መስከረም
18/ 2009 ዓ.ም
እረኛ እንደመሆን ከባድ አደራ
የለም፡፡ አደራው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ያከብደዋል፡፡ ለጴጥሮስ የተሠጠው የእረኝነት ሥልጣን በጎችን እንዲጠብቅ
ብቻ ሳይሆን በሚገባ እንዲያሰማራ ጭምር ነበር፡፡ መጠበቅ ቀላል ነው ማሰማራት ግን ከባድ ነው፡፡ የለመለመ ሣር በሌለበት፣ የእረፍት
ውኃ በማይገኝበት ቦታ መጠበቅ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን በጎቹ ይከሳሉ፣ ይጠቁራሉ፣ ይደክማሉ፣ ይራባሉ፣ ይጠማሉ በመጨረሻም ይሞታሉ፡፡
ይህ እረኝነት ችግር አለበት፡፡ ተኩላ ሊነጥቃቸው ቢመጣ ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ስለዚህ ነው ይህን እረኝነት ችግር
አለበት የምንለው፡፡ እረኝነት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ማሰማራትንም ይጠይቃል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የበጎቹን ባሕርይ በሚገባ ማዎቅ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም
የምናሰማራበትን ቦታ ለመምረጥ የበጎቹን ፍላጎት መረዳት ግድ ይላል፡፡ ውኃ የጠማቸውን በጎች ከለመለመ ሳር ውስጥ፣ የተራቡ በጎችን
ደግሞ በእረፍት ውኃ ዘንድ ብናሰማራቸው ምንም ዋጋ የለውም፡፡ ምክንያቱም ለጠማው ውኃ፤ ለራበው ደግሞ ሳር እንጅ ሌላ ፍላጎት እንደማይኖራቸው
የታወቀ ነውና፡፡ ስለዚህ ነው እንግዲህ እረኝነት ከባድ አደራ ነው የምንለው፡፡ እውነተኛው እረኛ ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል፡፡
ተኩላ ሊነጥቃቸው ቢመጣ በመጀመሪያ እረኛው ከተኩላው ጋር ይታገላል፡፡ እረኛው በትግሉ ከተሸነፈ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ በጎቹን
ተኩላ ሊነጥቃቸው የሚችለው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን በጎቹ በማንም አይነጠቁም፡፡ እረኝነት ይህ ነው ከእግዚአብሔር ስንቀበለው ደግሞ እጅግ
በጣም ከባድ ነው፡፡
በዚህ አስከፊ ዘመን እርስ በርሳችን ደም ስንፋሰስ ሰላም ስትርቀን ወንድሞቻችን ሲሞቱ፣ ሕጻናት
ሳይቀር ሲጨፈጨፉ፣ እናቶች በልጆቻቸው አስከሬን ላይ ቁጭ በሉ እየተባሉ ሲደበደቡ የሚያጽናናን አባት ማጣታችን ልባችንን ሰብሮት
ነበር፡፡ እንዲያውም ይባስ ብሎ ፓትርያርኩ ከምእመናን በተሰበሰበ ሽራፊ ሳንቲም በሚንቀሳቀሰው የቤተክርስቲያናችን ቴሌቪዥን ላይ
ብቅ እያሉ ማን የጻፈላቸውን እንደሆነ ባናውቅም ከአንድ እረኛ የማይጠበቅ መግለጫ መሰል ንግግራቸውን ሲያነበንቡብን በጣም እጅግ
አዝነን ነበር፡፡ ኤልያስ ስለ ናቡቴ ከንጉሡ አክአብና ንግሥት ኤልዛቤል ጋር የተጋጨው፣ ዮሐንስ መጥምቅ የወንድምህን ሚስት ልታገባት
ህግ አይፈቅድልህም በማለት ከንጉሥ ሔሮድስ ጋር የተጋፈጠው፣ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ አንዲት ደሃ መበለት ከንግሥት አውዶክስያ ጋር
የተከራከረው እና መከራን የተቀበለው፣ አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያ ለፋሽስት ባህል እምነት እንዳትገዛ በማውገዛቸው በጥይት የተገደሉ እረኝነታቸው እውነተኛ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬ ግን ፓትርያርኩ የሚሰጡት መግለጫ
እረኝነታቸውን የማያሳይ ምእመናንን ይበልጥ ውስጣቸውን እየጎዳቸው ያለ ነገር ነው፡፡ እረኝነት የሞቱ በጎቹን እየፈታ መቅበር ከዚያም
ነፍሳቸውን ማርልን ብሎ ማስተጋባት ብቻ አይደለም እንዳይሞቱ መጠበቅ ጭምር እንጅ፡፡
ለብዙ ዘመናት አባት የሌለን ልጆች ነን ስንል ነበር፡፡ ፓትርያርኩ የሚሰጡት መግለጫ የቅዱስ
ሲኖዶሱ እየመሰለን አባቶቻችንን ስንጠላቸው ኖረናል፡፡ ግን አይደለም፡፡ አባት አለን ልጆች መሆን ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ በደመራ
በዓል ላይ የምእራብ ጎጃም፣ የአዊ እና የመተከል አህጉረ ስብከቶች ሊቀጳጳስ
የሆኑት አቡነ አብርሃም የብዙ ንጹሐን ወገኖቻችን ደም በፈሰሰባት በባህር ዳር ከተማ መስቀል አደባባይ ላይ ተገኝተው
ከአንድ መልካም እረኛ የምንጠብቀውን ስንናፍቀው የኖርነውን የተመኘነውን የአባት ፍቅር ሰጥተውን ተመለከትን እና በጣም ደስ አለን፡፡
አባታችን እንደሚከተለው ነበር በህዝብና በመንግሥት መካከል በመሆን የሰላም ንግግር ያደረጉት፡፡
ከዚህ የተረዳነው ትልቁ ነገር የፓትርያርኩ መግለጫ የቤተክርስቲያናችን አለመሆኑን ነው፡፡ እርሳቸውንማ
ግማደ መስቀሉ ያለው ግሸን መሆኑን ዘንግተው አዲግራት ላይ አየናቸው እኮ፡፡
የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው ከአንድ ማኅጸን ተወልደው በአንድ ቤት አድገው የምሥራቅ
ጎጃሙ ሊቀጳጳስ አቡነ ማርቆስ ከአሜሪካ ስልክ መትተው “መስቀል አብርሃ”
ከሚለው መዝሙር ውጭ ሌላ እንዳይዘመር ሰንበት ትምህርት ቤቶችን አስጠነቀቁ አሉን፡፡ “አንመካም በጉልበታችን እግዚአብሔር ነው የእኛ
ኃይላችን፤ መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንእነ መስቀል ቤዛነ” እየተባለ እንዳይዘመር አስጠነቀቁ ተባልን እኛም “መስቀል አብርሃ” ስንል
ዋልን፡፡ አቡነ አብርሃም ደግሞ “ወታደሮች ከተሸከሙት መሣሪያ ይልቅ መስቀል ይበልጣል” በማለት በከበቧቸው ወታደርች መካከል ቆመው
እውነቱን መሰከሩ፡፡ ልጆቼ ከቤታቸው በሰላም ሲገቡ ሳላይ ወደ መንበሬ አልሄድም ብለው ልጆቻቸው በሰላም መግባታቸውን አይተው በእግራቸው
ወደ መንበራቸው ገቡ አሉን ደስ አለን፡፡
በዘመናችን መራራ የሆነውን እውነት ተጋፋጭ አቡነ አብርሃም ዳግማዊ አቡነ ጴጥሮስ ብላቸው እንዴት
ደስ ባለኝ ነበር ዳሩ ግን እኔ ስም የማውጣት መብቱ የለኝም፡፡ ለአባታችን ረዥም ዕድሜ ዘመንን ይስጥልን፡፡ አባታችን ስንለው ልጆቼ
የሚለን በማግኘታችንም ሁላችንም ኮርተናል ደስም ብሎናል፡፡ ነገር ግን በዚህ ንግግራቸው መከራ እና ስቃይ ሊደርስባቸው እንደሚችል
የታመነ ነው፡፡ በርግጥ እርሳቸው ለዚህ እንደማይበገሩ እናምናለን ምክንያቱም እግዚአብሔር ህዝቡን እንዲጠብቁ አደራ ሰጥቷቸዋልና፡፡
ሆኖም ግን ጠባቂው እግዚአብሔር እንደሆነ ብናውቅም የአባታችንን ጉዳይ
ግነ በቅርበት መከታተል እንደሚገባን አሳስባለሁ፡፡