Tuesday, March 7, 2017

ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፡፡ማቴ 16÷4፤12÷39 ---ክፍል ፬ (መጨረሻ ክፍል)




© መልካሙ በየነ
የካቲት 27/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
የክፉነት እና የአመንዝራነት መገለጫው ምልክትን መሻት ነው፡፡ በዚህ ዘመን በተለይ ወጣቱ ምልክትን ከመሻቱ የተነሣ ለተለያዩ አደጋዎች ሲጋለጥ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔርን ተአምር አሳየኝ ምልክትን አድርግልኝ እያለ ለራሱ ፈጣሪውን የሚማጸን ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ እየተበራከተ ነው፡፡ ወጣቱ እንደሚታረድ በግ እየተጎተተ ወደ መናፍቃን አዳራሽ እየተነዳ ያለው ምልክትን ማየት ስለሚሻ ነው፡፡ በመናፍቃኑ አዳራሽ ቅዠት የሆነውን የፈውስ እና የምስክርነት መርኃ ግብር መሳተፍን ይሻል፡፡ በመርኃ ግብሩ መሳተፍ ባይችል እንኳ እነርሱ የሚያደርጉት የፈውስ መርኃግብር እኮ ድንቅ ተአምር ነው ይላል ለራሱ፡፡ ሽባውን ተረተሩ፣ ዕውራንን አበሩ፣ ጎባጣውን አቀኑ፣ ከውስጥ ደዌው ገላገሉ፣ በህክምና አይድንም የተባለውን በሽታ ፈወሱ ወዘተ እያሉ ለራሳቸው ድንቅ የሚሉትን ተአምራዊ ገቢር ያደንቃሉ መመልከትም ይጀምራሉ፡፡ አንድ ቀንም ራሳቸው ተአምራቱን ለማረጋገጥ ወደ ምንፍቅናው አዳራሽ ጎራ ይላሉ፡፡ በዚህ የተነሣ ነው እንግዲህ አብዛኛው ወጣት ለመናፍቃኑ ሰይጣናዊ አሠራር ሰለባ የሆነው፡፡
አብዛኞች ምልክትን የሚሹ ሰዎች እንደምልክት አድርገው የሚቆጥሩት የፈውስን ድርጊት ነው፡፡ ለመሆኑ ግን ፈውስ ምንድን ነው? እስኪ እንመልከተው፡፡
ፈውስ
የፈውስ አይነቶች 2 ናቸው
1. የሥጋ ፈውስ
2. የነፍስ ፈውስ
የሥጋ ፈውስ ማለት ከሰውነት አካላት በሽታዎች መዳን ነው፡፡ የእጅ የእግር የዓይን የጆሮ ወዘተ የነፍስ ፈውስ ስንል ግን የነፍስ ከኃጢአት፣ ከበደል፣ ከአጋንንት ቁራኝነት መዳን ነው፡፡
ፈውስ ከማን ይገኛል ያልን እንደሆነ ከእግዚአብሔር በባሕርይው ከቅዱሳን በጸጋ ይገኛል፡፡ መላእክት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ አበው መነኮሳት ነቢያት ካሕናት ይፈውሳሉ፡፡
ፈውስ የት ይገኛል ስንል
1. በቤተ ክርስቲያን /ሐዋ 3÷1-10/
2. በመጠመቂያ ቦታዎች /ዮሐ 5÷1-18;
3. እግዚአብሔርን በመከተል /ማር 5÷25-34/
ፈውስ እውነተኛ እና ሐሰተኛ ተብሎም ይከፈላል፡፡ እውነተኛው ፈውስ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ስንል እግዚአብሔር በባሕርይው የሚሰጠን ፈውስ ወይም በቅዱሳኑ አድሮ በጸጋ የሚገኘውን ፈውስ ማለታችን ነው፡፡ ያ ፈውስ ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅም ሊሆን ይገባዋል፡፡ የመጠመቂያ ቦታዎች ላይ እግዚአብሔር አጋንንትን አሥሮ ያሰቃያቸዋል ለጥቂት ጊዜያት እንኳ ለመቆየት አይችሉምና ከሰዎች ዘንድ ይወጣሉ፡፡ ዳግም ላይመለሱም ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ በማርቆስ ወንጌል ምእራፍ 5÷25-34 የተጠቀሰችው ሴት 12 ዓመት ያህል ደም ይፈሳት ነበር የክርስቶስን ልብስ ነክታ ዳነች ዳግም ያ ደዌ አልመጣባትም፡፡ ዮሐ 5÷1-18 የምናየው የ38 ዓመት በሽተኛው መጻጉእ ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ ሄዷል፡፡ ሐዋ 3÷1-10 የተገለጠው ሽባ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥ ብለው ፈውሰውታል ዳግም ወደ ሽባነት አልተመለሰም፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያላስገረመው ሰው አሁን ይሠራል (ሠ ጠብቆ ይነበብ)  በሚሉት ነገር ሲደነቁ ልዩ ተአምር ተደረገ እያሉ ሲታለሉ በጣም ያሳዝናል፡፡ ወገኔ ሆይ አትደናገር! አይደለም በሽታ መፈወስ  ቅዱሳኑ ሙት አንሥተዋል እኮ፡፡ ኤልያስ አንድ ሙት ኤልሳዕ ሁለት ሙት አንሥተዋል፡፡ /መጽሐፈ ነገሥትን ተመልከቱ/ የሰው ልጅ በባሕርዩ ድንቅ በሚባል ተአምር ይታለላል፡፡ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስን እንዲሁም ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተአምራት የምናቃልል ሰዎች ዛሬ ተአምር እናደርጋለን በሚሉ ተኩላዎች አፋቸውን ከፍተው ጉድ ተሠራ እያሉ ሲከተሉ ማዬት አይቶም ዝም ማለት ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ጅልነትም ነው፡፡ አጋንንትን የማውጣት ጸጋ  የተሰጣቸው ቅዱሳን ጸጋቸው እንዳይገለጥባቸው ያደርጉ ነበር እግዚአብሔር ያስተማራቸው ያንን ነበርና፡፡ እግዚአብሔር በወንጌሉ በርካታ ቦታዎች ላይ ፈውስ ካደረገላቸው በኋላ ይህንን ተአምር ለማንም እንዳትናገሩ ይላቸው ነበር፡፡ /ማር 7÷36-37/፣ /ዮሐ5÷15/ ቅዱሳን  ፈውስን የሚያደርጉት በነጻ ያለምንም ክፍያ ነበር፡፡ ክርስቶስ ሐብተ ፈውስን ለሐዋርያት ከሰጣቸው በኋላ እንዲህ አላቸው ለእናንተ ለእጀጠባባችሁ ኪስ አይኑራችሁ እኔ በነጻ የሰጠኋችሁን እናንተም እንዲሁ በነጻ ስጡ፡፡ /ማቴ10÷9/ ለዚህም ነው ወርቅና ብር የለንም ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣ እያሉ በነጻ ሽባዎችን እየተረተሩ ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ያደርጉ የነበረው፡፡ ሐሰተኛ ፈውስ የምንለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ ፈውስ ጊዜያዊ ነው፡፡ በዓይናችን ስናየው እንደነቃለን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ተአምር ይመስለናል፡፡ አሁን ያልገባን ነገር አለ አጋንንት ደረጃ ደረጃ አላቸው፡፡ ተራ አጋንንት ወይም በደረጃቸው ዝቅ ያሉ አጋንንት በአለቃቸው ወይም ከእነርሱ በበለጡ አጋንንት ይወጣሉ፡፡ ተራ አጋንንት በአለቃቸው ለምን ይወጣሉ ቢሉ አለቃቸው ነፍስን ተቆራኝቶ በገሐነመ እሳት ለዘላለም መያዝ ስለሚፈልግ ነው፡፡ የሰይጣንን ጥበብ ብዙዎቻችን አልተረዳነውም፡፡  ሰው የሚደነቀው በሥጋው መፈወሱን ብቻ ነው ከፈውስ ባሻገር ነፍሱ ምን እንደምትሆን አይረዳም፡፡ ሥጋህ ለምን አይታመም ዋናው እኮ የነፍስ በሽታ ነው፡፡ የስጋ በሽታ እኮ በልብሳቸው እና በጥላቸው ይፈውሱ የነበሩት እነ ቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ጴጥሮስም ነበረባቸው፡፡ ነፍስህን አስብ ትውልዱ!!!!!
በዚህ ዘመን አጋንንትን እናወጣለን የሚሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ነው የሚያወጡ እንላለን፡፡ እውነት ነው የእግዚአብሔር ስም ሲጠራ እንሰማለን ከእግዚአብሔር ስም በስተጀርባ ምን ይደረጋል እርሱ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ ገና ብዙ ነገር ይቀረናል እኮ ምንም አልገባንም ክርስትናው፡፡ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ስንቱ መጫኛ ያቆማል፣ ድውይ ይፈውሳል፣ የግሉን ገንዘብ ያካብታል መሰላችሁ፡፡ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ ውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፡፡ /ማቴ7÷15-16/ የበግ ለምድ የተባለው የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር ስም፣ ጥምጣሙ፣ ካባው፣ አስኬማው ነው፡፡ ይህ ከላይ የምናየው ለምድ ነው በግ የሚያስመስለው፡፡ ውስጡ ግን እምነቱ፣ ምግባሩ፣ ቅድስናው ወዘተ ተኩላዎች ነጣቂዎች ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ የሚያፈሩት ትውልድ ለእግዚአብሔር የሆነ አይደለም ለራሳቸው መመጻደቂያ፣ ቡና የሚያፈላላቸውን፣ ጫማ የሚያስርላቸውን፣ በየሔዱበት አባቴ አባቴ የሚሏቸውን ነው፡፡ ትውልዱ በዚህ አትደነቅ በመጨረሻው ዘመን ከዚህ የበለጠ ተአምር እንደሚሠራ መጽሐፋችን ይነግረናል፡፡ በምትሀት ፀሐይን እና ጨረቃን ይዞ የሚመጣ ትውልድ የሚነሣበት ዘመን ይመጣል ያን ጊዜ የተመረጡ የሚባሉት እንኳ እስኪስቱ ድረስ ብዙ ተአምራትን ያደርጋሉ፡፡ አስቡት እንግዲህ የምጡን መጀመሪያ ዛሬ በዚህ ተራ በሆነ ቀላል ነገር ሕዝቡ እንዲህ ካመነ ያን ጊዜ ማን ይሆን ጸንቶ የሚቆመው? ማንም ሰው እንዲህ አድርግ እንዲህ አታድርግ ተብሎ የሚመለስበት ጊዜ ላይ አይደለንም ነጻ ፈቃድ የራሳችን ነው፡፡ የፈለግነውን የመከተል መብታችን የራሳችን ነው፡፡ አመጸኛ ትውልድ ምልክትን ይሻል እንዲል መጽሐፉ ተአምራትን ቤተክርስቲያን ገብታችሁ ተመልከቱ፡፡ ጸበል ቦታዎች ሄደን መጽናት ሲደክመን በቀላሉ የተገላገልን እየመሰለን ሰው አንከተል፡፡ አጋንንት የሚወጡት በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ሐዋርያት በአንድ ወቅት አጋንንት ያደረበትን ሰው መፈወስ አልችል አሉ፡፡ ኢየሱስም መጣ እና ያንን አጋንንት አስወጣው፡፡ ሐዋርያቱም እኛ ለምን አላወጣነውም ብለው ጠየቁት እርሱም መልሶ እንዲህ አይነቱ መንፈስ በጾምና በጸሎት ካልሆነ በቀር አይወጣም አላቸው ይላል ማቴዎስ ወንጌል፡፡ ለዚህም ነው በጸበል ቦታ አጋንንት የሚቃጠሉት እዚያ ላይ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት አለ፡፡ በአጠቃላይ እውነተኛ ፈዋሽ እንዴት እናውቃለን ለሚለው የሚከተሉትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ መሟላት አለበት፡፡
     1.    ጸጋ እግዚአብሔር ያደረበት፡፡ ጸጋ ለመሆኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ሁልጊዜ አብሮን አይኖርም በዚህ ይታወቃል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ሃብተ ትንቢት እንደተነሣው ያለ ማለት ነው፡፡
     2.    የሚጾም፣ የሚጸልይ፣ የሚሰግድ፣ በእምነት የጸና
     3.    ለፈወሰበት ጸጋ ገንዘብ የማይቀበል፡፡
     4.    ጸጋው በአደባባይ እንዳይገለጥ የሚያደርግ፡፡ አባቶቻችን እንዲህ ድንቅ ተአምራትን በማድረጋቸው ሰው ከተአምራታቸው መሳተፍ ፈልጎ ሲመጣባቸው ይሰወራሉ ይጠፋሉ ቦታቸውን ለቀው ይሄዳሉ ምክንያቱም ከንቱ ውዳሴ እንዳይሆንባቸው ነው፡፡
     5.    ቃለ እግዚአብሔርን ብቻ የሚናገር
     6.    መፈወስን ሥራው ያላደረገ፡፡ ይህ ጸጋ ነውና አምላክ ሊሰጠንም ሊነሣንም የሚችል በመሆኑ የሁልጊዜ ተግባችን ሊሆን አይችልም፡፡ እነ ቅዱስ ጳውሎስ በጥላቸው ቢፈውሱ እግዚአብሔር ጸጋቸውን ለመግለጽ ሲፈልግ አደረገላቸው እንጅ ዋና መተዳደሪያ ሥራው አላደረጉም፡፡
     7.    እግዚአብሔር ቅድስናቸውን ለመግለጽ ሲፈልግ የሚያደርግላቸው መሆን አለበት፡፡
     8.    በመርኃ ግብር ዛሬ እዚህ ነገ እዚህ እያሉ የማይሉ ምክንያም ፈውስን ማድረግ የጸጋ እንጅ የባሕርይ ስጦታችን ስላልሆነ እግዚአብሔር በፈቀደው እርሱ በወደደው ቦታ እና ጊዜ ድንቅ ሥራውን ያደርጋል እንጅ እኛ በፈቀድነውና እኛ በወደድነው ቦታ እና ጊዜ መፈጸም አንችልምና፡፡
     9.    ሁሉም በሽታ ይድናል ብሎ የሚናገር፡፡ ደዌ ዘበጸጋ አለ ለጸጋ እግዚአብሔርን እንድናመሰግንበት ከአምላክ የሚሰጠን ደዌ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላቸው በልብሳቸው ሰውን ሁሉ እየፈወሱ እነርሱ ግን በሽታ ነበረባቸው፡፡ ለጸጋ የተሰጣቸው ነውና፡፡
ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ የተባልነው ያንን የሚሠሩትን ሥራ እንድንገመግም ነው፡፡ በበለጠ ገዳማት ሔዳችሁ እውነተኛ ፈውስ ምን እንደሆነ አረጋግጡ፡፡ በእምነት አትጎስቁሉ፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የዋሃንን ከሚያታልሉ ተኩላዎች ራስህን ጠብቅ መልእክቴ ይህ ነው፡፡
ትውልዱ ለምን አቋራጭ ፈውስን ፈለገ?
ጸበል እንደሚፈውስ ክርስቲያኖች ሁሉ ያምናሉ ግን ዓመት ሁለት ዓመት ደጅ መጽናትን ይጠይቃል፤ መጾም፤ መጸለይ፤ መስገድ መመጽወት ያስፈልጋል እነዚህ ግን ወዲያውኑ እንደሄዱ ፈውሱን ይፈጽሙላቸዋል ለነገ የሚያድር ነገር የለም፡፡ ሳይጾሙ ሳይጸልዩ ሳይሰግዱ በቀላሉ ሳይደክሙ ፈውስን አገኙ ማለት ነው ለዚህ ነው አብዛኛው እንደበግ ሲነዳ የሚውለው ግን ጊዜያዊ የሥጋ ፈውስ እንጅ ዘላለማዊ የነፍስ ፈውስን አያገኙም፡፡
ፈጸምኩ፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ወጣቱ ንቃ!




© መልካሙ በየነ
የካቲት 28/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
=============================================
ጥበበኛው ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ ምእራፍ 12÷1 ላይ “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን ዐስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ” ይላል፡፡ የሰው ልጅ ህጻን ከመባል ሽማግሌ እስከ መባል ድረስ የራሱ የሆነ ጊዜ እና የዕድገት ሂደት አለው፡፡ የሰው ልጅ የዕድገት ሂደቱ በእግር እና በእጁ ከመሄድ አንሥቶ ቀስ በቀስ እያደገ እየጠነከረ ራሱን ችሎ በእግሮቹ ቆሞ መሄድ ይጀምራል፡፡ እንግዲህ ህጻንነት ላይ የዋሕነት ይቅር ባይነት ይኑር እንጅ እምነት የለም ምክንያቱም ማመዛዘን እና ማገናዘብ የለምና፡፡ የህጻንነት ዘመን ወደ ነዱን የምንነዳበት ወደ መሩን የምንመራበት ጊዜ ነው፡፡  ራሳችን ወደን ፈቅደን የምንሠራው አምላክን ደስ የሚያሰኝ ሥራ የለም፡፡ አናስቀድስም፣ አንጾምም፣ አንጸልይም፣ አንሰግድም ምክንያቱም የምናውቀው ነገር ስለሌለ፡፡ ሕጻንነት ላይ የሚጠቅመውን ከሚጎዳው መለየት እና ማመዛዘን የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለዚህም አብዘኛውን ጊዜያችንን በጫወታ ነው የምናሳልፈው፡፡

ወደ መጨረሻው ዘመናችን ስንቀርብ (ስናረጅ) ደግሞ ማመዛዘን፤ የሚጠቅመውን ከሚጎዳው መለየት ወዘተ እንችላለን፡፡  መጸለይ፣ መስገድ፣ መጾም ወዘተ እንፈልጋለን ነገር ግን ደፋ ቀና የምንልበት ጉልበት የለም፡፡ ዓይን ይፈዛል እግር ይደነግዛል በዚህ ወራት ራስን ችሎ ለመራመድም ይከብዳል፡፡ ራሳችንን መሸከም ስለማንችል ተሸካሚ ምርኩዝ እንፈልጋለን፡፡ አንድ አቡነ ዘበሰማያት ቆመን ማድረስ ይከብደናል፡፡ የዝሙት ጾር ጠፍቶልናል፣ ለአምላካችን ተገዝተናል፣ ትእዛዛትን ለመጠበቅ ተግተናል ግን ጥንካሬ የሚባል ነገር የለም መልፈስፈስ ብቻ ነው፡፡  ዓይን ይፈዛል የጸሎት መጻሕፍትን ማንበብ አንችልም እግር ይደነግዛልና ቤተክርስቲያን በቀላሉ መመላለስ አንችልም ሙቀት ልምላሜ ይለያልና በሌሊት ወደ አምላክ መቅረብ አንችልም ይከብደናል፡፡

በሕጻንነት እና በሽምግልና መካከል ደግሞ የወጣትነት (የጉብዝና) ወራት አለ፡፡ በዚህ ጉብዝና ወራት ዓይናችን ለማንበብ፤ እግራችን ወደ ቤቱ ለመመላለስ፣ እጃችን አጥብቆ ለመያዝ፣ አፋችን ቃለ ወንጌልን ለመናገር ስለት ነው፡፡ በዚህ ወራት ሁሉን ነገር ለማድረግ የሚቻልበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ የወጣትነት ወራት ኃጢአትን ለመሥራት የምንቸኩልበት፤ ሲጋራ ለማጨስ ጫት ለመቃም የምንፈጥንበት፤ ዝሙት ለመፈጸም የምንሯሯጥበት፤ ሰውን ለመግደል ከዚያም ለመስረቅ እና ለመዝረፍ እጃችንን የምንሰነዝርበት፤  በአንዱ ትክሻ ላይ ሌላው ለመንጠልጠል የሚፈጥንበት፤ አንዱን ቀብሮ ሌላው ለመበልጸግ የሚሞክርበት፤ ለበደል የምንቸኩልበት ጊዜ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር በዚህ ወራት ሮጠን የምናመልጥበት፣ ይዘን የምናስቀርበት፣ ኃይልና ብርታታችን ያልተለየበት ወቅት ነው፡፡ ነገር ግን የሰይታን ቀስቶች አብዝተው የሚወረወሩብን በዚህ ወራት ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን ዐስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ” በማለት ወጣቱ ፈጣሪውን አስቦ በእምነት ጎልምሶ እንዲኖር ይመክራል፡፡ በዚህ በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪያችንን ማሰብ ከቻልን ዝሙት አይፈትነንም፣ ጫት እና ሲጋራ አያታልለንም፣ መጠጥ አብዝተን ለስካር አንጋለጥም፣ ዓመቱን በሙሉ እንደ እንስሳት ስንበላ እና ስንጠጣ አንኖርም፣ ያየነውን ሁሉ አንመኝም፣ ራሳችንን ወደ ሱስ አንወረውርም፣ አንሰርቅም፣ አንገድልም፣ አናመነዝርም፣ አንበድልም፣ ኃጢአትን አናደርግም ነበር፡፡ ምክንያቱም ስለእኛ ኃጢአት ያለበደሉ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ ከባርነት ነጻነትን እንደሰጠን ፈጣሪያችንን አስበነዋልና፡፡ ነገር ግን አሁን እያስተዋልን ያለነው ጉዳይ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በተለይ ወጣቱ ውጭን ናፋቂ ኃጢአትን አድናቂ እየሆነ ነው፡፡ ውጭ የምላችሁ አሜሪካን ወይም አውሮፓን ወይም ዐረብ አገራትን  አይደለም ከቤተክርስቲያናችን ውጭ ማለቴ ነው እንጅ፡፡ በብዙው ወጣት ዘንድ መጾም፤ መጸለይ፤ መስገድ እንደ ሞኝነት ነው የሚታየው፡፡ በብዙው ወጣት ዘንድ ወደ ቤተክርስቲያን መገስገስ እንደ ጅልነት ነው የሚቆጠረው፡፡ በብዙው ወጣት ዘንድ ድንግልናን ጠብቆ መኖር እንደ ጅልነት ነው የሚታየው፡፡ ወጣቱ የምንፍቅና አባዜ እየተጠናወተው በየአዳራሹ መንፈስ ወረደልኝ እያለ ሲንከባለል መመልከት እጅጉን ያሳዝናል፡፡ ስንት ቅድስና መሥራት በሚችልበት የጉብዝና ወራቱ ለዝሙት እና ለመዳራት ወደ ምንፍቅና አዳራሾች መነዳት እንዴት ያሳዝናል፡፡

ወጣቱ ሆይ! ይህን የጉብዝና ወራታችንን በንስሐ እንመላለስበት፡፡ እንጹምበት እንጸልይበት፡፡ እምነታችንን እናጽናበት፡፡ እምነት ማለት ያላዩትን እንዳዩ አድርጎ ያለማጉረምረም መቀበል ነው፡፡ በእምነት ውስጥ ሰማያዊ ነገር እንጅ ምድራዊ ነገር የሚዘከርበት አይደለም፡፡  አሁን አሁን ግን አብዛኛው እምነትን በምድራዊ ቁስ ሲተካው እንመለከታለን፡፡ ወጣቱ በቁሳዊ ነገር ፈጣሪውን ሲክድ ለጣዖት ሲሰግድ እምነቱን ሲለውጥ እየተመለከትን እናዝናለን፡፡ እንደሚታረድ በግ እየተጎተተ ወደ ምንፍቅና አዳራሾች ሲጓዝ የሚለው ጾሙ ስለመረረው፣ ጸሎት ማድረግ ስለሰለቸው፣ ስግደቱ ስለከበደው፣ ንስሐ መግባት ስላስጨነቀው፣ ሁሉን ነገር በሥርዓት ማድረግ ስላስቸገረው ወዘተ ነው፡፡ እምነት ምን እንደሆነ ቢያውቅ ኖሮማ ሰማያዊ ምሥጢር ወደሚነገርበት ይገሰግስ ነበር እንጅ መንፈስ ቅዱስ ወረደልን እያሉ እንደ አህያ ወደሚንከባለሉበት አዳራሽ ባልተነዱ ነበር፡፡ ግን ሰይጣን ዓይናቸውን አውሮታልና ይነዳሉ፡፡ በርግጥ ዘፈኑ፣ ወንዱ ከሴት፤ ሴቱም ከወንድ ጋራ እንደፈለጉ መሆንን የሚሻ ወጣት ወደዚህ የዘፈን አዳራሽ ቢነዳ ላይደንቅ ይችላል፡፡ ግን አስተዋይ ልቡና ብሩህ ኅሊና ላለው ሰው ይህ ሰይጣናዊ ሥራ እንደሆነ መረዳት እና መገንዘብ በጣም ቀላል ነው፡፡ የሰይጣን ጦር በዋናነት የሚወረወረው ወደ ወጣቶች ነውና ወጣቶች መንቃት አለብን፡፡

Sunday, March 5, 2017

ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፡፡ማቴ 16÷4፤12÷39 ---ክፍል ፫




© መልካሙ በየነ
የካቲት 26/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================

በክፍል ፪ ያየናቸውና ሌሎችም በዚህ ክፍል ያላየናቸው ነገሮች ተአምራት ይባላሉ፡፡ እነዚህ ተአምራት ማንም የሚያደርጋቸው ለማንኛውም የሚደረጉለት አይደሉም ለተመረጡት ብቻ ነው እንጅ፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን ተአምራት የሚያደርጋቸው በሙሉ የተመረጠ ጻድቅ ብቻ ነው ብለን ማሰብ ከጀመርን ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር ቤት ለመውጣት እንገደዳለን፡፡ ስለዚህ  በቤቱ ለመጽናት መፍትሔ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ተአምርን (ምልክትን) አለመሻት ነው፡፡

ተአምርን ለማድረግ አትመኝ ተአምር የሚሠሩትንም ለመመልከት አትሻ፡፡ ምክንያቱም ተአምር የእምነታችን መሠረት እንዳልሆነ መረዳት ይገባሃልና፡፡ ከሐዋርያት ወገን የነበረው ይሁዳ ተአምራትን ያደርግ ነበር፡፡ የእርሱ ተአምር ምን እንደነበር ለማወቅ ካስፈለገህ ደግሞ ሙት ያነሣ እንደነበር ማቴ 7÷22 ላይ የተጻፈውን አንድምታ ትርጓሜ ተመልከተው፡፡ ተአምርን ማድረግ የመንግሥቱ ወራሽ እንደማያደርገን አምላካችን በማይታበል ቃሉ ነገሮናል “በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምኽ ትንቢት አልተናገርንምን በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምኽስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን ይሉኛል የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም እላቸዋለሁ” ይላል ማቴ 7÷22-23፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ድንቅ የሚባል እጅህን አፍህ ላይ የሚያስጭን ተአምር ሲሰሩ ብታይ አትደነቅ አትገረም፡፡ እንደዚያ ያለ ድንቅ ተአምር ብታደርግም አትመካ ምክንያቱም መንግሥቱን የሚያወርስህ አምላክ እንጅ የሠራኸው ተአምር አይደለምና፡፡
ከዚህ እንደምንረዳው ተአምር ከሰይጣንም የሚመጣ እንደሆነ ነው፡፡ በስሙ አጋንንትን ማውጣት እንደ ደቂቀ አስቂዋ፣ በስሙ ትንቢትን መናገር እንደ በለዓም፣ በስሙ ተአምራትን ማድረግ (ሙት ማንሣት እንደ ይሁዳ) ለመንግሥቱ አያበቃም፡፡ ስለዚህ በፍርድ ቀን አላውቃችሁም እንባላለን ማለት ነው፡፡  ስለዚህ የእግዚአብሔር የሆነውን የሰይጣን ከሆነው ተአምር ለይተን ማወቅ ስለማንችል በተአምረ ኢየሱስ በተአምረ ማርያም በድርሳኖቻቸው ላይ ያለውን ተአምረ መላእክት በገድሎቻቸው ላይ ያለውን ተአምረ ቅዱሳን እና ተአምረ ጻድቃን ከተቀበልን ለእኛ እሱ እረፍትን ያስገኘናል፡፡
ዛሬ ላይ ድንቅ ተአምርን የሚያደርግ ጻድቅ የለም ማለቴ አይደለም ነገር ግን የእኛ ብስለት መታየት አለበት፡፡ ከዘመኑ አጥማቂ ነን ባዮች ፈውስን እንሰጣለን እያሉ ገንዘብን ከሚሰበስቡ በስሙ ከሚነግዱ ተኩላዎች ሁሉ ራስን ማራቅ ተገቢ ነው፡፡ ምልክትን የሚሻ ሰው ለመንግሥቱ አይበቃም “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል” ብሏል ጌታችን በማቴ 16÷4፡፡ ስለዚህ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ተብለን እንዳይፈረድብን ምልክትን አንሻ ተአምርን አንፈልግ፡፡
ተአምርን የሚሻ ትውልድ ለመጥፋት እያቀደ እንደሆነ መረዳት ይኖርበታል፡፡ “…ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” ማቴ 24÷24 ይለናል፡፡ ስለዚህ በመጨረሻው ዘመን የሰውን ልጅ ሊያስቱበት የሚችሉበትን ተአምር ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እነሆ ክፉዎች ይነሣሉ፡፡ ከእነዚህ ክፉዎች ራስን መጠበቅ ይገባናል፡፡ ስለዚህ በቤቱ ለመጽናት የምትሻ ከሆነ ተአምራትን ለማየት ተአምራትንም ለመስራት አትሻ፡፡
የዋሃን ተአምራትን አይተው ተአምር አድራጊውን ሲከተሉ ይውላሉ፡፡ ለምን እንደሚከተሉ ሲጠየቁም የሚመልሱት የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ተአምራትን ስለሚያደርጉ ነው ብለው ነው፡፡ ሆኖም ግን ተአምራትን ያየ ወይም ያደረገ ሁሉ ለመንግሥቱ አይበቃም፡፡ ለዚህም ምስክሮቻችን ህዝበ እስራኤላውያን ናቸው፡፡ እነርሱ ባሕረ ኤርትራ ተከፍሎላቸው ተሻግረዋል፡፡ ኋላም መና ከደመና እየወረደላቸው ሲበሉ ውኃ ከጭንጫ ላይ እየፈለቀላቸው ሲጠጡ ነበር፡፡ ነገር ግን ጣዖት ሲያመልኩ ተመልክተናል፡፡ በነዘር እባብም ጎን ጎናቸውን ተወግተው እንደሞቱ አይተናል፡፡ የተስፋዪቱንም ምድር ሳያዩ በበረሃ ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ ተአምራትን ማየትም ሆነ መሥራት ለመንግሥቱ የሚያበቃ እንዳልሆነ ልትረዳ ይገባል፡፡ /ኦሪት ዘጸአትን ተመልከት/
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡

Friday, March 3, 2017

ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፡፡ማቴ 16÷4፤12÷39 ---ክፍል ፪



© መልካሙ በየነ
የካቲት 24/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
የመብራት መጥፋት ለውኃ መሄድ ምልክት ነው፤ የዝናብ መዝነም ለመብራት መሄድ ምልክት ነው፡፡ ስለዚህ ዝናም ሊዘንብ ከሆነ ዛሬ መብራት ይጠፋል እንላለን፡፡ መብራት ከጠፋ ደግሞ ዛሬ ውኃ ትሄዳለች እንላለን፡፡ ይህ በቃ የተለመደ ምልክታችን ሆኗል፡፡ የሚገርመው ነገር በበጋ መብራት ሲጠፋ ምን እንላለን መሰላችሁ “ዛሬ ደግሞ ምን ሆነው ነው ያጠፉት ዝናም የለ ደመና የለ” እንላለን በቃ ምልክት አድርገን ይዘነዋላ፡፡ እንደዚህ ሁሉ አምላካችንንም አምላካችን ነው ብለን ለመቀበል ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን እንሻለን፡፡ አምላካዊነቱን ለመቀበል ግን የምንሻው ምልክት ተአምራዊ ሥራን ነው፡፡
ተአምር ከሰው ልጅ የአስተሳሰብ አድማስ በላይ ከኅሊናም በላይ ምጡቅ የማይደረስበት ለማንም የማይሰጥ ልዩ ጸጋ ነው፡፡ ከመደበኛው የሰው ልጅ ተግባራትና ክዋኔዎች የተለየ ድርጊት ነው፡፡
ተአምር የምንለው እንደ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ከጸጉራቸው ጫፉ ከልብሳቸው ዘርፉ ምንም ሳይነካ መውጣት ነው፡፡ ትን ዳን 3÷26 እዚህ ላይ ልብ በሉ የእሳት የሁልጊዜ ተግባሩ ማቃጠል ነው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን ቅዱሳን ማቃጠል ተሳነው፡፡
ተአምር ማለት እንደ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድሰት እየሉጣ በፈላ ውኃ መካከል ገብቶ ሳይቀቀሉ መውጣት ነው፡፡ /ድርሳነ ገብርኤል ዘሐምሌ 19 ተመልከት/ የፈላ ውኃ ከድንጋይ በቀር የተጣለለትን መቀቀል የሁል ጊዜ ተግባሩ ነው ሆኖም ግን ቅድስት እየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን መቀቀል አልቻለምና እንደቀዘቀዘ ሆኖ ታየ፡፡
ተአምር ማለት እንደ ዳንኤል ለተራቡ አናብስት ተጥሎ ምንም ሳይነኩ መውጣት ነው፡፡ ትን ዳን 6÷22 ተመልከት፡፡ አናብስት ያውም ርቧቸው ቀርቶ ጠግበውም ቢሆን እንኳ የተጣለላቸውን ያገኙትን ነገር አይምሩም ይሰባብራሉ እንጅ ይህ የአናብስት የዘወትር ግብራቸው ነው፡፡ ነገር ግን ዳንኤልን ሰባብረው ለመብላት አልቻሉም እንዲያውም ለመስገድ ተገደዱና ሰገዱለትዳንኤልን በልተውራባቸውን ከማስታገስ ይልቅ ረሃባቸውን መረጡ፡፡
ተአምር ማለት እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ በገባዖን ሰማይ ፀሐይን ማቆም በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃን ማዘግየት ነው፡፡ መጽ ኢያሱ 10÷12-14 ተመልከት፡፡ ፀሐይ የዘወትር ግብሯ ጊዜዋን ጠብቃ በምሥራቅ በኩል ወጥታ በማደሪያዋ ምዕራብ መግባት ነበር፡፡ ዛሬ ግን በኢያሱ ግዘት ጠላቱን ድል እስከሚያደርግ ድረስ ቆማ ቆይታለች፡፡
ተአምር ማለት እንደ ጴጥሮስ በውኃ ላይ እንደ የብስ መራመድ ነው፡፡ ማቴ 14÷29 ባህር እንደየብስ ሆና ሰው ሄዶባት አታውቅም ምክንያቱም የማስጠም ግብር አላትና፡፡ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ና ብሎታልና ቅዱስ ጴጥሮስ ሲራመድባት እንደየብስ ሆነችለት አላሰጠመችውም ነበር፡፡
ተአምር እንደ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሽባን ተነሥ ብሎ ማንሣት ነው፡፡ የሐዋ 3÷7 ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ዐንካሳ የነበረ ሰው ተንሥእ (ተነሣ) ሲባል አፈፍ ብሎ መነሣት አይችልም ነበር፡፡ የዚህ ደግሞ የባሰ ነበር መልካም በሚሏት መቅደስ ደጅ የሚያስቀምጡት ሰዎች ተሸክመው ወስደው ነበር፤ አሁን ግን የማንንም እርዳታ ላይጠይቅ ለመጨረሻ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ተነሥ ብለው አስነሡት፡፡ እርሱም ተነሥቶ እስኪዘል ድረስ ደስታውን ገልጿል፡፡
ተአምር ማለት እንደበለዓም አህያ እንደቢታንያ ድንጋዮች አፍ አውጥቶ መናገር ነው፡፡ ዘኁ 22÷28 አህያ አፍ አውጥታ ስትናገር ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማነው የበለዓምን አህያ ነው፡፡ አህያዪቱ በለዓም ያላየውን የተመዘዘ ሰይፍ የያዘውን መልአክ ተመልክታ መንገዷን መቀጠል አልችል ባለች ጊዜ በለዓም አብዝቶ ደበደባት፡፡ በዚህም የተነሣ እግዚአብሔር የአህያዪቱን አፍ ከፍቶ እንድትናገር አደረገ፡፡ በተመሳሳይ ሉቃ19÷40 ላይ ፈሪሳውያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሆሳዕና በአርያም እያሉ ያመሰግኑት የነበሩትን ደቀመዛሙርቱን ገስጻቸው አሉት፡፡ እርሱም መልሶ እነዚህ ዝም ቢሉ እንኳ የቢታንያ ድንጋዮች ያመሰግኑኛል አላቸው፡፡
ተአምር ማለት አንደ ኤልያስና እንደ ኤልሳዕ ሙትን ማንሣት ነው፡፡ ኤልያስ አንድ ሙት ኤልሳዕ ሁለት ሙት አነሥተዋል፡፡ 1ኛ 17÷22 ላይ “እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ የብላቴናው ነፍስ ወደርሱ ተመለሰች እርሱም ዳነ” ይላል፡፡ ኤልያስ እንዲህ የሞተውን ዮናስን አንሥቶታል፡፡ የኤልያስ በረከት እጥፍ ሆኖ ያደረበት ኤልሳዕም በሕይወቱ አንድ ከዐረፈ በኋላ ደግሞ አንድ በድምሩ ሁለት ሙታንን አንሥቷል፡፡ 2ኛ ነገ 4÷35 ላይ “ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕጻኑ ላይ ተጋደመ ሕጻኑም ዐይኖቹን ከፈተ” ይላል፡፡ ከዐረፈ በኋላም ኤልሳዕ 2ኛ ነገ 13÷21 “ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ” ይላል፡፡ የሞተ ሰው ሲነሣ ያየነው እንግዲህ በኤልሳዕና በኤልያስ ነው፡፡
ተአምር ማለት እንደሙሴ ባሕርን ከፍሎ ህዝብን በሰላም ማሻገር ነው፡፡ ዘጸ 14÷21-ፍጻ ተመልከት፡፡ ባህር ተከፍሎ ውኃ እንደግድግዳ ቆሞ የብስ ሆኖ ህዘብን ያሻገረ ባህር አይተን አናውቅም ነበር ዛሬ ግን ከእስራኤላውያን ጋር ስንሰለፍ በሙሴ በትር ባህር ሲከፈል ውኃ ግድግዳ ሆኖ ሲቆም እነሆ ተመለከትን፤ በደረቅ መንገድም እነሆ ሄድን፡፡
ተአምር ማለት እንደ ሐዋርያት፣ እንደ አባ ኤፍሬምና እንደ አባ ባስልዮስ፣ እንደ አባ ሕርያቆስ የማያውቁትን ያልተማሩትን አውቆ ተምሮ በቅቶ መገኘት ነው፡፡ የሐዋ ሥራ 2ን ስንመለከት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ እነርሱ ከሚያውቁት ከሚናገሩት ቋንቋ በተጨማሪ 71 ቋንቋ ተገልጾላቸው ህዝቡን ሁሉ በየራሳቸው ቋንቋ ለማስተማር በቅተዋል፡፡ ውዳሴ ማርያም የሰኞ አንድምታን ስንመለከት ደግሞ በአስተርጓሚ ሲጨዋወቱ የነበሩት ባስልዮስና ኤፍሬም በጸሎታቸው የባስልዮስ ቋንቋ ጽርእ ለኤፍሬም፤ የኤፍሬምም ቋንቋ ሱርስት ለባስልዮስ ተገልጾላቸው ያለአስተርጓሚ ተነጋግረዋል፡፡ በቅዳሴ ማርያም ምእራፍ 1 አንድምታ ላይ ስንመለከት ደግሞ የምናገኘው አባ ሕርያቆስን ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ ያልተማረ ግበረ ገብ ካህን ነው፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ትእቢት የያዛቸው ካህናት ነገር ሰሩበት፡፡ ቀድሰህ አቁርበን እንበለው ብለው ተነሡበት፡፡ በዚህም መሠረት ቀድሰህ አቁርበን አሉት፡፡ ከዚያም ከፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግረውን ማንን እናውጣለት እያሉ ነገር ሲሠሩ እነሆ የአምላክ እናት ምሥጢርን ሁሉ ገልጣለት “ጎሥዐ ልብየ ቃለ ሰናየ፤ ልቤ መልካም ነገርን አወጣ” ብሎ አዲስ ቅዳሴ ለመድረስ በቅቷል፡፡
ይቀጥላል
ይቆየን፡፡