Wednesday, May 24, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፮

© መልካሙ በየነ

ግንቦት 9/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
09/09/09 ታሪካዊ ቀን!!!
፭ኛ አንቀጽ
ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት ተከፍሎ በሌለባት በአንዲት ባሕርይ ያለ የከዊን ስም ነው፡፡
የከዊን ስም “ልብ” አብ ለራሱ ለባዊ አዋቂው (አዋቂ) ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልቡና (ዕውቀት) መሆኑን የ ሚያመለክት ስም ነው:: ቃልም የወልድ የከዊን ስም ነው:: ለራሱ ነባቢ (ተናጋሪ) ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ መሆኑ የሚገለጽበት የከዊን (ቃል የመሆን) ስሙ ነው:: እስትንፋስ የመንፈስ ቅዱስ የከዊን ስሙ ነው:: መንፈስ ቅዱስ ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወት እንደሆነ የምና ውቅበት የከዊን (ሕይወተ አብ ወወልድ) የመሆን ስሙ ነው:: ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት ተከፍሎ በሌለባት በአንዲት ባሕርይ ያለ የከዊን ስም ነው፡፡ ይኸውም ልዩነት ሳለበት አንድነት አንድነትም ሳለበት ልዩነት አለበት:: ልዩነቱ በከዊን ነው አንድነቱ ግን በሕልውና መገናዘብ ነው:: ወልድ ሰው ሆነ በተባለ ጊዜ አካል ተዋሐደ እንጂ ባሕርይ አልተዋሐደም እንዳይባል ወንጌላዊ ቃል ሥጋ ኮነ አለ እንጂ ወልድ ሥጋ ኮነ አላለም:: ባሕርይም ከተዋሐደ የሥላሴ ባሕርይ አንድ ነውና:: ፫ቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ ከልብና ከእስትንፋስ ለይቶ “ቃል ሥጋ ኮነ” አለ:: ቃልም ማለት በአካለ አብና በአካለ መንፈስ ቅዱስ በኮዊን የምትለይ በሕልውና የምትገናዘብ እንደሆነች “ነገር በምሳሌ መዝሙር በሃሌ እንደተባለው አስቀድመን ምሳሌውን መርምረን በሁለተኛው አንቀጽ በነፋስና በፀሐይ በእሳትና በቀላይ መስለን ተናግረናልና በማስተዋል ይመለከቷል:: መለኮት እንደ አካላት ከ፫ ይከፈላል የሚል ሰው ይህን ነገር ከራሱ አንቅቶ በልብ-ወለድ ቃል ተናግሮታል እንጂ መጻሕፍት ከተናገሩት ኃይለ ቃልና ከመሰሉት ምሳሌ ምስክር አምጥቶ ለማስረዳት አይችልም:: የሥላሴን ባሕርይና አካል እንደ ሰው ባሕርይና አካል አድረጎ አካል የሌለው ባሕርይ፣ ባሕርይም የሌለው አካል የለምና ባሕርይ፣ አካልን ተከትሎ ከሦስት ይከፈላል ይላል:: መልስ:- ባያስተውለው ነው እንጂ ይህ ነገር ከሰማይና ከምድር ይልቅ የተራራቀ ነው:: የሰው ባሕርይ በአካል ቢከፈል በየራሱ ልብ፣ በየራሱ ቃል፣ በየራሱ እስትንፋስ ያለው ሆኖ በየራሱ ልዩ ልዩ ሥራውን ይሠራል:: አንዳንድ ቅዱሳንም በፀጋ ቢተዋወቁና አንዳንድ ሥራ ቢሠሩ ያደረባቸው መንፈስ ቅዱስ በሀብት አገናኝቷቸው ነው እንጂ የባሕርይና የሕልውና አንድነት ኖሯቸው አይደለም::ሥላሴ ግን አካላቸው የተለየ ሲሆን ባሕርያቸው ተከፍሎ የሌለበት አንድ ለመሆኑ ማስረጃው የሦስቱ ልብ አንድ አብ ሆኖ አንድ ዕውቀትን ያውቃሉ:: የሦስቱ ቃል አንድ ወልድ ሆኖ አንድ ነገርን ይናገራሉ:: የሦስቱ እስትንፋስ አንድ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ አንድ የሕይወትን ሥራ ይሠራሉ:: እንዲህም ከሆነ ሊቃውንት “ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት” ያሉትን ተመልክቶ ይልቁንም “አጤን ይበልጡ ቃለ አጤ'' እንዲሉ እርሱ ባለቤቱ “አነ ወአብ ፩ ንሕነ፤ እኔና አብ አንድ ነን” ዮሐ ፲÷፴:: “አነ በአብ ወአብ ብየ'' "እኔ በአብ ሕልው ነኝ አብም በእኔ ሕልው ነው” ዮሐ ፲፯፤፲:: ያለውን ተረድቶ ባሕርየ መለኮት በአካል ከሦስት የማይከፈል መሆኑን ማመን ይገባል:: ከዚህ ግን ወጥቶ መለኮት እንደ አካላት ከሦስት ይከፈላል ማለት ግን አብን ልብ ወልድን ቃል መንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ ማለትን ትቶ፣ ለሦስቱ በየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ አላቸው ብሎ፣ ሦስት አማልክት በማለት የዮሐንስ ተዐቃቢን ሃይማኖት መመስከር ነው:: ይወልደዋል አይቀድመውም ማለት ቅሉ አካል በተከፍሎ ሲለይ፣ አንድ ባሕርየ መለኮት ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ ሦስቱን አካላት በማገናዘብ /ማዋሐድ/ በቅድምና የነበረ ስለሆነ ነው:: ይህንም ለመረዳት:- ባስልዮስ ዘቂሣርያ የተናገረውን ይመልከቱ:: ፲፪ኛ ንባብ:- “ይደልወነ ናእምር ኀበ ኅብረተ ተዋሕዶተ መለኮት ዘ ፫ አካላት፣ ወናስተዋሕድ በአኀብሮ ዘዚአሆሙ ፩ መለኮት:: ንእመን በሃይማኖት ከመ ይትወሐድ መለኮት በአብ:: እስመ እምኀበ አብ ተወልደ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስሂ ወፅአ እምኔሁ:: እንዘ ኢይቀድም ፩ እምካልኡ፣ ወካልኡ እምሣልሱ፣ ወበልደተ ወልድ ወበጸአተ መንፈስ ቅዱስ እምአብ፣ ይትወሐድ መለኮተ ሥላሴሁ ለአምላክነ” ትርጉም:- “በአንድ መለኮት ተዋሕዶ የሦስቱን አካላት መገናዘብ ልናውቅ ይገባል:: በአንድ መለኮት በማገናዘብም ልዩ ልዩ የሆነ አካላትን እናዋሕድ:: መለኮት አንድ እንደሆነ በማመን፣ በአብ ያለ መለኮት ወልድን መንፈስ ቅዱስን እንዲዋሐድ እንመን:: አብ ከወልድ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ ሳይቀድም፣ ወልድ ከአብ ተወልድዋልና፣ መንፈስ ቅዱስም ከርሱ ሠርፆአል፣ ከአብ ወልድ በመወለዱ፣ መንፈስ ቅዱስም በመሥረፁ፣ የአምላካችን የሦስትነቱን አካል መለኮት ይዋሐዳል” ብሏልና:: (ክፍል ፪ ) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፴፪ ÷ ክፍል ፪ ቁ. ፬-፮ አሁን በዚህ መስመር ያነበብውን የባስልስዮስን ቃል አስተውሎ የሚመለከት ሰው:- መለኮትን በአካል ሦስት ማለት ከሚያመጣው ፫ ልብ፣ ቃል፣ ፫ እስትንፋስ ከማለት ተጠብቆ በአብ ልብነት ለባውያን፣ በወልድ ቃልነት ነባብያን፣ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሕያዋን ብሎ በአካል ፫ በመለኮት አንድ በምታሰኝ ሃይማኖት ይፀናል:: መለኮት እንደ አካላት ከሦስት ይከፈላል የሚል ሰው ግን ወልድ ከአብ የሚወለደው ልደት ሰው ሁሉ ከአባቱ እንደሚወለደው ልደት ነው ማለቱ እንደሆነ ጠንቅቆ ማስተዋል ያሸዋል:: ማናቸውም ልጅ ከአባቱ ሲወለድ ባሕርዩ በአካል የሚከፈልና የሚለይ ስለሆነ አባት ከልጁ ይቀድማል ይበልጣልም:: ማስረጃ:- ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ ፳ኛ:- ንባብ:- “ወእመሰ ኮነ ብእሲ አበ፣ ክሡት ነገሩ ከመ የዐቢ አብ እምወልድ:: ወስሞሂ ያጤይቅ ከመ ውእቱ እምቅድመ ወልዱ::'' ትርጉም:- “ሰው አባት ሲባል ከልጁ እንዲበልጥ ነገሩ የታወቀ ነው:: አባት መባሉም ከልጁ አስቀድሞ እንደነበረ ያስረዳል'' እንዳለ:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ÷ ክፍል ፩ ቁ. ፰ ወልድ ግን ከአብ ሲወለድ አካሉ በተከፍሎ ቢለይም ሕላዌ መለኮት በተከፍሎ መለየት የለበትም:: አወላለዱም ብርሃነ ፀሐይ ተከፍሎ መለየት ሳይኖርበት ከክበብ እንዲገኝ በሕላዌ መለኮት ከአብ ተከፍሎ መለየት ሳይኖርበት ነውና፣ መቅደም መቀዳደም መብለጥ መበላለጥ የለበትም:: አሁን ማስረጃ አድርገን የጠራነው ቴዎዶጦስ:- ንባብ:- “ወለነሰሂ ይደልወነ ነሐሊ ዘንተ በሕላዌ መለኮት:: አላ ነአምን በወልድ ዋሕድ ከመ ውእቱ ቀዳማዊ ምስለ አብ በኩሉ ዘመን፣ ወወልደ አብ ዋሕድ ይሰመይ ብርሃነ፣ እስመ ብርሃን ዘተወልደ እምብርሃን፣ ኢይትበሀል ተወልደ እምድኀረ ብርሃን አላ በጊዜ ዘኮነ ቦቱ ውእቱ ብርሃን፣ ይትረከብ ብርሃን ዘተወልደ እምኔሁ፣ ወወትረ ሕልው ምስሌሁ:: ብርሃንኒ ያጤይቀከ አምሳሊሁ ለወልድ ዘውእቱ ሕልው ምስለ አብ በኩሉ ጊዜ እምቅድመ ኩሉ ዓለም::'' ትርጉም:- “በመለኮት ባሕርይ ይህን ማሰብ ለእኛ አይገባንም፣ ወልድ ዋሕድ በዘመን ሁሉ ከአብ ጋር የነበረ ቀዳማዊ እንደሆነ እናምናለን እንጂ፣ ከአብ የተወለደ ዋሕድ ቃልም ብርሃን ይባላል:: ከክበብ የተገኘ ብርሃን ከክበብ በኋላ ተገኘ አይባልምና:: ብርሃን ክበብ በተገኘበት ጊዜ ተገኝቶ ከክበብ ሳይለይ አብሮ ይኖራል እንጂ፣ ብርሃንም የወልድ ምሳሌነቱን ያስረዳሃል ይኸውም ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ከአብ ጋራ ሁልጊዜ የነበረ ነው'' እንዳለ:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ክፍል ፩ ቁ. ፱ ይህን ምሳሌ ጠንቅቀን ብንመለከት አማናዊውን አጉልቶ ያሳየናል:: የሰውም ቃል በተወለደ ጊዜ አወላለዱ አሁን በተናገርነው በብርሃንና በክበብ አምሳል ነው:: ቃል ከልብ በተከፍሎ መለየት ሳይኖርበት፣ በአካል ከዊን ይወለዳል፣ በአካል ከዊን ተለይቶ መወለዱንም የሚያስረዳ ነገር፣ ከብራና ላይ በቀለም በተጻፈ ጊዜ አካል ገዝቶ ይታያል ይነበባልም:: ባሕርዩ ግን በተከፍሎ መለየት የለበትምና በልብ ውስጥ ሕልው ሆኖ ሲታሰብ ይኖራል:: ማስረጃ:- ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ ፳፭ኛ:- ንባብ:- “ወለከሂ ቃልከ ዘይትወለድ እምልብከ ይሄሉ ውስቴትክ ተወሊዶ እምልብከ::''  ትርጉም:- “ያንተስ ስንኳ ከልብህ የሚገኝ ቃልህ፣ ከልብህ ተገኝቶ፣ በልብህ ውስጥ ሕልው ሆኖ ይኖራል'' እንዳለ:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩)  ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ክፍል ፩ ቁ. ፲፯ ንባብ:- ዳግመኛም “ወህየንተ ልብ ዘዝየ ነአምሮ ለአብ ህየ፣ ወህየንተ ቃል ዘዝየ ነአምሮ ለቃል ዘእግዚአብሔር ከመ ቦቱ ሕላዌ ወቦቱ አካል በፍጹም ገጽ ወመልክዕ፣ ዘከመ ገጸ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ እስመ ውእቱ ወልዱ ለአብ::'' ትርጉም:- “በኛ ባለ በልብ አምሳል አብን እናውቀዋለን:: እንደ አብና እንደ መንፈስ ቅዱስ ባለ በፍጹም ገጽ በፍጹም መልክዕ አካልና ባሕርይ እንዳለው፣ በእኛ ባለ በቃል አምሳል ቃለ እግዚአብሔር ወልድን እናውቃለን፣ አብን አህሎ መስሎ የተወለደ የአብ ልጅ ነውና” ብሎ የአብ ልብነት በልብ፣ የወልድ ቃልነት በቃል፣ የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በእስትንፋስ መመሰላቸውን ያስረዳል:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ዝኒ ከማሁ ቁ ፳ ልጅ ከአባቱ ባሕርይ በአካል ተለይቶ የሚከፈል ስለሆነ አባትና ልጅ አንድ ልብ አንድ ቃል አንድ እስትንፋስ በመሆን አይገኙም:: ወልድ ግን ከአብ ሲወለድ፣ ባሕርይ እንደ አካሉ የማይከፈል አንድ ስለሆነ፣ ሦስት አካላት በአንድ ልብ በአንድ ቃል በአንድ እስትንፋስ ተገናዝበው ይኖራሉ:: ይህንም ለመረዳት በየአንቀጹ የተነገረውን መመልከት ነው::
፮ኛ አንቀጽ
ወልድ ማለት የተረክቦ ስሙ እንደሆነ ይናገራል (ተረክቦ ማለት መገኘት ማለት ነው) ወልድ ማለት አካሉ በቃልነቱ ከዊን ተድኀሮ  ሳይኖርበት (ወደ ኋላ ሳይቀር) አብን አህሎ መስሎ ከአብ አካል በመገኘቱ የሚጠራበት የተረክቦ ስሙ ነው:: ተረክቦውም ተፈልጦ ሳይኖርበት በሕልውና እያለ ነው:: የነፍስ ቃሏ ከልብነቷ ተገኝቶ ሳይለይ አካሏ ሕልው ሆኖ እንደሚኖር ማነጻጸር ነው:: ማስረጃ:- ቄርሎስ በእስተጉቡእ: ንባብ:- “ወልድ ዋሕድ በሕላዌሁ ዘእምኀበ እግዚአብሔር አብ ይሰመይ ቃለ፣ እስመ ፩ ውእቱ ተወለደ እም ፩ አብ::''ትርጉም:- “ወልድ ዋሕድ ከእግዚአብሔር አብ ተወልዶ በአብ ሕልው ሆኖ በሚኖርበት ባሕርዩ ቃል ይባላል:: “አንዱ እርሱ ከአንድ አብ ተወልዷልና” ብሏል:: ተወላዲ ማለት ግን በተከፍሎ የሚጠራበት የግብር ስሙ ነው:: ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት በግሥ አንቀጽ መልክ ፊደሉ አንድ ሲመስል፣ የምሥጢር ልዩነት እንዳለው አሁን የተናገርነውን የተረክቦንና የተከፍሎን ምሥጢር ጠንቅቆ ማስተዋል ነው:: ተረክቦ ያልነውም የአካሉ ሕላዌ ከአብ አካል የተለየ ሆኖ በፍጹም ገጽና በፍጹም መልክ መታወቁ ነው እንጂ፤ እግዚአበሔር የተገኘበት ጊዜ አይደለም:: ማስረጃ:- ሱኑትዩስ:- ንባብ:- “ወኢይትረከብ ሀልዎቱ እምኃበ ወኢምንትኒ”ትርጉም:- “አኗኗሩ ከምንም ከምን አይገኝም” እንዳለ:: “ከምንም ተገኘ አይባልም” ሃይማኖተ አ በው ምዕ ፻፲ ክፍል ፪ ቁ. ፬ ሠለስቱ ምዕትም በቅዳሴ:- ንባብ:- “ኢይክል መኑሂ ይባዕ ማዕከለ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ያዕምር ዘከመ እፎ ህላዌሁ፣ ወለዶ አብ ለወልዱ ኢይትበሀል ዘጊዜ ወበዘከመዝ መዋዕል ወለዶ፤ ኢይትአመር ልደቱ እም አብ እስመ ዕፁብ ውእቱ፣ ወኢይትአወቅ ህላዌሁ እስመ ስውር ውእቱ” ትርጉም:- “ማንም ማን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መካከል ሊገባ አይችልም:: አኗኗሩ እንደምንም እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፣ አብ ልጁን ወልዶታል:: ነገር ግን አብ ልጁን በዚህ ጊዜ እንዲህም ባለ ዘመን ወለደው አይባልም፤ ከአብ መወለዱ አይመረመርም፣ የሚያስጨንቅ ነውና፤ አኗኗሩ አይታወቅም የተሰወረ ነውና፤” እንዲሉ:: ተከፍሎም በመለየት እንደሆነ የሚያስረዳ ሊቃውንት በብዙ አንቀጽ ገልጸዋል:: ንባብ:- “ተጋብኦ በተከፍሎ ወተከፍሎ በተጋብኦ” ትርጉም:- "አንድነት በመለየት መለየትም በአንድነት አለ” ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፮÷ ፫ ፵፱ኛ አትናቴዎስ ዘአንጾኪያ ፶፪ኛ ሱኑትዩስ ዘእስክንድርያ ፶፬ኛ ክርስቶዶሉ ዘእስክንድርያ እመልዕክተ ሲኖዲቆን አንቀጽ ሁለተኛ እይ ፩. ፪. ፫. ንባብ፦ “ኀቡራን እንበለ ተሌልዮ ወሊሉያን እንበለ ትድምርት” ትርጉም:- “ባለመለያየት አንድ ናቸውና አንድ ባለመሆንም ልዩ ናቸው” እያሉ ይናገራሉና:: (ቆዝሞስ ዘእስክንድርያ ክፍል ፩ኛ ሃይ.አበው ፵፪ኛ)ሃይማኖተ አበው ምዕ ፺፭ ÷ ፫ ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት፣ በምሥጢር ልዩነት እንዳለበት በዚህ ማስተዋል ነው::
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment