ሰነፍ እግር የሚገሰግሰው ለኃጢአት ሥራ ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት
እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ የሚለውን የዳዊት መዝሙር አይወድም፡፡/መዝ121÷1/ ሰነፍ እግር በክፉዎችና በኃጢአተኞች ምክር ይጓዛል፤
የበደልንም ጫማ ይጫማል፡፡ የሚገሰግሰውም ወደ ሰዶምና ገሞራ ከተማ ነው፡፡ ለክርክር እና ለሙግት ይቸኩላል፡፡ እግዚአብሔር ከሚጠላቸው
ስድስት ነገሮች መካካል አንዱ ወደ ክፉ የሚሮጥን እግር ነው፡፡/ምሳ6÷18/ ሰነፍ እግር የሚረግጠውን አያስተውልም፤ የት ለመድረስ
እንደሚፈጥንም አያውቅም፡፡ሰነፍ እግር ቀራንዮ ድረስ የሚሄደው በክርስቶስ ምራቁን ሊተፋ አልያም ሊሳለቅ ነው፤ በመስቀሉ አጠገብም
የሚቆመው በልብሱ ዕጣ ለመጣጣል ነው፡፡ ሰነፍ እግር እንደ ቃየን እግር የሚቅበዘበዝ ይሆናል፡፡ በባዶ ሜዳ በድንጋጤ የሚሮጥ መድረሻውን
የማያውቅ ተንከራታች ይሆናል፡፡ ሰነፍ እግር ለጸሎት መቆምን አብዝቶ ይጠላል፡፡ ሰነፍ እግር ከምጽዋት ይልቅ ስርቆት፣ ከስግደት
ይልቅ ክፋት፣ ከጸሎት ይልቅ ትዕቢት፣ ለነፍሴ ከማለት ይልቅ ለኪሴ፣ ንስሓ ከመግባት ይልቅ ኃጢአት መሥራት፣ ከልጅነት ይልቅ ባርነት፣
ከሕይወት ይልቅ ሞት ይመርጣል፡፡ የሚጓዘውም በኃጢአተኞች መንገድ ነው፡፡ የሚሮጠውም ከነዓን ለመግባት ሳይሆን በእስራኤላውያን ላይ
አደጋ ለመጣል ነው፡፡ የእስራኤላውያን እግር ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገረው እርሱ ግን በኤርትራ ባሕር ውስጥ ይሰጥማል፡፡ ሰነፍ
እግር ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል ይንበረከካል፤ ጥበበኛ እግር ግን ሠለስቱ ደቂቅን ይከተላል፡፡ ሰነፍ እግር በጦርነት መካከል ይቆማል፤
ብልህ እግር ግን ሰላምን ይፈልጋል፡፡ ሰነፍ እግር ድንግል ማርያምን የሚከተላት በግብጽ በረሓ ለማሳደድ ነው፡፡ ሰነፍ እግር እስጢፋኖስ
ሲወገር ድንጋይ ያመላልሳል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲፈጭ ደብረ ይድራስ ሊበትነው ይቸኩላል፡፡ ወንድሜ አንተ ግን እግርህን ጠብቅ፤ ስንፍና
በእግርህ ዘንድ እንዳይመጣ ነቅተህ ጠብቅ፡፡ የጽድቅን ጫማ እንዲጫማ ወደ ጽድቅ ገበያ ውሰደው፡፡ ጉዞው እንደ ዮሐንስ ያለ ጉዞ
እስከ ቀራንዮ ተራራ ድረስ የሚጸና ይሆን ዘንድ አበርታው፡፡ እንደ ማርያም መግደላዊት እሾኹን እንቅፋቱን ሌሊቱን የሮማን ወታደር
ሳይፈራ የጌታን መቃብር የሚመለከት አድርገው፡፡ ትንሣኤውን ለዓለም ሁሉ የሚያበሥር እግር እንዲሆን ምከረው፡፡ የሐዋርያትን እግር
እንዲከተል አሰልጥነው፡፡ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ወንጌልን ለመስበክ የሚዞር ጠንካራ እግር ይሆንልህ ዘንድ ምከረው፡፡ መጥፎ ነገር
ለማርዳት ሳይሆን ጥሩውን ነገር ለማብሠር አፍጥነው፡፡ እግርህ የምሥራች የሚናገር ያማረ እንዲሆን ጸሎትህ አይቋረጥ፡፡ እንደ አረጋዊው
ዮሴፍ ልጅ ሰውን ለማስደንገጥ አይፍጠን፡፡ ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ ይህ ወልደ ዮሴፍ እየሮጠ ደረሰባቸውና እዚህ ተቀምጣችኋልን
የሔሮድስ ወታደሮች መጥተዋልና ተነሡ ባላቸው ጊዜ እመቤታችን እጅግ ደነገጠች ዕንባዋንም አፈሰሰች፡፡ ይህን ያህል በረሀ የተንከራተትሁ
ከሞት ላላተርፍህ ነውን ብላ አለቀሰች፡፡ ሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስም አመጣጥህ መልካም ነበር ነገር ግን እናቴን አስደንግጠሃታልና
በፍርድ ቀን አስነሥቼ እስክፈርድብህ ድረስ ድንጋይ ተንተርሰህ ተኛ አለው በዚያው ድንጋይ ሆኖ ቀረ፡፡ ይህ እግር አስደንጋጭ እግር
ነው በመሆኑም ተገቢውን ቅጣት አገኘ፡፡ አንተ ግን ከእንደዚህ አይነቱ እግር የተለየ እግር ሊኖርህ ይገባል፡፡
© በመልካሙ በየነ
ጥቅምት 10/2008 ዓ.ም
ደብረማረቆስ፣ ኢትዮጵያ