Tuesday, March 7, 2017

ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፡፡ማቴ 16÷4፤12÷39 ---ክፍል ፬ (መጨረሻ ክፍል)




© መልካሙ በየነ
የካቲት 27/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
የክፉነት እና የአመንዝራነት መገለጫው ምልክትን መሻት ነው፡፡ በዚህ ዘመን በተለይ ወጣቱ ምልክትን ከመሻቱ የተነሣ ለተለያዩ አደጋዎች ሲጋለጥ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔርን ተአምር አሳየኝ ምልክትን አድርግልኝ እያለ ለራሱ ፈጣሪውን የሚማጸን ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ እየተበራከተ ነው፡፡ ወጣቱ እንደሚታረድ በግ እየተጎተተ ወደ መናፍቃን አዳራሽ እየተነዳ ያለው ምልክትን ማየት ስለሚሻ ነው፡፡ በመናፍቃኑ አዳራሽ ቅዠት የሆነውን የፈውስ እና የምስክርነት መርኃ ግብር መሳተፍን ይሻል፡፡ በመርኃ ግብሩ መሳተፍ ባይችል እንኳ እነርሱ የሚያደርጉት የፈውስ መርኃግብር እኮ ድንቅ ተአምር ነው ይላል ለራሱ፡፡ ሽባውን ተረተሩ፣ ዕውራንን አበሩ፣ ጎባጣውን አቀኑ፣ ከውስጥ ደዌው ገላገሉ፣ በህክምና አይድንም የተባለውን በሽታ ፈወሱ ወዘተ እያሉ ለራሳቸው ድንቅ የሚሉትን ተአምራዊ ገቢር ያደንቃሉ መመልከትም ይጀምራሉ፡፡ አንድ ቀንም ራሳቸው ተአምራቱን ለማረጋገጥ ወደ ምንፍቅናው አዳራሽ ጎራ ይላሉ፡፡ በዚህ የተነሣ ነው እንግዲህ አብዛኛው ወጣት ለመናፍቃኑ ሰይጣናዊ አሠራር ሰለባ የሆነው፡፡
አብዛኞች ምልክትን የሚሹ ሰዎች እንደምልክት አድርገው የሚቆጥሩት የፈውስን ድርጊት ነው፡፡ ለመሆኑ ግን ፈውስ ምንድን ነው? እስኪ እንመልከተው፡፡
ፈውስ
የፈውስ አይነቶች 2 ናቸው
1. የሥጋ ፈውስ
2. የነፍስ ፈውስ
የሥጋ ፈውስ ማለት ከሰውነት አካላት በሽታዎች መዳን ነው፡፡ የእጅ የእግር የዓይን የጆሮ ወዘተ የነፍስ ፈውስ ስንል ግን የነፍስ ከኃጢአት፣ ከበደል፣ ከአጋንንት ቁራኝነት መዳን ነው፡፡
ፈውስ ከማን ይገኛል ያልን እንደሆነ ከእግዚአብሔር በባሕርይው ከቅዱሳን በጸጋ ይገኛል፡፡ መላእክት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ አበው መነኮሳት ነቢያት ካሕናት ይፈውሳሉ፡፡
ፈውስ የት ይገኛል ስንል
1. በቤተ ክርስቲያን /ሐዋ 3÷1-10/
2. በመጠመቂያ ቦታዎች /ዮሐ 5÷1-18;
3. እግዚአብሔርን በመከተል /ማር 5÷25-34/
ፈውስ እውነተኛ እና ሐሰተኛ ተብሎም ይከፈላል፡፡ እውነተኛው ፈውስ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ስንል እግዚአብሔር በባሕርይው የሚሰጠን ፈውስ ወይም በቅዱሳኑ አድሮ በጸጋ የሚገኘውን ፈውስ ማለታችን ነው፡፡ ያ ፈውስ ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅም ሊሆን ይገባዋል፡፡ የመጠመቂያ ቦታዎች ላይ እግዚአብሔር አጋንንትን አሥሮ ያሰቃያቸዋል ለጥቂት ጊዜያት እንኳ ለመቆየት አይችሉምና ከሰዎች ዘንድ ይወጣሉ፡፡ ዳግም ላይመለሱም ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ በማርቆስ ወንጌል ምእራፍ 5÷25-34 የተጠቀሰችው ሴት 12 ዓመት ያህል ደም ይፈሳት ነበር የክርስቶስን ልብስ ነክታ ዳነች ዳግም ያ ደዌ አልመጣባትም፡፡ ዮሐ 5÷1-18 የምናየው የ38 ዓመት በሽተኛው መጻጉእ ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ ሄዷል፡፡ ሐዋ 3÷1-10 የተገለጠው ሽባ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥ ብለው ፈውሰውታል ዳግም ወደ ሽባነት አልተመለሰም፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያላስገረመው ሰው አሁን ይሠራል (ሠ ጠብቆ ይነበብ)  በሚሉት ነገር ሲደነቁ ልዩ ተአምር ተደረገ እያሉ ሲታለሉ በጣም ያሳዝናል፡፡ ወገኔ ሆይ አትደናገር! አይደለም በሽታ መፈወስ  ቅዱሳኑ ሙት አንሥተዋል እኮ፡፡ ኤልያስ አንድ ሙት ኤልሳዕ ሁለት ሙት አንሥተዋል፡፡ /መጽሐፈ ነገሥትን ተመልከቱ/ የሰው ልጅ በባሕርዩ ድንቅ በሚባል ተአምር ይታለላል፡፡ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስን እንዲሁም ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተአምራት የምናቃልል ሰዎች ዛሬ ተአምር እናደርጋለን በሚሉ ተኩላዎች አፋቸውን ከፍተው ጉድ ተሠራ እያሉ ሲከተሉ ማዬት አይቶም ዝም ማለት ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ጅልነትም ነው፡፡ አጋንንትን የማውጣት ጸጋ  የተሰጣቸው ቅዱሳን ጸጋቸው እንዳይገለጥባቸው ያደርጉ ነበር እግዚአብሔር ያስተማራቸው ያንን ነበርና፡፡ እግዚአብሔር በወንጌሉ በርካታ ቦታዎች ላይ ፈውስ ካደረገላቸው በኋላ ይህንን ተአምር ለማንም እንዳትናገሩ ይላቸው ነበር፡፡ /ማር 7÷36-37/፣ /ዮሐ5÷15/ ቅዱሳን  ፈውስን የሚያደርጉት በነጻ ያለምንም ክፍያ ነበር፡፡ ክርስቶስ ሐብተ ፈውስን ለሐዋርያት ከሰጣቸው በኋላ እንዲህ አላቸው ለእናንተ ለእጀጠባባችሁ ኪስ አይኑራችሁ እኔ በነጻ የሰጠኋችሁን እናንተም እንዲሁ በነጻ ስጡ፡፡ /ማቴ10÷9/ ለዚህም ነው ወርቅና ብር የለንም ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣ እያሉ በነጻ ሽባዎችን እየተረተሩ ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ያደርጉ የነበረው፡፡ ሐሰተኛ ፈውስ የምንለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ ፈውስ ጊዜያዊ ነው፡፡ በዓይናችን ስናየው እንደነቃለን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ተአምር ይመስለናል፡፡ አሁን ያልገባን ነገር አለ አጋንንት ደረጃ ደረጃ አላቸው፡፡ ተራ አጋንንት ወይም በደረጃቸው ዝቅ ያሉ አጋንንት በአለቃቸው ወይም ከእነርሱ በበለጡ አጋንንት ይወጣሉ፡፡ ተራ አጋንንት በአለቃቸው ለምን ይወጣሉ ቢሉ አለቃቸው ነፍስን ተቆራኝቶ በገሐነመ እሳት ለዘላለም መያዝ ስለሚፈልግ ነው፡፡ የሰይጣንን ጥበብ ብዙዎቻችን አልተረዳነውም፡፡  ሰው የሚደነቀው በሥጋው መፈወሱን ብቻ ነው ከፈውስ ባሻገር ነፍሱ ምን እንደምትሆን አይረዳም፡፡ ሥጋህ ለምን አይታመም ዋናው እኮ የነፍስ በሽታ ነው፡፡ የስጋ በሽታ እኮ በልብሳቸው እና በጥላቸው ይፈውሱ የነበሩት እነ ቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ጴጥሮስም ነበረባቸው፡፡ ነፍስህን አስብ ትውልዱ!!!!!
በዚህ ዘመን አጋንንትን እናወጣለን የሚሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ነው የሚያወጡ እንላለን፡፡ እውነት ነው የእግዚአብሔር ስም ሲጠራ እንሰማለን ከእግዚአብሔር ስም በስተጀርባ ምን ይደረጋል እርሱ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ ገና ብዙ ነገር ይቀረናል እኮ ምንም አልገባንም ክርስትናው፡፡ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ስንቱ መጫኛ ያቆማል፣ ድውይ ይፈውሳል፣ የግሉን ገንዘብ ያካብታል መሰላችሁ፡፡ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ ውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፡፡ /ማቴ7÷15-16/ የበግ ለምድ የተባለው የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር ስም፣ ጥምጣሙ፣ ካባው፣ አስኬማው ነው፡፡ ይህ ከላይ የምናየው ለምድ ነው በግ የሚያስመስለው፡፡ ውስጡ ግን እምነቱ፣ ምግባሩ፣ ቅድስናው ወዘተ ተኩላዎች ነጣቂዎች ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ የሚያፈሩት ትውልድ ለእግዚአብሔር የሆነ አይደለም ለራሳቸው መመጻደቂያ፣ ቡና የሚያፈላላቸውን፣ ጫማ የሚያስርላቸውን፣ በየሔዱበት አባቴ አባቴ የሚሏቸውን ነው፡፡ ትውልዱ በዚህ አትደነቅ በመጨረሻው ዘመን ከዚህ የበለጠ ተአምር እንደሚሠራ መጽሐፋችን ይነግረናል፡፡ በምትሀት ፀሐይን እና ጨረቃን ይዞ የሚመጣ ትውልድ የሚነሣበት ዘመን ይመጣል ያን ጊዜ የተመረጡ የሚባሉት እንኳ እስኪስቱ ድረስ ብዙ ተአምራትን ያደርጋሉ፡፡ አስቡት እንግዲህ የምጡን መጀመሪያ ዛሬ በዚህ ተራ በሆነ ቀላል ነገር ሕዝቡ እንዲህ ካመነ ያን ጊዜ ማን ይሆን ጸንቶ የሚቆመው? ማንም ሰው እንዲህ አድርግ እንዲህ አታድርግ ተብሎ የሚመለስበት ጊዜ ላይ አይደለንም ነጻ ፈቃድ የራሳችን ነው፡፡ የፈለግነውን የመከተል መብታችን የራሳችን ነው፡፡ አመጸኛ ትውልድ ምልክትን ይሻል እንዲል መጽሐፉ ተአምራትን ቤተክርስቲያን ገብታችሁ ተመልከቱ፡፡ ጸበል ቦታዎች ሄደን መጽናት ሲደክመን በቀላሉ የተገላገልን እየመሰለን ሰው አንከተል፡፡ አጋንንት የሚወጡት በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ሐዋርያት በአንድ ወቅት አጋንንት ያደረበትን ሰው መፈወስ አልችል አሉ፡፡ ኢየሱስም መጣ እና ያንን አጋንንት አስወጣው፡፡ ሐዋርያቱም እኛ ለምን አላወጣነውም ብለው ጠየቁት እርሱም መልሶ እንዲህ አይነቱ መንፈስ በጾምና በጸሎት ካልሆነ በቀር አይወጣም አላቸው ይላል ማቴዎስ ወንጌል፡፡ ለዚህም ነው በጸበል ቦታ አጋንንት የሚቃጠሉት እዚያ ላይ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት አለ፡፡ በአጠቃላይ እውነተኛ ፈዋሽ እንዴት እናውቃለን ለሚለው የሚከተሉትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ መሟላት አለበት፡፡
     1.    ጸጋ እግዚአብሔር ያደረበት፡፡ ጸጋ ለመሆኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ሁልጊዜ አብሮን አይኖርም በዚህ ይታወቃል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ሃብተ ትንቢት እንደተነሣው ያለ ማለት ነው፡፡
     2.    የሚጾም፣ የሚጸልይ፣ የሚሰግድ፣ በእምነት የጸና
     3.    ለፈወሰበት ጸጋ ገንዘብ የማይቀበል፡፡
     4.    ጸጋው በአደባባይ እንዳይገለጥ የሚያደርግ፡፡ አባቶቻችን እንዲህ ድንቅ ተአምራትን በማድረጋቸው ሰው ከተአምራታቸው መሳተፍ ፈልጎ ሲመጣባቸው ይሰወራሉ ይጠፋሉ ቦታቸውን ለቀው ይሄዳሉ ምክንያቱም ከንቱ ውዳሴ እንዳይሆንባቸው ነው፡፡
     5.    ቃለ እግዚአብሔርን ብቻ የሚናገር
     6.    መፈወስን ሥራው ያላደረገ፡፡ ይህ ጸጋ ነውና አምላክ ሊሰጠንም ሊነሣንም የሚችል በመሆኑ የሁልጊዜ ተግባችን ሊሆን አይችልም፡፡ እነ ቅዱስ ጳውሎስ በጥላቸው ቢፈውሱ እግዚአብሔር ጸጋቸውን ለመግለጽ ሲፈልግ አደረገላቸው እንጅ ዋና መተዳደሪያ ሥራው አላደረጉም፡፡
     7.    እግዚአብሔር ቅድስናቸውን ለመግለጽ ሲፈልግ የሚያደርግላቸው መሆን አለበት፡፡
     8.    በመርኃ ግብር ዛሬ እዚህ ነገ እዚህ እያሉ የማይሉ ምክንያም ፈውስን ማድረግ የጸጋ እንጅ የባሕርይ ስጦታችን ስላልሆነ እግዚአብሔር በፈቀደው እርሱ በወደደው ቦታ እና ጊዜ ድንቅ ሥራውን ያደርጋል እንጅ እኛ በፈቀድነውና እኛ በወደድነው ቦታ እና ጊዜ መፈጸም አንችልምና፡፡
     9.    ሁሉም በሽታ ይድናል ብሎ የሚናገር፡፡ ደዌ ዘበጸጋ አለ ለጸጋ እግዚአብሔርን እንድናመሰግንበት ከአምላክ የሚሰጠን ደዌ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላቸው በልብሳቸው ሰውን ሁሉ እየፈወሱ እነርሱ ግን በሽታ ነበረባቸው፡፡ ለጸጋ የተሰጣቸው ነውና፡፡
ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ የተባልነው ያንን የሚሠሩትን ሥራ እንድንገመግም ነው፡፡ በበለጠ ገዳማት ሔዳችሁ እውነተኛ ፈውስ ምን እንደሆነ አረጋግጡ፡፡ በእምነት አትጎስቁሉ፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የዋሃንን ከሚያታልሉ ተኩላዎች ራስህን ጠብቅ መልእክቴ ይህ ነው፡፡
ትውልዱ ለምን አቋራጭ ፈውስን ፈለገ?
ጸበል እንደሚፈውስ ክርስቲያኖች ሁሉ ያምናሉ ግን ዓመት ሁለት ዓመት ደጅ መጽናትን ይጠይቃል፤ መጾም፤ መጸለይ፤ መስገድ መመጽወት ያስፈልጋል እነዚህ ግን ወዲያውኑ እንደሄዱ ፈውሱን ይፈጽሙላቸዋል ለነገ የሚያድር ነገር የለም፡፡ ሳይጾሙ ሳይጸልዩ ሳይሰግዱ በቀላሉ ሳይደክሙ ፈውስን አገኙ ማለት ነው ለዚህ ነው አብዛኛው እንደበግ ሲነዳ የሚውለው ግን ጊዜያዊ የሥጋ ፈውስ እንጅ ዘላለማዊ የነፍስ ፈውስን አያገኙም፡፡
ፈጸምኩ፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

No comments:

Post a Comment