©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፈው ቃል በገባሁላችሁ መሠረት ቃሌን ለመጠበቅ
ኢትዮጵያዊውን የመልካም ምኞት አገላለጽ እና አሁን እየተበረዘ ስላለበት ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን ከሌላው ዓለም
ሁሉ ልዩ የሚያደርገን በርካታ ነገር እንዳለው የታመነ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በደስታ በሐዘን የአንዱን ሌላው የሚጋራበት የባህል
ማዕከል ነው፡፡ ሌላው ዓለም ምናልባት ሃዘንህን የተጋራ ደስታህንም እንዲሁ የተጋራ ሊመስል ቢችልም የመልካም ምኞት አገላለጹ ግን
ሙሉ በመሉ ደስታህን እንዳልተጋራልህ ያሳያል፡፡ አንተ ስትደሰትም ሆነ ስታዝን ሌላው ሰው የሚጋራልህ ከሆነ እርሱ ኢትዮጵያዊነት
መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
ኢትዮጵያዊነት ደስታህ ደስታየ ነው ሲል “እንኳን
ደስ አለህ!” ይልሃል አንተም “አብሮ ደስ ይበለን” ብለህ ትመልሳለህ፡፡ ይህ መልካም ምኞት መግለጫችን ደስታህ ደስታየ መሆኑን
የሚጠቁም ነው፡፡ “አብሮ ደስ ይበለን” የሚለው ምላሽም እርሱን የሚያጎላ ነው ሁላችንንም ደስ ይበለን የሚል ስለሆነ፡፡ ሌላው
“እንኳን አደረሰህ” የሚለው ሲሆን “እንኳን አብሮ አደረሰን” የሚለውን ምላሽ ያስከትላል፡፡ ያንተ መድረስ ለእኔ የእኔም መድረስ
ላንተ ምኞታችን ነው ለዚህም ነው “እንኳን አደረሰህ” ስትባል “እንኳን አብሮ አደረሰን” የምትለው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁላችንንም
እንኳን አደረሰን ብለን የምንመልሰው የሌሎቹንም ለዚያ ቀን መድረስ ስለምንመኝ ስለምናስብ ነው፡፡ መልካም ምኞት አገላለጻችን አንድን
ወገን ብቻ የሚገልጽ አይደለም፡፡ ሌሎች ዓለማት ግን መልካም ምኞታቸው አንድ ወገን ተኮር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን ልዩ የሚያደርገን
መልካም ምኞታችን ሁለት ወገን ተኮር መሆኑ ነው፡፡
አንድ ወገን ተኮር መልካም ምኞታቸው ኢትዮጵያዊነታችንን
እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ ውጮቹ “CONGRATULATION” ይላሉ መላሹም “THANK YOU” ይላል፡፡ “እንኳን ደስ አለህ” ሲባል
“አመሰግናለሁ” ብሎ ይመልሳል ማለት ነው፡፡ የእኔ ደስታ አንተን አይመለከትም “እንኳን ደስ አለህ” ላልከኝ ግን “አመሰግናለሁ”
ማለት ነው እንግዲህ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ግን ደስታህ ደስታየ ነው እና አይመለከትህም አልልህም “አብሮ ደስ ይበለን” ብሎ ይመልሳል፡፡
ሌላው የምንመለከተው “የእንኳን አደረሳችሁ” መልእክታቸውን ነው፡፡ ውጮቹ “HAPPY NEW YEAR”፣ “HAPPY X_MASS”፣
“HAPPY EASTER” ወዘተ በማለት መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ መልካም ምኞቶች እኛ አገር ውስጥ ዋጋ የላቸውም፡፡
“መልካም አዲስ ዓመት”፣ “መልካም ገና”፣ “መልካም ፋሲካ” የሚል ቀጥተኛ ትርጉም ይይዛሉ፡፡ ታዲያ መላሹ “አመሰግናለሁ” ብሎ
ይመልስ? ወይስ “እንኳን አብሮ” አደረሰን ይበል? ኢትዮጵያዊነት መቸም “አመሰግናለሁ” ብቻ ብሎ መልካም ምኞቱን ለሌሎችም ሳያጋራ
ውጦ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በመጀመሪያ “መልካም አዲስ ዓመት” አይልም “መልካም ገና” እና “መልካም ፋሲካ” ብሎም መልካም
ምኞት አይገልጽም፡፡ የእኛ ያልሆነውን ነገር በፈረንጆቹ ተጽእኖ ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር ቀላቀልነው እንጅ እኛ የምንለው “እንኳን
ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሰህ” ነው፡፡ መላሹም “አመሰግናለሁ” ሳይሆን “እንኳን አብሮ አደረሰን” የሚል ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር
እኔ ብቻ ሳልሆን አንተንም እንኳን አደረሰህ እያለው ነው፡፡ ፈረንጆቹ ግን “አመሰግናለሁ” ይሉሃል ምክንያቱም ያንተ ለዛ ቀን መድረስ
አለመድረስ ምናቸውም አይደላማ!፡፡ ሌሎችንም በእነደዚህ ያለ ሁኔታ ነው እንኳን አደረሳችሁ የምንባባለው፡፡ ለገና በዓል “እንኳን
ለጌታችን ለመድኃታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በሰላም አደረሰህ” እንዲሁም ለትንሣኤ በዓል “እንኳን ለጌታችን ለመድኃታችን ለኢየሱስ
ክርስቶስ ትንሣኤ በሰላም አደረሰህ” እንባባላለን መላሹም ከላይ እንደተመለከትነው
“እንኳን አብሮ አደረሰን” ይላል፡፡
አሁን አሁን ግን በርካታ ኢትዮጵያዊነት ለዛችንን
እያጣን ያለንበት ሁኔታ ነው፡፡ “እንኳን ለልደትህ በሰላም አደረሰህ” በማለት ፋንታ “HAPPY BIRTH DAY” ማለት የሚቀናው
ኢትዮጵያዊ እየተበራከተ ነው፡፡ “መልካም ልደት”፣ “መልካም አዲስ ዓመት”፣ “መልካም ገና”፣ “መልካም ፋሲካ” ወዘተ እያልን የፈረንጆቹን
አንድ ወገን ተኮር የሆነ መልካም ምኞት መግለጫ መጠቀም መጀመራችን ታሪካችንን የሚፈታተን እና ማንነታችንን የሚያበላሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን
ከሌላው የዓለም ክፍል ሁሉ ልዩ ያደርገናል፡፡ የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የአነጋገር፣ የአረማመድ ልዩ ባህል አለን፡፡ ስንመገብ ዘመድ
ጎረቤቱ ተሰብስቦ በአንድ መሶብ ከብቦ አንዱ አንዱን እያጎረሰ ይመገባል፡፡ ይህ ልዩ ፍቅርን የሚያሳይ ነው የሚጎርሰው ሰው ቆርሶ
መጉረስ አልችል ብሎ አይደለም የምናጎርሰው ፍቅራችንን ለመግለጽ እንጅ፡፡ መተሳሰብ መረዳዳታችንን ለማሳየት የምንጠቀምባቸው ባህሎቻችን
ናቸው፡፡ስለዚህ በሌሎቹ ተጽእኖ ስር ከመውደቅ ራሳችንን እንጠብቅ የሚል መልእክት አስተላልፋለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment