Tuesday, March 7, 2017

ወጣቱ ንቃ!




© መልካሙ በየነ
የካቲት 28/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
=============================================
ጥበበኛው ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ ምእራፍ 12÷1 ላይ “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን ዐስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ” ይላል፡፡ የሰው ልጅ ህጻን ከመባል ሽማግሌ እስከ መባል ድረስ የራሱ የሆነ ጊዜ እና የዕድገት ሂደት አለው፡፡ የሰው ልጅ የዕድገት ሂደቱ በእግር እና በእጁ ከመሄድ አንሥቶ ቀስ በቀስ እያደገ እየጠነከረ ራሱን ችሎ በእግሮቹ ቆሞ መሄድ ይጀምራል፡፡ እንግዲህ ህጻንነት ላይ የዋሕነት ይቅር ባይነት ይኑር እንጅ እምነት የለም ምክንያቱም ማመዛዘን እና ማገናዘብ የለምና፡፡ የህጻንነት ዘመን ወደ ነዱን የምንነዳበት ወደ መሩን የምንመራበት ጊዜ ነው፡፡  ራሳችን ወደን ፈቅደን የምንሠራው አምላክን ደስ የሚያሰኝ ሥራ የለም፡፡ አናስቀድስም፣ አንጾምም፣ አንጸልይም፣ አንሰግድም ምክንያቱም የምናውቀው ነገር ስለሌለ፡፡ ሕጻንነት ላይ የሚጠቅመውን ከሚጎዳው መለየት እና ማመዛዘን የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለዚህም አብዘኛውን ጊዜያችንን በጫወታ ነው የምናሳልፈው፡፡

ወደ መጨረሻው ዘመናችን ስንቀርብ (ስናረጅ) ደግሞ ማመዛዘን፤ የሚጠቅመውን ከሚጎዳው መለየት ወዘተ እንችላለን፡፡  መጸለይ፣ መስገድ፣ መጾም ወዘተ እንፈልጋለን ነገር ግን ደፋ ቀና የምንልበት ጉልበት የለም፡፡ ዓይን ይፈዛል እግር ይደነግዛል በዚህ ወራት ራስን ችሎ ለመራመድም ይከብዳል፡፡ ራሳችንን መሸከም ስለማንችል ተሸካሚ ምርኩዝ እንፈልጋለን፡፡ አንድ አቡነ ዘበሰማያት ቆመን ማድረስ ይከብደናል፡፡ የዝሙት ጾር ጠፍቶልናል፣ ለአምላካችን ተገዝተናል፣ ትእዛዛትን ለመጠበቅ ተግተናል ግን ጥንካሬ የሚባል ነገር የለም መልፈስፈስ ብቻ ነው፡፡  ዓይን ይፈዛል የጸሎት መጻሕፍትን ማንበብ አንችልም እግር ይደነግዛልና ቤተክርስቲያን በቀላሉ መመላለስ አንችልም ሙቀት ልምላሜ ይለያልና በሌሊት ወደ አምላክ መቅረብ አንችልም ይከብደናል፡፡

በሕጻንነት እና በሽምግልና መካከል ደግሞ የወጣትነት (የጉብዝና) ወራት አለ፡፡ በዚህ ጉብዝና ወራት ዓይናችን ለማንበብ፤ እግራችን ወደ ቤቱ ለመመላለስ፣ እጃችን አጥብቆ ለመያዝ፣ አፋችን ቃለ ወንጌልን ለመናገር ስለት ነው፡፡ በዚህ ወራት ሁሉን ነገር ለማድረግ የሚቻልበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ የወጣትነት ወራት ኃጢአትን ለመሥራት የምንቸኩልበት፤ ሲጋራ ለማጨስ ጫት ለመቃም የምንፈጥንበት፤ ዝሙት ለመፈጸም የምንሯሯጥበት፤ ሰውን ለመግደል ከዚያም ለመስረቅ እና ለመዝረፍ እጃችንን የምንሰነዝርበት፤  በአንዱ ትክሻ ላይ ሌላው ለመንጠልጠል የሚፈጥንበት፤ አንዱን ቀብሮ ሌላው ለመበልጸግ የሚሞክርበት፤ ለበደል የምንቸኩልበት ጊዜ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር በዚህ ወራት ሮጠን የምናመልጥበት፣ ይዘን የምናስቀርበት፣ ኃይልና ብርታታችን ያልተለየበት ወቅት ነው፡፡ ነገር ግን የሰይታን ቀስቶች አብዝተው የሚወረወሩብን በዚህ ወራት ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን ዐስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ” በማለት ወጣቱ ፈጣሪውን አስቦ በእምነት ጎልምሶ እንዲኖር ይመክራል፡፡ በዚህ በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪያችንን ማሰብ ከቻልን ዝሙት አይፈትነንም፣ ጫት እና ሲጋራ አያታልለንም፣ መጠጥ አብዝተን ለስካር አንጋለጥም፣ ዓመቱን በሙሉ እንደ እንስሳት ስንበላ እና ስንጠጣ አንኖርም፣ ያየነውን ሁሉ አንመኝም፣ ራሳችንን ወደ ሱስ አንወረውርም፣ አንሰርቅም፣ አንገድልም፣ አናመነዝርም፣ አንበድልም፣ ኃጢአትን አናደርግም ነበር፡፡ ምክንያቱም ስለእኛ ኃጢአት ያለበደሉ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ ከባርነት ነጻነትን እንደሰጠን ፈጣሪያችንን አስበነዋልና፡፡ ነገር ግን አሁን እያስተዋልን ያለነው ጉዳይ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በተለይ ወጣቱ ውጭን ናፋቂ ኃጢአትን አድናቂ እየሆነ ነው፡፡ ውጭ የምላችሁ አሜሪካን ወይም አውሮፓን ወይም ዐረብ አገራትን  አይደለም ከቤተክርስቲያናችን ውጭ ማለቴ ነው እንጅ፡፡ በብዙው ወጣት ዘንድ መጾም፤ መጸለይ፤ መስገድ እንደ ሞኝነት ነው የሚታየው፡፡ በብዙው ወጣት ዘንድ ወደ ቤተክርስቲያን መገስገስ እንደ ጅልነት ነው የሚቆጠረው፡፡ በብዙው ወጣት ዘንድ ድንግልናን ጠብቆ መኖር እንደ ጅልነት ነው የሚታየው፡፡ ወጣቱ የምንፍቅና አባዜ እየተጠናወተው በየአዳራሹ መንፈስ ወረደልኝ እያለ ሲንከባለል መመልከት እጅጉን ያሳዝናል፡፡ ስንት ቅድስና መሥራት በሚችልበት የጉብዝና ወራቱ ለዝሙት እና ለመዳራት ወደ ምንፍቅና አዳራሾች መነዳት እንዴት ያሳዝናል፡፡

ወጣቱ ሆይ! ይህን የጉብዝና ወራታችንን በንስሐ እንመላለስበት፡፡ እንጹምበት እንጸልይበት፡፡ እምነታችንን እናጽናበት፡፡ እምነት ማለት ያላዩትን እንዳዩ አድርጎ ያለማጉረምረም መቀበል ነው፡፡ በእምነት ውስጥ ሰማያዊ ነገር እንጅ ምድራዊ ነገር የሚዘከርበት አይደለም፡፡  አሁን አሁን ግን አብዛኛው እምነትን በምድራዊ ቁስ ሲተካው እንመለከታለን፡፡ ወጣቱ በቁሳዊ ነገር ፈጣሪውን ሲክድ ለጣዖት ሲሰግድ እምነቱን ሲለውጥ እየተመለከትን እናዝናለን፡፡ እንደሚታረድ በግ እየተጎተተ ወደ ምንፍቅና አዳራሾች ሲጓዝ የሚለው ጾሙ ስለመረረው፣ ጸሎት ማድረግ ስለሰለቸው፣ ስግደቱ ስለከበደው፣ ንስሐ መግባት ስላስጨነቀው፣ ሁሉን ነገር በሥርዓት ማድረግ ስላስቸገረው ወዘተ ነው፡፡ እምነት ምን እንደሆነ ቢያውቅ ኖሮማ ሰማያዊ ምሥጢር ወደሚነገርበት ይገሰግስ ነበር እንጅ መንፈስ ቅዱስ ወረደልን እያሉ እንደ አህያ ወደሚንከባለሉበት አዳራሽ ባልተነዱ ነበር፡፡ ግን ሰይጣን ዓይናቸውን አውሮታልና ይነዳሉ፡፡ በርግጥ ዘፈኑ፣ ወንዱ ከሴት፤ ሴቱም ከወንድ ጋራ እንደፈለጉ መሆንን የሚሻ ወጣት ወደዚህ የዘፈን አዳራሽ ቢነዳ ላይደንቅ ይችላል፡፡ ግን አስተዋይ ልቡና ብሩህ ኅሊና ላለው ሰው ይህ ሰይጣናዊ ሥራ እንደሆነ መረዳት እና መገንዘብ በጣም ቀላል ነው፡፡ የሰይጣን ጦር በዋናነት የሚወረወረው ወደ ወጣቶች ነውና ወጣቶች መንቃት አለብን፡፡

No comments:

Post a Comment