© መልካሙ በየነ
ጥቅምት 5/
2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ሰውየው መዛኝ ነው፡፡ የሚገርመኝ ግን እርሱ ራሱ የተመዘነ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ በእኛ አገር
እንዲህ ዓይነቱ አሠራር የተለመደ ብቻ ሳይሆን የተዋሐደ ነው፡፡ ሳትመዘን መመዘን ትችላለህ ያ ማለት እኮ ሳትማር ማስተማር ትችላለህ፣
ሳትሰለጥን ታሰለጥናለህ ማለት ነው፡፡ ሳይመዘን የሚመዝነው ሰውየ
“ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ይጮኸል፡፡ ይህን ጩኸቱን የሰማ ሰው ዳግም በዚያ በኩል የሚያልፍ አይመስለኝም፡፡ ሰውየው
ከሚጮኸው በላይ የምትጮኽ መሣሪያ ከሚዛኑ አጠገብ አለች፡፡ እርሷ ታዲያ መጮኋን አታቋርም ትላዝናለች፡፡
መዛኙ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ይጮኸል፡፡ አንድ ኩንታል ሊሞላው ጥቂት ኪሎዎች
የሚቀረው ሰውየ ራሱን ሊመዝን ተጠጋ፡፡ ባለሚዛኑ 50ዋ እንዳትቀርበት እንጅ ሰውየውን መመዘን አልፈለገም፡፡ ሚዛኑን የሚሰብርበት
ነው የመሰለው፡፡ ሆኖም ግን መዛኝ ነውና የውስጡን ስሜት ዋጥ አድርጎ የሰማይ ስባሪ የሚያህለውን ሰውየ ወደ ሚዛኑ እንዲወጣ ጠቆመው፡፡
መዛኙ አሁንም “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ይጮኸል፡፡ አንድ ቀጫጫ ሰው የመዛኙን ጩኸት ሰምቶ ሊመዘን ቀረበ፡፡ የሰማይ
ስባሪ የሚያህለው ሰውየ ሚዛኗ ላይ እንደቆመ ነው፡፡ ጎንበስ ብሎ ማነበብ ስላልቻለ “ስንት ኪሎ ነኝ” ብሎ መዛኙን ጠየቀው፡፡ መዛኙም
“ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” ነህ አለው፡፡ ሰውየው ተናደደ፡፡ እኔ ግን በመዛኙ አልፈረድኩበትም ምክንያቱም አፉ “ሚዛን በ
50 ሚዛን በ 50” ከማለት ውጭ ሌላ አልለመደለትምና ነው፡፡ ልማድ ክፉ ነው በጣም ክፉ በሽታ ነው፡፡ እንዲያውም ሰው ተጣልቶ
ሲሳደብም “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” የሚል ነው የሚመስለኝ፡፡ ልማድ በሽታ ነው ሲባል ብዙ ነገር ትዝ ይለኛል፡፡ ሲጋራ ማጨስ
ልማድ የሆነባቸው ሰዎች ሲጋራ ካላገኙ ያዛጋሉ፡፡ የሚገርመው ነገር የሲጋራ ጢስ ሆድ የሚሞላ አለመሆኑ ነው፡፡ ሰው ጢስ ቀረብኝ
ብሎ ሲያዛጋ ስታዩ “አይ ልማድ” ማለታችሁ አይቀርም፡፡ ጫት የሚቆረጥሙትንም እንዲሁ ነው የምታዘባቸው፡፡ ፍየሎቻችን የናቁትን ቅጠል
ሰዎች ሲያመነዥኩ ሳይ “አይ ልማድ፤ ልማድ እኮ ክፉ በሽታ ነው” እላለሁ፡፡ ወደ ነገሬ ልመለስና ሰውየው 96 ኪሎ ነው፡፡ ሚዛኗ
ሰውየውን የፈራችው ትመስላለች 96ን ጽፋ ትርገበገባለች፡፡ መዛኙ 96 ኪሎ ነህ አለው፡፡ ተመዛኙ ሰውየም ከሚዛኗ ከመቅጽበት ወርዶ
50 ሳንቲሙን ወርውሮለት ሄደ፡፡
ቀጭኑ ተመዛኝ ወደሚዛኑ ወጣ፡፡ መዛኙ “ሚዛን በ 50 ሚዛን በ 50” እያለ ደጋግሞ ይጮኸል፡፡ ቀጫጫው ሚዛኗ ላይ የወጣው በአንድ እግሩ ነው፡፡
ቀጫጫው በአንድ እግሩ እንደቆመ “መዛኝ ስንት ኪሎ ነኝ” አለው፡፡ መዛኙም 45 ኪሎ ነህ አለው፡፡ ከሚዛኗ ወረደ እና 15 ሳንቲም
ወረወረለት፡፡ መዛኙ ግራ ገባው “ምንድን ነው ይኼ” አለው ተመዛኙን፡፡ ተመዛኙም “የቅድሙ ትልቁ ሰውየ 96 ኪሎውን በ50 ሳንቲም
ተመዝኖ እኔ 45 ኪሎውን ለዚያውም በ1 እግሬ ቆሜ ተመዝኘ 15 ሳንቲም አነሰህ” አለ፡፡ መዛኙ በጣም ተበሳጨና “ቀጫጫ በል
354 ሳንቲም ጨምር” አለው፡፡ ተመዛኙም ያልሰማ መስሎ ትቶት ሊሄድ ሲል መዛኙ አንቆ ያዘው፡፡ ተመዛኙ “በአንድ እግሬ ቆሜ
45 ኪሎ ለተለካሁት እና በ2 እግሩ ቆሞ 96 ኪሎ ለተለካ ሰው እኩል ታስከፍላለህ እንዴ” አለው፡፡ መዛኙም “ስትፈልግ ተኝተህም
መመዘን ትችል ነበር እርሱ ያንተ ሂሳብ ነው የእኔ ሂሳብ ደግሞ 50 ሳንቲም ነው” አለው፡፡ ተመዛኙም ነገሩ ስለከረረበት ተጨማሪውን
35 ሳንቲም ወርውሮለት ሄደ፡፡
በአንድ ሚዛን ሁለት ክብደት ሲመዘን ሳይ ገረመኝ፡፡ እንዳትስቁብኝ ግን ሚዛን እንኳን ይህን
ሌላስ ይመዝን አይደል እንዴ ምን ያስገርምሃል እንዳትሉኝ፡፡ በሁለት እግሩ ቆሞ የተመዘነ እና በአንድ እግሩ ቆሞ የተመዘነ ሰው
እኩል ሂሳብ መክፈላቸው በጣም ያስገርማል እንጅ፡፡ በአንድ ሚዛን ስለተመዘኑ ብቻ እኩል ክፍያ መክፈላቸው ያስገርማል፡፡ በዚህ ህግ
መሠረት ሳይሆን ይቀራል ፍርድ የሚፈረደው፡፡ በአንድ ዓይነት ወንጀል ሳይሆን በአንድ ዳኛ ስለተዳኙ ብቻ እኩል መቀጣታቸው አያስገርምም፡፡
በሬ የሰረቀ እና መርፌ የሰረቀ ሰው እኩል ሲፈረድባቸው አይደንቅም፡፡ በእርግጥ ይኼ ሰማያዊ ፍርድ ስላልሆነ ፍትሐዊ ይሆናል ማለት
አይቻልም፡፡ በሥራ ቅጥርስ ገጥሟችሁ አያውቅም፡፡ በአንድ ተቋም ስለተማራችሁ ብቻ እኩል የምትቀጠሩበት ጉዳይ አይገርማችሁም፡፡
5 ዓመት 3 ዓመት ወይም 2 ዓመት የተማረ ሰው በአንድ ተቋም ስለተማሩ ብቻ እኩል ደመወዝ ሲከፈላቸው ይገርመኛል፡፡ ቢያንስ እኮ
ያጠናኸው የትምህርት መስክ እና ያስመዘገብከው ውጤት ግምት ውስጥ መግባት ነበረባቸው፡፡ ግን የለም!
በአንድ ሚዛን ተመዘን እንጅ የግድ እኩል ትከፍላለህ፡፡ በአንድ ዳኛ ተዳኝ እንጅ እኩል ይፈረድብሃል፣
በአንድ ሃኪም ታከም እንጅ አንድ አይነት መድኃኒት ይታዘዝልሃል፣ በአንድ ተቋም ተማር እንጅ እኩል ትቀጠራለህ፣ በአንድ መምህር
ተማር እንጅ እኩል ውጤት ታገኛለህ፡፡ ይኼ የተለመደ ሆኗል፡፡ በእርግጥ
አንድ ሚዛን ሁለት ክብደት መለካቱን ስመለከት ከዚህም ባለፈ ያየሁት ነገር አለ፡፡ ሁለት ሰዎች በአንድ ህግ እኩል ሳይሆኑ ሲቀሩ
ታያለህ፡፡ ለምሳሌ ለእኔ የሚሰራ ህግ ላንተ ላይሰራ ይችላል፡፡ እኔ በተዳኘሁበት ህግ አንተ ላትዳኝ ትችላለህ፡፡ ሰው የገደለ ወንጀለኛ
በሙሉ አንድ ዓይነት ፍርድ አይጠብቃቸውም፡፡ አንዳንዱ መግደልን እንደመብትም የተሰጠው ይመስላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ እድሜ ልኩን
እስር ቤት ይጣላል አንዳንዱም ከ10 ዓመት በኋላ ይወጣል ብቻ ይለኛኛል፡፡ በአንድ ወንጀል እኩል አለመዳኘት እንደዚህ ነው፡፡ አንድ
ሚዛን ሁለት ክብደት እንደለካው ማለት ነው፡፡ ብቻ ብዙ ነገር አለ እናንተም ጨምሩበት!!!!
No comments:
Post a Comment