© መልካሙ በየነ
ኅዳር 14/
2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ይህ ጾም የገና ጾም በመባልም ይጠራል፡፡ ነቢያት እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠውን ተስፋ እየጠበቁ
አምላክ ይወርዳል ይወለዳል ብለው የጾሙት ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም በሦስቱ ዘመናት ማለትም በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ እና በዘመነ
ሉቃስ ኅዳር 16 ይጀምርና ታህሳስ 29 ይፈሰካል፤ በዘመነ ዮሐንስ ግን ኅዳር 15 ቀን ጀምሮ ታህሳስ 28 ቀን ይፈሰካል፡፡ እንደዚህ
ሲሆን በአራቱም ዓመታት የጾሙ ቀናት 43 ይሆናል ማት ነው፡፡ ነገር ግን ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ኅዳር 15 የሚገባው ጾም ስለሚረሳ
ሁልጊዜ ኅዳር 15 ቀን ጾሙ ይጀምራል፡፡ በዚህም የተነሣ በሦስቱ ዘመናት 44 ቀናት ይሆናል በዘመነ ዮሐንስ ግን 43 ቀናት ይጾማል፡፡
በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የጾሙ ቀናት በ 1 ቀን ይቀንሳል፤ በሦስቱ ዘመናት 44 ቀናትን የምንጾመው ለጾም ማድላት ተገቢ ስለሆነ
ነው፡፡
ስለዚህ ነቢያቱን አርአያ አብነት አድርገን እግዚአብሔር በተስፋ በበረከት ያኖረን ዘንድ፣ በጎውን
የልቦናችንንም መሻት ሁሉ ይፈጽምልን ዘንድ፣ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን በቃሉ እንኖር ዘንድ እንጾመዋለን፡፡ ይህ ጾም በፍትሐ ነገሥት
አንቀጽ 15 ቁጥር 568 ላይ “ከእነርሱም የሚያንስ እንደ ረቡዕና እንደ ዓርብ የሚሆን አለ፡፡ ይኸውም ከልደት አስቀድሞ የሚጾም
ጾም ነው፡፡ መጀመሪያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የገና በዓል ነው” በማለት መዝግቦት እናገኘዋለን፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ ወገኖች
የጾሙን መግቢያ እና መውጫ ሲከራከሩበት እናያለን፡፡ ነገር ግን ይህ ቀኖና ቤተክርስቲያን እንጅ ዶግማ ባለመሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ
ሊሆን አይገባውም፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔርን በማሰብ ወደ ፍቅር ተመልሰን ለጾም በማድላትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በማሰብ በፍቅር
እንድናደርገው አባቶች ይመክሩናል፡፡ ስለዚህ በተሠራልን ሥርዓት እንመራ ዘንድ እመክራለሁ፡፡
በዚህ ጾም የሚነሣው መሠረታዊ ጉዳይ ነቢያቱ ዐርባ ቀናትን ብቻ ነው የጾሙት ይህ በትርፍነት
የተጨመረው ዐራት ወይም ሦስት ቀን ከየት መጣ የሚል ነው፡፡ ነቢያቱ አርባ ቀናትን ጾሙ ስንል ኅዳር 19 ቀን ጀምረው ታህሳስ
29 ላይ ጾሙን ፈጸሙ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አኛ ኅዳር 15 ቀን ጾሙ ይጀምራል እንላለን ይህ አይጣላምን ቢሉ አይጣላም፡፡ ለዚህ
ማስረጃችን፡-
1ኛ.
ከላይ እንዳየነው ፍትሐ ነገሥቱ የዚህን ጾም መግቢያ ሲገልጽ የኅዳር እኩሌታ ስላለ ነው፡፡ የህዳር እኩሌታ ደግሞ ህዳር 15 እንጅ
ህዳር 19 አይደለም፡፡ 2ኛ. ስንክሳሩ ኅዳር 15 “ወበዛቲ ዕለት ጥንተ ጾመ ስብከተ ጌና ዘውእቱ ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ
ሎቱ ስብሐት ዘሠርዕዎ ክርስቲያን ያዕቆባውያን ዘግብጽ ሣህሉ ወምሕረቱ የሃሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን፤ በዚችም ቀን የስብከተ
ጌና ጾም መጀመሪያ ነው፡፡ ይህም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተወለደበት በግብጽ የሚኖሩ ያዕቆባውያን የሠሩት ነው፡፡
ይቅርታው ቸርነቱ ከእኛ ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን” በማለቱ የህዳር እኩሌታ የሚለውን ኅዳር 15 ነው እንላለን፡፡
3ኛ.
ሐዋርያው ፊልጶስ ኅዳር 16 በሰማእትነት ካሳረፉት በኋላ ሥጋውን ሊያቃጥሉ ሲነሡ መልአከ እግዚአብሔር ሥጋውን ሰወረባቸው፡፡ ከዚህ
በኋላ ደቀመዛሙርቱ ከዕለቱ ጀምረው 3 ቀናትን እንደጾሙ በኅዳር
18 ሥጋውን ሰጣቸውና ቀበሩት፡፡ ስለዚህም ሦስቱ ጾም ጾመ ፊልጶስ ተብሎ ተጨመረ፡፡
4ኛ. በዓለ ልደት ረቡዕና ዓርብ ቢውል ይበላበታልና
ለዚያ ማካካሻ ወይም ምትክ የምትሆን ጾም የገሐድ ጾም አንድ ቀን ከጾመ ፊልጶስ በፊት ተጨመረችና ኅዳር 15 ቀን እንዲጾም አዘዙን፡፡
ጌታ የጾመው ጾም ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ሆኖ ሳለ 55 ቀናትን እንደምንጾመው ያለ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል
የመጨረሻውን ሳምንት ደግሞ የሕማማት ሳምንት በማለት እንደምንጾመው ሁሉ ይህንንም እንዲሁ አደረግን፡፡ ይህም የአባቶቻችን ትእዛዝ
የአባቶቻችን ሥርዓት ነውና እኛም ተቀበልነው፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው በጾም ምክንያት ክርክር ቢነሣ መጾም ከመብላት እጅግ
ይሻላል እንዳሉን እንጾመው ዘንድ ይገባናል፡፡
No comments:
Post a Comment