Wednesday, May 24, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፮

© መልካሙ በየነ

ግንቦት 9/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
09/09/09 ታሪካዊ ቀን!!!
፭ኛ አንቀጽ
ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት ተከፍሎ በሌለባት በአንዲት ባሕርይ ያለ የከዊን ስም ነው፡፡
የከዊን ስም “ልብ” አብ ለራሱ ለባዊ አዋቂው (አዋቂ) ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልቡና (ዕውቀት) መሆኑን የ ሚያመለክት ስም ነው:: ቃልም የወልድ የከዊን ስም ነው:: ለራሱ ነባቢ (ተናጋሪ) ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ መሆኑ የሚገለጽበት የከዊን (ቃል የመሆን) ስሙ ነው:: እስትንፋስ የመንፈስ ቅዱስ የከዊን ስሙ ነው:: መንፈስ ቅዱስ ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወት እንደሆነ የምና ውቅበት የከዊን (ሕይወተ አብ ወወልድ) የመሆን ስሙ ነው:: ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት ተከፍሎ በሌለባት በአንዲት ባሕርይ ያለ የከዊን ስም ነው፡፡ ይኸውም ልዩነት ሳለበት አንድነት አንድነትም ሳለበት ልዩነት አለበት:: ልዩነቱ በከዊን ነው አንድነቱ ግን በሕልውና መገናዘብ ነው:: ወልድ ሰው ሆነ በተባለ ጊዜ አካል ተዋሐደ እንጂ ባሕርይ አልተዋሐደም እንዳይባል ወንጌላዊ ቃል ሥጋ ኮነ አለ እንጂ ወልድ ሥጋ ኮነ አላለም:: ባሕርይም ከተዋሐደ የሥላሴ ባሕርይ አንድ ነውና:: ፫ቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ ከልብና ከእስትንፋስ ለይቶ “ቃል ሥጋ ኮነ” አለ:: ቃልም ማለት በአካለ አብና በአካለ መንፈስ ቅዱስ በኮዊን የምትለይ በሕልውና የምትገናዘብ እንደሆነች “ነገር በምሳሌ መዝሙር በሃሌ እንደተባለው አስቀድመን ምሳሌውን መርምረን በሁለተኛው አንቀጽ በነፋስና በፀሐይ በእሳትና በቀላይ መስለን ተናግረናልና በማስተዋል ይመለከቷል:: መለኮት እንደ አካላት ከ፫ ይከፈላል የሚል ሰው ይህን ነገር ከራሱ አንቅቶ በልብ-ወለድ ቃል ተናግሮታል እንጂ መጻሕፍት ከተናገሩት ኃይለ ቃልና ከመሰሉት ምሳሌ ምስክር አምጥቶ ለማስረዳት አይችልም:: የሥላሴን ባሕርይና አካል እንደ ሰው ባሕርይና አካል አድረጎ አካል የሌለው ባሕርይ፣ ባሕርይም የሌለው አካል የለምና ባሕርይ፣ አካልን ተከትሎ ከሦስት ይከፈላል ይላል:: መልስ:- ባያስተውለው ነው እንጂ ይህ ነገር ከሰማይና ከምድር ይልቅ የተራራቀ ነው:: የሰው ባሕርይ በአካል ቢከፈል በየራሱ ልብ፣ በየራሱ ቃል፣ በየራሱ እስትንፋስ ያለው ሆኖ በየራሱ ልዩ ልዩ ሥራውን ይሠራል:: አንዳንድ ቅዱሳንም በፀጋ ቢተዋወቁና አንዳንድ ሥራ ቢሠሩ ያደረባቸው መንፈስ ቅዱስ በሀብት አገናኝቷቸው ነው እንጂ የባሕርይና የሕልውና አንድነት ኖሯቸው አይደለም::ሥላሴ ግን አካላቸው የተለየ ሲሆን ባሕርያቸው ተከፍሎ የሌለበት አንድ ለመሆኑ ማስረጃው የሦስቱ ልብ አንድ አብ ሆኖ አንድ ዕውቀትን ያውቃሉ:: የሦስቱ ቃል አንድ ወልድ ሆኖ አንድ ነገርን ይናገራሉ:: የሦስቱ እስትንፋስ አንድ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ አንድ የሕይወትን ሥራ ይሠራሉ:: እንዲህም ከሆነ ሊቃውንት “ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት” ያሉትን ተመልክቶ ይልቁንም “አጤን ይበልጡ ቃለ አጤ'' እንዲሉ እርሱ ባለቤቱ “አነ ወአብ ፩ ንሕነ፤ እኔና አብ አንድ ነን” ዮሐ ፲÷፴:: “አነ በአብ ወአብ ብየ'' "እኔ በአብ ሕልው ነኝ አብም በእኔ ሕልው ነው” ዮሐ ፲፯፤፲:: ያለውን ተረድቶ ባሕርየ መለኮት በአካል ከሦስት የማይከፈል መሆኑን ማመን ይገባል:: ከዚህ ግን ወጥቶ መለኮት እንደ አካላት ከሦስት ይከፈላል ማለት ግን አብን ልብ ወልድን ቃል መንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ ማለትን ትቶ፣ ለሦስቱ በየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ አላቸው ብሎ፣ ሦስት አማልክት በማለት የዮሐንስ ተዐቃቢን ሃይማኖት መመስከር ነው:: ይወልደዋል አይቀድመውም ማለት ቅሉ አካል በተከፍሎ ሲለይ፣ አንድ ባሕርየ መለኮት ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ ሦስቱን አካላት በማገናዘብ /ማዋሐድ/ በቅድምና የነበረ ስለሆነ ነው:: ይህንም ለመረዳት:- ባስልዮስ ዘቂሣርያ የተናገረውን ይመልከቱ:: ፲፪ኛ ንባብ:- “ይደልወነ ናእምር ኀበ ኅብረተ ተዋሕዶተ መለኮት ዘ ፫ አካላት፣ ወናስተዋሕድ በአኀብሮ ዘዚአሆሙ ፩ መለኮት:: ንእመን በሃይማኖት ከመ ይትወሐድ መለኮት በአብ:: እስመ እምኀበ አብ ተወልደ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስሂ ወፅአ እምኔሁ:: እንዘ ኢይቀድም ፩ እምካልኡ፣ ወካልኡ እምሣልሱ፣ ወበልደተ ወልድ ወበጸአተ መንፈስ ቅዱስ እምአብ፣ ይትወሐድ መለኮተ ሥላሴሁ ለአምላክነ” ትርጉም:- “በአንድ መለኮት ተዋሕዶ የሦስቱን አካላት መገናዘብ ልናውቅ ይገባል:: በአንድ መለኮት በማገናዘብም ልዩ ልዩ የሆነ አካላትን እናዋሕድ:: መለኮት አንድ እንደሆነ በማመን፣ በአብ ያለ መለኮት ወልድን መንፈስ ቅዱስን እንዲዋሐድ እንመን:: አብ ከወልድ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ ሳይቀድም፣ ወልድ ከአብ ተወልድዋልና፣ መንፈስ ቅዱስም ከርሱ ሠርፆአል፣ ከአብ ወልድ በመወለዱ፣ መንፈስ ቅዱስም በመሥረፁ፣ የአምላካችን የሦስትነቱን አካል መለኮት ይዋሐዳል” ብሏልና:: (ክፍል ፪ ) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፴፪ ÷ ክፍል ፪ ቁ. ፬-፮ አሁን በዚህ መስመር ያነበብውን የባስልስዮስን ቃል አስተውሎ የሚመለከት ሰው:- መለኮትን በአካል ሦስት ማለት ከሚያመጣው ፫ ልብ፣ ቃል፣ ፫ እስትንፋስ ከማለት ተጠብቆ በአብ ልብነት ለባውያን፣ በወልድ ቃልነት ነባብያን፣ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሕያዋን ብሎ በአካል ፫ በመለኮት አንድ በምታሰኝ ሃይማኖት ይፀናል:: መለኮት እንደ አካላት ከሦስት ይከፈላል የሚል ሰው ግን ወልድ ከአብ የሚወለደው ልደት ሰው ሁሉ ከአባቱ እንደሚወለደው ልደት ነው ማለቱ እንደሆነ ጠንቅቆ ማስተዋል ያሸዋል:: ማናቸውም ልጅ ከአባቱ ሲወለድ ባሕርዩ በአካል የሚከፈልና የሚለይ ስለሆነ አባት ከልጁ ይቀድማል ይበልጣልም:: ማስረጃ:- ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ ፳ኛ:- ንባብ:- “ወእመሰ ኮነ ብእሲ አበ፣ ክሡት ነገሩ ከመ የዐቢ አብ እምወልድ:: ወስሞሂ ያጤይቅ ከመ ውእቱ እምቅድመ ወልዱ::'' ትርጉም:- “ሰው አባት ሲባል ከልጁ እንዲበልጥ ነገሩ የታወቀ ነው:: አባት መባሉም ከልጁ አስቀድሞ እንደነበረ ያስረዳል'' እንዳለ:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ÷ ክፍል ፩ ቁ. ፰ ወልድ ግን ከአብ ሲወለድ አካሉ በተከፍሎ ቢለይም ሕላዌ መለኮት በተከፍሎ መለየት የለበትም:: አወላለዱም ብርሃነ ፀሐይ ተከፍሎ መለየት ሳይኖርበት ከክበብ እንዲገኝ በሕላዌ መለኮት ከአብ ተከፍሎ መለየት ሳይኖርበት ነውና፣ መቅደም መቀዳደም መብለጥ መበላለጥ የለበትም:: አሁን ማስረጃ አድርገን የጠራነው ቴዎዶጦስ:- ንባብ:- “ወለነሰሂ ይደልወነ ነሐሊ ዘንተ በሕላዌ መለኮት:: አላ ነአምን በወልድ ዋሕድ ከመ ውእቱ ቀዳማዊ ምስለ አብ በኩሉ ዘመን፣ ወወልደ አብ ዋሕድ ይሰመይ ብርሃነ፣ እስመ ብርሃን ዘተወልደ እምብርሃን፣ ኢይትበሀል ተወልደ እምድኀረ ብርሃን አላ በጊዜ ዘኮነ ቦቱ ውእቱ ብርሃን፣ ይትረከብ ብርሃን ዘተወልደ እምኔሁ፣ ወወትረ ሕልው ምስሌሁ:: ብርሃንኒ ያጤይቀከ አምሳሊሁ ለወልድ ዘውእቱ ሕልው ምስለ አብ በኩሉ ጊዜ እምቅድመ ኩሉ ዓለም::'' ትርጉም:- “በመለኮት ባሕርይ ይህን ማሰብ ለእኛ አይገባንም፣ ወልድ ዋሕድ በዘመን ሁሉ ከአብ ጋር የነበረ ቀዳማዊ እንደሆነ እናምናለን እንጂ፣ ከአብ የተወለደ ዋሕድ ቃልም ብርሃን ይባላል:: ከክበብ የተገኘ ብርሃን ከክበብ በኋላ ተገኘ አይባልምና:: ብርሃን ክበብ በተገኘበት ጊዜ ተገኝቶ ከክበብ ሳይለይ አብሮ ይኖራል እንጂ፣ ብርሃንም የወልድ ምሳሌነቱን ያስረዳሃል ይኸውም ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ከአብ ጋራ ሁልጊዜ የነበረ ነው'' እንዳለ:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ክፍል ፩ ቁ. ፱ ይህን ምሳሌ ጠንቅቀን ብንመለከት አማናዊውን አጉልቶ ያሳየናል:: የሰውም ቃል በተወለደ ጊዜ አወላለዱ አሁን በተናገርነው በብርሃንና በክበብ አምሳል ነው:: ቃል ከልብ በተከፍሎ መለየት ሳይኖርበት፣ በአካል ከዊን ይወለዳል፣ በአካል ከዊን ተለይቶ መወለዱንም የሚያስረዳ ነገር፣ ከብራና ላይ በቀለም በተጻፈ ጊዜ አካል ገዝቶ ይታያል ይነበባልም:: ባሕርዩ ግን በተከፍሎ መለየት የለበትምና በልብ ውስጥ ሕልው ሆኖ ሲታሰብ ይኖራል:: ማስረጃ:- ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ ፳፭ኛ:- ንባብ:- “ወለከሂ ቃልከ ዘይትወለድ እምልብከ ይሄሉ ውስቴትክ ተወሊዶ እምልብከ::''  ትርጉም:- “ያንተስ ስንኳ ከልብህ የሚገኝ ቃልህ፣ ከልብህ ተገኝቶ፣ በልብህ ውስጥ ሕልው ሆኖ ይኖራል'' እንዳለ:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩)  ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ክፍል ፩ ቁ. ፲፯ ንባብ:- ዳግመኛም “ወህየንተ ልብ ዘዝየ ነአምሮ ለአብ ህየ፣ ወህየንተ ቃል ዘዝየ ነአምሮ ለቃል ዘእግዚአብሔር ከመ ቦቱ ሕላዌ ወቦቱ አካል በፍጹም ገጽ ወመልክዕ፣ ዘከመ ገጸ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ እስመ ውእቱ ወልዱ ለአብ::'' ትርጉም:- “በኛ ባለ በልብ አምሳል አብን እናውቀዋለን:: እንደ አብና እንደ መንፈስ ቅዱስ ባለ በፍጹም ገጽ በፍጹም መልክዕ አካልና ባሕርይ እንዳለው፣ በእኛ ባለ በቃል አምሳል ቃለ እግዚአብሔር ወልድን እናውቃለን፣ አብን አህሎ መስሎ የተወለደ የአብ ልጅ ነውና” ብሎ የአብ ልብነት በልብ፣ የወልድ ቃልነት በቃል፣ የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በእስትንፋስ መመሰላቸውን ያስረዳል:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ዝኒ ከማሁ ቁ ፳ ልጅ ከአባቱ ባሕርይ በአካል ተለይቶ የሚከፈል ስለሆነ አባትና ልጅ አንድ ልብ አንድ ቃል አንድ እስትንፋስ በመሆን አይገኙም:: ወልድ ግን ከአብ ሲወለድ፣ ባሕርይ እንደ አካሉ የማይከፈል አንድ ስለሆነ፣ ሦስት አካላት በአንድ ልብ በአንድ ቃል በአንድ እስትንፋስ ተገናዝበው ይኖራሉ:: ይህንም ለመረዳት በየአንቀጹ የተነገረውን መመልከት ነው::
፮ኛ አንቀጽ
ወልድ ማለት የተረክቦ ስሙ እንደሆነ ይናገራል (ተረክቦ ማለት መገኘት ማለት ነው) ወልድ ማለት አካሉ በቃልነቱ ከዊን ተድኀሮ  ሳይኖርበት (ወደ ኋላ ሳይቀር) አብን አህሎ መስሎ ከአብ አካል በመገኘቱ የሚጠራበት የተረክቦ ስሙ ነው:: ተረክቦውም ተፈልጦ ሳይኖርበት በሕልውና እያለ ነው:: የነፍስ ቃሏ ከልብነቷ ተገኝቶ ሳይለይ አካሏ ሕልው ሆኖ እንደሚኖር ማነጻጸር ነው:: ማስረጃ:- ቄርሎስ በእስተጉቡእ: ንባብ:- “ወልድ ዋሕድ በሕላዌሁ ዘእምኀበ እግዚአብሔር አብ ይሰመይ ቃለ፣ እስመ ፩ ውእቱ ተወለደ እም ፩ አብ::''ትርጉም:- “ወልድ ዋሕድ ከእግዚአብሔር አብ ተወልዶ በአብ ሕልው ሆኖ በሚኖርበት ባሕርዩ ቃል ይባላል:: “አንዱ እርሱ ከአንድ አብ ተወልዷልና” ብሏል:: ተወላዲ ማለት ግን በተከፍሎ የሚጠራበት የግብር ስሙ ነው:: ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት በግሥ አንቀጽ መልክ ፊደሉ አንድ ሲመስል፣ የምሥጢር ልዩነት እንዳለው አሁን የተናገርነውን የተረክቦንና የተከፍሎን ምሥጢር ጠንቅቆ ማስተዋል ነው:: ተረክቦ ያልነውም የአካሉ ሕላዌ ከአብ አካል የተለየ ሆኖ በፍጹም ገጽና በፍጹም መልክ መታወቁ ነው እንጂ፤ እግዚአበሔር የተገኘበት ጊዜ አይደለም:: ማስረጃ:- ሱኑትዩስ:- ንባብ:- “ወኢይትረከብ ሀልዎቱ እምኃበ ወኢምንትኒ”ትርጉም:- “አኗኗሩ ከምንም ከምን አይገኝም” እንዳለ:: “ከምንም ተገኘ አይባልም” ሃይማኖተ አ በው ምዕ ፻፲ ክፍል ፪ ቁ. ፬ ሠለስቱ ምዕትም በቅዳሴ:- ንባብ:- “ኢይክል መኑሂ ይባዕ ማዕከለ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ያዕምር ዘከመ እፎ ህላዌሁ፣ ወለዶ አብ ለወልዱ ኢይትበሀል ዘጊዜ ወበዘከመዝ መዋዕል ወለዶ፤ ኢይትአመር ልደቱ እም አብ እስመ ዕፁብ ውእቱ፣ ወኢይትአወቅ ህላዌሁ እስመ ስውር ውእቱ” ትርጉም:- “ማንም ማን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መካከል ሊገባ አይችልም:: አኗኗሩ እንደምንም እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፣ አብ ልጁን ወልዶታል:: ነገር ግን አብ ልጁን በዚህ ጊዜ እንዲህም ባለ ዘመን ወለደው አይባልም፤ ከአብ መወለዱ አይመረመርም፣ የሚያስጨንቅ ነውና፤ አኗኗሩ አይታወቅም የተሰወረ ነውና፤” እንዲሉ:: ተከፍሎም በመለየት እንደሆነ የሚያስረዳ ሊቃውንት በብዙ አንቀጽ ገልጸዋል:: ንባብ:- “ተጋብኦ በተከፍሎ ወተከፍሎ በተጋብኦ” ትርጉም:- "አንድነት በመለየት መለየትም በአንድነት አለ” ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፮÷ ፫ ፵፱ኛ አትናቴዎስ ዘአንጾኪያ ፶፪ኛ ሱኑትዩስ ዘእስክንድርያ ፶፬ኛ ክርስቶዶሉ ዘእስክንድርያ እመልዕክተ ሲኖዲቆን አንቀጽ ሁለተኛ እይ ፩. ፪. ፫. ንባብ፦ “ኀቡራን እንበለ ተሌልዮ ወሊሉያን እንበለ ትድምርት” ትርጉም:- “ባለመለያየት አንድ ናቸውና አንድ ባለመሆንም ልዩ ናቸው” እያሉ ይናገራሉና:: (ቆዝሞስ ዘእስክንድርያ ክፍል ፩ኛ ሃይ.አበው ፵፪ኛ)ሃይማኖተ አበው ምዕ ፺፭ ÷ ፫ ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት፣ በምሥጢር ልዩነት እንዳለበት በዚህ ማስተዋል ነው::
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

Tuesday, May 16, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፭



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 8/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
 ======================================================
፫ኛ አንቀጽ
ሥላሴ በመለኮት አንድ የሚሆንበትን ምሥጢር ያሳያል፡፡
ሐተታ- ሥላሴ በመለኮት አንድ መባላቸው በብዕል አንዱ ከአንዱ ሳይበልጥ አንዱም ከአንዱ ሳያንስ የሚተካከሉ ባለጸጎች፣ ብዕላቸው በየቤታቸው ሳለ በመተካከላቸው አንድ እንዲባሉ መለኮታቸው በየአካላቸው ሳለ በክብር ስለተካከሉበት ነው ማለት ይገባናልን? መልስ፦ አይገባም:: ሥላሴ በመለኮት አንድ መባላቸውስ፣ መለኮት እንደ አካላት ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ በአንድነቱ ፀንቶ፣ አካላትን በተከፍሎ ሳሉ በሕልውና እያገናዘበ፣ አንድ ልብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ እስትንፋስ ስላደረጋቸው ነው እንጂ በክብር ስላስተካከላቸው አይደለም:: መለኮት ከአካል ጋር ከሦስት የሚከፈልስ ከሆነ አንድ ልብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ እስትንፋስ መሆን የለም:: ይህም ከሌለ በአብ ለባውያን፣ በወልድ ነባብያን፣ በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን መባል አይገኝም:: እንዲህም ከሆነ በአንደኛው አንቀጽ የተጠቀሰው አቡሊድስ:- ንባብ፦ “ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስኒ መንፈሶሙ ለአብ ወለወልድ፤ ወልድም ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው፣ መንፈስ ቅዱስም ለአብና ለወልድ እስትንፋሳቸው (ሕይወታቸው) ነው” ሃይማኖተ አበው  ያለው ሐሰት ሆኖ በየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አላቸው በማለት እንደ ዮሐንስ ተዐቃቢ ዘጠኝ መለኮት ያሰኛል:: ዮሐንስ ተዐቃቢ ከዚህ ሌላ አልተናገረምና:: ሕልውናም እንዲያገናዝባቸው::  ሃይማኖተ አበው ምዕ ፴፱ ÷፰-፱

ማስረጃ፦ ባለቤቱ ጌታችን:-
ንባብ፦ “ለግብርየ እመኑ ከመ ታእምሩ ወትጠይቁ ከመ አነ በአብ ወአብ ብየ::'' ትርጉም፦ “በሥራዬ እመኑ ታውቁ ትረዱም ዘንድ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ'' ብሏልና:: ዮሐ ፲፣፴፰ ንባብ፦ ዳግመኛ “ኢተአምንሁ ከመ አነ በአብ ወአብ ብየ፣ ወዝኒ ቃል ዘአነ ነገርኩክሙ አኮ ዘእምኀቤየ ዘነበብኩ አላ አብ ዘሀሎ ብየ ውእቱ ይገብሮ ለዝንቱ ግብር” ትርጉም፦ “አታምንምን እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ:: ይህ ለእናንተ የምነግራችሁ ነገር ከኔ ከራሴ የተናገርኩት አይደለም:: በእኔ ያለ እርሱ አብ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ” ብሎ ለፊልጶስ ነግሮታል:: ዮሐ ፲፬፣፲
ዮሐንስ ዘአንጾኪያም ፶፭ኛ:-
ንባብ፦ “አንኮ ዘንተአመን በ፫ እደው በ፫ አማልክት ወኢ በ፫ መለኮት አላ ንትአመን በ፫ አካላት ወበ፫ ገጻት እንተ ፩ ባሕርየ መለኮት” ትርጉም፦ "መገናዘብ እንደሌላቸው እንደ ፫ ሰዎች አድርገን በሦስት ሰዎች፣ በሦስት አማልክት፣ በሦስት መለኮት የምናምን አይደለንም:: ባሕርየ መለኮት አንድ በሚያደርጋቸው በሦስት አካላት በሦስት ገጻት እናምናለን እንጂ'' ብሏል:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ሃይማኖተ አበው  ምዕ ፻፲፬ ፥ ፮-፯ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ዮሐንስ:- ንባብ፦ “ንሕነ ንትአመን ከመ አብ ሕልው በወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወልድኒ ሕልው በአብ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወመንፈስ ቅዱሰኒ ሕልው በአብ ወወልድ'' ትርጉም፦ “አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሕልው እንደሆነ፣ ወልድ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ሕልው እንደሆነ፣ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ሕልው እንደሆነ እኛ እናምናለን'' ብሏል:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፯) ሃይማኖተ አበው  ምዕ ፺ ፥ ፲፩ ዲዮናስዮስም መለኮትን እንደ አካላት ብንለይ፣ ሰይጣናዊ እምነትን እናምናለን ማለቱ፣ መለኮትን ሦስት ብሎ፣ ሦስትነት ያለው አኃዝ በመለኮት ከተነገረ፣ መንገዱ የዮሐንስ ተዐቃቢ ነውና እምነቱ ሰይጣናዊ መሆኑን ሲያስረዳ ነው:: መጻሕፍት ሁሉ “ይትወሐዱ በመለኮት” እያሉ፣ ለአካላት ማስረጃ ያደርጉታል እንጂ መለኮትን ሦስት ብለው የሚከፍሉበት አንቀጽ አይገኝም:: ስለዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ መጻሕፍት ከተናገሩት ትምህርት ሳይወጡ ማመን ይገባል:: በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ መጻሐፍትን በድፍረትና በትዕቢት ሳይሆን በፈሪሃ እግዚአብሔርና በትሕትና ሆኖ የሚመለከታቸውን በአካል ሦስት፣ በመለኮት አንድ የሚያሰኘውን የሃይማኖት ምስጢር በመግለጽ ይጠቅማሉና:: ማስረጃ፦ ቅዱስ ጳውሎስ:- ንባብ፦ “ወኲሉ መጽሐፍ ዘበመንፈሰ እግዚአብሔር ተጽሕፈ ይበቁዕ በኲሉ ትምህርት ወተግሣጽ ወአርትኦ ወአጥብቦ ወጽድቅ፣ ከመ ይትገሠጽ ብእሴ እግዚአብሔር ውስተ ኲሉ ምግባረ ሠናይ::'' ትርጉም፦ “በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ መጽሐፍ ሁሉ፣ ፍፁም ትምህርትንና ምክርን በመሆን፣ ልቦናን በማቅናትና በማራቀቅ ጽድቅንም በማሠራት ይረባል ይጠቅማል፣ የእግዚአብሔር ሰው በጎ ሥራን ሁሉ ይማር ዘንድ'' እንዳለ:: ፪ኛ ጢሞ. ፫:፲፮-፲፯
፬ኛ አንቀጽ
ሥላሴን በባሕርይና በአካል፣ በግብርም የሚጠሩበትን ስም ለይቶ ያሳያል፡፡
ከብዙ ስሕተት የሚያደርስ የሥላሴ የስማቸውን ምሥጢር ለይቶ አለማወቅ ነው:: በባሕርይ የሚጠሩበት ስም አለ:: በአካል የሚጠሩበት ስም አለ፣ በግብር የሚጠሩበት ስም አለ:: በባሕርይ የሚጠሩበትን ስም ለአካልና ለግብር፣ በአካል የሚጠሩበትን ስም ለባሕርይና ለግብር፣ በግብር የሚጠሩበትን ስም ለባሕርይና ለአካል ሰጥተው ሲናገሩ የአንድነታቸው፣ የሦስትነታቸው ምሥጢር ፈራሽ ሆኖ ይገኛል:: ስለዚህ ጠንቅቆ አስተውሎ መመልከት ይገባል:: አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ መባል የአካል ስም ነው:: አብ ማለት ጥንት መሠረት መገኛ ማለት ነው:: ጥንት መሠረት መገኛ በመሆንም ወላዲ አሥራጺ ይባላል:: ጥንት መሠረት አስገኝ በመሆን ወላዲ አሥራጺ ተባለ እንጅ ወላዲ አሥራጺ በመሆኑ አብ የተባለ አይደለም:: ይህንም ለመረዳት ጎርጎርዮስ ፲፰ኛ የተናገረውን መመልከት ነው:: ንባብ፦ “አእምር ኲሎ ግብረ፣ እም፫ ግብራት፣ ዘውእቶሙ አስማት፣ ወውእቱ ፍጥረት ወስም ወዘመድ ዘይተበሀል ሰብእ ወገብር ወመጋቢ:: ሰብእሰ በእንተ ፍጥረተ ጠባይዒሁ ወገብርኒ በእንተ ግብርናቲሁ ወመጋቢኒ በእንተ ስም ዘተሠይመ:: ወናሁ ንቤ ካዕበ በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአኮ እሉ አስማት ዘቦኡ ላዕሌሆሙ ድኀረ አላ እሙንቱ አካላት:: ወብሂለ ሰብእሂ አኮ ውእቱ ስም ዳዕሙ ውእቱ ፍጥረቱ:: እስመ ለኩሎሙ ሰብእ ቦሙ ፩ ስም በበይናቲሆሙ ለለ፩ እምኔሆሙ:: እሉ እሙንቱ አዳም አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ:: ወአቃኒመ እግዚአብሔርሰ እሙንቱ አስማት ወአስማትኒ እሙንቱ አቃኒም እስመ ትርጓሜሁ ለአቃኒም፣ አካላት ጽኑዓን ወቀዋምያን ፍጹማነ ገጽ ወመልክዕ ብሂል:: ወሥሉስ ቅዱስ ይሰመዩ አስማተ ጽኑዐነ::'' ትርጉም፦ “በ፫ አካላት ያለውን ግብር ሁሉ በሦስት ግብራት እወቅ እኒህም ፍጥረት፣ ስም፣ ዘመድ የሚባሉ ስሞች ናቸው:: ፍጥረት የተባለው ሰብእ (ሰው) መባል ነው:: ስም የተባለው ገብር (አገልጋይ) መባል ነው:: ዘመድ የተባለውም መጋቢ መባል ነው:: ሰብእ መባሉ ስለ ባሕርዩ መገኘት ነው:: ገብር መባሉም ተገዥ ስለሆነ ነው:: መጋቢ መባሉ ስለተሾመ ነው:: ሰው ስለ አካሉ መገኘት “ሰብእ” እንደተባለ ስለ አካላቸው ሕላዌ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ:: ስለ ተገዛ ገብር፣ ስለ ተሾመም “መጋቢ” እንዲባል ስለ ወለደ ወላዲ፣ ስለተወለደ ተወላዲ፣ ስለ ሠረጸ ሠራጺ እንላለን:: እኒህም ስሞች አካላት ሲኖሩ የኖሩ ናቸው እንጂ ኑረው ኑረው ኋላ የተጠሩባቸው አይደለም:: ሰብእ መባልም በተፈጥሮው የወጣ ስም ነው እንጂ ኋላ የወጣ ስም አይደለም:: ለሰዎች ሁሉ እያንዳንዳቸው የሚጠሩበት ኋላ የወጣላቸው ስም አለና:: ይኸውም አዳም፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ እንዳለው ነው:: የእግዚአብሔር ዓቃኒም ግን አስማት ናቸው:: አስማትም ዓቃኒም ናቸው:: የዓቃኒም ትርጓሜ በመልክ፣ በገጽ፣ ፍጹማን ሆነው፣ ፀንተው የሚኖሩ አካላት ማለት ነውና:: ልዩ ሦስት የሚሆኑ አካላትም ፀንተው በሚኖሩ በነዚህ ስሞች ይጠራሉ'' ብሏል:: (ሃይማኖተ አበው ድርሳን ፩ኛ) ጎርጎርዮስ ገባሬ ተአምራት ሃ.አበው ምዕ ፲፫ ክፍል ፩ ቁ. ፬-፮

መቃርዮስ ዘእስክንድርያም ፵፫:-
ንባብ፦ “ወአስማቲሆሙ ለአካላት አኮ ግብር ከንቱ ሶበ ንሰምዮ ለአብ አበ፣ በእንተ ዘኮነ ወላዲ ወለ ወልድኒ ወልደ በእንተ ዘተወልደ እምአብ፣ ወለመንፈስ ቅድስኒ መንፈስ ቅድስ በእንተ ዘውጽአ እምአብ::'' ትርጉም፦ “አብ ስለ ወለደ አብ ብንለው፣ ወልድንም ከአብ ስለተወለደ ወልድ ብንለው፣ መንፈስ ቅዱስንም ከአብ ስለሠረፀ መንፈስ ቅዱስ ብንለውም አካላት ስማቸው ግብር የሌለው ከንቱ አይደለም'' ብሏል:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ሃ ይማኖተ አ በው ምዕ ፺ ፰፥ ክፍል ፩ ቁ. ፬ ነገር ግን አንባቢ ሆይ አብን በእንተ ዘኮነ ወላዲ፣ ወልድንም በእንተ ዘተወልደ፣ መንፈስ ቅዱስም በእንተ ዘሠረጸ ስላለ (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) የግብር ስም መስሎህ እንዳትሳሳት:: አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት የአካል ስም መሆኑን አስተውል:: አካል ግብርን ያስገኛል እንጂ ግብር አካልን የሚያስገኝ አይደለምና መጻሕፍትም የፊቱን ወደ ኋላ የኋላውን ወደ ፊት ማድረግ ልማድ ነው:: ማስረጃ፦ ጌታችን:- ንባብ፦ “አልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ እጓለ እመሕያው::'' ትርጉም፦ “ማንም ወደ ሰማይ የወጣ የለም:: ከሰማይ የወረደው ነው እንጂ፣ እርሱም የሰው ልጅ በሰማይ የሚኖር'' እንዳለ ዮሐ ፫ ፤ ፲፫:: ንባብ፦ጳውሎስም:- “ክርስቶስ ውእቱ ዘወረደ እም ሰማይ'' ትርጉም፦ “ከሰማይ የወረደ ክርስቶስ ነው'' እንዳለ:: ሮሜ ፲፥፯ ዳግመኛም ንባብ፦ “ወዳግም ብእሲ እምሰማይ ሰማያዊ'' ትርጉም፦ “ከሰማይ የመጣው ሁለተኛው ሰው ሰማያዊ ነው'' እንዳለ:: ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ፤ ፵፯ ይህን የመሰለ በየአንቀጹ ብዙ አለና ያስተውሏል:: አካል በመለኮት ከዊን ይገናዘባልና መለኮት ተብሎ ይጠራል:: የአካል ግብር አይገናዘብምና ወላዲ መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት፣ ሠራጺ መለኮት ሊባል አይገባም:: የሚለያዩበትም የግብር ስም በመሆኑ ሦስት መለኮት ከማለት የሚያደርስ ይመስላልና/ያደርሳልና/ አብ መለኮት፣ ወልድ መለኮት መንፈስ ቅዱስ መለኮት ቢል ግን አካል በመለኮት ከዊን የሚገናዘብ ስለሆነ አያስነቅፍም:: አንባቢ ሆይ ሥላሴ በባሕርይና በባሕርይ ግብር፣ በአካልና በአካል ግብር፣ የሚጠሩበት ስም አለና:: በባሕርይ የሚጠሩበትን በአካል ከሚጠሩበት፣ በአካል የሚጠሩበትን በባሕርይ ከሚጠሩበት፣ በባሕርይ ግብር የሚጠሩበትን በአካል ግብር ከሚጠሩበት፣ በአካል ግብር የሚጠሩበትን በባሕርይ ግብር ከሚጠሩበት ስም እያቀላቀልህ እንዳትቸገር በቅጥነተ ሕሊና ሁነህ አስተውል:: የመጻሕፍትን ከላይ መነሻቸውን ከታች መድረሻቸውን ጠንቅቀህ ተመልከት:: አንዳንድ ጊዜ ስለ አንዳንድ ነገር በንባብ የሚገናኙበት ምክንያት አይታጣምና እንዳትሳሳት:: አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት የአካል ስም እንደሆነ ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራጺ ማለት ግን የግብር ስም እንደሆነ በዚህም ልዩነት እንዳለበት በላይኛው አርእስት የተናገረውን በትሕትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነህ ተመልከት::
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

Monday, May 15, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፬


© መልካሙ በየነ
ግንቦት 7/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ

ክፍል ፩
ዳግመኛም ይኸው በነፍስ ከዊን የተገለጠው የሥላሴ ከዊን፥ በእሳትና በፀሐይ በቀላይም ከዊን ይገለጣል:: እሳት አንድ ባሕርይ ሲሆን፣ ሦስት ከዊን አለው። ይኸውም ነበልባል፤ብርሃን፤ ዋዕይ ነው:: በነበልባሉ አብ፥ በብርሃኑ ወልድ፥ በዋዕዩ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ:: ይኸውም ተፈልጦ ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ በአንድ ሕላዌ የሚኖር ነው:: አናዋሩ፦ ነበልባሉ ከእንጨት ወይም ከፈትልና ከዘይት ጋራ ብርሃኑንና ሙቀቱን ይሰጣል:: ብርሃን ከነበልባልና ከዋዕይ ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ በራሱ ከዊን ከዓይን ብርሃን ጋራ ይዋሐዳል:: እንደዚሁም ወልድ በቃልነቱ ከዊን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ፣ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ:: ብርሃነ እሳት ከዓይን ጋራ በተዋሐደ ጊዜ፣ ነበልባልና ዋዕይ እንዳልተዋሐዱ፣ ወልድም ሰው በሆነ ጊዜ፣ መለኮት አንድ ስለሆነ፣ አብና መንፈስ ቅዱስ ተዋሐዱ አያሰኝም፤ ባሕርይ አንድ ሲሆን ከዊን ይለየዋልና:: ይህንም የሚያስረዳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አንዋርህ እንዴት ነው ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ቢጠይቀው፣ ንባብ፦ “አቡየ እሳት ውእቱ ወአነ ብርሃኑ ወመንፈስ ቅዱስ ዋዕዩ’’ ትርጉም፦ “አባቴ እሳት/ነበልባል/ ነው፣ እኔ ብርሃን ነኝ፣ መንፈስ ቅዱስም ዋዕዩ /ሙቀቱ/ ነው'' ብሎ የአንድነቱንና የሦስትነቱን አኗኗዋር በእሳት መስሎ ነግሮታል:: /ቀሌምንጦስ/ ሠለስቱ ምዕትም:- ንባብ፦ “አቡየ ወአነ ወመንፈስ ቅዱስ፣ እሳት ወነበልባል፣ ወፉሕም” አለ ጌታ ብለዋል:: ቅዳሴ አባ ሕርያቆስም:- ንባብ፦ “አብ እሳት ወልድ እሳት መንፈስ ቅዱስ እሳት አሐዱ ውእቱ እሳተ ሕይወት ዘእምአርያም" ብሏል። (ቅዳሴ ማርያም) በልዕልና ያለ አንድ የሕይወት እሳት ማለቱ ነው:: ፀሐይም አንድ ባሕርይ ሲሆን ሦስት ከዊን አለው:: ይኽውም ክበብ፣ ብርሃን፣ ዋዕይ ነው:: በክበቡ አብ፣ በብርሃኑ ወልድ፣ በዋዕዩ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ:: ብርሃነ ፀሐይ ከክበቡና ከዋዕዩ ተፈልጦ ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ በራሱ ከዊን ከዓይን ብርሃን ጋራ ይዋሐዳል:: እንዲሁም ወልድ በቃልነቱ ከዊን፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ፣ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ:: ብርሃነ ፀሐይ ከዓይን ጋራ በተዋሐደ ጊዜ፣ ክበብና ዋዕዩ እንዳይዋሐዱ፣ ወልድ ሰው በሆነ ጊዜም መለኮት አንድ ስለሆነ፣ አብ መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆኑ አያሰኝም:: ማስረጃ፦ ባለቤቱ ጌታችን ክርስቶስ በቀሌምንጦስ:- ንባብ፦ “አቡየ ፀሐይ፣ ወአነ ብርሃኑ፣ ወመንፈስ ቅዱስ ዋዕዩ::" ትርጉም፦ “አባቴ ፀሐይ ነው፣ እኔም ብርሃኑ ነኝ፣ መንፈስ ቅዱስም ዋዕየ ነው'' እንዳለ:: ሠለስቱ ምዕትም:- ንባብ፦ “አቡየ ወአነ ወመንፈስ ቅዱስ ፀሐይ/ክበብ/ ወብርሃን፣ ወዋዕዩ/ሙቀት/ '' ብለዋል :: ቅዳሴ አባ ሕርያቆስም:- ንባብ፦ “አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ ወመንፈስ ቅዱስ ፀሐይ አሐዱ ውእቱ ፀሐየ ጽድቅ ዘላዕለ ኲሉ'' ብሏል:: /ቅዳሴ/ ከሁሉ በላይ የሚሆን አንድ ፀሐየ ጽድቅ ማለት ነው::ባሕርም፣ አንድ ባሕር ሲሆን ሦስት ከዊን አለው:: ይኸውም ስፋት፣ ርጥበት፣ ሁከት ነው:: በስፋቱ አብ፣ በርጥበቱ ወልድ፣ በሁከቱ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ:: ሰው ከባሕር ገብቶ ዋኝቶ ሲወጣ ፣ በአካሉ ላይ ርጥበት ይገኛል እንጂ ፣ ስፋትና ሁከት እንዳይገኙ፣ ወልድም በቃልነቱ ከዊን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ፣ በተለየ አካሉ ሰው በሆነ ጊዜ፣ በመለኮት አንድ ስለሆነ፣ አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆኑ አያሰኝም:: የዚህንም ምሳሌነቱ በአረጋዊ መንፈሳዊ እንደተነገረ፣ በአሥራ አንደኛው አንቀጽ እናመጣዋለን:: ይህን ሁሉ ተመልክተን መለኮት በአካል ሦስት ከማለት ርቀን፣ በአንድ መለኮት ሦስት አካላትና ሦስት ኲነታት እንዳሉ አምነን፣ ወልድ በተለየ አካሉ ከአንድ መለኮት ተፈልጦ ስሌለበት በቃልነቱ ከዊን ሰው ሆነ ብለን ብናምን ሦስቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ የሚያስረዳ ነገር፣ ፯ኛ ሊቅ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አግናጥዮስ እንደሚከተለው ተናግሯዋል:: ንባብ፦ “ኀደረ አሐዱ አካል እም ሠለስቱ አካላት ውስተ ከርሣ ለድንግል ማርያም:: ወበእንተ ተዋሕዶተ መለኮት ዘንትናገር በዝየ፣ ዘህልው በወልድ፣ ወአኮ በእንተ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወኢንቤ ግሙራ ከመ እሙንቱ ኀደሩ ለተሰብኦ ውስተ ከርሣ ለድንግል፣ ዘእንበለ ዳእሙ ወልድ ባሕቲቱ አሐዱ አካል እም ሠለስቱ አካላት::" ትርጉም፦ “ሦስቱ አካለት አንዱ አካል በማኅጸነ ማርያም አደረ:: በዚህ አንቀጽ ኀደረ ብለን የምንናገረው የመለኮት ተዋሕዶ፣ በወልድ በቃልነቱ ስላለው ከዊን አይደለም፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ብቻ ሰው ለመሆኑ በማኅጸነ ድንግል አደረ እንላለን እንጂ፣ አብ መንፈስ ቅዱስ ሰው በመሆን አደሩ አንልምና” ብሏል:: (አንደኛ መልዕክት ሃይማኖተ አበው) ሃይማኖት አበው ምዕራፍ ፲፩ ፥ ፫  መለኮት ዘሕልው በወልድ ያለው፣ የወልድ የቃልነቱ ከዊን እንድሆነ እዝነ ልቦና ያለው ሰው በቅጥነተ ልብ ሆኖ ያስተውል::
ክፍል ፪
የመለኮት አንድነት አካላትን እንዳይጠቀልል፣ የአካላትም ሦስትነት መለኮትን እንዳይከፍል የሚያስረዳ ነገር የአንጾኪያው ሊቀ ዻዻሳት አትናቴዎስ ፵፱ኛ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ ንባብ፦ “ወሶበሂ ንቤ አሐዱ እግዚአብሔር፣ ወ፩ዱ ሕላዌ፣ ወ ፩ዱ መለኮት፣ አኮ ዘያበጥል ላዕሌነ ዝንቱ ተስምዮተ ፫ አካላት:: እስመ ለለ፩ እም ፫ አካላት ሃላውያን በበአካላቲሆሙ:: ወመለኮትሂ ሕልው በሕላዌሁ፣ ወኢይትፈለጥ ለከዊነ ፫ መለኮት፣ እስመ ቅድስት ሥላሴ ፩ እሙንቱ በተዋሕዶ እንበለ ፍልጠት”  ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻ ፮ ፥ ፰-፱ ትርጓሜ፦ "አንድ እግዚአብሔር አንድ ሕላዌ አንድ መለኮት ብንል፣ አንድ ማለታችን ፫ አካላት ማለትን የሚፈርስብን አይደለም:: ሦስት አካላት ማለታችንም መለኮትን ከሦስት የሚከፍልብን አይደለም:: ከሦስቱም አካላት አንዱም አንዱ በየአካላቸው ፀንተው የሚኖሩ ናቸውና፣ መለኮትም በአንድነቱ ፀንቶ የሚኖር ነው እንጂ:: ሦስት መለኮት ለመሆን የሚከፈል አይደለም፣ ቅድስት ሥላሴ ያለመለያየት በተዋሕዶ አንድ ናቸውና" ብሏል:: (ሃይ. አበው፣ እመልዕክተ ሲኖዲቆስ ፶፪ኛ ክፍል ፩)። የእንስክድሪያ ሊቀ ጳጳሳት ሱንትዮስም ይህን የአትናቴዎስን ቃል በሙሉ ተናግሮታል፤ እመልዕክተ ሲኖዲቆን ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻ ፩ ፶፫ኛ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳትም- ዲዮናስዮስ:- ንባብ፦ "ወንትአመን በዝንቱ ሕላዌ ወንሰግድ አሐተ ስግድተ እስመ መለኮትሰ ፩ ውእቱ ዘሠለስቲሆሙ:: ወሠለስቲሆሙ: ፩ዱ እሙንቱ በመለኮት፤ ወዝንቱ የአክል ለዘቦቱ ልብ ወአእምሮ፤ ይትዋሐዱ በመለኮት ወይሤለሱ በአካላት:: በከመ ይቤ ጎርጎርዩስ ነባቤ መለኮት፣ እስመ መለኮትሰ አኮ ውፁዕ እም ፫ አካላት ከመ ኢይባእ ተጋብኦተ አማልክት ወኢነ አምን ካልአ እምዝንቱ ወኢንበል ፫ተ አማልክተ ወኢመለኮት ፍሉጠ:: ወእመሰ ንቤ ፍሉጥ መለኮት፣ንከውን ዐላውያነ ወናመጽእ ድካመ ለመለኮት:: ወሶበሂ ንሬሲ ቅድስተ ሥላሴ ፍሉጣነ መለኮት፣በከመ አካላቲሆሙ፣ ንትአመን እምነተ ሰይጣናዌ ከመ አይሁድ እለ አልቦሙ አምላክ” ትርጉም፦ “በዚህ ባሕርይ እናምናለን አንዲት ስግደትም እንሰግዳለን:: የሦስቱ አካላት መለኮት አንድ ነውና:: ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸውና:: ዕውቀትና አእምሮ ላለው በመለኮት አንድ በአካል ሦስት ናቸው ብሎ ማመን ይበቃል:: የመለኮትን ነገር የሚናገር ጎርጎርዮስ በመለኮት አንድ በአካል ሦስት ናቸው ብሎ እንደተናገረ መለኮትስ ከሦስቱ አካላት የወጣ ልዩ አይደለም:: ብዙ አማልክት አሉ ማለት በሰው ልቦና እንዳያድር ከዚህ ሌላ አናምንም:: ሦስት አማልክት አንልም:: መለኮትንም ልዩ ነው አንልም:: መለኮትን እንደ አካላት ልዩ ነው ብንል ግን ከሐድያን እንሆናለን:: በመለኮትም ድካምን እናመጣለን:: ቅድስት ሥላሴን እንደ አካላቸው በመለኮት ልዩ ብናደርግ፣ አምላክ የለም እንደሚሉ እንደ አይሁድ ከሰይጣን የተገኘ እምነትን እናምናለን” ብሏል:: /እመልእክተ ሲኖዲቆን/ ፶፬ኛ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ክርስቶዶሉም አትናቴዎስና ሱኑትዩስ የተናገሩትን ንባብ ተናግሮታል:: እመልክተ ሲኖዲቆን። ይህን የመሰለ የተናገሩ ሊቃውንት ብዙ ናቸው:: በየአንቀጹ መመልከት ነው::
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፫



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 6/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ

ፍኖተ እግዚአብሔር
፩ኛ አንቀጽ
ወላዲ መለኮት ተወላዲ መለኮት ሠራጺ መለኮት ማለት እንዳይገባ ይናገራል፡፡
ጥያቄ፡- ወላዲ መለኮት ተወላዲ መለኮት ሠራጺ መለኮት ማለት አይገባምን? መልስ፦ ምንም ቢሆን ወላዲው ተወላዲ ሠራጺ፣ ተወላዲውም ወላዲ ሠራጺ፣ ሠራጺውም ወላዲ ተወላዲ ሊሆን የማይችል ነው:: አካላትን ቅሉ፣ ልዩ ልዩ የሚያሰኛቸው ይህ ወላዲ፣ ተወለዲ፣ ሠራጺ የሚለው ንባብ ነው:: መለኮትን አካላት በሚለያዩበት ስም ጠርቶ ወላዲ መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት፣ ሠራጺ መለኮት ማለት መለኮትን እንደ አካላት ሦስት ማለት እንደሆነ አስተዋይ ልቦና ይረዳዋል:: እንዲህም ከሆነ ሊቃውንት በየአንቀጹ “ይሤለሱ በአካላት፣ ወይትወሐዱ በመለኮት'' ያሉት ንባብ ሐሰት ሆነ ማለት ነዋ:: መለኮት በራሱ ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራጺ ከተባለ፣ ሦስት በመሆኑ የመንገዱ ጥርጊያ ወደ ዮሐንስ ተዐቃቢ ቤት የሚያገባ መሆኑ አይጠረጠርም:: መለኮትን ወላዲ፣ ተወለዲ፣ ሠራጺ ማለትም፣ ሦስቱ አካላት መለኮት፣ መለኮት፣ መለኮት፣ የተባሉበትን ምሥጢር ባለማስተዋል የታሰበ ስሕተት ነው:: ሊቃውንት ሦስቱን አካላት መለኮት፣ መለኮት፣ መለኮት፣ ብለው ማመናቸው መለኮት በአካል ልዩ ነው ብለው አይደለም:: አንድ መለኮት በሦስት አካላት ልዩ ነው ብለውም አይደለም:: አንድ መለኮት በሦስት አካላት ህልው ነው ብለው ነው እንጂ::
ማስረጃ፡-
፳፯ኛ ሊቅ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት:
ንባብ፡- “ወኢይትሀበሉ ሕጉላን ያብኡ ውስተ ቅድስት ሥላሴ ፍልጠተ መለኮት፣ ወኢድማሬ አካላት፣ ወኢንሰግድ ለ፫ቱ አማልክት፣ አላ ለ፩ አምላክ:: ወንሰምዮሙ በ፫ አስማት፣ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ፣ ፩ መለኮት፣ ወ ፩ ኃይል፣ እንዘ ፫ አካላት እኁዛን በጽምረተ ፩ መለኮት ወህላዌ” ትርጓሜ፦ “ከዕውቀት የተሳሳቱ ሰዎች ልዩ በሆነች ሦስትነት፣ የመለኮትን ልዩነት፣ የአካላትን አንድነት አግብተው ይናገሩ ዘንድ አይድፈሩ፣ ለአንድ አምላክ እንሰግዳለን እንጂ ፣ለሦስት አማልክት አንሰግድምና፣ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ ብለን በሦስት ስሞች እንጠራቸዋለን:: እኒህም ሦስቱ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ ባንድ መለኮትና /ሕይወት/ በአንድ ሕልውና አንድነት የተገናዘቡ ሦስት ሲሆኑ፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ኃይል ናቸው” ብሏልና:: (ድርሳን ፩ ሃይማኖተ አበው) ከታተመው ሃይማኖተ አበው ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት ምዕ ፷፥ ፮-፯ ይመልከቱ፡፡

ባስልዮስ ዘአንጾኪያም ፵፩ኛ:-
ንባብ፡- “እንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር፣ ዕብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ እስመ አሐዱ ውእቱ መለኮተ ሥላሴ፣ ወሠለስቲሆሙ አሐዱ እሙንቱ በመለኮት፣ ወእሙነ እብል ከመ እሙንቱ መለኮት ወህላዌ፣ ወለለ አሐዱ እምአካላተ ሠላሴ፣ ያበጽሕ ፍጹመ መለኮት፣ ምስለ ዚአሁ አካል ወስም'' (ክፍል ፩ ሃይማኖተ አበው) ዝኒ ከማሁ ሃይማኖተ አበው ምዕ ፷፮ ፥ ፮-፯፡፡

ትርጓሜ፡- “እኔ እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ማለትን ስለ አብ፣ ስለ ወልድ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ እናገራለሁ:: የሦስቱ መለኮት አንድ ነውና:: ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸው:: እኒህም መለኮትና /ሕይወት/ ሕልውና /ባሕርይ/ እንዲባሉ በእውነት እናገራለሁ:: ልዩ ሦስትነት ካላቸው አካላትም፣ አንዱም አንዱም ከገንዘቡ አካልና ከገንዘቡ ስም ጋራ ፍጹም መለኮትን ገንዘብ
ያደርጋሉ” ብሏል::
፯ኛው ሊቅ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያም:
ንባብ፦ “እሉ ሠለስቱ አካላት ፍጹማን ዲበ መንበረ ስብሐት፣ ወእኁዛን በፅምረተ አሐዱ መለኮት፣ ዘውእቱ አሐዱ ብርሃን ዘይሠርቅ እምኔሁ ሥላሴ” ትርጓሜ፡- “እኒህ ሦስቱ አካላት በጌትነት ዙፋን ላይ ያሉ ፍጹማን ናቸው:: በአንዱ መለኮት አንድ አድራጊነትም የተገናዘቡ ናቸው:: ይህም መለኮት /ባሕርይ/ የአካል ሦስትነት ከሱ የሚገኝለት አንድ ብርሃን ነው” ብሏል:: (ክፍል ፩ ሃይማኖተ አበው) ከታተመው ሃይማኖተ  አበው ምዕ ፲፩ ፥ ፰-፱ ይመልከቱ፡፡

አቡሊዲስ ዘሮም ፲፫ ሊቅ
ንባብ፦ “ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ፣ ወመንፈስ ቅዱስኒ መንፈሶሙ ለአብ ወወልድ፣ ወበዝንቱ አእምርነ ከመ ፩ መለኮተ ሥላሴ፣ ወሎቱ ንሰግድ፣ ወአበዊነሂ እለተጋብኡ በኒቅያ ይቤሉ እመቦ ዘይፈልጥ መለኮቶ ለእግዚአብሔር አብ እምወልድ ወእም መንፈስ ቅዱስ ውጉዘ ለይኩን::'' ትርጓሜ፦ “ወልድ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው:: መንፈስ ቅዱስ ለአብና ለወልድ እስትንፋሳቸው ነው:: በዚህም የምንሰግድለት የሦስቱ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ መለኮት አንድ እንደሆነ አወቅን:: በኒቅያ የተሰበሰቡ አባቶቻችንም የአብን መለኮት ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ የሚለይ ሰው ቢኖር የተለየ ይሁን ብለዋል'' ብሏል:: (ክፍል ፪ ሃይማኖተ አበው) ዝኒ ከማሁ ሃይማኖተ አበው ምዕ ፴፱ ፥ ፰-፱ ይህን የመሰለ በየአንቀጹ የተነገረ ብዙ ነው:: ሐተታ፡- ሦስቱ መለኮት፣ መለኮት፣ መለኮት መባላቸው አንድ መለኮት በሦስቱ አካላት ሕልው ሆኖ፣ ሦስቱን አካላት ስለአገናዘበ ነው እንጂ መለኮት በአካል የተለየ ሆኖ እንዳይደለ አስተዋይ ልቦና ያለው ሰው መጻሕፍትን በጥንቃቄ ቢመረምር ይረዳዋል:: መለኮት በአካል የተለየ ቢሆን፣ ሦስቱ ሁሉ ባልተጠሩበትም ነበር:: አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ መባል ግን፣ በአካል የተለየ ቢሆን በየራሳቸው ተጠሩበት እንጂ ሦስቱ ሁሉ እንዳልተጠሩበት።
፪ኛ አንቀጽ
በአንድ መለኮት ሦስት ኲነት እንዳለ፣ የኲነትም ሦስትነቱ፣ እንደ አካላት እንዳይደለ፣ ይናገራል
ጥያቄ፡- መለኮትን በአካል ሦስት ብሎ መለኮት የተባለ አካል ነው ማለት ይገባልን?
መልስ:- አይገባም፤ መለኮትን አካል ብሎ፣ አካል ለአካል ሦስት ማለት፣ ዘጠኝ አካላት ከማለት የሚያደርስ መሆኑ አይጠረጠርምና።
ጥያቄ፡- መለኮትን በአካል ሦስት ማለት ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ ከማለት አይጠብቅምን?
መልስ፡- አዎን አይጠብቅም፤ ሦስት አማልክት ዘጠኝ አካላት ያሰኛል እንጅ፤ ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ ከማለት የሚጠብቅስ በአንድ መለኮት ሦስት አካላትና ሦስት ኲነታት እንዳሉ ማመን ነው።
ማስረጃ፡ ሠለስቱ ምዕት፦ ንባብ፦ "በስመ እግዚአብሔር ዋሕድ በመለኮት ዘይሴለስ በአካላት ወኲነታት" ትርጉም፡- "በመለኮት አንድ፣ በአካላትና በኲነታት ሦስት፣ በሚሆን በእግዚአብሔር ስም እናምናለን” እንዳሉ። /መጽሐፈ ሥርዓት ፩ኛ አንቀጽ/ እንዲህ ግን ስለሆነ የኲነታት ሦስትነት እንደ አካላት አይደለም፤ አካላት መጠቅለልና መቀላቀል ሳይኖርባቸው፣ በተከፍሎ በተፈልጦ፣ በፍጹም ገጽ፣ በፍጹም መልክ፣ በየራሳቸው የሚቆሙ ናቸው፤ ኲነታት ግን ተፈልጦ ተከፍሎ /መለየት መከፈል/ ሳይኖርባቸው በተዋሕዶና በተጋብኦ በአንድነት አካላትን በሕልውና /በአኗኗር/ እያገናዘቡ፣ በአንድ መለኮት የነበሩ፣ ያሉ፣ የሚኖሩ ናቸው፤ እሊህም ከዊነ አብ፣ ከዊነ ቃል፣ ከዊነ እስትንፋስ ናቸው። “ከዊነ አብ” በአብ መሠረትነት እራሱ ለባዊ ሆኖ፣ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ዕውቀት /ማወቂያ/ መሆን ነው። “ከዊነ ቃል” በአብ መሠረትነት ለራሱ ነባቢ ሆኖ፤ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ /ማናገሪያ/ መሆን ነው። “ከዊነ እስትንፋስ” በአብ መሠረትነት ለራሱ ሕያው ሆኖ፣ ለአብና ለወልድ ሕይወት መሆን ነው። ሦስት ኩነታት ያልናቸው እሊህ ናቸው። የሊህም ኩነታት ምሥጢር፣ "ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ" "ሰውን በመልካችንና በምሳሌያችን እን ፍጠር" ያለውን ንባብ /ዘፍ ፩፥፳፮/ መሠረት አድርጎ፣ የነፍስን የአካሏንና የባሕርይዋን ከዊን ቢመረምሩ ይታወቃል ይረዳልም። ሲመረመርም የባሕርያቸው ከዊን በአካሏ ከዊን፤ የአካለቸውም ከዊን፣ በባሕርይዋ ከዊን፣ ይመረምረዋል፣ ነፍስ በአካሏ፣ ከሦስት የማትከፈል ከዊን አላት። ይኸውም ከዊነ ልብ፥ ከዊነ ቃል፥ ከዊነ እስትንፋስ ነው:: በባሕርይዋ ሦስት ከዊን ያላት መሆንዋ፤ አካሏን ከሦስት አይከፍለውም:: እንዲህ ሳትከፈል፣ የልብነትዋ ከዊን /ልብ መሆንዋ/ ከቃሏና ከእስትንፋሷ ከዊን ሳይለይ፣ በራስዋ ከዊን ከሥጋዊ ልብ ጋር ይዋሐዳል። በቃልነትዋም ከዊን /የቃሏም ከዊን/ ከልብነትዋ ከዊንና ከእስትንፋስዋ ከዊን ሳይለይ፤ በራሱ ከዊን ከሥጋ አንደበት ጋራ ይዋሐዳል:: የእስትንፋሷም ከዊን ከልብነትዋ ከዊንና ከቃልዋም ከዊን ሳይለይ፣ በራሱ ከዊን ከሥጋ እስትንፋስ ጋር ይዋሕዳል:: እንዲህ አድርጎ የሥላሴን ከዊን በነፍስ ከዊን ቢመረምሩ፣ ሦስቱ ሰው ሆኑ ከማለት ይጠብቃል:: መለኮትን በአካል ሦስት ማለት ግን፤ ሊቃውንት ሁሉ በየአንቀጹ፣ "ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት" "በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ናቸው" (ሃይማኖተ አበው)  ያሉትን አፍርሶ፣ ሦስት አማልክት፣ ዘጠኝ አካላት፥ ከማለት ያደርሳል እንጅ፣ ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ ከማለት የሚጠብቅ አይደለም።
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡