Monday, October 12, 2015

ፍርሐት


©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
…ሌላው ከእግዚአብሔር እንድንርቅ ምክንያት የሆነው ፍርሐት ነው፡፡ ዓላውያን ነገሥታት፣ ከሐድያንና መናፍቃን ሲነሡ ስለ እግዚአብሔር አምላክነት ለመመስከር ፍርሐት አለ፡፡ እነዚህ ሊገድሉህ ቢችሉ እንኳን ሥጋህን እንጅ ነፍስህን ሊገድሏት አይችሉም፡፡ እነዚህን መፍራት እንደማይገባም በወንጌል እንዲህ ተገልጿል “ሥጋህንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ” /ማቴ10÷28/ አንተ መፍራት ያለብህ ገሃነም ሊያስገባህ የሚችልውን ኃጢአት ነው፡፡ ሰው ቢዝትብህም፣ ቢያስፈራራህም፣ ቢያስጨንቅህም ፍርሐት ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ አይገባውም፡፡ መግደላዊት ማርያም ሴት ሳለች ሴትነቷ ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚያርቅ ፍርሐት አላመጣባትም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን መቃብር ይጠብቁ የነበሩትን የታጠቁ ወታደሮች ከምንም አልቆጠረቻቸውም ፍርሐት የለባትም ነበርና፡፡ በማለዳ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ሄደች ሌሊቱ አላስፈራትም፡፡/ማቴ28÷1-10/ ሌሎች ፍርሐት ሲያርቃቸው እርሷ ግን ትንሣኤውን ለማየት የመጀመሪያ ሆነች፡፡ ሰለስቱ ደቂቅን የሚነድደው እሳት 49 ክንድ ያህል ከፍ ከፍ ሲል አላስፈራቸውም፡፡ የናቡከደነጾር ንጉሥ መሆን አላሸበራቸውም፡፡ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደሆነ መሰከሩ፡፡ ከፊታቸው የሚነድደው እሳት ወላፈኑ ልባቸውን አላስደነገጠውም፡፡ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል እንዲሰግዱ በብዙ ነገሮች አስፈራራቸው፡፡ እነርሱ ግን ምንም አይነት ፍርሐት የለባቸውም ነበር፡፡ ንጉሥ ሆይ አንተ ላቆምከው ምስል በፍጹም አንሰግድም አንተንም እኛንም ዓለምን በፈጠረ እግዚአብሔር እናመልካለንና አሉት፡፡ በዚህም የተነሣ ወደ እቶኑ እጃቸውን ታስረው ተጣሉ ቅዱስ ገብርዔል መጥቶ እሳቱን እንደ ውኃ አቀዘቀዘላቸው በእሳቱ መካከልም እየተመላለሱ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡/ዳን3÷1-ፍጻ/ እነዚህን ሕጻናት የሚነድደው እሳት አላስፈራቸውም፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያድናቸው ፍጹም እምነት ነበራቸው፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ከእሳቱ ባያወጣን ማለትም ሰማእትነትን እንድንቀበል ቢተወን እንኳን አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም ብላው ፍጹም እምነታቸውን አሳዩ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚቆረጥበት ስለት የሚፈጭበት ወፍጮ ሲቀርብለት አልፈራም በእግዚአብሔር ጸና እንጅ፡፡ ንጉሡ ዱድያኖስ እስኪያፍርና እስኪፈራ ድረስ እየሞተ እየተነሣ ስለ እግዚአብሔር አምላክነት መሰከረ፡፡ ንጉሡ እጅግ ተጨነቀ፤ ገደልኩት አረፍኩት ሲል ተነሥቶ ይመጣበታል፡፡ አሁንም እኔን ከሞት ባስነሳ አንተንም በፈጠረ ዓለምን ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር ባመጣ አምላክ በእግዚአብሔር እመን እያለ ይገስጸዋል፡፡ንጉሡ ግን መስማትን እንቢ አለ፡፡ይህን የተቀደሰ ምስክርነት ለመጠበቅ አንተም የፍርሐትን ጫማ አውልቀህ ልትጥል ያስፈልጋል፡፡ እስከመጨረሻው ድረስ ፍርሐትን አርቀህ ከተከተልህ የድል አክሊልን ትቀዳጃለህ፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስን ልብ በል፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ፈርተው ሲሸሹ እርሱ ግን እስከ ቀራንዮ ድረስ ፍርሐቱን አስወግዶ ተከተለው፡፡ በመስቀሉ አጠገብ በመገኘቱም ድንግል ማርያምን የምታህል እውነተኛ ቅድስት እናትእነኋት እናትህ ተብሎ ከአምላኩ ለመቀበል በቅቷል፡፡/ዮሐ19÷27/ አንተም እንደዚህ ባለው ጭንቅ ቀን እንኳን ሳይቀር ልትታመን ያስፈልጋል፡፡ በሰላም እና በደስታ ጊዜ ሁሉም ተከታይ ነው በመከራ ጊዜ ግን ሁሉ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ምግቡን እያበረከተ ሲመግብ ይመገብ የነበረው ያ ሁሉ ሕዝብ እስከ ቀራንዮ ድረስ መስቀሉን ተሸክሞ ሲወድቅ ሲነሣ ሊያሳርፈው የተከተለ አልነበረም፡፡ ፍርሐትን ከልብህ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፡፡ ያየኸውን ሁሉ ፈርተህ ከእግዚአብሔር ርቀህ ልትኖር አትውደድ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሐት ልትመሰክር አደራ አለብህ፡፡ ልምን ይህን ትናገራለህ? የሚልህ ቢነሣ ለእግዚአብሔር የሚገባ ስለሆነ ተናገርሁ ብለህ መልስለት፡፡ ስለ እምነትህ የሚገባውን ሁሉ ልታደርግ ከእግዚአብሔር ዘንድ መብት ተሰጥቶሃል፡፡ ይህን መብትህን እንዳትጠቀም የሚኮረኩምህ ከሃዲ ቢነሣ እጅህን አትስጠው የፍርሐት ስሜትም አይሰማህ፡፡ የነቢዩ ሙሴ መንድም አሮን የፈራውን ፍርሐት ከልብህ አርቀው፡፡ ሙሴከእግዚአብሔር ጋር 6 ቀን ቃል በቃል እየተነጋገረ 34 ቀን እየነገረ ሲያስጽፈው ለ40 ቀን በሲና ተራራ በቆየ ጊዜ ሕዝበ እስራኤል አሮንን ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ም እንደሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት፡፡ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔ ሌላ አማልክት አይሁኑልህ፡፡/ዘጸ20÷3/ የሚለውን አምላካዊ ትዕዛዝ ለመሻር ወሰኑ፡፡ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ የግድ ሙሴ አብሯቸው መኖር ነበረበት እንዴ? አሮን ሕዝቡን ፈራ ገንዘብ ወዳጆች ናቸውና በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁአምጡልኝ አላቸው፡፡ ነገር ግን ሰይጣን አነሣሥቷቸዋልና ለወርቃቸውም አላዘኑም፡፡ ሕዝቡም እንደታዘዙት ወርቃቸውን ወደ አሮን አቀረቡት፤ እርሱም በመቅረጫ ቀረጸው ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፡፡ ቁጡዓን የሆኑትን ሕዝበ እስራኤል የፈራው አሮን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡ እንዲህም አላቸው እስራኤል ሆይ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጧችሁ አማልክት ናቸው አላቸው፡፡ ለዚያም ምስል መሥዋዕት እየሰዉ እየበሉና እየጠጡ እየዘፈኑም ሰገዱ፡፡በዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ተቆጣ፡፡ /ዘጸ32÷1-ፍጻ/ ይህ አይነት ፍርሐት ከእግዚአብሔር ያርቃል፡፡ ለጣዖት ሲሰግዱ መሥዋዕት ሲሰው በፍርሐት የሚመለከት ሰው ከእግዚአብሔር ለመራቅ የወሰነ ሰው ነው፡፡ ይህን አይነቱን ፍርሐት ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ጭንቅ ሲመጣብህ ፈተና ሲደርስብህ መጽናት ከቻልክ ብቻ ነው የዘላለም ርስት ወራሽ የምትሆነው፡፡ ሐዋርያት ልብሳቸውን ጥለው እስከ መሮጥ ድረስ ያደረሳቸው ፍርሐት ነው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስን 3 ጊዜ ለመካድ ያበቃው ፍርሐት ነው፡፡ ምንም እንኳን በኋላ ኃይልን ለብሰው አንገታቸውን ለስለት ጀርባቸውን ለግርፋት እስከመስጠት ድረስ የደረሰ ፍጹም ጽናት የተሰጣቸው ቢሆንም መጀመሪያ ላይ ግን ፍርሐት ነበረባቸው፡፡/ማር14÷50-52/፣ /ማር14÷66-71/ በአርግጥ እንደዚህ አይነቱ ፍርሐት ጊዜያዊ ፍርሐት በመሆኑ በንስሓ የመመለስ ዕድል ይሰጣል፡፡ የአሮንም ሆነ የሐዋርያት ፍርሐት ለጊዜው ነው፡፡ እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ያለ ፍርሐት ማለት ነው፡፡ንጉሡ ዖዝያን የማይገባውን ሥራ በቤተ መቅደስ ገብቶ አጥናለሁ ሲል ንጉሥ በመሆኑ ፈራው በዚህም የተነሣ ለምጽ ወጣበት ትንቢት ተነሣው፡፡ በኋላ ግን ተመልሶለታል ጊዜያዊ ፍርሐት ነበርና፡፡/ኢሳ6÷1-8/ ነገር ግን ያ በትንሹ የጀመረ ፍርሐት እያደገ ንስሓን በር ጭምር የሚዘጋ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለጊዜው ነው በሚል አስተሳሰብ ኃጢአት መሥራት አይገባም፡፡ የመመለሻ ዕድሜ ይኑረን አይኑረን የምናውቀው ነገር ስለሌለ ዘሬ ፍርሐትን ልናስወግድ ያስፈልጋል፡፡ እስከ መጨረሻው መጽናት ያስፈልጋል፡፡ እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል ይላልና፡፡/ማቴ2413/ እዚህ ላይ የቅድስት ሶስናን ታሪክ እንመልከት፡፡ ሶስና መልከ ቀና ስለነበረች በሐፀ ዝሙት የተነደፉ ረበናት ወይም ሥርዓት አስተማሪ ነን ባዮች በአትክልት ቦታ ውስጥ ሰውነቷን ስትታጠብ ሄደው እሺ በእጄ በይን እንቢ ካልሽ ግን ከጎረምሳ ጋር ስትዳራ አገኘናት ብለን በድንጋይ እናስወግርሻለን አሏት፡፡ ነገር ግን ይህን ኃጢአት አድርጌው እግዚአብሔር ከሚፈርድብኝ ሳላደርገው ሞት ቢፈረድብኝ ይሻለኛል ብላ በድንጋይ ነመወገርን ሳትፈራ ጮኸች፡፡ እነርሱም አብረው ጮኹ ከወንድ ጋር ስትዳራ አገኘናት ብለው አዕሩገ እስራኤል ተሰብስበው ተወግራ እንድትሞት ፈረዱባት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ዳንኤልን ልኮ አዳናት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ነገር ሠሪዎችን እንደ አክርማ ሰነጠቃቸው፡፡/መጽሐፈ ሶስናን ተመልከት/

No comments:

Post a Comment