© መልካሙ በየነ
ጥቅምት
22/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
የምበላው የምጠጣው የለኝም ለዚህም ነው አምላኬን የማላመሰግነው፡፡
አንዳንዱን በጥጋብ ብዛት እያዘለለ እኔን በረሃብ አለንጋ ይገርፈኛል
ለዚህም ነው “ተመስገን” የማልለው፡፡ እኔ የምኖርበት ጎጆ የለኝም፡፡ የቀን ፀሐይ የሌሊት ቁር ይፈራረቅብኛል ውሎ እና አዳሬ መንገድ
ዳር ነው፡፡ ያዘነ ይሰጠኛል ያላዘነም ይሰድበኛል በዚህ መልኩ ነው የምኖረው፡፡ መንገድ ዳር አላፊ እና አግዳሚውን ስለምን የምውል
ችግረኛ ነኝ ለዚህም ነው አምላኬን “ተመስገን” የማልለው፡፡ እኔ የምለብሰው የሌለኝ የፀሐዩ ሙቀት ያቃጠለኝ የሌሊቱ ቁር ያኮማተረኝ
የታረዝኩ ችግረኛ ነኝ፡፡ ሌላው ሦስት አራት ልብስ እየቀያየረ ባለበት ጊዜ፤ ጠዋት የለበሰውን ማታ ቀይሮ በሚወጣበት ጊዜ እኔ ግን
እርቃኔን እንደ ድንጋይ ብርድና ሙቀት ይፈራረቅብኛል ለዚህም ነው አምላኬን የማላመሰግነው፡፡ እኔ በየሰው ቤት እየዞርኩ ጭቃ የማቦካ
እንጨት የምፈልጥ ድንጋይ የምሰብር ቁፋሮ የምቆፍር የቀን ሰራተኛ ነኝ፡፡ እጀ እስኪያብጥ ድረስ አሠራለሁ ጉልበቴ እስኪዝል ድረስ
እሸከማለሁ ነገር ግን ኑሮየን ሊቀይር የሚችል ገንዘብ አላገኝም፡፡ ጠዋት በሠራሁበት ምሳ ከሠዓት በኋላ በሠራሁበት እራት እመገብበታለሁ፤
ኑሮየ ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ አንድ ቀን ሥራ ባቆም ማንም አያበላኝም፡፡ የማድርበት ቤት ደግሞ የለኝም በረንዳ ላይ ነው ወድቄ
የማድረው፡፡ ለዚህም ነው አምላኬን “ተመስገን” የማልለው፡፡
እኔ ጤና አጥቸ እንቅልፍ ተነሥቼ የምኖር በሽተኛ ነኝ፡፡ በየህክምና
ቦታው ተመላለስኩ መፍትሔ የለውም፤ በየፀበል ቦታዎች ሁሉ ተንከራተትኩ ምንም መፍትሔ አላገኘሁም፡፡ በባሕላዊ መንገድ ይፈውሳሉ ፍቱን
መድኃኒት አላቸው ከሚባሉ ባለመድኃኒተኞችም ዘንድ ተመላልሻለሁ፡፡ ነገር ግን ገንዘቤን ከመበተን ውጭ ምንም ትርፍ ነገር አላገኘሁበትም፡፡
ከአልጋ ጋር እንደ ትኋን ተጣብቄ መኖር ከጀመርኩ ረዥም ዘመን ሆኗል፡፡ አንድ ቀን ብሎ የፈጣሪየ እርዳታ አልመጣልኝም አንድ ቀን
እንኳ ከበሽታየ እንዳገግም ፈጣሪየ አላደረገም ለዚህም ነው የማላመሰግነው፡፡
እኔ በባእድ አገር ኑሮ አልሳካልኝ ብሎ የምኖር ስደተኛ ነኝ፡፡
ቋንቋቸውን አልችለውም ባሕላቸውን አልተላመድኩትም ምግባቸውን አልወደድኩትም፡፡ ነገር ግን የእንጀራ ጉዳይ ነውና በግድ እኖራለሁ፡፡
ገንዘቡ አልጠራቀምልህ ብሎኛል፤ ቤተሰቦቼን አሳልፍላቸዋለሁ ብየ ወጥቼ ራሴን እንኳ ማስተዳደር አልችል አልኩኝ፡፡ ቀን ከሌሊት ያዝዙኛል
እንቅልፍ የሚባል ነገር በዓይኔ ከዞረ ከሳምንት በላይ ሆኗል፡፡ አገሬ የምመለስበት ገንዘብ አላጠራቀምኩም ኑሮየ ከእጅ ወደ አፍ
ብቻ ነው፡፡ ሁሉ ነገር ለእኔ ባእዳ ነው፡፡ አገሬ መልሰኝ ብየ ፈጣየን ተማጸንኩት እርሱ ግን ይባስ ብሎ ለክፉ አሠሪዎች አሳልፎ
ሰጠኝ ለዚህም ነው አላመሰግንህም የምለው፡፡ በስደት አገር የተወኝ ለችግር የጣለኝ እርሱ ነው ታዲያ እንዴት አመሰግነዋለሁ?
ብዙ ችግር፣ ብዙ መከራ፣ ብዙ ፈተና አለብን፡፡ ፈጣሪ የፈጠረው
ፍጥረት ሁሉ አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ አንዱን ድሃ ሌላውን ሃብታም፣ አንዱን ቀይ ሌላውን ጥቁር፣ አንዱን የተማረ ሌላውን ያልተማረ፣
አንዱን ረዥም ሌላውን አጭር፣ አንዱን ጌታ ሌላውን ባሪያ፣ አንዱን መልካም ሌላውን መጥፎ ወዘተ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ፈጣሪ ሲፈጥረን
በተለያየ መልኩ አድርጎ ነው፡፡ አላውቅ ብየ እንጅ ለዚህ ነበር ምስጋና የሚገባው፡፡ እኔ ድሃ ካልሆንኩ ሌላው ሃብታም ሊባል አይችልም
በመካከላችን ያለውን ልዩነት እያየሁ ራሴን በተስፋ እንዳኖር ይረዳኛል፡፡ በበጎ ባስበው ኖሮ አምላክን ማመስገን የሚገባኝ እኔን
ተመጽዋች ሌላውን መጽዋች ስላደረገው ነበር፡፡ እምነት ካለኝ ብታመም ያድነኛል ምናልባት ዋጋ የሚያሰጠኝ ህመም ከሆነ ግን ተመስገን
ብለው ሲዖልን እንዳላይ ያደርገኛል፡፡ ኢዮብን ዘመዴ አደርገዋለሁ ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ስለሌለኝ ፈጣሪየን አላመሰግነውም የምለው
ለምንድን ነው? ገንዘብን መውደድ የይሁዳን ልብ አውሮ ፈጣሪውን በ30 ብር እንዲሸጥ ያደረገው እኮ ነው፡፡ ገንዘብ ቢኖረኝ ምናልባት
ፈጣሪየን አሳዝንበት ይሆናል እንጅ እንደ አብርሃም ፈጣሪየን አላስደስትበትም፡፡ የምበላው የምጠጣው አጣሁ ብየ ፈጣሪየን አላመሰግንም
ካልኩኝ ስበላ እና ስጠጣ ስጠግብ እንደምረሳው አውቃለሁ፡፡ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ መና ከደመና እየወረደላቸው ተመግበው
ውኃ ከጭንጫ አለት ላይ እየፈለቀ ጠጥተው ሲጠግቡ ፈጣሪያቸውን ረስተው ጣዖት አሠርተው ለጣዖት ተንበርክከዋል፡፡ ጥጋብ እንዲህ ፈጣሪን
ያስረሳል፡፡
No comments:
Post a Comment