© መልካሙ በየነ
የካቲት 26/
2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
በክፍል ፪ ያየናቸውና ሌሎችም በዚህ ክፍል
ያላየናቸው ነገሮች ተአምራት ይባላሉ፡፡ እነዚህ ተአምራት ማንም የሚያደርጋቸው ለማንኛውም የሚደረጉለት አይደሉም ለተመረጡት ብቻ
ነው እንጅ፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን ተአምራት የሚያደርጋቸው በሙሉ የተመረጠ ጻድቅ ብቻ ነው ብለን ማሰብ ከጀመርን ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር
ቤት ለመውጣት እንገደዳለን፡፡ ስለዚህ በቤቱ ለመጽናት መፍትሔ ማድረግ
ያለብን ነገር ቢኖር ተአምርን (ምልክትን) አለመሻት ነው፡፡
ተአምርን ለማድረግ አትመኝ ተአምር የሚሠሩትንም ለመመልከት አትሻ፡፡ ምክንያቱም ተአምር የእምነታችን መሠረት
እንዳልሆነ መረዳት ይገባሃልና፡፡ ከሐዋርያት ወገን የነበረው ይሁዳ ተአምራትን ያደርግ ነበር፡፡ የእርሱ ተአምር ምን እንደነበር
ለማወቅ ካስፈለገህ ደግሞ ሙት ያነሣ እንደነበር ማቴ 7÷22 ላይ የተጻፈውን አንድምታ ትርጓሜ ተመልከተው፡፡ ተአምርን ማድረግ የመንግሥቱ
ወራሽ እንደማያደርገን አምላካችን በማይታበል ቃሉ ነገሮናል “በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምኽ ትንቢት አልተናገርንምን
በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምኽስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን ይሉኛል የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም እላቸዋለሁ” ይላል
ማቴ 7÷22-23፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ድንቅ የሚባል እጅህን አፍህ ላይ የሚያስጭን ተአምር ሲሰሩ ብታይ አትደነቅ አትገረም፡፡
እንደዚያ ያለ ድንቅ ተአምር ብታደርግም አትመካ ምክንያቱም መንግሥቱን የሚያወርስህ አምላክ እንጅ የሠራኸው ተአምር አይደለምና፡፡
ከዚህ እንደምንረዳው ተአምር ከሰይጣንም የሚመጣ እንደሆነ ነው፡፡ በስሙ አጋንንትን ማውጣት እንደ ደቂቀ
አስቂዋ፣ በስሙ ትንቢትን መናገር እንደ በለዓም፣ በስሙ ተአምራትን ማድረግ (ሙት ማንሣት እንደ ይሁዳ) ለመንግሥቱ አያበቃም፡፡
ስለዚህ በፍርድ ቀን አላውቃችሁም እንባላለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ
የእግዚአብሔር የሆነውን የሰይጣን ከሆነው ተአምር ለይተን ማወቅ ስለማንችል በተአምረ ኢየሱስ በተአምረ ማርያም በድርሳኖቻቸው ላይ
ያለውን ተአምረ መላእክት በገድሎቻቸው ላይ ያለውን ተአምረ ቅዱሳን እና ተአምረ ጻድቃን ከተቀበልን ለእኛ እሱ እረፍትን ያስገኘናል፡፡
ዛሬ ላይ ድንቅ ተአምርን የሚያደርግ ጻድቅ የለም ማለቴ አይደለም ነገር ግን የእኛ ብስለት መታየት አለበት፡፡
ከዘመኑ አጥማቂ ነን ባዮች ፈውስን እንሰጣለን እያሉ ገንዘብን ከሚሰበስቡ በስሙ ከሚነግዱ ተኩላዎች ሁሉ ራስን ማራቅ ተገቢ ነው፡፡
ምልክትን የሚሻ ሰው ለመንግሥቱ አይበቃም “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል” ብሏል ጌታችን በማቴ 16÷4፡፡ ስለዚህ ክፉና
አመንዝራ ትውልድ ተብለን እንዳይፈረድብን ምልክትን አንሻ ተአምርን አንፈልግ፡፡
ተአምርን የሚሻ ትውልድ ለመጥፋት እያቀደ እንደሆነ መረዳት ይኖርበታል፡፡ “…ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ
እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” ማቴ 24÷24 ይለናል፡፡ ስለዚህ በመጨረሻው ዘመን የሰውን ልጅ ሊያስቱበት የሚችሉበትን
ተአምር ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እነሆ ክፉዎች ይነሣሉ፡፡ ከእነዚህ ክፉዎች ራስን መጠበቅ ይገባናል፡፡ ስለዚህ በቤቱ ለመጽናት የምትሻ
ከሆነ ተአምራትን ለማየት ተአምራትንም ለመስራት አትሻ፡፡
የዋሃን ተአምራትን አይተው ተአምር አድራጊውን ሲከተሉ ይውላሉ፡፡ ለምን እንደሚከተሉ ሲጠየቁም የሚመልሱት
የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ተአምራትን ስለሚያደርጉ ነው ብለው ነው፡፡ ሆኖም ግን ተአምራትን ያየ ወይም ያደረገ ሁሉ ለመንግሥቱ
አይበቃም፡፡ ለዚህም ምስክሮቻችን ህዝበ እስራኤላውያን ናቸው፡፡ እነርሱ ባሕረ ኤርትራ ተከፍሎላቸው ተሻግረዋል፡፡ ኋላም መና ከደመና
እየወረደላቸው ሲበሉ ውኃ ከጭንጫ ላይ እየፈለቀላቸው ሲጠጡ ነበር፡፡ ነገር ግን ጣዖት ሲያመልኩ ተመልክተናል፡፡ በነዘር እባብም
ጎን ጎናቸውን ተወግተው እንደሞቱ አይተናል፡፡ የተስፋዪቱንም ምድር ሳያዩ በበረሃ ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ ተአምራትን ማየትም ሆነ መሥራት
ለመንግሥቱ የሚያበቃ እንዳልሆነ ልትረዳ ይገባል፡፡ /ኦሪት ዘጸአትን ተመልከት/
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡
No comments:
Post a Comment