“ፀሐይኒ አእመረ ምዕራቢሁ፣ ታመጽእ ጽልመተ ወይከውን ሌሊተ” መዝ 103÷20 እንዳለው ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት፡፡ “ፀሐይም መግቢያውን አወቀ፣ ጨለማን ታመጣለህ ሌሊትም ይሆናል” በሚለው ግርድፍ አማርኛ እንቀይረውና በምንግባባበት መጠን እንግባባ፡፡ ለማንኛውም ግእዙን በቀጥታ የመፍታት አቅሜ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ የምትረዱት እንደሆነ ባውቅም ከዋናው የቅዱስ ዳዊት ሃሳብ ግን እምብዛም የራቅሁ አይመስለኝም፡፡ ይህንን ጥቅስ የመረጥኩት ሌሊት የሚባለው የጊዜ ቀመር ፀሐይ የምትጠልቅበት ጊዜ እንደሆነ እንረዳ ዘንድ ነው፡፡ ነገርን ነገር ያመጣዋልና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 3 ቀናት እና 3 ሌሊት በከርሰ መቃብር ማደሩን የምንቆጥረው አንዱ በዚህ አቆጣጠር ዘዴ ነው፡፡ አርብ ከቀኑ 11 ሰዓት ወደ መቃብር ወረደ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሌሊት 6 ሰዓት ተነሣ በጠቅላላው 31 ሰዓታት ማለት ነው፡፡ ይህን ነገር በምንም አይነት ቀመር 3 ቀን እና 3 ሌሊት ማለት አይቻልም፡፡ 1 ቀን እኩል ይሆናል 24 ሰዓት ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ 3 ቀናት 36 ሰዓታት 3 ሌሊት 36 ሰዓታት በጠቅላላው 72 ሰአታትን በከርሰ መቃብር ማደር ነበረበት፡፡ ነገር ግን ቀመሩ እንዲህ አይደለም፡፡ አቆጣጠሩ ፀሐይ ስትኖር ቀን፤ ስትጠልቅ ደግሞ ሌሊት በሚል ቀመር ነው፡፡ አርብ ከተያዘበት እስከተሰቀለበት 6 ሰዓት ድረስ( 1ኛቀን)፣ ከ 6- 9 ሰዓት ጨለማ ሆነ (1ኛሌሊት)፣ ከ9-11 ሰዓት ብርሃን ሆነ(2ኛቀን)፣ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ(2ኛ ሌሊት)፣ ቅዳሜ ሙሉ ቀን(3ኛ ቀን)፣ ቅዳሜ ለእሁድ እስከተነሣበት ድረስ(3ኛ ሌሊት)፡፡ በእርግጥ ሌላ አቆጣጠርም አለው ነገር ግን ከዚህ ሃሳብ ጋር የሚመሳሰለው ይኼኛው አቆጣጠር ስለሆነ ብቻ በዚህ እናብቃ፡፡ በአጠቃላይ ሌሊት ማለት ጨለማ የሚሆንበት ወይም ፀሐይ የምትጠልቅበት ጊዜ ማለት ነው፡፡
ሌሊት ምን እንደሆነ ከተረዳን ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡ የዚያ የማላውቀው ሰውዬ አባባል ከሞላ ጎደል በግርድፉ እኔ በተረዳሁበት አገላለጽ እንዲህ አልኩት ፡- “በጨለማ ሁሉም ቀለሞች ይስማማሉ”፡፡ ቀይ ቀይ የሚሆነው ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ አረንጓዴም አረንጓዴ የሚሆነው ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ቢጫም ቢጫ የሚሆነው ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ሰማያዊም ሰማያዊ የሚሆነው ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ነጭም ነጭ የሚሆነው ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ ቀለም ቀለም የሚሆነው ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ለካ ቀይ የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ለካ አረንጓዴም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ ለካ ቢጫም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ለካ ሰማያዊም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ለካ ነጭም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለካ የቀለም አይነቶችን የምንዘረዝረው በፀሐይ ነው፡፡ ቀለምን ቀለም የሚያሰኘው ለካ ጊዜው ኖሯል፡፡ ለካ ቀለሞች ያልተስማሙት አንድ ያልሆኑት ፀሐይ ስላለች ነው፡፡
አሁን ምልከታዬ ሰፋ እያለ መጣ፡፡ ለካ ሃብታም ሃብታም የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ደሃም ደሃ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ለካ ባለሥልጣንም ባለሥልጣን የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ አልቃሽም አልቃሻ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ የራበውም ረሃብተኛ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ካገሩ የወጣም ስደተኛ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ የተቸገረ ሰውም ችግረኛ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ የታመመ ሰውም በሽተኛ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ያልተማረ ሰውም ማይም የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ጊዜ የማይለውጠው ዘመን የማይሽረው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ ለካ ሁሉም በጊዜ ይለወጣል፣ በዘመንም ይሻራል፡፡
እኔ ደሃ ነኝ አንድ ቀን ግን ከሃብታሙ ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ ረሃብተኛ ነኝ አንድ ቀን ግን ከጠገቡት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ አልቃሻ ነኝ አንድ ቀን ግን ከሚስቁት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ ችግረኛ ነኝ አንድ ቀን ግን ካልተቸገሩት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ በሽተኛ ነኝ አንድ ቀን ግን ከጤነኞች ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ ያልተማረኩ ማይም ነኝ አንድ ቀን ግን ከተማሩት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ ይህ አንድ የሚያደርገኝ ቀን ሩቅ አይደለም ቅርብ ነው፡፡ ቀለሞችን ሁሉ አንድ ያደረጋቸው ጨለማ እኔ ጋርም አለ፡፡ እርሱ አንድ ቀን ከሌሎች ጋር አንድ ያደርገኛል፡፡ ትልልቅ መሪዎች፣ አስፈሪ ወታደሮች፣ የተከበሩ ምሑራን፣ ሁሉ የሞላቸው ባለጠጎች፣ ሕዝብን በግፍ ያንገላቱ ጨካኞች፣ ፀሐይ ስትወጣላቸው የምንፈራቸው፣ በሥልጣን ኮርቻ ሲቀመጡ የበደሉን ሁሉ ነገ አንድ እንሆናለን፡፡ ቀይ፣ አረንጓዴ ፣ቢጫ፣ ሰማያዊ፣ ነጭ በጨለማ ሁሉም ተስማምተው ጥቁር እንደሚሆኑ ሁሉ እኛም እነደዚሁ የማንረታው፣ ጥበባችን የማያርቀው፣ መቼ እንደሚመጣ የማናውቀው ፣ ባለሥልጣን፣ ሃብታም፣ ደሃ የማይለየው ለሁሉም እኩል የሚፈርደው ሞት ሲመጣ ያኔ እኩል እንሆናለን፡፡ የተበደለው ከበደለው ጋር፣ የተገደለው ከገደለው ጋር፣ ያለቀሰው ካስለቀሰው ጋር፣ በግፍ የተንገላታው ከአንገላታው ጋር፣ የተንቋሸሸው ከአንቋሸሸው ጋር፣ የተደበደበው ከደበደበው ጋር፣ የተሰደደው ከአሳደደው ጋር፣ የተገረፈው ከገረፈው ጋር፣ የተሰረቀው ከሰረቀው ጋር፣ የተደፈረው ከደፈረው ጋር፣ የተሸማቀቀው ካሸማቀቀው ጋር፣ የተመራው ከመሪው ጋር፣ የተቀለደበት ከቀለደበት ጋር… ፩ ቀን ፩ እንሆናለን፡፡ ሕይወት አላስማማን ቢልም ቅሉ ፩ ቀን ግን ሞት ያስማማናልና በዚህ እንጽናናለን፡፡ ለካ አላስማማን ያለ ጊዜው ነው፡፡ የፀሐይ መኖር አላስማማቸው ያሉ ቀለሞች በጨለማ ሁሉም ጥቁር ሆነው እንደሚስማሙ ሁሉ ጊዜው ሲደርስ በሕይወት አልስማማ ያልን ሁሉ በሞታችን እንስማማለን፡፡
No comments:
Post a Comment