Monday, May 15, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፬


© መልካሙ በየነ
ግንቦት 7/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ

ክፍል ፩
ዳግመኛም ይኸው በነፍስ ከዊን የተገለጠው የሥላሴ ከዊን፥ በእሳትና በፀሐይ በቀላይም ከዊን ይገለጣል:: እሳት አንድ ባሕርይ ሲሆን፣ ሦስት ከዊን አለው። ይኸውም ነበልባል፤ብርሃን፤ ዋዕይ ነው:: በነበልባሉ አብ፥ በብርሃኑ ወልድ፥ በዋዕዩ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ:: ይኸውም ተፈልጦ ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ በአንድ ሕላዌ የሚኖር ነው:: አናዋሩ፦ ነበልባሉ ከእንጨት ወይም ከፈትልና ከዘይት ጋራ ብርሃኑንና ሙቀቱን ይሰጣል:: ብርሃን ከነበልባልና ከዋዕይ ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ በራሱ ከዊን ከዓይን ብርሃን ጋራ ይዋሐዳል:: እንደዚሁም ወልድ በቃልነቱ ከዊን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ፣ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ:: ብርሃነ እሳት ከዓይን ጋራ በተዋሐደ ጊዜ፣ ነበልባልና ዋዕይ እንዳልተዋሐዱ፣ ወልድም ሰው በሆነ ጊዜ፣ መለኮት አንድ ስለሆነ፣ አብና መንፈስ ቅዱስ ተዋሐዱ አያሰኝም፤ ባሕርይ አንድ ሲሆን ከዊን ይለየዋልና:: ይህንም የሚያስረዳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አንዋርህ እንዴት ነው ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ቢጠይቀው፣ ንባብ፦ “አቡየ እሳት ውእቱ ወአነ ብርሃኑ ወመንፈስ ቅዱስ ዋዕዩ’’ ትርጉም፦ “አባቴ እሳት/ነበልባል/ ነው፣ እኔ ብርሃን ነኝ፣ መንፈስ ቅዱስም ዋዕዩ /ሙቀቱ/ ነው'' ብሎ የአንድነቱንና የሦስትነቱን አኗኗዋር በእሳት መስሎ ነግሮታል:: /ቀሌምንጦስ/ ሠለስቱ ምዕትም:- ንባብ፦ “አቡየ ወአነ ወመንፈስ ቅዱስ፣ እሳት ወነበልባል፣ ወፉሕም” አለ ጌታ ብለዋል:: ቅዳሴ አባ ሕርያቆስም:- ንባብ፦ “አብ እሳት ወልድ እሳት መንፈስ ቅዱስ እሳት አሐዱ ውእቱ እሳተ ሕይወት ዘእምአርያም" ብሏል። (ቅዳሴ ማርያም) በልዕልና ያለ አንድ የሕይወት እሳት ማለቱ ነው:: ፀሐይም አንድ ባሕርይ ሲሆን ሦስት ከዊን አለው:: ይኽውም ክበብ፣ ብርሃን፣ ዋዕይ ነው:: በክበቡ አብ፣ በብርሃኑ ወልድ፣ በዋዕዩ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ:: ብርሃነ ፀሐይ ከክበቡና ከዋዕዩ ተፈልጦ ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ በራሱ ከዊን ከዓይን ብርሃን ጋራ ይዋሐዳል:: እንዲሁም ወልድ በቃልነቱ ከዊን፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ፣ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ:: ብርሃነ ፀሐይ ከዓይን ጋራ በተዋሐደ ጊዜ፣ ክበብና ዋዕዩ እንዳይዋሐዱ፣ ወልድ ሰው በሆነ ጊዜም መለኮት አንድ ስለሆነ፣ አብ መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆኑ አያሰኝም:: ማስረጃ፦ ባለቤቱ ጌታችን ክርስቶስ በቀሌምንጦስ:- ንባብ፦ “አቡየ ፀሐይ፣ ወአነ ብርሃኑ፣ ወመንፈስ ቅዱስ ዋዕዩ::" ትርጉም፦ “አባቴ ፀሐይ ነው፣ እኔም ብርሃኑ ነኝ፣ መንፈስ ቅዱስም ዋዕየ ነው'' እንዳለ:: ሠለስቱ ምዕትም:- ንባብ፦ “አቡየ ወአነ ወመንፈስ ቅዱስ ፀሐይ/ክበብ/ ወብርሃን፣ ወዋዕዩ/ሙቀት/ '' ብለዋል :: ቅዳሴ አባ ሕርያቆስም:- ንባብ፦ “አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ ወመንፈስ ቅዱስ ፀሐይ አሐዱ ውእቱ ፀሐየ ጽድቅ ዘላዕለ ኲሉ'' ብሏል:: /ቅዳሴ/ ከሁሉ በላይ የሚሆን አንድ ፀሐየ ጽድቅ ማለት ነው::ባሕርም፣ አንድ ባሕር ሲሆን ሦስት ከዊን አለው:: ይኸውም ስፋት፣ ርጥበት፣ ሁከት ነው:: በስፋቱ አብ፣ በርጥበቱ ወልድ፣ በሁከቱ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ:: ሰው ከባሕር ገብቶ ዋኝቶ ሲወጣ ፣ በአካሉ ላይ ርጥበት ይገኛል እንጂ ፣ ስፋትና ሁከት እንዳይገኙ፣ ወልድም በቃልነቱ ከዊን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ፣ በተለየ አካሉ ሰው በሆነ ጊዜ፣ በመለኮት አንድ ስለሆነ፣ አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆኑ አያሰኝም:: የዚህንም ምሳሌነቱ በአረጋዊ መንፈሳዊ እንደተነገረ፣ በአሥራ አንደኛው አንቀጽ እናመጣዋለን:: ይህን ሁሉ ተመልክተን መለኮት በአካል ሦስት ከማለት ርቀን፣ በአንድ መለኮት ሦስት አካላትና ሦስት ኲነታት እንዳሉ አምነን፣ ወልድ በተለየ አካሉ ከአንድ መለኮት ተፈልጦ ስሌለበት በቃልነቱ ከዊን ሰው ሆነ ብለን ብናምን ሦስቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ የሚያስረዳ ነገር፣ ፯ኛ ሊቅ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አግናጥዮስ እንደሚከተለው ተናግሯዋል:: ንባብ፦ “ኀደረ አሐዱ አካል እም ሠለስቱ አካላት ውስተ ከርሣ ለድንግል ማርያም:: ወበእንተ ተዋሕዶተ መለኮት ዘንትናገር በዝየ፣ ዘህልው በወልድ፣ ወአኮ በእንተ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወኢንቤ ግሙራ ከመ እሙንቱ ኀደሩ ለተሰብኦ ውስተ ከርሣ ለድንግል፣ ዘእንበለ ዳእሙ ወልድ ባሕቲቱ አሐዱ አካል እም ሠለስቱ አካላት::" ትርጉም፦ “ሦስቱ አካለት አንዱ አካል በማኅጸነ ማርያም አደረ:: በዚህ አንቀጽ ኀደረ ብለን የምንናገረው የመለኮት ተዋሕዶ፣ በወልድ በቃልነቱ ስላለው ከዊን አይደለም፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ብቻ ሰው ለመሆኑ በማኅጸነ ድንግል አደረ እንላለን እንጂ፣ አብ መንፈስ ቅዱስ ሰው በመሆን አደሩ አንልምና” ብሏል:: (አንደኛ መልዕክት ሃይማኖተ አበው) ሃይማኖት አበው ምዕራፍ ፲፩ ፥ ፫  መለኮት ዘሕልው በወልድ ያለው፣ የወልድ የቃልነቱ ከዊን እንድሆነ እዝነ ልቦና ያለው ሰው በቅጥነተ ልብ ሆኖ ያስተውል::
ክፍል ፪
የመለኮት አንድነት አካላትን እንዳይጠቀልል፣ የአካላትም ሦስትነት መለኮትን እንዳይከፍል የሚያስረዳ ነገር የአንጾኪያው ሊቀ ዻዻሳት አትናቴዎስ ፵፱ኛ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ ንባብ፦ “ወሶበሂ ንቤ አሐዱ እግዚአብሔር፣ ወ፩ዱ ሕላዌ፣ ወ ፩ዱ መለኮት፣ አኮ ዘያበጥል ላዕሌነ ዝንቱ ተስምዮተ ፫ አካላት:: እስመ ለለ፩ እም ፫ አካላት ሃላውያን በበአካላቲሆሙ:: ወመለኮትሂ ሕልው በሕላዌሁ፣ ወኢይትፈለጥ ለከዊነ ፫ መለኮት፣ እስመ ቅድስት ሥላሴ ፩ እሙንቱ በተዋሕዶ እንበለ ፍልጠት”  ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻ ፮ ፥ ፰-፱ ትርጓሜ፦ "አንድ እግዚአብሔር አንድ ሕላዌ አንድ መለኮት ብንል፣ አንድ ማለታችን ፫ አካላት ማለትን የሚፈርስብን አይደለም:: ሦስት አካላት ማለታችንም መለኮትን ከሦስት የሚከፍልብን አይደለም:: ከሦስቱም አካላት አንዱም አንዱ በየአካላቸው ፀንተው የሚኖሩ ናቸውና፣ መለኮትም በአንድነቱ ፀንቶ የሚኖር ነው እንጂ:: ሦስት መለኮት ለመሆን የሚከፈል አይደለም፣ ቅድስት ሥላሴ ያለመለያየት በተዋሕዶ አንድ ናቸውና" ብሏል:: (ሃይ. አበው፣ እመልዕክተ ሲኖዲቆስ ፶፪ኛ ክፍል ፩)። የእንስክድሪያ ሊቀ ጳጳሳት ሱንትዮስም ይህን የአትናቴዎስን ቃል በሙሉ ተናግሮታል፤ እመልዕክተ ሲኖዲቆን ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻ ፩ ፶፫ኛ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳትም- ዲዮናስዮስ:- ንባብ፦ "ወንትአመን በዝንቱ ሕላዌ ወንሰግድ አሐተ ስግድተ እስመ መለኮትሰ ፩ ውእቱ ዘሠለስቲሆሙ:: ወሠለስቲሆሙ: ፩ዱ እሙንቱ በመለኮት፤ ወዝንቱ የአክል ለዘቦቱ ልብ ወአእምሮ፤ ይትዋሐዱ በመለኮት ወይሤለሱ በአካላት:: በከመ ይቤ ጎርጎርዩስ ነባቤ መለኮት፣ እስመ መለኮትሰ አኮ ውፁዕ እም ፫ አካላት ከመ ኢይባእ ተጋብኦተ አማልክት ወኢነ አምን ካልአ እምዝንቱ ወኢንበል ፫ተ አማልክተ ወኢመለኮት ፍሉጠ:: ወእመሰ ንቤ ፍሉጥ መለኮት፣ንከውን ዐላውያነ ወናመጽእ ድካመ ለመለኮት:: ወሶበሂ ንሬሲ ቅድስተ ሥላሴ ፍሉጣነ መለኮት፣በከመ አካላቲሆሙ፣ ንትአመን እምነተ ሰይጣናዌ ከመ አይሁድ እለ አልቦሙ አምላክ” ትርጉም፦ “በዚህ ባሕርይ እናምናለን አንዲት ስግደትም እንሰግዳለን:: የሦስቱ አካላት መለኮት አንድ ነውና:: ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸውና:: ዕውቀትና አእምሮ ላለው በመለኮት አንድ በአካል ሦስት ናቸው ብሎ ማመን ይበቃል:: የመለኮትን ነገር የሚናገር ጎርጎርዮስ በመለኮት አንድ በአካል ሦስት ናቸው ብሎ እንደተናገረ መለኮትስ ከሦስቱ አካላት የወጣ ልዩ አይደለም:: ብዙ አማልክት አሉ ማለት በሰው ልቦና እንዳያድር ከዚህ ሌላ አናምንም:: ሦስት አማልክት አንልም:: መለኮትንም ልዩ ነው አንልም:: መለኮትን እንደ አካላት ልዩ ነው ብንል ግን ከሐድያን እንሆናለን:: በመለኮትም ድካምን እናመጣለን:: ቅድስት ሥላሴን እንደ አካላቸው በመለኮት ልዩ ብናደርግ፣ አምላክ የለም እንደሚሉ እንደ አይሁድ ከሰይጣን የተገኘ እምነትን እናምናለን” ብሏል:: /እመልእክተ ሲኖዲቆን/ ፶፬ኛ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ክርስቶዶሉም አትናቴዎስና ሱኑትዩስ የተናገሩትን ንባብ ተናግሮታል:: እመልክተ ሲኖዲቆን። ይህን የመሰለ የተናገሩ ሊቃውንት ብዙ ናቸው:: በየአንቀጹ መመልከት ነው::
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment