Friday, March 3, 2017

ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፡፡ማቴ 16÷4፤12÷39 ---ክፍል ፪



© መልካሙ በየነ
የካቲት 24/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
የመብራት መጥፋት ለውኃ መሄድ ምልክት ነው፤ የዝናብ መዝነም ለመብራት መሄድ ምልክት ነው፡፡ ስለዚህ ዝናም ሊዘንብ ከሆነ ዛሬ መብራት ይጠፋል እንላለን፡፡ መብራት ከጠፋ ደግሞ ዛሬ ውኃ ትሄዳለች እንላለን፡፡ ይህ በቃ የተለመደ ምልክታችን ሆኗል፡፡ የሚገርመው ነገር በበጋ መብራት ሲጠፋ ምን እንላለን መሰላችሁ “ዛሬ ደግሞ ምን ሆነው ነው ያጠፉት ዝናም የለ ደመና የለ” እንላለን በቃ ምልክት አድርገን ይዘነዋላ፡፡ እንደዚህ ሁሉ አምላካችንንም አምላካችን ነው ብለን ለመቀበል ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን እንሻለን፡፡ አምላካዊነቱን ለመቀበል ግን የምንሻው ምልክት ተአምራዊ ሥራን ነው፡፡
ተአምር ከሰው ልጅ የአስተሳሰብ አድማስ በላይ ከኅሊናም በላይ ምጡቅ የማይደረስበት ለማንም የማይሰጥ ልዩ ጸጋ ነው፡፡ ከመደበኛው የሰው ልጅ ተግባራትና ክዋኔዎች የተለየ ድርጊት ነው፡፡
ተአምር የምንለው እንደ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ከጸጉራቸው ጫፉ ከልብሳቸው ዘርፉ ምንም ሳይነካ መውጣት ነው፡፡ ትን ዳን 3÷26 እዚህ ላይ ልብ በሉ የእሳት የሁልጊዜ ተግባሩ ማቃጠል ነው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን ቅዱሳን ማቃጠል ተሳነው፡፡
ተአምር ማለት እንደ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድሰት እየሉጣ በፈላ ውኃ መካከል ገብቶ ሳይቀቀሉ መውጣት ነው፡፡ /ድርሳነ ገብርኤል ዘሐምሌ 19 ተመልከት/ የፈላ ውኃ ከድንጋይ በቀር የተጣለለትን መቀቀል የሁል ጊዜ ተግባሩ ነው ሆኖም ግን ቅድስት እየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን መቀቀል አልቻለምና እንደቀዘቀዘ ሆኖ ታየ፡፡
ተአምር ማለት እንደ ዳንኤል ለተራቡ አናብስት ተጥሎ ምንም ሳይነኩ መውጣት ነው፡፡ ትን ዳን 6÷22 ተመልከት፡፡ አናብስት ያውም ርቧቸው ቀርቶ ጠግበውም ቢሆን እንኳ የተጣለላቸውን ያገኙትን ነገር አይምሩም ይሰባብራሉ እንጅ ይህ የአናብስት የዘወትር ግብራቸው ነው፡፡ ነገር ግን ዳንኤልን ሰባብረው ለመብላት አልቻሉም እንዲያውም ለመስገድ ተገደዱና ሰገዱለትዳንኤልን በልተውራባቸውን ከማስታገስ ይልቅ ረሃባቸውን መረጡ፡፡
ተአምር ማለት እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ በገባዖን ሰማይ ፀሐይን ማቆም በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃን ማዘግየት ነው፡፡ መጽ ኢያሱ 10÷12-14 ተመልከት፡፡ ፀሐይ የዘወትር ግብሯ ጊዜዋን ጠብቃ በምሥራቅ በኩል ወጥታ በማደሪያዋ ምዕራብ መግባት ነበር፡፡ ዛሬ ግን በኢያሱ ግዘት ጠላቱን ድል እስከሚያደርግ ድረስ ቆማ ቆይታለች፡፡
ተአምር ማለት እንደ ጴጥሮስ በውኃ ላይ እንደ የብስ መራመድ ነው፡፡ ማቴ 14÷29 ባህር እንደየብስ ሆና ሰው ሄዶባት አታውቅም ምክንያቱም የማስጠም ግብር አላትና፡፡ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ና ብሎታልና ቅዱስ ጴጥሮስ ሲራመድባት እንደየብስ ሆነችለት አላሰጠመችውም ነበር፡፡
ተአምር እንደ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሽባን ተነሥ ብሎ ማንሣት ነው፡፡ የሐዋ 3÷7 ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ዐንካሳ የነበረ ሰው ተንሥእ (ተነሣ) ሲባል አፈፍ ብሎ መነሣት አይችልም ነበር፡፡ የዚህ ደግሞ የባሰ ነበር መልካም በሚሏት መቅደስ ደጅ የሚያስቀምጡት ሰዎች ተሸክመው ወስደው ነበር፤ አሁን ግን የማንንም እርዳታ ላይጠይቅ ለመጨረሻ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ተነሥ ብለው አስነሡት፡፡ እርሱም ተነሥቶ እስኪዘል ድረስ ደስታውን ገልጿል፡፡
ተአምር ማለት እንደበለዓም አህያ እንደቢታንያ ድንጋዮች አፍ አውጥቶ መናገር ነው፡፡ ዘኁ 22÷28 አህያ አፍ አውጥታ ስትናገር ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማነው የበለዓምን አህያ ነው፡፡ አህያዪቱ በለዓም ያላየውን የተመዘዘ ሰይፍ የያዘውን መልአክ ተመልክታ መንገዷን መቀጠል አልችል ባለች ጊዜ በለዓም አብዝቶ ደበደባት፡፡ በዚህም የተነሣ እግዚአብሔር የአህያዪቱን አፍ ከፍቶ እንድትናገር አደረገ፡፡ በተመሳሳይ ሉቃ19÷40 ላይ ፈሪሳውያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሆሳዕና በአርያም እያሉ ያመሰግኑት የነበሩትን ደቀመዛሙርቱን ገስጻቸው አሉት፡፡ እርሱም መልሶ እነዚህ ዝም ቢሉ እንኳ የቢታንያ ድንጋዮች ያመሰግኑኛል አላቸው፡፡
ተአምር ማለት አንደ ኤልያስና እንደ ኤልሳዕ ሙትን ማንሣት ነው፡፡ ኤልያስ አንድ ሙት ኤልሳዕ ሁለት ሙት አነሥተዋል፡፡ 1ኛ 17÷22 ላይ “እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ የብላቴናው ነፍስ ወደርሱ ተመለሰች እርሱም ዳነ” ይላል፡፡ ኤልያስ እንዲህ የሞተውን ዮናስን አንሥቶታል፡፡ የኤልያስ በረከት እጥፍ ሆኖ ያደረበት ኤልሳዕም በሕይወቱ አንድ ከዐረፈ በኋላ ደግሞ አንድ በድምሩ ሁለት ሙታንን አንሥቷል፡፡ 2ኛ ነገ 4÷35 ላይ “ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕጻኑ ላይ ተጋደመ ሕጻኑም ዐይኖቹን ከፈተ” ይላል፡፡ ከዐረፈ በኋላም ኤልሳዕ 2ኛ ነገ 13÷21 “ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ” ይላል፡፡ የሞተ ሰው ሲነሣ ያየነው እንግዲህ በኤልሳዕና በኤልያስ ነው፡፡
ተአምር ማለት እንደሙሴ ባሕርን ከፍሎ ህዝብን በሰላም ማሻገር ነው፡፡ ዘጸ 14÷21-ፍጻ ተመልከት፡፡ ባህር ተከፍሎ ውኃ እንደግድግዳ ቆሞ የብስ ሆኖ ህዘብን ያሻገረ ባህር አይተን አናውቅም ነበር ዛሬ ግን ከእስራኤላውያን ጋር ስንሰለፍ በሙሴ በትር ባህር ሲከፈል ውኃ ግድግዳ ሆኖ ሲቆም እነሆ ተመለከትን፤ በደረቅ መንገድም እነሆ ሄድን፡፡
ተአምር ማለት እንደ ሐዋርያት፣ እንደ አባ ኤፍሬምና እንደ አባ ባስልዮስ፣ እንደ አባ ሕርያቆስ የማያውቁትን ያልተማሩትን አውቆ ተምሮ በቅቶ መገኘት ነው፡፡ የሐዋ ሥራ 2ን ስንመለከት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ እነርሱ ከሚያውቁት ከሚናገሩት ቋንቋ በተጨማሪ 71 ቋንቋ ተገልጾላቸው ህዝቡን ሁሉ በየራሳቸው ቋንቋ ለማስተማር በቅተዋል፡፡ ውዳሴ ማርያም የሰኞ አንድምታን ስንመለከት ደግሞ በአስተርጓሚ ሲጨዋወቱ የነበሩት ባስልዮስና ኤፍሬም በጸሎታቸው የባስልዮስ ቋንቋ ጽርእ ለኤፍሬም፤ የኤፍሬምም ቋንቋ ሱርስት ለባስልዮስ ተገልጾላቸው ያለአስተርጓሚ ተነጋግረዋል፡፡ በቅዳሴ ማርያም ምእራፍ 1 አንድምታ ላይ ስንመለከት ደግሞ የምናገኘው አባ ሕርያቆስን ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ ያልተማረ ግበረ ገብ ካህን ነው፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ትእቢት የያዛቸው ካህናት ነገር ሰሩበት፡፡ ቀድሰህ አቁርበን እንበለው ብለው ተነሡበት፡፡ በዚህም መሠረት ቀድሰህ አቁርበን አሉት፡፡ ከዚያም ከፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግረውን ማንን እናውጣለት እያሉ ነገር ሲሠሩ እነሆ የአምላክ እናት ምሥጢርን ሁሉ ገልጣለት “ጎሥዐ ልብየ ቃለ ሰናየ፤ ልቤ መልካም ነገርን አወጣ” ብሎ አዲስ ቅዳሴ ለመድረስ በቅቷል፡፡
ይቀጥላል
ይቆየን፡፡

No comments:

Post a Comment