© መልካሙ በየነ
ጥቅምት
10/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
በመጀመሪያ ይህንን እንደ ርእስነት እንድጠቀምበት በውስጥ መስመር
ለላከልኝ ፀገየ ባዩ አመሰግናለሁ፡፡
“አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1 ይህንን ቃል የተናገረው
አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ቃሉ የተነገረው በዘመኑ ለነበሩት የሕዝብ መሪዎች ለሆኑ ነቢያት እና ካህናት ቢሆንም ፍጻሜው ግን
በዘመናችን ላሉ የሃይማኖት አባቶች ሁሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ በዋናነት ሁለት ነገሮችን ማንሣት ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ የመጀመሪያው
እግዚአብሔር ሕዝቤ የሚላቸው እነማንን ነው የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማጽናናት ምንድን ነው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር
በመጀመሪያ ከፍጥረት ሁሉ አክብሮ እና አብልጦ ሲፈጥረን የመንግሥቱ ወራሾች የሥሙ ቀዳሾች እንድንሆን እንጅ በከንቱ እንድንጠፋበት
አይደለም፡፡
የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚባለው በእግዚአብሔር አምላክነት የሚያምንና
በእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚመራ ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃችን እግዚአብሔር ሙሴን አሥነስቶ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ ሊወጣቸው በወደደ ጊዜ የግብጹን ፈርዖን
“ህዝቤን ልቀቅ” ብሎታል፡፡ እነዚህ በግብጽ ባርነት ውስጥ አገዛዝ የከበዳቸው እስራኤላውያን በእግዚአብሔር አምላክነት የሚያምኑ
እና በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሥርዓት የሚመሩ ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር “ህዝቤ” የሚላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የነጻነት ጉዞውን
በሙሴ መሪነት ጀመሩ፡፡ የኤርትራን ባህር ከፍሎ አሻገራቸው፡፡ አሁን ሲና ተራራ ላይ ደርሰዋል ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ለቃል
ሊነጋገር ወደ ተራራው ወጥቷል፡፡ ሙሴ በጣም እንደዘገየባቸው ሲረዱ ሕዝበ እስራኤላውያን “ሙሴ አመሌ አመሌ ሲል እሳት አቃጥሎት
ሞቶ እንደሆነ አናውቅማና አምላክ ሥራልን” ብለው ወንድሙ አሮንን አስቸገሩት፡፡ አሁን ህዝበ እስራኤላውያን አምላካቸው እግዚአብሔር
እንደሆነ ዘንግተዋል፡፡ የሚገርመው ነገር “አምላክ ሥራልን” ማለታቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ባህረ ኤርትራን ከፍሎ አሻግሮ፣ መና
ከደመና እያወረደ መግቦ ውኃ ከጭንጫ እያፈለቀ አጠጥቶ፣ ዋዕየ ፀሐይን በደመና ከልሎ እየመራቸው ለዚህ ደርሰዋል እነርሱ ግን ይህንን
ሁሉ ውለታ ዘነጉ፡፡ አሮንም ከግብጽ ስትወጡ ይዛችሁት የመጣችሁትን
ንብረታችሁን ሰብስቡ አላቸው፡፡ ለገንዘባቸው ቀናዒ ናቸውና አንሰጥህም ይሉኛል ጊዜ አገኛለሁ እስከዚያ ድረስም ወንድሜ
ይመጣልኛል አርፋቸዋለሁ ብሎ ነበር፡፡ እነርሱ ግን ወዲያውኑ ገንዘባቸውን ሰብስበው “አምላክ ሥራልን” አሉት፡፡ አርሱም ጉድጓድ
አስምሶ እሳት አስነድዶ ወርቅ ብራቸውን ከዚያ ላይ ጣለው የጥጃ ምስል ሆኖ ወጣላቸው፡፡ አምላካችን ይኼ ነው ብለው ዘፈኑለት ሰገዱለት
መስዋእት ሰውለት፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር “ሙሴ ህዝብህ በደለኝ”
አለው፡፡ ቅድም “ህዝቤ” ያላቸውን አሁን “ህዝብህ” አለው ጠብ ተጀመረ
ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብነት ዝም ብሎ የሚኖር የባሕርያችን አይደለም ማለት ነው፡፡ ጠቅለል ሲል ህዝብ ማለት በእግዚአብሔር የሚያምን፣
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጠብቅ፣ በእግዚአብሔር ሥርዓት የሚኖር ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ “ማጽናናት” የሚለው ነው፡፡ ይህ ህዝብ ያዝናል፣
ይተክዛል፣ ይራባል፣ ይጠማል፣ ይሰደዳል፣ ይገደላል፣ ሃብት ንብረቱ ይዘረፋል፣ በበሽታ ይሰቃያል፣ ይታሰራል፣ ይንገላታል ወዘተ፡፡
በዚህ ጊዜ እንባውን አባሽ፣ መካሪ፣ አይዞህ ባይ ይሻል፡፡ ማጽናናት ሃዘንን ማስረሳት ነው፡፡ ማጽናናት ችግሩን መፍታት ነው፡፡
ማጽናናት አይዞህ አለንልህ ብቻህን አይደለህም ብሎ ከጎኑ መቆም ነው፡፡ ማጽናናት ሲራብ ማብላት ሲጠማ ማጠጣት ሲታረዝ ማልበስ ነው፡፡
ማጽናናት የጠፋበትን ሃብትና ንብረት መተካት ነው፡፡ ማጽናናት ማለት የሚያድርበትን የሚያርፍበትን ጎጆ መቀለስ ነው፡፡ ማጽናናት
ማለት ከኃጢአት ባርነት መመለስ ነው፡፡ ማጽናናት ማለት ንስሐን ማስተማር ነው፡፡ ማጽናናት ማለት የተስፋ ቆራጭነትን ስሜት ማጥፋት
ነው፡፡ ማጽናናት ማለት ተስፋን ማለምለም ነው፡፡
እግዚአብሔር “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1 ሲል ከላይ
በተመለከትነው መልኩ ነው፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር ህዝቦች በሥጋቸውም በነፍሳቸውም እግዚአብሔርን ሲያመልኩ እንዲኖሩ፣ በፍቅር በደስታ
ምድርን እንዲሞሏት፣ መከራ ጭንቀታቸውን እንዲረሱ፣ ኃጢአታቸውን ትተው ወደ ጽድቅ እንዲመለሱ አድርጉ ማለቱ ነው፡፡
አባቶቻችን ዛሬም እኛ ከሃዘናችን፣ ከመከራችን፣ ከስቃያችን ሁሉ
እንድንጽናና ምክራችሁ ትምህርታችሁ ያስፈልገናል፡፡ ማጽናናት እንደማስለቀስ እንደማሳዘን ቀላል አይደለም፡፡ ልቡ የተሰበረን ህዝብ
አጽናኑ፣ የእኛ ተስፋ ነገ ብቻ ነው፡፡ ነገ አዲስ ቀን ነው ነገ ይችን ምድር ተሰናብተን ለዘለዓለም የምንሄድበት ቀን ነው፡፡ ነገ
እንደ ሥራችን ገነት ወይም ሲዖል የምንገባበት ነው፡፡ ዕድሜ ዘመናችንን በምድር ላይ አናሳልፍም፡፡ እርስ በርሳችን አንጠላላ፣ እርስ
በርሳችን አንገዳደል፣ አርስ በርሳችን አንወቃቀስ፣ እርስ በርሳችን ቂም በቀል አንያዝ ሁላችንም ነገ ከመቃብር በታች ነን፡፡ ይች
ምድር አትጥበበን ነገ ጥለናት የምንሄድ ሰዎች ነን፡፡ ሁላችን በፍቅር እንተያይ፡፡ አባቶቻችን ካህናት፣ ጳጳሳት ሆይ “አጽናኑ ሕዝቤን
አጽናኑ” ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሃዘናችንን አስረሱን፣ ኃጢአት በደላችንን በንሥሐ እጠቡት፣ ፍቅር ማጣታችንን በፍቅር ግዙት፣ መገዳደላችንን
ደም መፋሰሳችንን በመስቀላችሁ ሰላም አቁሙት፣ እናንተ የመጽናናት መንገድን ምሩን እኛም እስከ ገነት ድረስ እንከተላችሁ፡፡ ያለእናንተ
እኛ ምንድን ነን? ያለእናንተ ማን ሊያጽናናን ይችላል? ያለ እናንተ ማን ሊደርስልን ይችላል? ለሞቱት እረፍትን እና ምሕረትን ላሉት
ፍቅር አንድነትን ከፈጣሪ ዘንድ ለምኑልን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘለዓለም እንድንኖር እርዱን፡፡ ይህን ካላደረጋችሁ ግን በኃጢአት
ወድቀን “ህዝቤ” ያለንን “ህዝብህ” ብሎ ለጠላት አሳልፎ ይሰጠናል፡፡
ለጠላት “ህዝብህ” ከመባላችን በፊት እናንተ ከፈጣሪያችን ጋር አገናኙን አጽናኑን፡፡ አጽናኙ መንፈስ እስኪመጣልንም ድረስ በኢየሩሳሌም
እንጠብቃለን፡፡ “አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ኢሳ 40÷1
No comments:
Post a Comment