማድረግ ሌላ አካልን አይሻም። እስኪ እናንተ ቅባቶች በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ነው ሥጋ አምላክ የሆነ ካላችሁ አካላዊ ቃል ሰው የሆነውስ በምንድን ነው? ወይስ ደግሞ አምላክነትን የሰጠ ቅብዐት ሰውነትንም አብሮ የሚያድል ነው? አገናዛቢው ተዋሕዶ ነው ትሉና እንደገና በድንቁ ምስጢር ላይ አመድን ትነሰንሳላችሁ። ተዋሕዶው አምላክን ሰው አድርጎታል ሰውን ደግሞ አምላክ አድርጎታል። ሰውን አምላክ ለማድረግ አካላዊ ቃል መዋሐዱ በቂ ነው። አምላክን ሰው ለማድረግም እንዲሁ ተዋሕዶው በቅቶታል። እንደናንተ ከሆነ ግን ሰው አምላክ ለመሆን የሚያስፈልገው ቅብዐትና አምላክ ሰው ለመሆን የሚያስፈልገው ቅብዐት የተለያየ ነውና መንፈስ ቅዱስም ሁለት ነው ማለታችሁ ነው። መቼም አምላክ ያደረገ ቅባት ሰው ያደርጋል አትሉም። ሰው የሚያደርገው ሌላ አምላክ የሚያደርገው ሌላ ነው ትሉ ይሆናል እንጂ።
ዮሐ 8፥54ን በተመለከተ ከዚህ በላይ ጽፌዋለሁና ያንን ተመልከቱ፡፡
ጥያቄ፡- ይሄ ከዚህ በታች የተጻፈው ቅኔ ደግሞ ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስን ነግፎ በተዋሕዶ ከበረ የሚለውን ማስረጃ አልባ፣ ወፍ ዘራሽ፣ የእነ ጳውሎስ ሳምሳጢ የሆነውን ትምህርት ለመደገፍ የተዘረፈ ቅኔ ነው:: የሚያሳዝነው ቅኔው ለሃይማኖት ማስረጃ ተብሎ መጠቀሱ ነው::
የቄሰ ገበዝ ኑርልኝ ቅኔ(ፈጠራ) እንዲህ ይላል:-
“ጓሉ የተባሉ ሊቅ በቅኔያቸው እንዲህ ይላሉ። መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ በመድሎተ አሚን መጽሐፋቸው ላይ እንደመዘገቡት።
ኢየኀሥሥ ለአብርሆ ቅብዐ ዘይት ፀሐይ ዘላዕለ ኵሉ።
ወዘየዓቢ ፀሐይ ከማሁ ቅብዐ መንፈስ ቅዱስ ክብረነ።
ኢየኃሥሥ አምጣነ ፀሐይ ዘያበርህ ለነ።
ወኢይትሐወክ ብዙኀ በዝንቱ አርዮሳዌ ዘኮነ።
ከመ ቃል ብርሃነ ኀበ ኢአምነ።
ዐይንኑ የኀሥሥ ካልአ ዐይነ።
ወብርሃን ካልአ ብርሃነ።
ቅኔው ወደ አማርኛ ሲተረጐምም እንዲህ የሚል ትርጒም ይኖረዋል፡-
ከኹሉ በላይ ያለ ፀሐይ ላብራ ባለ ጊዜ ዘይትን ለቅብዐትነት አይፈልግም እንደዚኸውም ከዚህ ዓለም ፀሐይ የሚበልጥ ኢየሱስ ክርስቶስም ለእኛ የሚያበራ እውነተኛ ፀሐይ እንደመኾኑ መጠን ለእኛ ክብር የሚኾን መንፈስ ቅዱስን አይሻም የሚል ነው” በማለት ሕይወት የሆነውን መንፈስ ቅዱስ ክደው ግብር አፋልሰው እራሱ ወልድ አክባሪ፣ ክብር፣ ሥጋ ከባሪ በማለት በአንድ አካል ሁለት ባሕርይ የሚለውን የልዮንን ትምህርት ምንም እንኳ ከቅዱሳን አበው ማስረጃ ባይኖራቸውም በቅኔም፣ በአፈ ታሪክም፣ በአሉ ተባለም ለመደጋገፍ ዘወትር ሲማስኑ ይስተዋላሉና ወገኔ ያለህን አጥብቀህ ያዝ ይህ በተዋሕዶ ከበረ የሚለው ምንፍቅና ያልተሸከመው ክህደት የለምና::
መልስ፡- የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ ምን ሆኖ ነው የተፋለሰበት? አለማወቅ እኮ ኃጢአት አይደለም ለማወቅ አለመጣር ግን ኃጢአት መሆኑ አይቀርም። ቅኔውን የተቀኙት ዛሬ በእናንተ ዘመን ቢሆን ኖሮ ልትንቁት ልታቃልሉት በቻላችሁ ነበር። ይህ ቅኔ ግን ከ60 ዓመት በፊት የተደረሰ ቅኔ ነው። ምናልባትም እናንተ ገና ሳትታሰቡ መሆኑ ነው። ቅኔውን ወፍ ዘራሽ ተራ ነው የጳውሎስ ሳምሳጢ ትምህርት ነው ወዘተ ለማለት በመጀመሪያ መማር ያስፈልጋል። ሳያውቁ ላሳውቅ ማለት ከዚህ የተሻለ ነገርን አያስገኝም። አንድ ጥቅስ ሳይጠቅሱ አንድ አስረጅ ሳያቀርቡ ዝም ብሎ መንቀፍ ራስነብ ያስነቅፋል።
በተዋሕዶ ከበረ የሚለው ግብር የሚፋልሰ ሳይሆን ግብርን የሚተብቅ ነው። ግብራቸውን አለማወቅ ነው እንጂ የማን ግብር ተፋለሰ ቢባል መልስ ላቸውም እኮ። ሕይወትነት የማን ግብር ነው? መንፈስ ቅዱስ ከመሥረጽ ውጭ ሌላ ግብር አለውን? ታዲያ ማነው የማንን ግብር ወሰደው? ማን ግብር ነው ለማን የተሰጠ? ወልድ በተዋሕዶ ተወለደ አልን እንጅ በተዋሕዶ ሰረጸ አላልንም እኮ። አንዳንዴማ እኮ የምንለውንም መስማት ይገባል። አካላዊ ቃል ክቡር አምላክ ነው። ይህ ክቡር አምላክ የተዋሐደውን ሥጋ ያከብራል ነው። ማክበር ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ብቻ ሥራ ነው የሚል ካለ ማስረጃ ሊያቀርብ ይችላል። ከዚህ ውጭ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው የተወገዘ ትምህርት ነውና በጊዜ ልብ ግዙ።
ቅዱስ ቄርሎስ ሃይማኖተ አበው ፸፫÷፵፱ ላይ፡-
«ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው፤ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፤ በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል የሚለው፤ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው፤ የአምላክነትንም ሥራ እርሱ ራሱ ይሠራል የማይል ቢኖር ውጉዝ ይኹን» ይላል።
ጥያቄ፡- አንሰ አእመርኩ ወአንከርኩ ፍካሬያተ ለመጽሐፍት በከመ ዜነው በእንተ መጥባሕት እንዘ ይብሉ እሉሰ መጥባሕት ይትናገሩ ፈጠራ ዝሰ ነገር ሙሱን ውእቱ በከመ ልብየ አእመራ::
መልስ፡- ስለሰይፍ ስለ ማረጃ (በእናንተ አነጋገር ካራ) መጻሕፍት የተናገሩትን የምታውቅ የምታደንቅም ከሆነ አንተ አራጅ ነህ እንጂ መቼ ሃይማኖተኛ ሆንክሳ። ስለሰይፍ የሚያወራ ሰይፈኛ ነው። ሰይፍ ያነሳ በሰይፍ ይጠፋልና። መጻሕፍት ስለ ሰይፍና ስለካራ የተናገሩትን ምታውቅና የምታደንቅም ከሆንክ አንድ ማስረጃ ስጠንና እኛም እንወቅ እናድንቅም።
ካራዎች ፈጠራ ነገርን ይናገራሉ በማለት ካራ እንደሚናገር መጻፍ ቅኔ አይደለም። ካራ ከማረድ እና እናንተ ከምታውቁትና ከምታደንቁት የተለየ ሥራ የለውም። የሚርድ ደግሞ ያርዳል እንጂ ላርድ ነው ብሎ ሲናገር ሰምተን አናውቅም። የፈጠራ የምትለውን ትንሽ ፈጠራ ብትነግረን መልካም ነው።
ዝሰ ነገር... እና አእመራ የምትለዋ ማሰሪያ ግን የተስማሙ አልመሰለኝም። እስኪ እንደገና ለማስማማት ሞክር። ዝሰ ነገር ይህንስ ነገር ... አእመራ አወቃት። ይህንስ ነገር አወቃት። ብሎ ነገር አላውቅም። እስኪ ይታረም!
ጥያቄ፡- ክብርና ምስጋና ዓለማትን በጥበቡ ፈጥሮ ለሚገዛ በቸርነቱ ለጠበቀን በምህረቱም ለጎበኘን ለልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር አምላክ ወለእሙ ድንግል ይሁን!
መልስ፡- አሜን።

No comments:

Post a Comment