Monday, July 8, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 130

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፳፯።
                    ******
፳፭፡ ወአውሥኡ ኵሉ ሕዝብ ወይቤሉ ደሙ ላዕሌነ ወላዕለ ውሉድነ፡፡
                    ******
፳፭፡ ደሙ በእኛም በልጅ ልጆቻችንም ይሁን አሉ፤
(ሐተታ) እንዲህ ብለው የተናገሩበት አንደበታቸው የሚሸት የሚከረፋ ሁኑዋል ልጆቻቸውም ወንድ የሆነ እንደሆነ በእጁ ደም ጨብጦ በአፉ ደም ጎርሶ የሚወለድ ሁኑዋል። ሴት የሆነች እንደሆነ በተፈትሆ የምትወለድ ሁናለች።
                    ******
፳፮፡ ወእምዝ አሕየወ ሎሙ በርባንሃ።
                    ******
፳፮፡ ከዚህ በኋላ በርባንን ፈታላቸው።
ወቀሠፎ ለእግዚእ ኢየሱስ ወመጠዎሙ ይስቅልዎ።
ጌታን ገርፎ ስቀሉ ብሎ ሰጣቸው።
(ሐተታ) ካልቀረስ በምር ደስ ይበላቸው ብሎ።
አንድም ራርተው ይተውታል መስሎት።
አንድም ወመጠውኩ ዘባንየ ለቅሥፈት ያለው ትንቢት ሊደርስ ሊፈጸም።
አንድም ዲያብሎስ የአዳምን ዘባነ ልቡናውን እየገረፈ ገሃነም አውርዶት ነበርና ለዚያ ካሳ ሊሆን፡፡
አንድም በጌታ የግፍ ድርብ ይደረግበታልና ለልማዱ የሚሰቀል አይገረፍም የሚገረፍ አይሰቀልም ነበር። እሱን ግን ገርፈው የሚሰቅሉት ነውና።
                    ******
ዘከመ ተሣለቁ በላዕለ ኢየሱስ።
፳፯፡ ወእምዝ መስተራትዓተ ሐራ ነሥእዎ ለእግዚእ ኢየሱስ እምውስተ ዓውድ ወወሰድዎ ኀበ ምኵናን። መዝ ፳፩፥፲፯። ማር ፲፭፥፲፮።
                    ******
፳፯፡ ከዚህ በኋላ ጭፍራውን የሚሠሩ የሚያቅናኑ ከአደባባይ ወደሚፈረድበት ቦታ ይዘውት ሄዱ።
(ሐተታ) ቤተ አንሳ ቤተ አይጥ የሚባሉ ሰቃይ ቈራጭ ባለወጎች በቤተ መንግሥት እንዳሉ።
ወአስተጋብኡ ኵሎ ሠርዌ ሐራ
አለቆች ጭፍራቸውን ሰበሰቡ፡፡
አንድም ኵሎ ሠርዌ ሐራ ጭፍሮች አለቆችን።
አንድም ወአስተጋብኡ ኵሎ ሠርዌ ሐራ ብለህ አናበህ ጭፍሮች ያሏቸው አለቆች ሕዝቡን ሰበሰቡ።
ወሰለብዎ አልባሲሁ።
ልብሱን ገፈፉት።
(ሐተታ) የአዳም ልጅነት እንደሄደበት ያጠይቃል።
                    ******
፳፰፡ ወአልበስዎ ከለሜዳ ዘለይ።
                    ******
፳፰፡ ቀይ ግምጃ አለበሱት። ደምህ ይፈሳል ሲሉ።
አንድም ደማችንን በአርባ ዘመን በጥጦስ ታፈሰዋለህ ሲሉ።
                    ******
፳፱፡ ወጸፈሩ ሐራ አክሊለ ዘሦክ ወአስተቀጸልዎ ዲበ ርእሱ። ዮሐ ፲፱፥፪።
                    ******
፳፱፡ ጭፍሮች የእሾህ አክሊል ታተው ደፉለት።
(ሐተታ) አነገሥንህ ብለውታልና በፍና ተሣልቆ።
አንድም ወወደዩ ጌራ መድኃኒት ዲበ ርእሱ በአክሊል ዘአስተቀጸለቶ እሙ ያለው ትንቢት ሊደርስ ሊፈጸም ድርሳነ መድኃኔ ዓለም ሽህ ጥቃቅን ሰባ ታላላቅ እሾህ ያለው የብረት ዘውድ ነው ይላል፡፡ እንደ ምን ነው ቢሉ ነገር እንደዚህ ነው ያስ ቢሆን ኢትስብሩ ዓፅሞ ያለው በፈረሰ ነበር፡፡
ወአስተአኃዝዎ ህለተ ውስተ የማኑ።
በቀኝ እጁ ዘንግ አስያዙት አነገሥንህ ብለውታልና በፍና ተሣልቆ
አንድም ብርዓ ይላል አብነት፡፡ ብርዕ አስያዙት ሥራ ፈት ነህ ሲሉ፡፡ ጽሕፈትንማ ርእሰ ጥበባት እንጅ ይለዋል ብሎ ኃጢአታችንን በፍዳ ታጽፍብናለህ ሲያሰኛቸው ነው፡፡
ወአስተብረኩ ቅድሜሁ፡፡
ሰገዱለት፡፡
ወተሣለቁ ላዕሌሁ
ዘበቱበት፡፡
ወይቤልዎ በሀ ንጉሠ አይሁድ፤
የአይሁድ ንጉሣቸው ቢሰኛህን ጠበኛህን አያውለው አያሳድረው አሉት፡፡ ከእነሱ ሌላ ቢሰኛ ጠበኛ አለውን አያውለን አያሳድረን ሲያሰኛቸው ነው።
                    ******
፴፡ ወይወርቁ ላዕሌሁ።
                    ******
፴፡ በፊቱ ተፉበት።
(ሐተታ) እንዳለፈው።
ወነሥኡ ህለተ ወኰርዕዎ ርእሶ።
ያስያዙትን ዘንግ ተቀብለው ራሱን መቱት፡፡
(ሐተታ) እንዳለፈው፡፡
                    ******
፴፩፡ ወተሣሊቆሙ ላዕሌሁ ሰለብዎ ውእተ ከለሜዳ ዘለይ፡፡
                    ******
፴፩፡ ከዘበቱበት በኋላ ያለበሱትን ቀይ ግምጃ ገፈፉት።
ወአልበስዎ አልባሲሁ።
የጥንት ልብሱን አለበሱት የአዳም ልጅነት እንደተመለሰለት ያጠይቃል።

ወወሰድዎ ይስቅልዎ።
ሊሰቅሉት ይዘውት ሄዱ።
                    ******
ወእንዘ ይወጽኡ ረከቡ ብእሴ ቀሬናዊ ዘስሙ ሰምዖን እትወቶ እምሐቅል። ማር ፲፭፥፳፩፡፡ ሉቃ ፳፫፥፳፮።
                    ******
፴፪፡ ሊሰቅሉት ይዘውት ሲሄዱ ስምዖን የሚባል የቀራንዮ ሰው ከተሠወረበት ሲመለስ አገኙ፤
ወአበጥዎ ይፁር መስቀሎ፡፡
መስቀሉን ይሸከም ዘንድ ጎተቱት
(ሐተታ) ነገር ፈርቶ ተሰውሮ ውሏል ነገር ተፈጽሟል ብሎ ሲወጣ አገኙት አንተም የእሱ ወገን ነህ መስቀሉን ተሸከም ብለው አሸክመውታል፡፡ ምሥጢሩ ግን ጌታ ከበረከተ መስቀሉ እንዳሳተፈው ያጠይቃል፡፡
                    ******
ወበጺሖሙ ብሔረ ዘስሙ ጎልጎታ ዘበትርጓሜሁ ቀራንዮ። ማር ፲፭፥፳፪። ሉቃ ፳፫፥፴፫፡፡ ዮሐ ፲፱፥፲፯።
                    ******
፴፫፡ በአንዱ ልሳን ቀራንዮ ወደሚሉት ጎልጎታ በደረሱ ጊዜ።
                    ******
፴፬፡ ወወሀብዎ ይስተይ ወይነ ወሐሞተ ድሙረ
                    ******
፴፬፡ ሐሞት የተቀላቀለበት ወይን ይጠጣ ዘንድ ሰጡት፡፡
ወጥዒሞ ዓበየ ሰትየ።
ቀምሶ አልጠጣም አለ።
                    ******
ዘከመ ተሰቅለ አ.የሱስ
፴፭፡ ወእምዝ ሰቀልዎ፡፡ ማር ፲፭፥፳፬፡፡ ሉቃ ፳፫፥፴፬። ዮሐ ፲፱፥፳፫፡፡ መዝ ፳፩፥፲፱።
                    ******
፴፭፡ ከዚህ በኋላ ሰቀሉት።
ወተካፈሉ አልባሲሁ እንዘ ይትዓፀዉ።
ልብሱን በዕፃ ተካፈሉ፡፡ በከመ ጽሑፍ ወተካፈሉ አልባስየ ለርእሶሙ ወተዓፀዉ ዲበ አራዝየ ተብሎ በነቢይ እንደ ተጻፈ፡፡
                    ******
፴፮፡ ወነበሩ የዓቅብዎ ህየ
                    ******
፴፮፡ ሲጠብቁት ዋሉ፡፡
                    ******
፴፯፡ ወአንበሩ መልዕልተ ርእሱ ጽሒፎሙ መጽሐፈ ጌጋዩ ዘይብል ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሦሙ ለአይሁድ፡፡
                    ******
፴፯፡ የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሣቸው ነው የሚል በደሉን የሚነግር ደብዳቤ ከራሱ በላይ ከመስቀሉ ትርፍ ጠርቀው ተውት፣
                    ******
፴፰፡ ወእምዝ ሰቀሉ ምስሌሁ ፪ተ ፈያተ፡፡
                    ******
፴፰፡ ከዚህ በኋላ ሁለት ወንበዶች ከእሱ ጋራ ሰቀሉ፡፡
አሐደ በየማኑ
አንዱን በቀኙ
ወአሐደ በጸጋሙ
አንዱን በግራው፡፡ አነገሥንህ ብለውታልና በፍና ተሣልቆ
(ሐተታ) ቀኝ አዝማችና  ግራ አዝማች ቢትወደድ ግራ ቢትወደድ ሾምንልህ ሲሉ፡፡
አንድም ለማሳሳት በቀኝ በግራ የመጣው ያ ምንድ ነው፤ ወንበዴ ይሉታል፡፡ ያሳ የመከከለኛው ይላል ያስ ከዚህን ልዩ ነው ለማለት፡፡
አንድም ተኆለቈ ምስለ ጊጉያን ያለው ትንቢት ሊደርስ ሊፈጸም፤ ይህንም ሊቁ ከመ ይደምረነ ምስለ ነፍሰ ጻድቃን ብሎ ተርጕሞታል ምሥጢሩን ግን እኛን ኃጥአንን በግራ ታቆመናለህ ሲያሰኛቸው ነው፣
                    ******
፴፱፡ ወእለሂ የኃልፉ ይጸርፉ ላዕሌሁ እንዘ የሐውሱ ርእሶሙ
                    ******
፴፱፡ የሚያልፉ የሚያገድሙት ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበር፡፡
                    ******
፵፡ ወይብሉ ኦ ዘይነሥቶ ለቤተ መቅደስ ወየሐንፆ በሣልስት ዕለት አድኅን ርእሰከ። ዮሐ ፪፥፲፱፡፡
                    ******
፵፡ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስተኛው ቀን እሰራዋለሁ የምትል ራስክን አድን እያሉ።
እመሰ አማን ወልደ እግዚአብሔር አንተ ረድ እመስቀልከ
የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ከመስቀልህ ውረድ።
                    ******
፵፩፡ ወከማሁ ሊቃነ ካህናት ይሣለቁ ምስለ ጸሐፍት ወሊቃናት።
                    ******
፵፩፡ እኒያ እንደሰደቡት ሊቃነ ካህናትም ከጸሐፍትና ከአለቆች
ጋራ ሰደቡት።
                    ******
፵፪፡ እንዘ ይብሉ ባዕደ ያድኅን ወርእሶ ኢይክል አድኅኖ፡፡ ማቴ ፪፥፲፰፡፡
                    ******
፵፪፡ ሌላውን ያድናል ራሱን ማዳን አይቻለውም እያሉ።
እመሰ ንጉሠ እስራኤል ውእቱ ለይረድኬ ይእዜ እምነ መስቀሉ ንርአይ ወንእመን ቦቱ።
የእስራኤልስ ንጉሥ ከሆነ ከመስቀሉ ይውረድና አይተን እንመንበት።
(ሐተታ) ወርዶም ቢሆን ፈርቶ ነው ባሉ ነበር እንጂ ባላመኑትም ነበር፡፡ ሶበሰ ወረደ እግዚእነ እምነ መስቀሉ እመርሀ ከመ ውእቱ ፈርሀ እሞት እንዲል፡፡
                    ******
፵፫፡ እመሂ ተአመነ በእግዚአብሔር ናሁ ይእዜ ያድኅኖ። መዝ ፳፩፥፰።
                    ******
፵፫፡ በእግዚአብሔር ከታመነ ማለት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ እነሆ ዛሬ ያድነው።
አመ ይፈቅዶ።
ስንኳን ይወልደው ይወደው እንደሆነ።
እስመ ይብል ወልደ እግዚአብሔር አነ።
የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላልና።
                    ******
ወከማሁ ፈያትኒ እለ ተሰቅሉ ምስሌሁ ይዘነጕግዎ፡፡
                    ******
፵፬፡ እነዚያ እንደሰደቡት፤ ከእሱ ጋራ የተሰቀሉ ወምበዶችም ሰደቡት፤ ፈያታይ ዘየማንም ቢሉ ፀሐይን አይቶ እስኪመለስ ድረስ ጥቂት ጥቂት ያደራርግ ነበር።
                    ******
በእንተ ፃዕሩ ወሞቱ ለኢየሱስ
፵፭፡ ወእምስሱ ሰዓት ጸልመ ኵሉ ዓለም እስከ ተሱዓት ሰዓት፡፡
፵፭፡ ከቀትር እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ጨለማ ሆነ፡፡
                    ******
  ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
02/11/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment