© መልካሙ በየነ
መስከረም 25/
2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
“ሚጠት” መመለስ
ነው “ምጽአት” ደግሞ መምጣት ነው፡፡ መከራ፣ ስቃይ፣ እንግልት፣
ረሃብ፣ ጥም፣ እርዛት፣ ሰሚ ማጣት ያሰድዳል፡፡ መሰደድ ፍርሐት አይደለም፡፡
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አረጋዊው ዮሴፍን ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን
እና እናቱ ድንግል ማርያምን ይዘህ ወደ ግብጽ ሂድ ብሎታል፡፡ አምላክ
ሁሉን ማድረግ ይችላል፤ ንጉሡ ሔሮድስን በተቀመጠበት ዙፋን ላይ ጸጥ ማድረግ ይችላል፤ 14 እልፍ የቤተልሄም ሕጻናት እንዳይሞቱ
ማድረግ ይችላል ግን መከራ ሲመጣባችሁ ፈተና ሲገጥማችሁ ክፉ ንጉሥ ሲነሣባችሁ እኔ ያደረግሁትን አድርጉ ለማለት አርአያነቱን ለማሣየት
ተሰደደ፡፡ አሁን ወደ ግብጽ እየተሰደዱ ናቸው፡፡ የስደታቸው ምክንያት ደግሞ የክፉው ንጉሥ የሔሮድስ አሰቃቂ ግድያ ነው፡፡ ለዚህ
ነው መሰደድ ፍርሐት አይደለም ያልኩት፡፡ ሕጻኑ ያለጊዜው ደሙ አይፈስም ስለዚህ ነው መሰደድን የመረጠው፡፡ ሆኖም ግን ጊዜው በደረሰ
ጊዜ ደሙ የሚፈስበት ቀን ሲደርስ ራሱ በፈቃዱ ለገዳዮቹ እጁን ሰጥቷል፡፡ እዚህ ላይ የምንገነዘበው ነገር ለሚገድሉት እጁን ሰጠ
እንጅ ልግደላችሁ አላለም፡፡ ለዚህ ነው ክርስትና ውስጥ እንሞታለን እንጅ አንገድልም እንደማለን እንጅ አናደማም እንቆስላለን እንጅ
አናቆስልም የምንለው፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና በዚህ በዘመነ ሄሮድስ ሁለት ምርጫዎች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ የመጀመሪያው
በንጉሡ እጅ መሞት ሌላኛው ደግሞ መሰደድ ናቸው፡፡ እንግዲህ ሁለተኛው ምርጫ ነው ለአረጋዊው ዮሴፍ የተነገረው እርሱም እንደተነገረው
ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡ ከዚያም ምን ቢገዙ፣ ምን ቢነዱ፣ ምን ቢጨክኑ ከሞት እጅ ማምለጥ አይቻልምና ይህ ጨካኝ ንጉሥ ሔሮድስ ሞተ
ያን ጊዜ “ተመየጢ ተመየጢ ተመየጢ ሱላማጢስ” ተባለች፡፡ አወ አሁን በቤተልሔም መገደል የለም፣ ያ ጨካኙ ንጉሥ ከመቃብር በታች
ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተልሄም መመለስ አለባቸው “ሚጠት” ማለት ይህ ነው፡፡ ሰው የሚሰደደው አገሩን ጠልቶ አይደለም ችግር ሆኖበት
እንጅ፤ ስለዚህ ያ ችግር ሲፈታ መመለሱ አይቀርም፡፡ የንጉሡ ሞት ለሚጠት ዋዜማ ነበር፡፡
እስራኤላውያንም
በግብጽ የባርነት ታሪክ ውስጥ ብዙ እንደተቸገሩ እናውቃለን፡፡ ዛሬ “የግብጽ ፒራሚድ” እያልን ግብጽን የምናነሣት ያኔ ድሮ እስራኤላውያን
ራሳቸውን እንደ እባብ እየተቀጠቀጡ ባቦኩት ጭቃና ሲሚንቶ የተገነባ ነው፡፡ ራሄል የመውለጃዋ ቀን ደረሰ ነገር ግን ማንም ሊያሳርፋት
አልቻለም ነበር፡፡ ምጧ ደረሰ ጭቃ እያቦካች ነው፡፡ አሁንም እየተደበደበች ምጧን ዋጥ አድርጋ ጭቃ ታቦካ ጀመረች፡፡ አልቻለችም
እዛው ጭቃው ላይ ወለደች፡፡ ከዚያም ልጆችሽን ከጭቃው ጋር እርገጫቸው ደማቸው ጭቃችንን ያጠነክርልናልና ተባለች፡፡ አስቡት ይህን
ግፍ፡፡ ይህ ግፍ ለእስራኤላውያን “ሚጠት” ዋዜማ ነበር፡፡ እንባዋን ወደ ሰማየ ሰማያት ረጨች አምላክ እንባዋን ተቀበለ ድንቅ መሪ
የሆነውን ሙሴ አዘጋጀ ከዚያም ግብጽን ዳግም ባሪያ ሆነው ላይኖሩባት ተሰናብተው ወደ ርስት ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ ይህ የእስራኤላውያን
ሚጠት ነው፡፡
በተመሳሳይ ወደ
ፋርስ ባቢሎን በባርነት በተሰደዱ ጊዜ ኤርምያስ ሳይቀር አብሮ ተሰዷል፡፡ በዚህ ወቅት ሀገሪቱ ተፈታለች ሰው የሚባል ፍጡር ጠፍቶባታል፡፡
ይህ የሚሆነው ለ70 ዓመታት ያህል ነበር፡፡ ከዚህ ጥፋት በእግዚአብሔር ጥበብ የተሠወሩት የኤርምያስ ደቀመዛሙርት ባሮክና አቤሜሌክ
ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው ህዝብ ግን የአገሩን ጥፋት በዓይኑ ተመልክቷል፤በባርነት ተሰዷል፡፡ አቤሜሌክ ለድውያን የሚቀባ መድኃኒት ሊያመጣ
ተላከ ባሮክም መቃብረ ነገሥትን እንዲጠብቅ ተደረገ፡፡ የሚገርመኝ የአቤሜሌክ ጉዳይ ነው፡፡ መድኃኒቷን ቆርጦ ሲመጣ ደከመውና ከጥላ
ሥር አረፍ አለ በዚያው 66 ዓመት ተኛ ሲነቃ እንቅልፉ በደንብ አልለቀቀውም ነበር፡፡ ተነሥቶ መንገዱን ሊቀጥል ሲል መንገዱ ሁሉ
ጠፋበት አገሪቱ ጠፍታለች ሰው አይኖርባትም በኋላ ግን መልአኩ ከባሮክ ጋር አገናኝቶታል፡፡ ከዚያም መድኃኒቷን ለኤርምያስ በንስር
አሞራ ላኩለት፡፡ ያኔ ለሚጠት ዋዜማ ነበር 4 ዓመት ብቻ ነበር የቀራቸው፡፡
አገራችን እንግዳ
ተቀባይ፣ በማንም ወራሪ ጠላት ያልተንበረከከች የጀግኖች መፍለቂያ፣ የፍቅር አገር ናት፡፡ ለራበው የሚያበላ፣ ለጠማው የሚያጠጣ፣
ለበረደው የሚያለብስ፣ ለጠላት እጁን የማይሰጥ፣ ለማንም የውጭ ኃይል የማይንበረከክ ጀግና የሚፈልቅባት ቅድስና የማይጠፋባት፣ ጥበብ
የሚመነጭባት፣ ጠላት የሚያፍርባት፣ በገንዘብና በብልጭልጭ ነገር የማይታለል ህዝብ ያላት አገር ናት፡፡ ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ የመጣውን የጣሊያን ጦር በቆራጥ የአገር ፍቅር እንዴት
እንዳንቀጠቀጠ ህዝባችንን አይተናል፡፡ ዛሬ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ጀግና ተብሎ ማዕርግ እንደሚጨመርለት ያለ ወኔ አይደለም የጥንቱ
ጀግንነት፡፡ ዛሬ እንደ ሔሮድስ፣ እንደ ሂትለር እጃችን በደም ጨቅይቷል፡፡
ወንዞቻችን ደም እያጎረፉ ናቸው፣ ሴቶቻችን ተገዳዮችን እያረገዙ ናቸው፣ የቻሉት ስደትን መርጠው እየተሰደዱ ናቸው ያልቻሉትም በአገራችን
መቃብራችንን አድርግልን ብለው ፈጣሪያቸውን እየተማጸኑ ናቸው፡፡ ይህ ዘመን ለሀገራችን ከባድ የሀዘን፣ የዋይታ፣ የለቅሶ፣ የስቃይ
ዘመን እየሆነ ነው፡፡ ታዲያ “ሚጠት” ነው ወይስ “ምጽአት” ነው እየቀረበን ያለው፡፡
“ምጽአት” የጌታ
ለዘላለም ፍርድ ወደዚህ ዓለም መምጣት ነው፡፡ የምጽአት ዋዜማዎች በርካቶች ናቸው ከእነዚህ ውስጥ ግን በማቴ 24 ላይ “ጦርንም
የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ” ይላል፡፡ ዛሬ በእኛ ላይም እንደዚያ
እየሆነ ነው፡፡ ጦርን የጦርንም ወሬ በርቀት ሳይሆን በቅርበት እየሰማን ነው፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እየተነሣ
ነው፡፡ ለአገራችን አስከፊ የሚሆነው ህዝብ በህዝብ ላይ ከተነሣ ብቻ ነው፡፡ መንግሥት በመንግሥት ላይ፤ መንግሥት በሕዝብ ላይ ቢነሣ
ምንም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሚያመጣው ተጽእኖ ከባድ አይሆንም ህዝብ የሌለው መንግሥት ምንም ሊያደርግ ስለማይቻለው፡፡
ህዝብ በህዝብ ላይ ከተነሣ ግን ተጽእኖው ከበድ ያለ ይሆናል፡፡ ህዝብ በህዝብ ላይ ከተነሣ ቋንቋ፣ ቀለም፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ጎጥ፣ የደም
ዓይነት ሁሉ የጥላቻ ምንጭ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥትንም እንዳይቆም ያደርገዋል ሀገርንም ያፈራርሳል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን
“ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም
በመንግሥት ላይ ይነሣሉ” የሚለው ቃል የምጽአት ዋዜማ ነው፡፡ አገራችንን እንደቀደመ ክብሯ ለማስቀጠል ካስፈለገን ህዝብ በህዝብ
ላይ መነሣት የለበትም፡፡ በዘር፣ በጎሳ፣ በብሄር፣ በቋንቋ አንከፋፈል አንድ እንሁን፡፡ መከፋፈል ካለብን ወድደን ባመጣነው ነገር
ብቻ እንጅ ተፈጥሮ በቸረን ነገር ሊሆን አይገባውም፡፡ ከሆነ ዘር፣ ከሆነ ብሄር፣ ከሆነ እምነት፣ ከሆነ ቋንቋ ተናጋሪ በሆነ ብሔር
የተፈጠርነው ፈልገን አይደለም ይህ የፈጣሪ ሥራ ብቻ ነው፡፡ አገራችን ደግሞ በህብረ ብሔሯ ዓለምን የምታስቀና ናት፡፡ ስለዚህ ይህን
ህብረ ብሔር አንድ ማድረግ ካልቻልን መለያየታችን ሞታችንን ያፋጥነዋል፡፡
ለዚህ ነው አሁን በአገራችን እየተፈጸመ ባለው
ግድያ የእናቶች ለቅሶ ከፍ ብሎ ሲሰማ ሳስተውል ዋዜማነቱ ወደ ቀደመ ክብራችን ወደ ቀደመ ኃያልነታችን ወደ ቀደመ አልደፈርም ባይነታችን
ወደ ቀደመ ጀግንነታችን ልንመለስ ይሆን ወይስ “ጦርንም
የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ” እንዳለው ምጽአት ቀርቦ ይሆን ብየ
እንዳስብ የተገደድኩት፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ወይ ለ “ሚጠት” ወይ ለ “ምጽአት” ዋዜማ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አምላከ ቅዱሳን ለአገራችን
ሰላምን እንዲሰጥልን ሁላችንም እንጸልይ መፍትሔው ከፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የፈቃድ ጾም ቢሆንም ነገ መስከረም 26 ጀምሮ
የጽጌ ጾም ይጀመራል እስኪ ለዚሁ ዓላማ ብለን ዘንድሮ እንጹመው ሱባኤ እንያዝ፡፡ ሌላው እምነትም በራሱ ለዚሁ ብሎ በእምነት ሥርዓቱ
የሚገባውን ያድርግ፡፡
No comments:
Post a Comment