“… ሰው ነኝ! አዎ ሰው ነኝ! ሰውስ ብላችሁ
ሰው መሰልኳችሁ! ዓለምን የዞርኩ፣ ዓለምን ያጣጣምኩ፣ ሁሉን የቀመስኩ፣ ሁሉ ያልቀረኝ፣ ሁሉን የሠራሁ፣ በነፈሰበት የነፈስኩ፣ በወረደበት
የወረድኩ፣ በዘነበበት የዘነብኩ፣ በበረሩበት የበረርኩ ሁሉን የሆንኩ ሰው ነኝ፡፡ ያኔ ገና “ሀ” ብዬ ራሴን ለማይገባ ሱስ እጄን
ሳነሣ ተው ባይ አጣሁ፤ እኔም በዛው ገፋሁበትና በጫት የጀመርኩት ሱስ በሲጋራ፣ በሲሻ እና በመጠጥ አጎለመስኩት፡፡ በፊት በፊት
የሰፈር ጓደኞቼ የነበሩት ትምህርት ቤት የመማር ዕድል ሲያገኙ እኔ ግን ወላጆቼ ማስተማር ስላልቻሉ ነበር ወደ ጎዳና የወጣሁት፡፡
በእርግጥ ጎዳና መውጣቴ ለሱስ ዳረገኝ የሚል ጸጸት የለብኝም ምክንያቱም ትልልቅ የሚባሉት አገራችን በብዙ ዋጋ ውጭ አገር ድረስ
ልካ ያስተማረቻቸው የአገር መከታና አለኝታ ይሆናሉ የተባሉ “ምሁራን” ሳይቀሩ የሱስ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የአገራችን
ትልልቅ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የሚኒሰትር መስሪያ ቤት ተጠሪዎች ሁሉ ሱስ አጥቅቷቸው እንደኔ ሆነው ሳያቸው እጽናናለሁ፡፡ ሲጋራው
ጫቱ ሁሉም አይቀራቸውም እኔ የጎዳና ተዳዳሪው እና እነርሱ አንድ እኩል የሚያደርገን ነገር ሱስ ብቻ ነው፡፡
ዛሬ እነዚያ የሰፈሬ ልጆች ትልልቅ ሰዎች ሆነው
ትልልቅ ከሚባሉ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ በሱስ ብዙ ዘመናትን ያሳለፍኩ ከንቱ ሰው እንደሆንኩ አስባለሁ፡፡ ይህ
ከንቱነቴ ይበልጥ የሚያስለቅሰኝ የእኔ እኩዮች የሰፈሬ ልጆች ሲያገኙኝ ሰላም ለማለት ተጠይፈውኝ እንደማያውቁኝ ሲያልፉኝ ነው፡፡
በጣም አለቅሳለሁ በጣምም አነባለሁ እጅግም አዝናለሁ እንዴት የሰፈሬ ልጆች ይጠየፉኛል? ቢያንስ አብረን አፈር ፈጭተን ጭቃ አቡክተን
አኩኩሎሽ ተጫውተን ያደግነውን እንዴት ይዘነጉታል? ወይስ የእኔ በሱስ መውደቅ የእነርሱን ክብር የሚነካ መስሎ ታይቷቸው ይሆን?
ይህን ሳመላልስ ኅሊናዬ በጣም ይደማል እጅግ አዝናለሁ፡፡ ለነገሩ ልክ ናቸው እንደእኔ ያለ ከንቱ እንደነርሱ ላለ ትልቅ ሰው ጓደኛ
መሆን ክብራቸውን የሚነካ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡
እኔ ከዚያ ሱስ መውጣት አልቻልኩም በእርግጥ
እንድወጣም የሚመክረኝ ሰው የለኝም፡፡ በጣም የምበሳጨውም በዚህ ነው፡፡ ሰው ሕይወቴን ለመቀየር ባይጥር ምክር መለገስ ምን ይከብደዋል?
ምን ወጭ ያስወጣዋል? እኔ በኃጢአት ባሕር እንደምዋኝ በኃጢአት ማዕበል እንደምናጥ አውቀዋለሁ፡፡ ዛሬ ከአንዷ ነገ ደግሞ ከሌላኛዋ
ጋር፤ ብቻ ካገኘዋት ጋር ሁሉ አንሶላ ተጋፍፌያለሁ፡፡ ያ በሽታም ሳይኖርብኝ አይቀርም ስላልተመረመርኩ ነው እንጅ፡፡ በጣም ጎስቁያለሁ
ከውሻ ጋር እየተሻማሁ እመገባለሁ ዞሮ ያየኝ ሰው አለመኖሩ ውስጤን ያሳዝነዋል፡፡ መንግሥትስ ቢሆን ምን አረገልኝ? ተው ጫት አትቃም፣
ሲጋራ አታጭስ፣ ዝሙት አትፈጽም በማለት ፈንታ በጥቃቅን በምናምን አደራጀሁ እያለ አይደል እንዴ ሴቶችን የሚቀያይርልን፡፡ ዝሙት
አትፈጽም ብሎ ከመምከር ይልቅ ኮንዶም ተጠቀሙ እያለ ነው ማስታወቂያ የሚሰራልን፡፡ ዛሬ ሴተኛ አዳሪዎች ስንት ናቸው? እንደእኔ
ካገኛት ጋር የሚተኛው ወንድስ ስንት ነው? ጫት መቃሚያ ቤቶች የሚዘጉት እኮ ግብር አልከፍል ሲሉ እንጅ ወጣቱን ሱሰኛ ስላደረጉት
አይደለም፡፡ ታዲያ እንደዚህ አይነት መንግሥት ባለበት አገር ላይ እኔ ራሴን ማዳን ካልቻልኩ በቀር ማን ዞሮ ያየኛል? የሰውን ኅሊና
ከመገንባት ይልቅ ሕንጻ መገንባት ላይ ትኩረት ባደረገች አገር ውስጥ ከሱስ ነጻ መሆን ይከብዳል፡፡
አብሮ አደጎቼ ሆይ! ዛሬ እንዲህ ስጎሰቁል፣
መካሪ ሳጣ፣ አይዞህ ባይ ረዳት ሲርቀኝ፣ ሰው የመሆን ህልሜ ሲዳፈን አይታችሁ ጨከናችሁ አይደል? ተውት ለእኔስ እግዚአብሔር አለኝ
እመብርሃን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም እናቴ አለችኝ፡፡ ዛሬ እና ነገ የእኔን ማንነት አንድ ሆኖ አታዩትም፡፡ ያንን ሱሰኛ
ጓደኛችሁን ዳግም በዚያ ሁኔታ ላታዩት እስከወዲያኛው ይሰናበታል፡፡ ይኼው በቃ! ማል ካላችሁኝ ማልሁላችሁ ሲጋራዬን ሰባብሬ፣ ጫቴን
አሽቀንጥሬ፣ ዝሙቴን መዳራቴን ሁሉ ትቼ ንስሐ ገብቼ ከአምላኬ ጋር ታርቄ ልኖር ወስኛለሁ፡፡ በቃ አለቀ! ታሪኬን እቀይራለሁ ሲጋራ
ማጨሴን ጫት መቆርጠሜን ዳግም ላልመለስባቸው ላልደርስባቸውም ወረወርኳቸው፡፡ ነገር ግን ሰው ስሆን ያኔ ሰው ሆኜ ስሞት ያኔ እንዳትቀብሩኝ
ምክንያቱም በቁሜ ቀብራችሁኝ ስለነበር፡፡ ያን ያህል አይዞህ ባይ ባጣሁበት፣ ከውሻ ጋር ተሻምቼ በተመገብኩበት ማደሪያ አጥቼ ግድግዳ
ተደግፌ በማነጋሁበት ሌሊት፣ በሲጋራ ሳንባዬ በነደደ ሰዓት ልባችሁን አጨክናችሁብኝ አልነበር? ሰላም እንዳትሉኝ ተጠየፋችሁኝ አይደል?
በእርግጥ አልቀየማችሁም ነገር ግን ስሞት እንዳትቀብሩኝ እናዘዝላችኋለሁ፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ ሰውነት በቁም መረዳዳት ብቻ ነው ሲሞቱ
አልቅሶ መቅበር አይደለም ስለዚህ በቁሜ ስሞት ለቀበራችሁኝ አብሮ አደጎቼ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሆኜ ስሞት ለቅሶ ደረሱ ለመባል
ያህል ቀብሬ ላይ መጥታችሁ እንዳትቀብሩኝ፡፡ እንዳታለቅሱልኝ፡፡ አደራ በሰማይ አደራ በምድር፡፡ አበቃሁ…”
No comments:
Post a Comment