Thursday, September 8, 2016

“ሰውነታችንን ካላስቀደምን ሰላምን አናመጣም”

ጳጉሜን 3/ 2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
========================
በመጀመሪያ ይህንን ገጽ ላይክ ያድርጉ facebook.com/beyenemlkm
========================
ሁላችን አሁን ከደረስንበት ደረጃ ከመብቃታችን በፊት ሰው ነበርን፡፡ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ሃይማኖት የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ብሔር የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ዘር የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ጎሳ የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ጎጥ የለንም፡፡ ከዚህ ሁሉ ቀድሞ የነበረው ሰውነት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ በስፋት ከሚያስተምሩ የቤተክርስቲያናችን ፈርጦች መካከል አንዱ የሆኑት ብርቅየ ሊቅ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ ናቸው፡፡ እርሳቸው ሰው እንሁን እንደ ሰው እናስብ እያሉ ሁልጊዜ ይሰብካሉ ያስተምራሉ ይመክራሉ ነገር ግን ሰሚ ጆሮ ያጡ ይመስላል፡፡ ሰው እንሁን ሰውነታችንን እናስቀድም ማለት ፖለቲካ አልያም ሃይማኖታዊ ስብከት አይደለም፡፡
ሰውነታችንን ስናስቀድም በሃይማኖት አንለያይም ምክንያቱም ሃይማኖት ሰው ከመሆናችን በኋላ የሚመጣ ጉዳይ ነውና፡፡ የኦርቶዶክ ተዋሕዶ፣ የፕሮቴስታንት፣ የእስልምና፣ የካቶሊክ ወዘተ እምነት ተከታዮች መሆን የጀመርነው ሰው ከመሆናችን በኋላ ነው፡፡ ስለዚህ በሃይማኖት ልዩነትን ፈጥረን አንዱ ለአንዱ ጠላት የሚሆነው ሰውነታችንን ስለማናስቀድም ብቻ ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ እንመለከታለን፣ መስጊዶች ሲፈራርሱ እናስተውላለን ይህ ክስተት የሚፈጠረው ሰውነታቸውን ባላስቀደሙ ሰዎች ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ሰው ከመሆናቸው ያስቀደሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትን እንደልዩነት በመጠቀም ከሰውነት አንድነታችን መውጣት የለብንም፡፡ ምንም እንኳ በሃይማኖት ብንለያይም ሰው በመሆናችን ግን እንተባበራለን፡፡ ትብብራችን ደግሞ ቀድሞ ባገኘነው የሰውነት ጸጋ እንጅ በኋላ ባገኘነው የሃይማኖት ጸጋ መሆን አይገባውም፡፡
ሌላው ሰውነታችንን ስናስቀድም በሃገር፣ በዘር፣ በብሔር፣ በጎሳ፣በጎጥ ወዘተ አንለያይም፡፡ አገሬ፣ ዘሬ፣ ብሔሬ፣ ጎሳየ፣ ጎጤ ወዘተ ከማለታችን በፊት ሰው መሆናችን ይቀድማል፡፡ ሰው ስንሆን ያን ጊዜ አምላክ ባወቀ በሆነ አገር፣ በሆነ ብሔር፣ በሆነ ጎጥ፣ ከሆነ ዘር እንድንወለድ አደረገን፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ፈልገን የተወለድንበት አገር፣ ብሔር፣ ዘር፣ ጎሳ እንደሌለ ነው፡፡ የአምላክ ፈቃድ ሆኖ ከሆነ አገር፣ ከሆነ ብሔር፣ ከሆነ ጎጥ፣ ከሆነ ዘር ፈጠረን እንጅ እኛ የመረጥነው እንዳልሆነ እናስተውላለን፡፡ ስለዚህ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በዘር ከመከፋፈላችን እና አንድነታችንን ከመበታተናችን በፊት ሰውነታችንን እናስቀድም፡፡ ሰውነታችንን ካስቀደምን በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ በብሔር አንከፋፈልም፡፡ ደግሞም እኮ ሁሉን ያደረገልንን አምላክ ልናመሰግነው ይገባል እንጅ በእነዚህ ነገሮች መለያየትን እንዴት እንቀበላለን፡፡ ዛሬ በብሔር በቋንቋ እና በዘር እንድንከፋፈል ያደረገን ሰውነታችንን ስላላስቀደምን ብቻ ነው፡፡ የትም ተወለድ የት፣ የትም ተፈጠር የት ሰው ነህ፡፡ ሰው በመሆንህ ደግሞ አንድነትን ታጠነክርበታለህ እንጅ ልዩነትን አትፈጥርበትም፡፡ ምክንያቱም ሰው ከሰው በምንም ሊለያይ አይችልምና፡፡
ሰውነታችንን ስናስቀድም ማንም ማንንም አይገድልም፤ ማንም በማንም አይሞትም አይገደልምም፡፡ አንዱ ባለስልጣን ሌላው ሎሌ፣ አንዱ ገዳይ ሌላው ተገዳይ፣ አንዱ ሰጭ ሌላው ተቀባይ፣ አንዱ ጠጋቢ ሌላው ተራቢ፣ አንዱ ረጋጭ ሌላው ተረጋጭ በመሆን መለያየት የመጣው ሰው ከመሆናችን በኋላ ነው፡፡ እንደ ሰው ስታሰብ ሌሎች ባንተ ላይ ሊያደርግብህ የማትፈቅደውን ነገር በሌሎች ላይ አታደርግም፡፡ ስለዚህ አንተን እንዲገድሉህ እንደማትፈቅድ ሁሉ ሌሎችን ለመግደል አትፈቅድም፡፡ አንተን ሲረግጡህ ሲጨቁኑህ እንደማትወድ ሁሉ ሌላውን አትረግጥም አትጨቁንም፡፡ ስለዚህ ነው ሰውነታችንን ማስቀደም አለብን የምንለው፡፡ አንተ ባማረ በተዋበ ባሸበረቀ በዕንቁ ባጌጠ ቪላ ቤት ላይ እየተንፈላሰስክ ሌላው መንገድ ላይ ወድቆ በብርድ ሲሰቃይ መመልከት እንደ ሰውነቱ ለማያስብ እንጅ እንደሰውነቱ ለሚያስብ ሰው እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡
እንደሰውነታችን ስናስብ ሰውን አንገድልም ምክንያቱም እኛን እንዲገድሉን ስለማንፈልግ፡፡ አሁን ግን እያስቀደምነው ያለ ጉዳይ ከሰውነታችን በኋላ የመጡ ጉዳዮችን ሆኗል፡፡ በቅርቡ ያየነው እና ያስተዋልነው የአገራችን ጉዳይ ሰውነታቸውን ካላስቀደሙ ወገኖች በተሰነዘረ ጥቃት የብዙዎች ደም ፈስሷል፡፡ ሁልጊዜ ሳስበው ከኅሊናየ አልወጣልህ ያለኝ ግን ማረሚያ ቤቶች ሲቃጠሉ ለማምለጥ ሞክረዋል ተብለው በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉት ንጹሐን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በእውነት እንደሰውነት ለሚያስብ ሰው ማረሚያ ቤቱ ሲቃጠል ታሳሪዎች ምን ማድረግ ነበረባቸው? በእሳት ላለመቃጠል ከማምለጥ ውጭ ምን ተስፋ አላቸው? ከእሳቱ ከማምለጥ ውጭስ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው? ሳስበው በጣም ይዘገንነኛል፡፡ በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ መወሰን ሰው ከመሆን ውጭ ያለው የሚያስበው ከንቱ ሀሳብ ነው፡፡ እንደ ሰውነታችን ካሰብን በእርግጠኝነት እንዳይቃጠሉ እንተባበራቸው ነበር እንጅ አመለጡ ብለን ተኩሰን አንገድላቸውም ነበር፡፡
ሰውነት አንድ ያደርጋል፡፡ በመወለድ አንድ ሆነናል በመሞትም አንድ እንሆናለን፡፡ በመብላት አንድ ሆነናል በመጠጣትም አንድ እንሆናለን፡፡ ዘርን በመተካት አንድ ሆነናል በማሰብም አንድ እንሆናለን፡፡ ስለዚህ ከሁሉ አስቀድመን ሰው መሆናችንን እናረጋግጥ ከዚያ በኋላ ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ጎሳ ከዚህ በኋላ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ሰው ስንሆን ለሁሉ እንራራለን፣ ሰው ስንሆን ለሁሉ እናስባለን፣ ሰው ስንሆን ሁሉን እንመግባለን፣ ሰው ስንሆን ሁሉን እንታደጋለን፣ ሰው ስንሆን ሁሉን በፍቅር እንመለከታለን፣ ሰው ስንሆን አድልዎ አንፈጽምም፣ ሰው ስንሆን ለሁሉ እኩል እንጨነቃለን፡፡ ሰው ካልሆንን ግን የዚህ ተቃራኒ እንሆናለን፡፡ እኛ ጮማ እየቆረጥን ጠጅ እያንቆረቆርን ሌላው በረሃብ ሲያልቅ እንስቃለን፡፡ እኛ ባማረ ቤት ሞቆን እየኖርን የሚወጥሩት ሸራ እንኳን አጥተው መንገድ ላይ የሚያድሩትን ወገኖቻችንን አናስባቸውም፡፡ ስለዚህ እንደሰውነታችን እናስብ እንደሰውነታችን ካሰብን ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት ማንም ሊቀማን ማንም ሊነፍገን የማይችላቸው ሃብቶቻችን ይሆናሉ፡፡

No comments:

Post a Comment