Friday, November 11, 2016

“ሁለቱ የሰይጣን ቀስቶች”

© መልካሙ በየነ

ኅዳር 2/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ዲያብሎስ ጥንተ ጠላታችን ነው፡፡ በአዳምና በሔዋን ላይ መርዙን ረጭቶ ከተድላ ቦታቸው ከገነት አስወጥቷቸዋል፡፡ ይህ ጠላት ዛሬ ድረስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቀስቱን ይወረውርብናል፡፡ ከቀስቱ ማምለጥና አለማምለጥ ግን በራሳችን ብርታትና ድክመት የተወሰነ ነው፡፡ ሰይጣን በዋናነት ሁለት ቀስቶችን ይወረውርብናል፡፡ የሚገርመው ነገር አንዱን ቀስት ስታመልጡ የውጊያ ስልቱን ቀይሮ በሌላ ቀስት መጠቀም እና ማጥቃት መቻሉ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ሰይጣንን እንደ ቁራ ጥቁር፣ ጥርሱ የገጠጠ፣ ዓይኑ የፈጠጠ፣ ጥፍሩ የዘረዘረ ወዘተ ስለሚመስለን ጸአዳ ሆኖ በውበት አምሮና ደምቆ ሲመጣ እንታለላለን፡፡  ለመሆኑ ሰይጣን የሚጠቀማቸው ቀስቶች ምንድን ናቸው?

እኛን ለማጥቃት እና ለመማረክ ሰይጣን በዋናነት ሁለት ቀስቶችን ይጠቀማል፡፡ እነዚህንም እንደሚከተለው እንዘረዝራለን፡፡
1.   ጽድቅ እንዳትሠራ ማድረግ፤ ሰይጣን የጽድቅ ሥራ ሁሉ ጠላት ነው፡፡ ምክንያቱም ጽድቅ አይስማማውምና ነው፡፡ ሰይጣን የሚችለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ ከጽድቅ ሥራ ያርቅሃል፡፡ አንተ በነፍስህ ተገድደህ ጽድቅ ልትሠራ ስትሞክር እርሱ ሥጋህን ተጠቅሞ ወደ ኃጢአት ይመራሃል፡፡ ስለዚህም ሰይጣን እንዳትጾም፣ እንዳትጸልይ፣ እንዳትሰግድ፣ እንዳትመጸውት፣ እንዳትራራ፣ ህግጋተ እግዚአብሔርን እንዳትጠብቅ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዳታነብ፣ ቅዱሳት መካናትን እንዳትሳለም፣ ንስሐ እንዳትገባ፣ ሥጋ ወደሙን እንዳትቀበል፣ እንዳታስቀድስ፣ እንዳትዘምር፣ ድሆችን እንዳትረዳ፣ የተራቡትን እንዳትመግብ፣ የታሠሩትን እንዳትጠይቅ፣ የታመሙትን እንዳትጎበኝ፣ ወንጌልን እንዳትማር እና እንዳታስተምር፣ ቅዱሳንን አማላጆቼ እንዳትል፤ በእግዚአብሔር ህልውና እንድትጠራጠር፣ ጉቦ እንድትቀበል፣ በአራጣ እንድታበድር፣ በሃሰት እንድትመሰክር ወዘተ ያደርግሃል፡፡ የቅድስና ሥራ የሚባል ነገር እንዳትሠራ ሰይጣን ቀስቱን ይወረውርብሃል፡፡ አንተም ቀስቱን መመከት ካልቻልክ ዕድሜ ልክህን የጽድቅ ሥራ ሳትሠራ ትኖራለህ፡፡ ነገር ግን ቀስቱን የመመከት አቅም ኖሮህ ሰይጣንን ማሳፈር ከቻልክ ወደ ጽድቅ መንገድ እንደገባህ ታውቃለህ፡፡ ሆኖም ግን ከሰይጣን ቀስት አሁንም ቢሆን አታመልጥም፡፡ ጽድቅ እንዳትሠራ ከሚያደርግህ ጠላት ጋር ተዋግተህ ማሸነፍ ከቻልክ ሰይጣን ቀስቱን ይቀይራል፡፡ ምክንያቱም ጽድቅን ለመሥራት ቆርጠሃልና፡፡ ጽድቅን ለመሥረት ከቆረጥክ ያን ጊዜ ሰይጣን በሌላ ቀስት ይዘጋጅና ይመጣሃል፡፡ እርሱም ሁለተኛው ቀስት ሲሆን በውስጡ ሁለት የውጊያ ስልቶችን የያዘ ነው፡፡
2.  ዋጋ እንዳታገኝበት ማድረግ፤ ጽድቅን እንዳትሠራ ታግሎህ አንተ ግን አልሸነፍም ብለህ የሰይጣንን ምክር አልሰማም ካልክ ሰይጣን በዚህኛው ቀስት ሊያጠቃህ ይሞክራል፡፡ አሁን ሰይጣን ጽድቅ እንዳትሠራ ማድረግ ላይ ተስፋ ቆርጧል፡፡ ስለዚህ በምትሰራው የጽድቅ ሥራ ዋጋ እንዳታገኝ ማድረግ ይጀምራል፡፡ ይህንንም ቀስት የሚወረውርባቸው ሁለት ስልቶች አሉት፡፡ እነዚህም፡-
v  ባለህ ማስቀጠል፤  ሰይጣን በምትሠራው ሥራ ዋጋ እንዳታገኝበት እና ተስፋ የምታደርጋትን ቦታ እንዳትወርስ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ያለው ምርጫ የጀመርካትን ነገር ሳታሳድግ ሳታጎለምስ በዚያው እንድትቀጥል ማድረግ ነው፡፡ ጾም፣ጸሎት፣ስግደት፣ ምጽዋት ወዘተ ማድረግን በትንሹ እና በጥቂቱ ጀምረሃል፡፡ ነገር ግን በዚሁ በጥቂቱ በጀመርከው የጽድቅ ሥራ ብቻ እንድትቀጥል ያድርግሃል፡፡ ለምሳሌ ጾም ስትጀምር እስከ 6 ሰዓት ድረስ ብቻ ከሆነ የምትጾም ሕጉ እስከ 9 እና ከዚያም በላይ እንደሆነ እያወቅህ ከዚህ ሰዓት በላይ ማለፍ እንዳትችል ያደርግሃል፡፡ እዚህ ላይ የጀመርካቸውን የጽድቅ ሥራዎች ሕጉ ከሚለው በታች እንድትሠራ በማድረግ ነው የሚፈትንህ፡፡ ንስሐ ለመግባት ቆርጠሃል በቃ በዚህ እንደማይፈትንህ አርግጠኛ ሆነሃል፡፡ ነገር ግን ንስሐ ስትገባ ወይ ከባድ ኃጢአት የምትለውን እንዳትናዘዝ ያደርግሃል አለበለዚያም ንስሐህን በቁርባን እንዳትደመድም ያደርግሃል፡፡ ጸሎት ላይም እንዲሁ ስትጀምር ውዳሴ ማርያምን በመጸለይ ከጀመርህ በቃ ከዚህ ሌላ ጸሎት እንደሌለ አድርጎ በዚሁ ጸሎት ብቻ ያስቀጥልሃል፡፡ ያውም በተመስጦ በተሰበሰበ ኅሊና ያይደለ ቃሉን በማነብነብ ብቻ እንድትጸልይ ያደርግሃል፡፡ በአጠቃላይ እዚህ ላይ ቅድስናን በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ በትንሹ ከህጉ በታች በሆነ መልኩ ከተሰማራህ በኋላ በዚያው ከህጉ በታች እንድትቀጥል በማድረግ ዋጋ ማሳጣት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ብዙ ዘመናትን ካቆየህ በኋላ አንተው ተሰላችተህ ከዚህ ሥራህ እንትሸሽ ያደርግሃል፡፡ ዋናውም ዓላማ ከጽድቅ ሥራ ማራቅ ነውና፡፡
v  ከንቱ ውዳሴን መጨመር፡- ሰይጣን ጽድቅን እንዳትሠራ ከታገለህ በኋላ በዚያ ከተሸነፈ በጀመርካት ትንሽየ ነገር በዚያው እንድትቀጥል ያደርግሃል፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ እንድትተዋት ያደርግሃል፡፡ ነገር ግን አልተወውም ብለህ የጽድቅ ሥራህን እያበዛህ ስትሄድ ከንቱ ውዳሴ የተባለውን አረም ይዘራብሃል፡፡ ከዚያም ሳትሠራ ሁሉ ሠራሁ ማለትን ያስጀምርሃል፡፡ ከእኔ በላይ ጿሚ፤ ከእኔ በላይ ሰጋጅ፤ ከእኔ በላይ ቆራቢ፤ ከእኔ በላይ መጽዋች፤ ከእኔ በላይ ሰባኪ፤ ከእኔ በላይ ዘማሪ፣ ከእኔ በላይ ንስሐ ገቢ፣ ከእኔ በላይ አገልጋይ ወዘተ ማለት ያስጀምረናል፡፡ ከዚያ በኋላ የቅዱሳኑን ገድል ሳይቀር መናቅ ትጀምራለህ፡፡ ከዚሁ ጋር ትእቢት ይይዝሃል፡፡ በቃ ሁሉን ነገር ከእኔ በላይ ለኃሳር ነው ማለት ትጀምራለህ፡፡ ከዚህ በኋላ የመናገር ሱስ ይይዝሃል፡፡ የሰራኸውንም ያልሰራኸውንም እየቀጣጠልህ እየጨማመርህ ማውራትን ትለምዳለህ፡፡ ለታይታ እና ለማስመሰል መባከን ትጀምራለህ፡፡ መለከት በፊቴ ካልተነፋልኝ ከበሮ ካልተደለቀልኝ ማለትን ትጀምራለህ፡፡ መድረኩን ይዘህ ማይኩን ጨብተህ ቅዱሳን እንዲህ ተጋደሉ ማለቱን ትዘነጋውና እኔ እንዲህ አድርጌ እንዲህ ፈጥሬ ወዘተ ማለት ትጀምራለህ ፡፡ አገልግሎትህ በሙሉ ራስህን በማስተዋወቅ ላይ የተጠመደ ይሆናል፡፡

ሰይጣን ጽድቅን እንዳትሠራ ማድረግ አልችል ካለ ያለው ምርጫ ወይ ባለህበት ማስቆም ነው አልያም ከንቱ ውዳሴን ማምጣት ነው፡፡ ስለዚህ ሰይጣንን ድል ነስቸዋለሁ ብለን ልንናገር የምንችልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም ማለት ነው፡፡ ሰይጣንን ድል መንሳታችንን ማረጋገጥ ያለብን በጌታ ፍርድ ቆመን “ኑ የአባቴ ቡሩካን…” የሚለውን አጥንት አለምላሚ ቃል ከሰማን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በየትኛው አቅማችን በየትኛው ቅድስናችን አፋችንን ሞልተን ሰይጣንን ድል እንደነሳነው እንናገራለን፡፡ ስለዚህ ከሰይጣን ፈተና ማምለጥ አይቻልምና የትግል ስልታችንን እንደአመጣጡ መቀያየር ተገቢ ነው፡፡ 

No comments:

Post a Comment