Monday, May 15, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፫



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 6/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ

ፍኖተ እግዚአብሔር
፩ኛ አንቀጽ
ወላዲ መለኮት ተወላዲ መለኮት ሠራጺ መለኮት ማለት እንዳይገባ ይናገራል፡፡
ጥያቄ፡- ወላዲ መለኮት ተወላዲ መለኮት ሠራጺ መለኮት ማለት አይገባምን? መልስ፦ ምንም ቢሆን ወላዲው ተወላዲ ሠራጺ፣ ተወላዲውም ወላዲ ሠራጺ፣ ሠራጺውም ወላዲ ተወላዲ ሊሆን የማይችል ነው:: አካላትን ቅሉ፣ ልዩ ልዩ የሚያሰኛቸው ይህ ወላዲ፣ ተወለዲ፣ ሠራጺ የሚለው ንባብ ነው:: መለኮትን አካላት በሚለያዩበት ስም ጠርቶ ወላዲ መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት፣ ሠራጺ መለኮት ማለት መለኮትን እንደ አካላት ሦስት ማለት እንደሆነ አስተዋይ ልቦና ይረዳዋል:: እንዲህም ከሆነ ሊቃውንት በየአንቀጹ “ይሤለሱ በአካላት፣ ወይትወሐዱ በመለኮት'' ያሉት ንባብ ሐሰት ሆነ ማለት ነዋ:: መለኮት በራሱ ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራጺ ከተባለ፣ ሦስት በመሆኑ የመንገዱ ጥርጊያ ወደ ዮሐንስ ተዐቃቢ ቤት የሚያገባ መሆኑ አይጠረጠርም:: መለኮትን ወላዲ፣ ተወለዲ፣ ሠራጺ ማለትም፣ ሦስቱ አካላት መለኮት፣ መለኮት፣ መለኮት፣ የተባሉበትን ምሥጢር ባለማስተዋል የታሰበ ስሕተት ነው:: ሊቃውንት ሦስቱን አካላት መለኮት፣ መለኮት፣ መለኮት፣ ብለው ማመናቸው መለኮት በአካል ልዩ ነው ብለው አይደለም:: አንድ መለኮት በሦስት አካላት ልዩ ነው ብለውም አይደለም:: አንድ መለኮት በሦስት አካላት ህልው ነው ብለው ነው እንጂ::
ማስረጃ፡-
፳፯ኛ ሊቅ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት:
ንባብ፡- “ወኢይትሀበሉ ሕጉላን ያብኡ ውስተ ቅድስት ሥላሴ ፍልጠተ መለኮት፣ ወኢድማሬ አካላት፣ ወኢንሰግድ ለ፫ቱ አማልክት፣ አላ ለ፩ አምላክ:: ወንሰምዮሙ በ፫ አስማት፣ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ፣ ፩ መለኮት፣ ወ ፩ ኃይል፣ እንዘ ፫ አካላት እኁዛን በጽምረተ ፩ መለኮት ወህላዌ” ትርጓሜ፦ “ከዕውቀት የተሳሳቱ ሰዎች ልዩ በሆነች ሦስትነት፣ የመለኮትን ልዩነት፣ የአካላትን አንድነት አግብተው ይናገሩ ዘንድ አይድፈሩ፣ ለአንድ አምላክ እንሰግዳለን እንጂ ፣ለሦስት አማልክት አንሰግድምና፣ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ ብለን በሦስት ስሞች እንጠራቸዋለን:: እኒህም ሦስቱ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ ባንድ መለኮትና /ሕይወት/ በአንድ ሕልውና አንድነት የተገናዘቡ ሦስት ሲሆኑ፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ኃይል ናቸው” ብሏልና:: (ድርሳን ፩ ሃይማኖተ አበው) ከታተመው ሃይማኖተ አበው ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት ምዕ ፷፥ ፮-፯ ይመልከቱ፡፡

ባስልዮስ ዘአንጾኪያም ፵፩ኛ:-
ንባብ፡- “እንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር፣ ዕብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ እስመ አሐዱ ውእቱ መለኮተ ሥላሴ፣ ወሠለስቲሆሙ አሐዱ እሙንቱ በመለኮት፣ ወእሙነ እብል ከመ እሙንቱ መለኮት ወህላዌ፣ ወለለ አሐዱ እምአካላተ ሠላሴ፣ ያበጽሕ ፍጹመ መለኮት፣ ምስለ ዚአሁ አካል ወስም'' (ክፍል ፩ ሃይማኖተ አበው) ዝኒ ከማሁ ሃይማኖተ አበው ምዕ ፷፮ ፥ ፮-፯፡፡

ትርጓሜ፡- “እኔ እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ማለትን ስለ አብ፣ ስለ ወልድ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ እናገራለሁ:: የሦስቱ መለኮት አንድ ነውና:: ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸው:: እኒህም መለኮትና /ሕይወት/ ሕልውና /ባሕርይ/ እንዲባሉ በእውነት እናገራለሁ:: ልዩ ሦስትነት ካላቸው አካላትም፣ አንዱም አንዱም ከገንዘቡ አካልና ከገንዘቡ ስም ጋራ ፍጹም መለኮትን ገንዘብ
ያደርጋሉ” ብሏል::
፯ኛው ሊቅ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያም:
ንባብ፦ “እሉ ሠለስቱ አካላት ፍጹማን ዲበ መንበረ ስብሐት፣ ወእኁዛን በፅምረተ አሐዱ መለኮት፣ ዘውእቱ አሐዱ ብርሃን ዘይሠርቅ እምኔሁ ሥላሴ” ትርጓሜ፡- “እኒህ ሦስቱ አካላት በጌትነት ዙፋን ላይ ያሉ ፍጹማን ናቸው:: በአንዱ መለኮት አንድ አድራጊነትም የተገናዘቡ ናቸው:: ይህም መለኮት /ባሕርይ/ የአካል ሦስትነት ከሱ የሚገኝለት አንድ ብርሃን ነው” ብሏል:: (ክፍል ፩ ሃይማኖተ አበው) ከታተመው ሃይማኖተ  አበው ምዕ ፲፩ ፥ ፰-፱ ይመልከቱ፡፡

አቡሊዲስ ዘሮም ፲፫ ሊቅ
ንባብ፦ “ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ፣ ወመንፈስ ቅዱስኒ መንፈሶሙ ለአብ ወወልድ፣ ወበዝንቱ አእምርነ ከመ ፩ መለኮተ ሥላሴ፣ ወሎቱ ንሰግድ፣ ወአበዊነሂ እለተጋብኡ በኒቅያ ይቤሉ እመቦ ዘይፈልጥ መለኮቶ ለእግዚአብሔር አብ እምወልድ ወእም መንፈስ ቅዱስ ውጉዘ ለይኩን::'' ትርጓሜ፦ “ወልድ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው:: መንፈስ ቅዱስ ለአብና ለወልድ እስትንፋሳቸው ነው:: በዚህም የምንሰግድለት የሦስቱ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ መለኮት አንድ እንደሆነ አወቅን:: በኒቅያ የተሰበሰቡ አባቶቻችንም የአብን መለኮት ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ የሚለይ ሰው ቢኖር የተለየ ይሁን ብለዋል'' ብሏል:: (ክፍል ፪ ሃይማኖተ አበው) ዝኒ ከማሁ ሃይማኖተ አበው ምዕ ፴፱ ፥ ፰-፱ ይህን የመሰለ በየአንቀጹ የተነገረ ብዙ ነው:: ሐተታ፡- ሦስቱ መለኮት፣ መለኮት፣ መለኮት መባላቸው አንድ መለኮት በሦስቱ አካላት ሕልው ሆኖ፣ ሦስቱን አካላት ስለአገናዘበ ነው እንጂ መለኮት በአካል የተለየ ሆኖ እንዳይደለ አስተዋይ ልቦና ያለው ሰው መጻሕፍትን በጥንቃቄ ቢመረምር ይረዳዋል:: መለኮት በአካል የተለየ ቢሆን፣ ሦስቱ ሁሉ ባልተጠሩበትም ነበር:: አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ መባል ግን፣ በአካል የተለየ ቢሆን በየራሳቸው ተጠሩበት እንጂ ሦስቱ ሁሉ እንዳልተጠሩበት።
፪ኛ አንቀጽ
በአንድ መለኮት ሦስት ኲነት እንዳለ፣ የኲነትም ሦስትነቱ፣ እንደ አካላት እንዳይደለ፣ ይናገራል
ጥያቄ፡- መለኮትን በአካል ሦስት ብሎ መለኮት የተባለ አካል ነው ማለት ይገባልን?
መልስ:- አይገባም፤ መለኮትን አካል ብሎ፣ አካል ለአካል ሦስት ማለት፣ ዘጠኝ አካላት ከማለት የሚያደርስ መሆኑ አይጠረጠርምና።
ጥያቄ፡- መለኮትን በአካል ሦስት ማለት ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ ከማለት አይጠብቅምን?
መልስ፡- አዎን አይጠብቅም፤ ሦስት አማልክት ዘጠኝ አካላት ያሰኛል እንጅ፤ ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ ከማለት የሚጠብቅስ በአንድ መለኮት ሦስት አካላትና ሦስት ኲነታት እንዳሉ ማመን ነው።
ማስረጃ፡ ሠለስቱ ምዕት፦ ንባብ፦ "በስመ እግዚአብሔር ዋሕድ በመለኮት ዘይሴለስ በአካላት ወኲነታት" ትርጉም፡- "በመለኮት አንድ፣ በአካላትና በኲነታት ሦስት፣ በሚሆን በእግዚአብሔር ስም እናምናለን” እንዳሉ። /መጽሐፈ ሥርዓት ፩ኛ አንቀጽ/ እንዲህ ግን ስለሆነ የኲነታት ሦስትነት እንደ አካላት አይደለም፤ አካላት መጠቅለልና መቀላቀል ሳይኖርባቸው፣ በተከፍሎ በተፈልጦ፣ በፍጹም ገጽ፣ በፍጹም መልክ፣ በየራሳቸው የሚቆሙ ናቸው፤ ኲነታት ግን ተፈልጦ ተከፍሎ /መለየት መከፈል/ ሳይኖርባቸው በተዋሕዶና በተጋብኦ በአንድነት አካላትን በሕልውና /በአኗኗር/ እያገናዘቡ፣ በአንድ መለኮት የነበሩ፣ ያሉ፣ የሚኖሩ ናቸው፤ እሊህም ከዊነ አብ፣ ከዊነ ቃል፣ ከዊነ እስትንፋስ ናቸው። “ከዊነ አብ” በአብ መሠረትነት እራሱ ለባዊ ሆኖ፣ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ዕውቀት /ማወቂያ/ መሆን ነው። “ከዊነ ቃል” በአብ መሠረትነት ለራሱ ነባቢ ሆኖ፤ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ /ማናገሪያ/ መሆን ነው። “ከዊነ እስትንፋስ” በአብ መሠረትነት ለራሱ ሕያው ሆኖ፣ ለአብና ለወልድ ሕይወት መሆን ነው። ሦስት ኩነታት ያልናቸው እሊህ ናቸው። የሊህም ኩነታት ምሥጢር፣ "ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ" "ሰውን በመልካችንና በምሳሌያችን እን ፍጠር" ያለውን ንባብ /ዘፍ ፩፥፳፮/ መሠረት አድርጎ፣ የነፍስን የአካሏንና የባሕርይዋን ከዊን ቢመረምሩ ይታወቃል ይረዳልም። ሲመረመርም የባሕርያቸው ከዊን በአካሏ ከዊን፤ የአካለቸውም ከዊን፣ በባሕርይዋ ከዊን፣ ይመረምረዋል፣ ነፍስ በአካሏ፣ ከሦስት የማትከፈል ከዊን አላት። ይኸውም ከዊነ ልብ፥ ከዊነ ቃል፥ ከዊነ እስትንፋስ ነው:: በባሕርይዋ ሦስት ከዊን ያላት መሆንዋ፤ አካሏን ከሦስት አይከፍለውም:: እንዲህ ሳትከፈል፣ የልብነትዋ ከዊን /ልብ መሆንዋ/ ከቃሏና ከእስትንፋሷ ከዊን ሳይለይ፣ በራስዋ ከዊን ከሥጋዊ ልብ ጋር ይዋሐዳል። በቃልነትዋም ከዊን /የቃሏም ከዊን/ ከልብነትዋ ከዊንና ከእስትንፋስዋ ከዊን ሳይለይ፤ በራሱ ከዊን ከሥጋ አንደበት ጋራ ይዋሐዳል:: የእስትንፋሷም ከዊን ከልብነትዋ ከዊንና ከቃልዋም ከዊን ሳይለይ፣ በራሱ ከዊን ከሥጋ እስትንፋስ ጋር ይዋሕዳል:: እንዲህ አድርጎ የሥላሴን ከዊን በነፍስ ከዊን ቢመረምሩ፣ ሦስቱ ሰው ሆኑ ከማለት ይጠብቃል:: መለኮትን በአካል ሦስት ማለት ግን፤ ሊቃውንት ሁሉ በየአንቀጹ፣ "ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት" "በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ናቸው" (ሃይማኖተ አበው)  ያሉትን አፍርሶ፣ ሦስት አማልክት፣ ዘጠኝ አካላት፥ ከማለት ያደርሳል እንጅ፣ ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ ከማለት የሚጠብቅ አይደለም።
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment