© መልካሙ በየነ
ጥቅምት
21/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
እመ አምላክ (የአምላክ እናት) ድንግል ማርያም፡፡ ይህ አገላለጽ
ከእናታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ውጭ ለማንም ለማን የማይነገር ብቸኛ አገላለጽ ነው፡፡ እናትነትን
ከድንግልና ጋራ አስተባብራ የምትገኝ ሴት ከድንግል ማርያም ውጭ በየትኛውም ዓለም ውስጥ አትገኝም፡፡ እም ወድንግል ቢሉ የአዳም
ተስፋ ምክንያተ ድኅነታችን የገነት በር የተከፈተባት እናታችን ብቻ ናት፡፡ ይህ ነገር ከሰው ኅሊና በላይ ነው፡፡ አእምሯችን ምጡቅ
ሥራችን ረቂቅ ነው የሚሉ ጠቢባን ሁሉ ይህንን ነገር ሊረዱት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እናት እና ድንግል ሲባል መስማት ለጆሮም እንግዳ
ነውና፡፡ ሌሎች ሴቶች ድንግል ከተባሉ እናት፤ እናት ከተባሉም ድንግል መባል አይችሉም፡፡ በምንም ተአምር ይህንን ማስተባበር አይችሉም፡፡
ከዓለም መፈጠር በፊት በአምላክ ኅሊና ተስላ የነበረች ንጽሕት ዘር እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ይህንን አስተባብራ ከፍጥረታት
ሁሉ ልቃ ተገኘች፡፡ አስቡት ይህንን ድንቅ ምሥጢር! ይህ ነገር እኮ ከእኛ ኅሊና በላይ ወደ ላይ ብንወጣ የማናገኘው፣ ወደ ታች
እመቀ እመቃት ወደ ጥልቁ ብንወርድ የማንረዳው፣ ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ ብንበርር የማንገነዘበው ምጡቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የእናታችን ምስጋና የበዛለት አባ ኤፍሬም “ኦ
ዝ ነገር” በማለት በአንክሮ የሚናገረው፡፡ እውነት ነው ነገሩ ይረቃል፣ ነገሩ ይደንቃል፣ ነገሩ ይከብዳል፣ ነገሩ ለመረዳት ያስቸግራል፣
ነገሩ እጹብ እጹብ ብቻ የሚባል ነው፡፡
ሴቶች ልጅ በመጽነሳቸው ደስ ይላቸዋል በመውለዳቸው ደግሞ አብልጠው
ደስ ይላቸዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ደግሞ ወንድ ይወለድላችኋል ሲባሉ ደስ ይላቸዋል፡፡ አያችሁት የእናታችንን ደስታ! በመልአኩ ብሥራት
ትጸንሻለሽ መባል ምንኛ ያስደስታል!!! ይህንንማ ሌሎች ሴቶችስ የሚያገኙት አይደለምን ቢሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ነቢይ
ነው በዚያ ይደሰታሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ሐዋርያ ነው በዚያ ይደሰታሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ቅዱስ አባት
ቅድስት እናትን ነው በዚያ ይደሰታሉ፡፡ ሌሎች ሴቶች ትወልዳላችሁ ቢባሉ ጳጳስ ሊቀጳጳስ ካህንን ነው በዚያ አብዝተው ይደሰታሉ፡፡
እናታችን ግን ትወልጃለሽ ብትባል የሰማይ እና የምድር ጌታን እርሷንም የፈጠራትን አምላክ ነው፡፡ ይህ ያስደስታል! በዚህም ላይ
ድንግልናን ከእናትነት ጋራ ማስተባበር ምንኛ ያስደስት፡፡ ይህ ድንቅ ነገር የተደረገው ለእናታችን ለድንግል ማርያም ብቻ ነው፡፡
ፈጣሪን ጸንሶ መውለድ ምንኛ ረቂቅ ምሥጢር ነው? ይህ ረቂቅ ምሥጢር በድንግል ማርያም ሲደረግ ስናይ እናታችንን አብዝተን ወደድናት
አብዝተንም አደነቅናት አብዝተንም ተስፋችን አልናት፡፡ አብዝተን ስንደነቅ አብዝተን ስንወዳት አብዝተን ተስፋችን ነሽ ስንላት ግን
ቅንጣት ታህል የምንጨምርላት ነገር ኖሮ አይደለም ነገሩ ቢረቅብን ነው እንጅ፡፡ በእውነት በእናታችን ፍቅር ተነድፈን አፋችን ለዘለዓለም
ድንግል እናቴ ድንግል እናቴ አማልጅኝ ሲል ቢኖር ምንኛ በታደልን! ከእናታችን ፍቅር ርቀው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ፍቅሯ ጣዕሟ
ባይገባቸው ነው፡፡ ቢገባቸውማ እናቴ ለማለት ቅጽበት ባልወሰደባቸውም ነበር፡፡ አምላካችን ፈጣሪያችን ከእናቱ ከእናታችን ከድንግል
ማርያም ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡