© መልካሙ በየነ
ኅዳር 21/
2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
በመጀመሪያ በሰላም በፍቅር በአንድነት ጠብቆ ለዚህ ለተቀደሰው ዕለት ያደረሰንን የፍጥረታት
ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን አምላካችንን አመሰግነዋለሁ፡፡ ይህች ዕለት የተከበረች እና የተቀደሰች ከፍ ከፍም ያለች ናት፡፡ ካህኑ ዘካርያስ
በቤተመቅደስ እንደ ፋና ስታበራ እመቤታችንን ተመልክቶባታል፡፡ ምንኛ የታደለ ካህን ነው? ቤተመቅደሳችንን አረከሰችብን ብለው ከቤተመቅደስ
ለማባረር ነገር የሚሸርቡ ካህናት በነበሩበት በዚያ ወቅት የእግዚአብሔር አገልጋይ ቅዱሱ ካህን አምላክን ያጠመቀውን ትልቅ ነቢይ
የወለደ ዘካርያስ እመቤታችንን ያከብራት እና ይገዛላት ይታዘዛትም ነበር፡፡ ይህ ካህን ከሴቶች ሁሉ የተለየ ድንቅ ነገር በእርሷ
እንደሚደረግ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለታል፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌ በእርሷ እንደሚከናወን ተረድቷል፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእውራን ብርሃናቸው፣ ለኃንካሳዎች
ምርኩዛቸው፣ ለማይሰሙትም የመስሚያ ጆሯቸው፣ ለማይናገሩትም ልሳናቸው መግባቢያቸው፣ ለተራቡት ምግባቸው፣ ለታመሙት መድኃኒታቸው፣
ለተቸገሩት ደራሻቸው፣ ለተጨነቁት አረጋጊያቸው፣ ለተሠበሩት ጠጋኛቸው ናት፡፡ በእውነት ማንም የማይመስላት ማንም የማይተካከላት ማንም
የማይደርስባት በማንም የማትመረመር ድንቅ እና ልዩ ፍጥረት ናት፡፡ በእግረ ኅሊናችን የዓለምን ዳርቻ ሁሉ ብናዳርስ፣ በክንፈ ኅሊናችን
ሰማየ ሰማያት ብንመጥቅ፣ ወደ ጥልቁ እመቀ እመቃት ብንወርድ አንደርስባትም፡፡
ድንግል ማርያም እናት ናት፡፡ እናትነቷ ግን በዘር በሩካቤ ለተወለደ
ህጻን አይደለም፤ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ያለ ዘር ያለ ሩካቤ በማይመረመር ምሥጢር ለወለደችው አምላክ ነው እንጅ፡፡ እርሷ ልጅ ተብላለች፡፡
ወለተ ዳዊት ወለተ ኢያቄም (የዳዊት የኢያቄም ልጅ) ብለናታል፡፡ እርሷስ በዘር በሩካቤ ከሃና እና ከኢያቄም የተገኘች ናት፡፡ እርሷስ
ልጅ ስትባል ብትቆይም እናት ለመባል በቅታለች፡፡ ድንግል ወእም (ድንግል እና እናት) ብለናታል፡፡ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ ቅዱሳን፣
ሊቃውንት ድንግል ማርያምን በልዩ ልዩ ምሳሌዎች እየመሰሉ አስረድተውናል፤ በተለያዩ ቃላት አመስግነዋታል፡፡ ከምስጋናቸውም በላይ
ስትሆንባቸው፤ የተደረገላትን ድንቅ ምሥጢርም ሲመረምሩ “ናርምም፤ ዝም እንበል” ይላሉ፡፡ አባ ሕርያቆስ እመቤታችንን የሚመስልበት
ምሣሌ ቢያጣ “በመኑ ወበአምሳለ መኑ ናስተማስለኪ፣ በምን እና በምን
ምሳሌ እንመስልሻለን” አለ፡፡ ይህ ቅዱስ አባት ምሳሌ አጣላት፡፡ ከፍ ብሎ በሰማይ ዝቅ ብሎ በምድር እንዳይመስላት የሰማይ እና
የምድርን ፈጣሪ ዘጠኝ ወር በማኅጸኗ ተሸክማዋለች፡፡ ፈጣሬ ኩሉ (የሁሉ ፈጣሪ እና አስገኝ) ጌታን በጭኗ ታቅፈዋለችና፡፡ በእውነት
በምን እንመስላታል?
ድንግል ማርያም እናት ተባለች፡፡ እናትነቷ ለዘለዓለም ልጅ ሲባል
ለሚኖረው አምላክ ነው፡፡ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነስቶ በተዋሕዶ ተወልዷል፡፡ እርሱ በዘመን
ብዛት አባት አይባልም፡፡ እኛ ልጅ ስንባል ብንኖር አባት ወይም እናት የምንባልበት ዘመን ይመጣል፡፡ እኛ ከእናት እና ከአባቶቻችን
ብንወለድ እና ልጆች ብንባልም ባል ወይም ሚስት አግብተን ትዳር መስርተን ልጆችን ወልደን ልጅ ከመባል አባት ወይም እናት ወደመባል
እንሸጋገራለን፡፡ አምላካችን ፈጣሪያችን ግን ለዘላለም ወልድ ሲባል ይኖራል፡፡ አስቀድሞ በማይመረመር ምሥጢር ከአብ ያለ እናት አሁን
ደግሞ ከድንግል ማርያም ያለ አባት እንበለ ዘርእ ተወለደ፡፡ በፊትም ከአብ ሲወለድ ወልድ (ልጅ) ነው ዛሬም ከእመቤታችን ሲወለድ
ወልድ (ልጅ) ነው፡፡ ዘመን ሲበዛ ወልድ (ልጅ) ወልድነቱ (ልጅነቱ) ተለውጦ አብ (አባት) አይሆንም፡፡ እመቤታችን ከሃና እና
ከኢያቄም ተወልዳ ልጅ ስትባል ብትቆይም በኋላ ግን እናት ተብላለች፡፡ አምላክ ግን በፊትም አሁንም ያው ወልድ ነው፡፡ በፊትም አሁንም
ወልድ (ልጅ) ለሚባል አምላክ ወልድ (ልጅ) ከመባል እናት ወደ መባል ለተሸጋገረችበት ምሥጢር ኅሊናችን እጹብ ድንቅ ይላል፡፡