© መልካሙ በየነ
ግንቦት 8/
2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ
ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
======================================================
፫ኛ አንቀጽ
ሥላሴ በመለኮት አንድ የሚሆንበትን ምሥጢር ያሳያል፡፡
ሐተታ- ሥላሴ በመለኮት አንድ መባላቸው በብዕል አንዱ ከአንዱ ሳይበልጥ አንዱም ከአንዱ ሳያንስ የሚተካከሉ
ባለጸጎች፣ ብዕላቸው በየቤታቸው ሳለ በመተካከላቸው አንድ እንዲባሉ መለኮታቸው በየአካላቸው ሳለ በክብር ስለተካከሉበት ነው ማለት
ይገባናልን? መልስ፦ አይገባም:: ሥላሴ በመለኮት አንድ መባላቸውስ፣
መለኮት እንደ አካላት ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ በአንድነቱ ፀንቶ፣ አካላትን በተከፍሎ ሳሉ በሕልውና እያገናዘበ፣ አንድ ልብ፣ አንድ
ቃል፣ አንድ እስትንፋስ ስላደረጋቸው ነው እንጂ በክብር ስላስተካከላቸው አይደለም:: መለኮት ከአካል ጋር ከሦስት የሚከፈልስ ከሆነ
አንድ ልብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ እስትንፋስ መሆን የለም:: ይህም ከሌለ በአብ ለባውያን፣ በወልድ ነባብያን፣ በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን
መባል አይገኝም:: እንዲህም ከሆነ በአንደኛው አንቀጽ የተጠቀሰው አቡሊድስ:- ንባብ፦ “ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስኒ መንፈሶሙ ለአብ ወለወልድ፤ ወልድም ለአብና
ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው፣ መንፈስ ቅዱስም ለአብና ለወልድ እስትንፋሳቸው (ሕይወታቸው) ነው” ሃይማኖተ አበው ያለው ሐሰት ሆኖ በየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አላቸው በማለት እንደ
ዮሐንስ ተዐቃቢ ዘጠኝ መለኮት ያሰኛል:: ዮሐንስ ተዐቃቢ ከዚህ ሌላ አልተናገረምና:: ሕልውናም እንዲያገናዝባቸው:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፴፱ ÷፰-፱
ማስረጃ፦ ባለቤቱ ጌታችን:-
ንባብ፦ “ለግብርየ እመኑ ከመ ታእምሩ ወትጠይቁ ከመ አነ በአብ ወአብ ብየ::'' ትርጉም፦ “በሥራዬ
እመኑ ታውቁ ትረዱም ዘንድ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ'' ብሏልና:: ዮሐ ፲፣፴፰ ንባብ፦ ዳግመኛ “ኢተአምንሁ ከመ አነ በአብ
ወአብ ብየ፣ ወዝኒ ቃል ዘአነ ነገርኩክሙ አኮ ዘእምኀቤየ ዘነበብኩ አላ አብ ዘሀሎ ብየ ውእቱ ይገብሮ ለዝንቱ ግብር” ትርጉም፦
“አታምንምን እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ:: ይህ ለእናንተ የምነግራችሁ ነገር ከኔ ከራሴ የተናገርኩት አይደለም:: በእኔ ያለ
እርሱ አብ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ” ብሎ ለፊልጶስ ነግሮታል:: ዮሐ ፲፬፣፲
ዮሐንስ ዘአንጾኪያም ፶፭ኛ:-
ንባብ፦ “አንኮ ዘንተአመን በ፫ እደው በ፫ አማልክት ወኢ በ፫ መለኮት አላ ንትአመን በ፫ አካላት ወበ፫
ገጻት እንተ ፩ ባሕርየ መለኮት” ትርጉም፦ "መገናዘብ እንደሌላቸው እንደ ፫ ሰዎች አድርገን በሦስት ሰዎች፣ በሦስት አማልክት፣
በሦስት መለኮት የምናምን አይደለንም:: ባሕርየ መለኮት አንድ በሚያደርጋቸው በሦስት አካላት በሦስት ገጻት እናምናለን እንጂ''
ብሏል:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፲፬
፥ ፮-፯ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ዮሐንስ:- ንባብ፦ “ንሕነ
ንትአመን ከመ አብ ሕልው በወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወልድኒ ሕልው በአብ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወመንፈስ ቅዱሰኒ ሕልው በአብ ወወልድ''
ትርጉም፦ “አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሕልው እንደሆነ፣
ወልድ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ሕልው እንደሆነ፣ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ሕልው እንደሆነ እኛ እናምናለን'' ብሏል:: (ሃይማኖተ
አበው ክፍል ፯) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፺ ፥ ፲፩ ዲዮናስዮስም መለኮትን
እንደ አካላት ብንለይ፣ ሰይጣናዊ እምነትን እናምናለን ማለቱ፣ መለኮትን ሦስት ብሎ፣ ሦስትነት ያለው አኃዝ በመለኮት ከተነገረ፣
መንገዱ የዮሐንስ ተዐቃቢ ነውና እምነቱ ሰይጣናዊ መሆኑን ሲያስረዳ ነው:: መጻሕፍት ሁሉ “ይትወሐዱ በመለኮት” እያሉ፣ ለአካላት
ማስረጃ ያደርጉታል እንጂ መለኮትን ሦስት ብለው የሚከፍሉበት አንቀጽ አይገኝም:: ስለዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ መጻሕፍት
ከተናገሩት ትምህርት ሳይወጡ ማመን ይገባል:: በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ መጻሐፍትን በድፍረትና በትዕቢት ሳይሆን በፈሪሃ እግዚአብሔርና
በትሕትና ሆኖ የሚመለከታቸውን በአካል ሦስት፣ በመለኮት አንድ የሚያሰኘውን የሃይማኖት ምስጢር በመግለጽ ይጠቅማሉና:: ማስረጃ፦ ቅዱስ ጳውሎስ:- ንባብ፦ “ወኲሉ መጽሐፍ ዘበመንፈሰ እግዚአብሔር
ተጽሕፈ ይበቁዕ በኲሉ ትምህርት ወተግሣጽ ወአርትኦ ወአጥብቦ ወጽድቅ፣ ከመ ይትገሠጽ ብእሴ እግዚአብሔር ውስተ ኲሉ ምግባረ ሠናይ::''
ትርጉም፦ “በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ መጽሐፍ ሁሉ፣ ፍፁም ትምህርትንና ምክርን በመሆን፣ ልቦናን በማቅናትና በማራቀቅ ጽድቅንም
በማሠራት ይረባል ይጠቅማል፣ የእግዚአብሔር ሰው በጎ ሥራን ሁሉ ይማር ዘንድ'' እንዳለ:: ፪ኛ ጢሞ. ፫:፲፮-፲፯
፬ኛ አንቀጽ
ሥላሴን በባሕርይና በአካል፣ በግብርም የሚጠሩበትን ስም ለይቶ ያሳያል፡፡
ከብዙ ስሕተት የሚያደርስ
የሥላሴ የስማቸውን ምሥጢር ለይቶ አለማወቅ ነው:: በባሕርይ የሚጠሩበት ስም አለ:: በአካል የሚጠሩበት ስም አለ፣ በግብር የሚጠሩበት
ስም አለ:: በባሕርይ የሚጠሩበትን ስም ለአካልና ለግብር፣ በአካል የሚጠሩበትን ስም ለባሕርይና ለግብር፣ በግብር የሚጠሩበትን ስም
ለባሕርይና ለአካል ሰጥተው ሲናገሩ የአንድነታቸው፣ የሦስትነታቸው ምሥጢር ፈራሽ ሆኖ ይገኛል:: ስለዚህ ጠንቅቆ አስተውሎ መመልከት
ይገባል:: አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ መባል የአካል ስም ነው:: አብ ማለት ጥንት መሠረት መገኛ ማለት ነው:: ጥንት መሠረት መገኛ
በመሆንም ወላዲ አሥራጺ ይባላል:: ጥንት መሠረት አስገኝ በመሆን ወላዲ አሥራጺ ተባለ እንጅ ወላዲ አሥራጺ በመሆኑ አብ የተባለ
አይደለም:: ይህንም ለመረዳት ጎርጎርዮስ ፲፰ኛ የተናገረውን መመልከት ነው:: ንባብ፦ “አእምር ኲሎ ግብረ፣ እም፫ ግብራት፣ ዘውእቶሙ
አስማት፣ ወውእቱ ፍጥረት ወስም ወዘመድ ዘይተበሀል ሰብእ ወገብር ወመጋቢ:: ሰብእሰ በእንተ ፍጥረተ ጠባይዒሁ ወገብርኒ በእንተ
ግብርናቲሁ ወመጋቢኒ በእንተ ስም ዘተሠይመ:: ወናሁ ንቤ ካዕበ በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአኮ እሉ አስማት ዘቦኡ ላዕሌሆሙ
ድኀረ አላ እሙንቱ አካላት:: ወብሂለ ሰብእሂ አኮ ውእቱ ስም ዳዕሙ ውእቱ ፍጥረቱ:: እስመ ለኩሎሙ ሰብእ ቦሙ ፩ ስም በበይናቲሆሙ
ለለ፩ እምኔሆሙ:: እሉ እሙንቱ አዳም አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ:: ወአቃኒመ እግዚአብሔርሰ እሙንቱ አስማት ወአስማትኒ እሙንቱ
አቃኒም እስመ ትርጓሜሁ ለአቃኒም፣ አካላት ጽኑዓን ወቀዋምያን ፍጹማነ ገጽ ወመልክዕ ብሂል:: ወሥሉስ ቅዱስ ይሰመዩ አስማተ ጽኑዐነ::''
ትርጉም፦ “በ፫ አካላት ያለውን ግብር ሁሉ በሦስት ግብራት እወቅ እኒህም ፍጥረት፣ ስም፣ ዘመድ የሚባሉ ስሞች ናቸው:: ፍጥረት
የተባለው ሰብእ (ሰው) መባል ነው:: ስም የተባለው ገብር (አገልጋይ) መባል ነው:: ዘመድ የተባለውም መጋቢ መባል ነው:: ሰብእ
መባሉ ስለ ባሕርዩ መገኘት ነው:: ገብር መባሉም ተገዥ ስለሆነ ነው:: መጋቢ መባሉ ስለተሾመ ነው:: ሰው ስለ አካሉ መገኘት “ሰብእ”
እንደተባለ ስለ አካላቸው ሕላዌ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ:: ስለ ተገዛ ገብር፣ ስለ ተሾመም “መጋቢ” እንዲባል ስለ ወለደ
ወላዲ፣ ስለተወለደ ተወላዲ፣ ስለ ሠረጸ ሠራጺ እንላለን:: እኒህም ስሞች አካላት ሲኖሩ የኖሩ ናቸው እንጂ ኑረው ኑረው ኋላ የተጠሩባቸው
አይደለም:: ሰብእ መባልም በተፈጥሮው የወጣ ስም ነው እንጂ ኋላ የወጣ ስም አይደለም:: ለሰዎች ሁሉ እያንዳንዳቸው የሚጠሩበት
ኋላ የወጣላቸው ስም አለና:: ይኸውም አዳም፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ እንዳለው ነው:: የእግዚአብሔር ዓቃኒም ግን አስማት
ናቸው:: አስማትም ዓቃኒም ናቸው:: የዓቃኒም ትርጓሜ በመልክ፣ በገጽ፣ ፍጹማን ሆነው፣ ፀንተው የሚኖሩ አካላት ማለት ነውና::
ልዩ ሦስት የሚሆኑ አካላትም ፀንተው በሚኖሩ በነዚህ ስሞች ይጠራሉ'' ብሏል:: (ሃይማኖተ አበው ድርሳን ፩ኛ) ጎርጎርዮስ ገባሬ
ተአምራት ሃ.አበው ምዕ ፲፫ ክፍል ፩ ቁ. ፬-፮
መቃርዮስ ዘእስክንድርያም ፵፫:-
ንባብ፦ “ወአስማቲሆሙ ለአካላት አኮ ግብር ከንቱ ሶበ ንሰምዮ ለአብ አበ፣ በእንተ ዘኮነ ወላዲ ወለ
ወልድኒ ወልደ በእንተ ዘተወልደ እምአብ፣ ወለመንፈስ ቅድስኒ መንፈስ ቅድስ በእንተ ዘውጽአ እምአብ::'' ትርጉም፦ “አብ ስለ ወለደ
አብ ብንለው፣ ወልድንም ከአብ ስለተወለደ ወልድ ብንለው፣ መንፈስ ቅዱስንም ከአብ ስለሠረፀ መንፈስ ቅዱስ ብንለውም አካላት ስማቸው
ግብር የሌለው ከንቱ አይደለም'' ብሏል:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ሃ ይማኖተ አ በው ምዕ ፺ ፰፥ ክፍል ፩ ቁ. ፬ ነገር
ግን አንባቢ ሆይ አብን በእንተ ዘኮነ ወላዲ፣ ወልድንም በእንተ ዘተወልደ፣ መንፈስ ቅዱስም በእንተ ዘሠረጸ ስላለ (አብ፣ ወልድ፣
መንፈስ ቅዱስ) የግብር ስም መስሎህ እንዳትሳሳት:: አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት የአካል ስም መሆኑን አስተውል:: አካል ግብርን
ያስገኛል እንጂ ግብር አካልን የሚያስገኝ አይደለምና መጻሕፍትም የፊቱን ወደ ኋላ የኋላውን ወደ ፊት ማድረግ ልማድ ነው:: ማስረጃ፦
ጌታችን:- ንባብ፦ “አልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ እጓለ እመሕያው::'' ትርጉም፦ “ማንም ወደ ሰማይ
የወጣ የለም:: ከሰማይ የወረደው ነው እንጂ፣ እርሱም የሰው ልጅ በሰማይ የሚኖር'' እንዳለ ዮሐ ፫ ፤ ፲፫:: ንባብ፦ጳውሎስም:-
“ክርስቶስ ውእቱ ዘወረደ እም ሰማይ'' ትርጉም፦ “ከሰማይ የወረደ ክርስቶስ ነው'' እንዳለ:: ሮሜ ፲፥፯ ዳግመኛም ንባብ፦ “ወዳግም
ብእሲ እምሰማይ ሰማያዊ'' ትርጉም፦ “ከሰማይ የመጣው ሁለተኛው ሰው ሰማያዊ ነው'' እንዳለ:: ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ፤ ፵፯ ይህን የመሰለ
በየአንቀጹ ብዙ አለና ያስተውሏል:: አካል በመለኮት ከዊን ይገናዘባልና መለኮት ተብሎ ይጠራል:: የአካል ግብር አይገናዘብምና ወላዲ
መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት፣ ሠራጺ መለኮት ሊባል አይገባም:: የሚለያዩበትም የግብር ስም በመሆኑ ሦስት መለኮት ከማለት የሚያደርስ
ይመስላልና/ያደርሳልና/ አብ መለኮት፣ ወልድ መለኮት መንፈስ ቅዱስ መለኮት ቢል ግን አካል በመለኮት ከዊን የሚገናዘብ ስለሆነ አያስነቅፍም::
አንባቢ ሆይ ሥላሴ በባሕርይና በባሕርይ ግብር፣ በአካልና በአካል ግብር፣ የሚጠሩበት ስም አለና:: በባሕርይ የሚጠሩበትን በአካል
ከሚጠሩበት፣ በአካል የሚጠሩበትን በባሕርይ ከሚጠሩበት፣ በባሕርይ ግብር የሚጠሩበትን በአካል ግብር ከሚጠሩበት፣ በአካል ግብር የሚጠሩበትን
በባሕርይ ግብር ከሚጠሩበት ስም እያቀላቀልህ እንዳትቸገር በቅጥነተ ሕሊና ሁነህ አስተውል:: የመጻሕፍትን ከላይ መነሻቸውን ከታች
መድረሻቸውን ጠንቅቀህ ተመልከት:: አንዳንድ ጊዜ ስለ አንዳንድ ነገር በንባብ የሚገናኙበት ምክንያት አይታጣምና እንዳትሳሳት::
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት የአካል ስም እንደሆነ ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራጺ ማለት ግን የግብር ስም እንደሆነ በዚህም ልዩነት
እንዳለበት በላይኛው አርእስት የተናገረውን በትሕትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነህ ተመልከት::
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment