Thursday, February 7, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 3


===================
ወአሠርቱ አቅማራት ።
ዐሥሩን ሰንጠረዥ መጻፍንም እንጀምራለን፡፡ አንድም ሰንጠረዥን መቅድም አድርግ ፤ የአራቱ ወንጌል መቅድም የሚሆን ዐሥሩ ሰንጠረዥ መጻፍን እንጀምራለን ፤ አንድም ጽሒፍን አውርድ፤ ጽሒፈ መቅድመ ፲ቱ አቅማራት ፤ የዐሥሩ ሰንጠረዥ መቅድም የሚሆን ሰባቱን ክፍል መጻፍን እንጀምራለን፡፡ ሐተታ ምኑናት መጻሕፍተ ዕዳ መጻሕፍተ ደብዳቤ አሉና ከዚያ ሲለይ ክቡራት አለ ፤ ርኩሳት መጻሕፍተ ጥንቆላ አሉና ከዚያ ሲለይ ንጹሐት አለ፡፡
በሰላመ እግዚአብሔር አብ አሜን።
እግዚአብሔር አንድ ቢያደርገን፤ ሐተታ። አእለፈ እስራኤል አንድ ቢያደርጋቸው ንሴብሖ እንዳሉ፤ ሠለስቱ ምእት ሊቃውንት ነአምን በ፩ዱ አምላክ እንዳሉ ።
ወእምድኅረ ዝንቱ፤ 
በሰላመ እግዚአብሔር አብ ብሎ ነበርና እግዚአብሔር አብ አንድ ካደረገን በኋላ አንድም ንቀድም በረድኤተ እግዚአብሔር ብሎ ነበርና በእግዚአብሔር እጋዥነት ከጀመርነ በኋላ፤ አንድም በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ ነበርና በሦስቱ ስም ካመንን በኋላ።  
ይሤኒ ዘይቀድም መቅድመ ነገር ፍሡሕ፤ 
ዘይቀድምና መቅድም አንድ ወገን፤ ነገር  ወንጌል ናት ሥነዜና ለዘለዓለም እንዲል፤ ፍሡሕ አላት፤ ወጻድቃንሰ ውሰተ ሕይወት ዘለዓለም ትላለችና የወንጌልን መቅድም መጻፍ ይመቻል። አንድም እየራሱ ለማውጣት የወንጌልን የመቅድሙን መቅድም መጻፍ ይመቻል።
ወይትከሠት ቦቱ አንብቦቱ ርቱዕ።
የቀና መመልከቱ የሚገለጽበት።
አኮቴት ለእግዚአብሔር።
ክብር ይግባውና። ሠዋሪ።
ባሕርዩን በባሕርዩ የሚሠውር ሥውር ብከ ዕበይከ ለሊከ ብከ ተከደንከ ወለሊከ ኪያከ አንጦላዕከ እንዲል፤ አንድም ትዱሳንን በክብር የሚሠውር ወይሤውር ኅሩያነ በደመና እንዲል፤ አንድም ጻድቃንን ከመከራ የሚሠውር እስመ ሠወርከነ ወረዳእከዕነ እንዲል።    ወከዳኒ።
በነፍስ በሥጋ ከባቴ አበሳ። 
ነባቢ ቃል። ወከሃሊ።
አካላዊ። አንድም ነባቢ ለይኩን ለይኩን ብሎ የተናገረ ወከሃሊ፤ ያንኑ ማድረግ የተቻለው ሐተታ። እሱ ተናግሮት ሳይደረግ የቀረ የለምና ወእምከመ ወጽአ ቃል ይትገበር ግብር እንዲል። አንድም ነባቢ እወርዳለሁ እወለዳለሁ ብሎ ያናገረ፤ ወከሃሊ ያንኑ ማድረግ የተቻለው። አንድም ነባቢ ሰማይ ወምድር የኃልፍ ብሎ የተናገረ ወከሃሊ ያንኑ ማድረግ የሚቻለው ። ሕያው።
ሕያው ለራሱ ፤   ወማኅየዊ።
ማኅየዊ ለሌላው፤  ወመዋኢ።
መዋኤ ኃጢአት እስመ ንጹሐት ጠባይዓቲሁ ለእግዚአብሔር ዘእንበለ ነውር እንዲል ፤ እንድም መዋኤ ሥርዓት ወያፈልስ ሥርዓተ ውስተ ሥርዓት እንዲል እምሥርዓትም ይላል ። አንድም መዋዔ ሕሊናት እስመ ሕሊና ይደክም ወየሐጽር እምአእምሮተ እግዚአብሔር እንዲል።
ዘአንቅሐ አልባቢነ ኀበ ዝክሩ።
በልብ ወደመታሰቡ በቃል ወደመነገሩ ልቡናችንን ያነቃቃ፤    
ወመርሐ ልሳናቲነ ኀበ አኮቴቱ ወስብሐቲሁ ።
እሱን ፈጽሞ ወደማመስገን አንደበታችንን መርቶ ያደረሰ። አኮቴተ ስብሐቲሁ ይላል ጌትነቱን ወደማመስገን አንደበታችንን መርቶ ያደረሰ ።
ንሰብሖ እንከ በእንተ ዘወሀበነ እምነ ሠናያተ ኂሩቱ በቸርነቱ ከሚገኝ ከበጐ ነገር ወገን ስለሰጠን እናመስግነው ። ሐተታ ሠናያት ያለው ልጅነት ነው ሀብትኬ መንፈስ ቅዱስ ውእቱ እንዲል። 
ወናእኩቶ እንበይነ ዘጸገወነ እምዕበየ ጸጋቲሁ በለጋስነቱ ከሚሰጠው ክብር ወገን ስሰሰጠን እናመስግነው ዕበየ ጸጋ ያለው ልጅነትን ገንዘብ አድርጎ እስከ ከዊነ እሳት ያለው ማዕርግ ነው።
ወንቀድስ ስሞ ክቡረ ቀድሶቶ ድልወ።  
ክቡር ስሙን የሚገባ ምስጋና እናመስግነው። ሐተታ ባንድነቱ ምንታዌ በሦስትነቱ ርባዔ ሳንቀላቅል ። አንድም ሰውን ጻድቅ ቢሉት ሐሰት፤ ባዕል ቢሉት ንዴት ኃያል ቢሉት ድካም ይስማማዋል እሱ ግን ጻድቅ ዘአልቦ ሐሰት።  ባዕል ዘአልቦ ንዴት ኃያል ዘአልቦ ድካም ነውና።   
በእንተ ዘከሠተ ለነ እምነ ምሥጢራተ ሃይማኖት በተዋሕዶተ ባሕርዩ ለሊሁ። ከሠተ ለሊሁ በባሕርይ አንድ መሆኑን ከማመን ምስጢር ወገን ስሰገለጸልን እናመስግነው  ሐተታ በከፊል ተናገረ የወጣኒ የማዕከላዊ የፍጹም አለና። ቦኑ እምነቶሙ ክመ እምነተ አብርሃም እንዲል።
ወትሥልስተ አካላቲሁ። 
በአካል ሦስት መሆኑን። ወገጻቲሁ በቅርጽ፤ ወመልክዑ በገጽ፤   ወአሳሪሁ አንድ አድራጊውን ከማመን ምሥጢር ወገን ስለገለጸልን እናመስግነው ወአሠረ ፪ተ ሕላዌያተ እንዲል።
በእንተ ዘወሀበነ ቦቱ።   
ኪያሁ ሲል ነው አብ ቢሉ ልጁን ስለሰጠን ወልድ ቢሉ አካሉን ለተዋሕዶ ሰለ ሰጠልን ሥጋውን ደሙን ስለ ሰጠን፤  
ወበእንተ ዘአዕተተ እምኔነ ኩሎ ምግባረ ዕልወታት በዘአምጽአ ቦቱ ውስተ ወንጌሉ ቅዱስ።
ሰው ሁኖ በሠራት በወንጌል ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኃን ባለው ኢትጥአምን ኢትልክፍን ስለአሳለፈልን። አንድም አዳምና ሔዋን ያመጡትን ፍዳ ስለአራቀልን ፈጽመን እናመስግነው። በግብራቸው ዕልወታት አላቸው።
ወቦቱ አስተርአየት ተአምራቲሁ ድውይ መፈወሱ።
ወተከሥተት መንክራቲሁ ጋኔን ማውጣቱ።
ወኃይላቲኒሁ። 
ሙት ማንሣቱ የተገለጸችበት።
ወስብሐት ሎቱ   ክብር ይግባውና።
ይዕበይ ክብሩ።
ጌትነቱ ይክበር ይመስገንና።
ወይትለዓል ዝክሩ።  
በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና።
ወፍጽምናሁ።
ሕልውናው አንድነቱ ከፍ ከፍ ይበልና። 
ወምስለ ዝንቱ ኩሉ ከመ እስትጉቡእ ዘይትፈቀድ ኀበ ጥያቄሃ ወፈቂድ ኀቤሃ ውስተ ኩሉ መጽሐፍ ፯ቱ ይህም ይህ ነው ከዚህ ጋራ በዚህ ላይ እሷን ከሹዋት ከመረመሯት ዘንድ ልቡና የሚሻው ነገር ሁሉ እንደ ተሰበሰበ ሁኖ አለ ጸውዓተኒ ማንሻ ።
አንድም ይህም ይህ ነው ከዚህ ጋራ በዚህ ላይ እሷን ከሹዋት ከመረመሯት ዘንድ ልቡና የሚሻው ነገር ኩሉ በሰባቱ ክፍል እንደተሰበሰበ ሁኖ እሷን በጽሕፈት ወደ መሻት ወደ ማሰብ ማለት እሷን ወደ መጻፍ።
ወናሁ ጸውዐተኒ መፍቅድ ኀበ ኃሢሠ ዘክሮታ ።
እሷን በጽሕፈት ወደመሻት ወደማሰብ ፈቃደ ንጉሥ ፈቃደ ነፍስ ፈቃደ መንፈስ ቅዱስ አነሣሣችኝ፡፡ መፍቅድ ዐፀባ ይላል አብነት ቁርጽ ፈቃድ ፤ የላይ ቤት አማርኛ እገባሪ ፈቃድ።
ወጽሕፈቱ ውስተ ዝንቱ መጽሐፍ ንጹሕ ከመ ይኩን ብጽሐተ ለረባሕ፡፡ ከፈቃደ ሥጋ ንጹሕ በሚሆን በወንጌል እጠግብ ይህ መቅድም መጻፉ ለወንጌል መዳረሻ ሊሆን ነው ሐተታ። ይህማ በሌላ ተጽፎ ተምረውት ቢገቡ ይከለክለናልን ብሎ  ጽሕፈቱ በዝንቱ ከፈቃደ ሥጋ ንጹሕ የሚሆን የመቅድም መጻፍ ለወንጌል መዳረሻ ልሆን ነው።
ወመርሐ ለዘየኃሥሦ ዘይትፈቀድ። የሚወደደው የሚሻው ምሥጢር ለሚሻ ደቀ መዝሙር መርህ ሊሆን ነው።
ወዛቲ ይእቲ ግብር ቀዳማዊ። ይህ ነው መጀመሪያውን ግብር ቀዳማዊ ብለውታል፡፡ ግብር ቀዳማዊ ይባላል ።
ወካልዑ በቁዔት ። ሁለተኛውን በቁዔት ብለውታል በቁዔት ይባላል ወዳግሙ ይላል ።
ወሣልሱ ሥርዓት ሦስተኛውን ሥርዓት ብለውታል ሥርዓት ይባላል
ወራብዑ ስም አራተኛውን ስም ብለውታል ስም ይባላል፡፡ ሰምዮት ትእምርት ይላል አብነት ።
ወኃምሱ መሠረት ። አምስተኛውን መሠረት ብለውታል መሠረት ይባላል እምአይቴ ይላል አብነት። 
ወሳድሱ ምስማክ። ስድስተኛውን ምስማክ ብለውታል ምስማክ ይባላል፡፡
ወሳብዑ አርእስተ ነገር። ሰባተኛውን ክፍለ ነገር ብለውታል ክፍለ ነገር ይባላል ።
ግብር ቀዳማዊ መጀመሪያውን ግብር ቀዳማዊ ብለውታል ግብር ቀዳማዊ ይባላል፡፡ አያይዞ ለመንገር ደገመው።
ወግብሩሰ ለዝንቱ መጽሐፍ ማሕየዊ ። ማሕየዊ የሚሆን የዚህ የመጽሐፍ ሥራው። ከመ ይርባሕ ቦቱ ሕይወተ ሕይወት ዘለዓለም ለደቂቀ ዕጓለ እመሕያው ። ጌታ ለደቂቀ ዕጓለ እመሕያው የዘለዓለም ድኅነትን ያስገኝበት ዘንድ ፤ ደቂቀ ዕጓለ እመሕያው የዘለዓለም ደኅንነትን ያገኙበት ዘንድ ነው  ለደቂቀ ዕጓለ እመሕያው የዘለዓለም ድኅነት ይገኝበት ዘንድ ነው፡፡
ወበጺሖቶሙ ኀበ ፈጣሪሆሙ። 
ወደፈጣሪያቸው መድረሳቸውን ፤ ተላጽቆቶሙ ከፈጣሪያቸው ጋራ አንድ መሆናቸውን  ተመስሎቶሙ ፈጣሪያቸውን መምሰልን ያገኙበት ዘንድ ነው፡፡ ሁሉንም ያስተረጐማል ። በቃል ባነጋገገር፤
ወበምግባር
በሥራ ሁለት አርእስት ተናገረ ለሁለቱም ያመጣል በቃልስ እስመ ውእቱ ይጼውዕ ወይስሕብ ኀበ አእምሮተ እግዚአብሔር ።   
በቃል ያልሁት እግዚአብሔርን ወደማወቅ ያደርሳልና ስለዚህ ነው ።
ይትባረክ። ይክበር ይመስገንና ።
ወይትለዓል ዝክሩ፡፡  
በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና፡፡
በተዋሕዶተ ባሕርዩ።   በባሕርይ አንድ መሆኑን።
ወመለኮቱ ።
በአገዛዝ በጌትነት አንድ መሆኑን ።
ወትሥልስተ አካላቲሁ፡፡   
በአካል ሦስት መሆኑን።   
ወገጻቲሁ።   በገጽ።
ወመልክኡ።  በቅርጽ ሦስት መሆኑን ።
ወአሣሪሁ።
አንድ አድራጊውን ወደማወቅ ያደርሳልና ስለዚህ ነው  ወአሠረ ፪ተ ህላዌያተ እንዲል።
ወያጤይቅ ተሥጉተ ፩ዱ ሕላዌ እም፫ቱ ሕላዌያት ከሦስቱ አካላት የአንዱን አካል ሰው መሆኑን ያስረዳልና ስለዚህ ነው።
ወተዋሕዶቶ በዘተሰብአ ቦቱ ።
ከተዋሐደው ሥጋ ጋራ አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን ያስረዳልና ስለዚህ ነው፡፡ 
ወይዜኑ ኅዳጠ በተሐውሶቱ ወበአንሶስዎቱ ውስተ ዓለም እምጊዜ ልደቱ እምቅድስት ድንግል ንጽሕት እስከ ጊዜ ተንሥኦቱ ወዕርገቱ ውስተ ሰማያት ንጽሕት ከምትሆን ከእመቤታችን ከተወለደ ዥምሮ እስከሚነሣበት እስከሚያርግበት ድረስ በዚህ ዓለም ሠላሳ ሦስት ዓመት ከአራት ወር ከዐሥር ቀን መኖሩን ያስረዳልና ስለዚህ ነው።
ወበምግባርሰ፤ 
ቃል ላለው ጨርሶ ምግባር ላለው አመጣ በምግባርም ያልሁት።      
እስመ በተግሣጻቲሁ ልዕልት ይወስድ ኀበ ምግባራት ሠናያት ወፍጹማት ወመሥመርያት።
አንሰ እብለክሙ ባለው ፍጹማት ወደሚሆኑ ምግባራት ያደርሳልና ስለዚህ ነው ።
ወገድል ትርፍት ወክብርት። 
ፍጽምት ክብርት ወደምትሆን ወደገድለ ልቡና ያደርሳልና ስለዚህ ነው።
ወበኪዳኑ እንተ ጸርሐ ባቲ ወይቤ እመቦ ዘዐቀበ ቃልየ ይገብር ግብረ ዚአነ እገብር ወዘየዓቢ እምኔሁ ይገብር ።      
እመቦ ዘዓቀበ ቃልየ ባለው ወበአስፍዎተ ኪዳኑ ይላል አብነት በወንጌል እመቦ ዘዓቀበ ቃልየ ባለው ያደርሳልና ስለዚህ ነው።
ወዓዲ ትከውኖ ሕይወተ ዘለዓለም፤
ዳግመኛ በዚህ ዓለም ብቻ ተአምራት አድርጋለት እንደ ጋን መብራት ሁናበት አትቀርም በወዲያው ዓለም የዘለዓለም ድኅነትን ታሰጠዋለች ።  
ወዘክሡትሰ
በዚህ ዓለም ብቻ ተአምራት አድርጋለት እንደ ጋን መብራት ሁናበት እንዳትቀር በወዲያውም ዓለም የዘለዓለም ድኅነትን እንድታሰጠው የሚያስታውቅ የሚያስረዳ ነገር ። ላዕለ እለ ገብሩ ትእዛዞ አስተርእየት ላዕለ እደዊሆሙ ተአምራት ወመንክራት ወኃያላት ዓቢያት፤
ላዕለ እደዊሆሙ ለእበለገብሩ ትእዛዞ ፤ ሕጉን በፈጸሙ በሕጉ በጸኑ በሐዋርያት ቃል በሐዋርያት ቃል ሥልጣን ጋኔን ማውጣት ሙት ማንሣት ተደረገ።  
እስከ ውእቶሙ ከሠቱ እዕይንተ ዕውራን 
ዕውራንን እስከ ማብራት ደርሰው እስመ  ውእቶሙ ከሠቱ ዕውራነ። ዕውራንን አብርተዋልና ።
ወአንጽሑ እለ ለምጽ፡፡  
ልሙጸንን እስከማዳን ደርሰው አድነዋልና ።
ወሞእዎ ለሞት ።  
ሞትን ድል እስከ መንሳት ደርሰው ድል ነስተውታልና ፤ ሐተታ ሞእዎ አለ ቢያም ይፈውሱበታል ቢገድል ያሥነሡበታል ኃጠአት ቢሠራ ስርየት ይሰጡበታልና ፤       
ወከብረት ነፍሶሙ በውስተ ዓለማት ፪ኤቲ ዘዝየ ወዘከሐ፡፡   
ሰውነታቸው በወዲህም በወዲያም ዓለም ከበረች ሐተታ ፤ በወዲህ አማልክት ተመሰሉ ሰብአ ወወረዱ ኀቤነ ብለዋቸዋል፤ በወዲያውም ወሀሎ ይትዌሰኩ ሥነ በዲበ ሥን ይለዋል ።
ወአምፍርሃተ ቃሉ ርኀቁ ጸድቃን እምነ ምግባራት ምኑናት ወፍትወተ ዓለም ርኅቀተ ጥቀ ። ወይወድይዎሙ ውስተ እቶነ እሳት ያለውን ነገር ከመፍራት የተነሣ ጻድቃን ከዓለማዊ ግብር ፈጽመው ተከለከሉ  አንድም ወበፍርሃተ ቃሉ አርኃቀ ይላል ። ወይወድይዎሙ ውስተ እቶነ እሳት ባለው ነገር ጌታ ጻድቃንን ከዓለማዊ ግብር ፈጽሞ ከለከለ አንድም ወፍርሃተ ቃሉ ይላል ፤ ወይወድይዎሙ ውስተ እቶነ እሳት ያለውን ነገር መፍራት ጸድቃንን ከዓለማዊ ግብር ፈጽማ ከለከለች  አንድም ቃሉ ባለው በቀሉ ይላል ዕፄሁ ዘኢይነውም ወእሳቱ ዘኢይጠፍእ ያለውን ነገር ከመፍራት የተነሣ ጻድቃን ከዓለማዊ ግብር ፈጽመው ተከለከሉ፡፡  አንድም እንዲህ ባለው ነገር ጌታ ጻድቃንን ፈጽሞ ከለከለ ፤ አንድም እንዲህ ያለውን ነገር መፍራት ጻድቃንን ከዓለማዊ ግብር ፈጽማ ከለከለች፡፡
ወተግኅሡ እምነጽሮታ ወዘክሮታ ፤ 
በዓይን ከማየት በልብ ከማሰብ ፈጽመው ተከለከሉ፡፡
ወጸርየት አልባቢሆሙ ። ሰውነታቸው እንይ ፀሐየ ፊላ ማለት ፀሐይ እንደወደቀበት ዕንቁ ጸራችላቸው። ወተጠበበት ሕሊናሆሙ ልቡናቸው ተራቀቀችላቸው ።
እስከ በጽሑ ኀበ ሥርዓት ዘመላእክት ፤ ወደ መላእክት አነዋወር እስኪደርሱ ድረስ፡፡ ወበተግሣጸቲሁ አንሰ እብለክሙ ባለው ወበተካይዶቱ እመቦ ዘዓቀበ ቃልየ ባለው ወበነጊሮቱ፡፡  
ወጸድቃንስ ውስተ ሕይወት ዘለዓለም
ረሰዮሙ ለደቂቀ ዕጓለ እመሕያው ተመሳልያነ ኀበ ፈጣሪሆሙ ። ደቂቀ ዕጓለ እመሕያው ፈጣሪያቸውን እንዲመስሉ ልጹቃነ  ከፈጣሪያቸው ጋራ አንድ እንዲሆኑ። ብጹሕነ ወደ ፈጣሪያቸው እንዲደርሱ አደረጋቸው፤ ከመ ይግበሩ ምግባራቲሁ ወይረሱ መንግሥቶ ሥራውን ሠርተው ክብሩን ይወርሱ ዘንድ።
 ፪ተኛ ጉባኤ።
ወካልዑ በቁዔት ።
ይቆየን፡፡
 ****************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
30/05/2011 ዓም

Wednesday, February 6, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 2

=======================
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።  

ታሪክ

ይሀን መጽሐፍ አሞንዮስ አውሳብዮስ ተናግረውታል። እነዚህስ መነሣታቸው ከሠለስቱ ምእት በፊት ነውን ወይስ በኋላ ቢሉ በፊት ነው። ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ ከሠለስቱ ምእት በኋላ የተነሡ ሊቃውንት ከመዝ ይቤሉ አበዊነ ከመዝ ይቤሉ አጋእዝቲነ ከመዝ ይቤሉ መምሕራኒነ እያሉ ሠለስቱ ምእትን ያነሣሉ እሊህ ባለማንሣታቸው። ያስ ከሠለስቱ ምእት በኋላ የተነሡ ሊቃውንት እንዲህ እያሉ ሠለስቱ ምእትን ማንሣታቸው በሃይማኖት ቢከራከሩ ጉባዔ ቢያቆሙ ነው። እኒህ አለማንሣታቸው በሃይማኖት ባይከራከሩ ጉባዔ ባያቆሙ ነው። መነሣታቸውም ከሠለስቱ ምእት በኋላ ነው። ይህን ስለ ሦስት ነገር ተናገረውታል።

መጀመሪያውን ግብር ቀዳማዊ ብለውታል ግብር ቀዳማዊ ይባላል። ለኦሪት ግብር አላት። በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ ትላለች ለወንጌል ምን ግብር አላት እንዳይሉ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሰው እንደሆነ ትናገራለችና ይህን ለመንገር ወካልዑ በቁዔት ይላል ። 

፪ተኛውን በቁዔት ብለውታል በቁዔት ይባላል ለኦሪት በቁዔት አላት ፳ኤል ፪፻ ከ፲፭ ዘመን ኑረው ከግብፅ እንደወጡ ትናገራለች ለወንጌል ምን በቁዔት አላት እንዳይሉ ነፍሳት ፭ ሽህ ፭፻ ዘመን በገሃነም ኑረው እንደወጡ ትናገራለችና ይህን ለመናገር ፡፡

ወሣልሱ ሥርዓት ይላል ሦስተኛውን ሥርዓት ብለውታል ሥርዓት ይባላል ለኦሪት ሥርዓት አላት እመኒ እንዘ ትነውም ወእመኒ እንዘ ትነቅሕ እመኒ እንዘ ትነብር ወእመኒ እንዘ ትትነሣእ እመኒ እንዘ ትቀውም ወእመኒ እንዘ ተሐውር ኢትርሣእ ተዘክሮተ እግዚኣብሔር አምላክክ በኩሉ ጊዜ ወበኩሉ ሰዓት ትላለች፡ ለወንጌል ምን ሥርዓት አላት እንዳይሉ ይእቲኬ አንብቦቱ በኩሉ ጊዜ ትላለችና ይህን ለመንገር፡፡

ወራብዑ ስም ይላል ፬ተኛውን ስም ብለውታል ስም ይባላል፤ ለኦሪት ስም አላት ኦሪት ትባላለች፤ ለወንጌል ምን ስም አላት እንዳይሉ ወንጌል ትባላለችና ይሀን ለመንገር፡፡
ወኃምሱ መሠረት ይላል አምስተኛውን መሠረት ብለውታል መሠረት ይባላል፤ ለኦሪት መሠረት አላት አስገኝዋ ጌታ ጸሐፊዋ ሙሴ እንደሆነ ትናገራለች ለወንጌል ምን መሠረት አላት እንዳይሉ አሰገኝዋ ጌታ እንደሆነ አራት ጸሐፍት አንደጻፏት ትናገራለችና ይህን ለመንገር፡፡

ወሳድሱ ምስማክ ይላል ስድሰተኛውን ምስማክ ብለውታል ምሰማክ ይባላል ለኦሪት ምስማክ አላት ለአመ ዓቀብከ ኦሪተከ ትበልዕ ከራሜ ከራሚከ ወይሰፍፍ ማኅበብተ ወይንከ ወትሬኢ ውሉደ ውሉደከ እስከ ሣልስ ወራብዕ ትውልድ ትላለች፤ ለወንጌል ምን ምስማክ አላት እንዳይሉ ከአርአያ እግዚአብሔር አሰጥታ ታከብራለችና ይሀን ለመንገር፡፡

ወሳብእ አርእስተ ነገር ይላል ሰባተኛውን ክፍለ ነገር ብለውታል ክፍለ ነገር ይባላል፤ ለኦሪት ክፍል አላት አራት ወገን ሁና ተጽፋለችና ለወንጌል ምን ክፍል አላት እንዳይሉ አራት ወገን ሁና ተጽፋለችና ይህን ለመንገር፤ ይህ አንድ ወገን ነው፤ ሁለተኛ ባዳራሸ ገብቶ ወደ እልፍኝ ማለፍ እርካብ ተረግጦ ወደኮርቻ መውጣት እንዲመች መቅድሙን ተምሮ ወደወንጌል ሲገቡ ይመቻልና። ከማያውቁት አገር የሚያውቁትን ሰው ቢያገኙት ደስ እንዲያሰኝ፤መቅድሙን ተምሮ ወደ ወንጌል ሲገቡ ደስ ያሰኛልና፤ ፪ቱን አንድ ወገን አድርገህ ፪ት በል። ሦስተኛም ለመጻሕፍት መልክ ለመስጠት ዓቢዩን በቀይ ንዑሱን በጥቁር ዘሩን በነጥብ ለመለየት፤ ሐዋርያት በዘላን አሞንዮስ አውሳብዮስ በቋሚ ይመሰላሉ፤ ዘላን ላሙን ነድቶ አምጥቶ አስረክቦ ይሄዳል እንጂ ላሙን አርዶ ሥጋውን አወራርዶ ይህ ብልት ይህ ነው ብሎ አያስረክብም ቋሚ ግን ከዘላን ተቀብሎ ላሙን አርዶ ሥጋውን  አወራርዶ ይህ ብልት ይህ ነው ብሎ ሰፍሮ ቆጽሮ ያስረክባል እንዳይሠረቅ፡፡ ዘላን ላሙን ነድቶ አምጥቶ አንዲያስረክብ ሐዋርያትም አራት አድርገው ጻፉ እንጂ ይህን ያህል ዓቢይ ምዕራፍ ይህን ያህል ንዑስ ምዕራፍ ይህን ያህል ዘር ብለው አልጻፉም፡፡ ቋሚ ከዘላን ተቀብሎ ላሙን አርዶ ሥጋውን አወራርዶ ይህ ብልት ይህ ነው ብሉ ሰፍሮ ቆጽሮ እንዲያስረክብ እንዳይሠረቅ አሞንዮስ አውሳብዮስም ይህን ያህል ዓቢይ ምዕራፍ ይህን ያህል ንዑስ ምዕራፍ ይህን ያህል ዘር ብለው ይጽፋሉና ስለዚህ ሐዋርያት በዘላን አሞንዮስ አውሳብዮስ በቋሚ ይመሰላሉ።

በስመ አብ።

በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን፡፡ 

ወወልድ  

በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን።

ወመንፈስ ቅዱስ ።

በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱሰን ሠራጺ ብለን፡፡

፩ዱ አምላክ ዘለዓለም ። 

ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብንል በባሕርይ በሕልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን ንቀድም ። አንድም አብን በልብ ወልድን በቃል መንፈስ ቅዱስን በእስትንፋስ መስለን በባሕርይ በሕልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን። 

ንቀድም በረድኤተ እግዚአብሔር ። 

በእግዚአብሔር አጋዥነት እንጀምራለን፡፡

ሐተታ እግዚአብሔርን አጋዥ ካላደረጉ እማር አስተምር አነብ እተረጐም እጽፍ እደጐስ ቢሉ አይቻልምና ኩላኬ ፍድፉዴ እንተ ይገብራ ብእሲ ኢትትፌጻም ዘእንበለ በረድኤተ እግዚአብሔር በከመ ቃሉ ለእግዚእነ ወዘእንበሌየሰ አልቦ ዘትክሉ ገቢር ወኢምንትኒ እንዲል ። አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዳስ ዘለዓለም፡፡  አሐዱ ዘለዓለም አምላክ ዘለዓለም ብለህ ግጠም ። አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ዘለዓለም አለ በሦስትነታቸው ርባዔ የለባቸውምና፡፡  አሐዱ ዘለዓለም አለ ባንድነታቸው ምንታዌ የለባቸውምና ። አምላክ ዘለዓለም አለ ከዚህ ዓለም ንጉሥ ሲለይ ። የዚሀ ዓለም ንጉሥ አንዱ ሲያልፍ አንዱ ሲተርፍ ነው። ሥላሴ ግን ቅድመ ዓለም ማዕከለ ዓለም ድኀረ ዓለም ንጉሥ ናቸውና  ሎቱ ስብሐት። ክብር ይግባውና፡፡

ይትባረክ ሥሙ ።

ሥሙ ይክበር ይመስገንና ። 

ወይትለዓል ዝክሩ ።

በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና።

ወፍጽምናሁ ።

ሕልውናው አንድነቱ ከፍ ከፍ ይበልና ።

ዘእምኔሁ ሢመተ ኩሉ ኃይል ። 

የመላእክት ሹመት ከሱ የሚገኝ። ሠያምያነ መላእክት ኄራን እንዲል፡፡  አንድም የቀሳውስት ሹመት ከሱ የሚገኝ። ወውእቱ ዘይሠይሞሙ ለሰብአ ዛቲ መዓርግ እንዲል ። አንድም የነገሥታት የመኳንንት ሹመት ከሱ የሚገኝ። አእምር ከመ ልዑል ይኴንን መንግሥተ ደቂቀ እጓለ እመሕያው ወለዘፈቀደ ይሁብ እስመ ኢይሰየም መኰንን ዘእንበለ እምኀበ እግዚአብሔር እንዲል ።  

ወቦቱ ተፍጻሜተ ኩሉ ስዕለት ።

የልመና ሁሉ ፍጻሜ በሱ የሚሆን ወኢይትከሃል ያቅርቡ ወኢምንተኒ ዘእንበለ በአራቅይናሁ ለወልድ እንዲል። 

ወኀቤሁ ምብጻሐ ኩሉ አስተብቁዖት።

የምልጃ ሁሉ መዳረሻ ወደርሱ የሚሆን። ሐተታ ጻድቃን መላአክት ቢያማልዱ ፍጻሜው ወያሱ ነውና ። ስዕለት አስተብቀዖት የሚለው እንደምን ነው ቢሉ ስዕለት የሚለው በሰባቱ በዐሥራ ሁለቱ በሃያ አራቱ ጊዜያት የሚጸለየው ነው አስተብቀዖት የሚለው ሰው ሰለሚሻው ነገር ግብር ገብቶ ቀኖና ይዞ የሚያመለክተው ነው፡፡ 

በጽሒፈ መቅድመ አርባዕቱ ወንጌላት ቅዱሳት ።

ንቀድም ጽሒፈ በ በግዕዝ ቦታ የገባ ነው አንተሰ ኢቀባዕከኒ በዘይት ርእስየ ለምሑራነ ልብ በጥበብ። ቀስተ ዮናታን ኢተቀብዓት በቅብዕ ዘእንበለ በደመ ኃያላን፡፡ ኦሪት ወነቢያት ወወንጌል ሰበኩ በክርስቶስ እንዲል ። የአራቱን ወንጌል መቅድም ሰባቱን ክፍል መጻፍን እንጀምራለን ። አንድም በ ን ስለ ማውጣት በመጻፍ እንጀምራለን በቃል መጀመር አለና፡፡ አንድም ወታቀንተኒ ኃይለ በጸብዕ እንዲል በጽሒፍ ጊዜ ረድኤተ እግዚአብሔርን መጠጋትን ለነገራችን ጥግ እናደርጋለን።
****************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
29/05/2011 ዓም

Tuesday, February 5, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 1


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ቅዱስ ወንጌልን ሊቃውንት መተርጉማን አባቶቻችን የተረጎሙትን ቤተክርስቲያናችን የምትጠቀምበትን አንድምታ ትርጓሜ አምላከ ቅዱሳን እንደፈቀደ በየቀኑ ጥቂት ጥቂት በማድረግ ለማስነበብ እንሞክራለን ይህን ማድረግ በጣም አድካሚና ፈታኝ እንደሚሆን አስባለሁ ግን በእግዚአብሔር አጋዥነት በእመ ብርሃን በወላዲተ አምላክ ምልጃ በእናንተም በወንድሞቸ እና በእህቶቼ ጸሎት በርትቼ ለፍጻሜ እንደምበቃ እተማመናለሁ፡፡
ይችን የዛሬዋን ቀን አንድ ብላችሁ ቁጠሩልኝ ለማንበብ እንዳትሰለቹ እኔ ለመጻፍ አልሰለቸሁምና፡፡
ስጽፍ ፊደል ብገድፍ ምስጢር ባጓድል እናንተ እየተመለከታችሁ እንድታርሙኝ በእግዚአብሔር ስም ከወዲሁ አሳስባለሁ፡፡ መልካም ንባብ!
“ይኸው ዛሬ ጀምረናል!”
ብዙዎች እንዲመለከቱት እንዲማሩበት ማጋራትን እንዳትረሱ facebookcom/melkamubeyeneB የሚለውን ይህን ገጽም መወዳጀትዎን አይዘንጉ!
***ወንጌል ቅዱስ ክፍል 1***
==================
አርባዕቱ ወንጌላውያን 
አበው “በቃል ያለ ይረሳል በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል” እንዲሉ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሁለቱ፤ ከሰብዓ አርድእት ሁለቱ በመንፈስ ቅዱስ ተመርጠው ቅዱስ ወንጌልን በመጻፋቸው አራቱ ወንጌላውያን ተብለው ተሰይመዋል። እነሱም ቅዱስ ማቴዎስ፤ ቅዱስ ማርቆስ፤ ቅዱስ ሉቃስ፤ ቅዱስ ዮሐንስ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ይደልዎ ለዘያነብብ ቅድመ ይዝክር ሰሞ ለበዓለ መጽሐፍ ወእምዝ ይምሐር ወያንብብ” እንደ አለው (ተግሣጽ ፰ ገጽ ፺፱) ስለ አራቱ ወንጌሎች ከመጻፋችንና ከመናገራችን አስቀድሞ ስለ አራቱ ወንጌላውያን የሕይወት ታሪከ በአጭሩ ልንገልጽ እንወዳለን።
፩. ሀ/ ቅዱስ ማቴዎስ
በዕብራይስጥና በአረማይስጥ ቋንቋ ማቴዎሰ ማለት ሀብተ አምላክ ወይም የአምላክ ስጦታ ማለት እንደሆነ ይነገራል። በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የስም ዝርዝር ውስጥ በሁለተኛውና በሦስተኛው ማለትም በማርቆስና በሉቃስ ወንጌል በተራ ቁጥር ሰባተኛ ሲሆን ስሙም ማቴዎስ በመባል ተመዝግቦአል። (ማር ፫፥፲፮-፲፱፤ ሉቃ ፮፥፲፬-፲፮) ራሱ በጻፈው ወንጌልና በሐዋርያት ሥራ ደግሞ በተራ ቁጥር ስምንተኛ ሆኖ ማቴዎስ በመባል ተመዝግቦአል። (ማቴ ፲፥፪-፬፤ የሐዋ ሥራ ፩፥፲፫) ሌዊ ለሐዋርያነት ከመመረጡ በፊት የተጠራበት ስሙ ሲሆን ማቴዎስ ደግሞ ለወንጌል አገልግሎት ለሐዋርያነት ከተጠራ በኋላ የተጠራበት ስሙ ነው።
ለ/ የመጀመሪያ ሥራው
ቅዱስ ማቴዎስ ለሐዋርያነት ከመጠራቱ በፊት ሥራው (ሊቀ መጸብሐን) ቀራጭ ነበር። በሐዲስ ኪዳን የትምህርት አገላለጽ ቀራጮች እንደ አመንዝሮች፤ ዓመፀኞች ሌቦች ይቆጠሩ ነበር። (ሉቃ ፲፰፥፲፩-፲፪) በዚህ አንጻር ማቴዎሰ ቀራጭ እንደ መሆኑ መጠን የዘመኑ የሃይማኖት ሰዎች ይጠሉት ነበር። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማቴዎሰን በመቅረጫው ቦታ አገኘውና “ተከተለኝ በማለት ስለ ጠራው ሁሉን ትቶ ተከተለው። (ማቴ ፱፥፱) ቀራጩ ማቴዎስ ሐዋርያና ወንጌላዊ ሆነ፤ መደቡ ከአመንዝሮችና ከአመፀኞች ጋር የነበረ ነው ሌዊ ከአሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ። ከአራቱ ወንጌሎች የመጀመሪያውን ወንጌል ጌታ ከዐረገ ስምንተኛው ተፈጽሞ ዘጠነኛው ሲጀመር  ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት በዕብራይስጥ ቋንቋ ጻፈ።
ሐ/ ምልክቱ
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በሥጋ ከአብርሃምና ከዳዊት ዘር መወለዱን ለማስረዳት ከአብርሃም እስከ ቅድስት ድንግል ማርያም ድረሰ በሰፊው ስለጻፈ ከጥንት ጀምሮ ማቴዎስ በገጸ ሰብእ ተመስሎአል። ከሦስቱ ወንጌላውያን ይልቅ በማቴዎስ ወንጌል ክርስቶስ ወልደ እጓለ እመሕያው (የሰው ልጅ) በመባል ብዙ ጊዜ ስለተጠራ ለማቴዎስ የገጸ ሰብእ ምልክት ከአሰጡት ምክንያቶች አንዱ ነው። 
፪. ሀ/ ቅዱስ ማርቆስ
ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያና ወንጌላዊ፤ እንደዚሁም ሰማዕት ነው። ከዚህም ጋር የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን መሥራች አባት ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆሰ ኢየሩሳሌም ውስጥ ክርስቲያኖች በቤቷ ለጸሎትና ለትምህርት ይሰበሰቡ የነበረችው የማርያም ልጅ ሲሆን አባቱ አርስጦሎስ፤ አጐቱ በርናባስ ነበሩ። ቅዱሳን ሐዋርያት ሁልጊዜ በእናቱ ቤት እየተሰበሰቡ ጸሎት በማድረግ ፈጣሪያቸውን ያመስግኑ ነበር። (የሐዋ ሥራ ፲፪፥፲፪) እናቱ ማርያም እጅግ የከበረች ባለጸጋ እንደነበረችም በመጽሐፈ ስንክሳር ተጠቅሶአል። ቅዱስ ማርቆስ በመጀመሪያ ዮሐንሰ እየተባለ ይጠራ ነበር እናቱም ልጇን ማርቆስን በዕብራይሰጥና በዮናናውያን ቋንቋ እያስተማረች እንዳሳደገችው ይታመናል። ቅዱስ ማርቆስ በወጣትነት ዘመኑ የጌታን ትምህርት ሰምቶ ልቡ ሰለተነካ ሁሉንም ነገር ትቶ የክርስቶስን ወንጌል መንግሥተ ሰማያት ለመስበክ ቆርጦ ተነሣ። ጌታ ከዐረገ በኋላ ቅዱስ ማርቆስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በመሆን ወንጌልን በማስተማሩ ቅዱስ ጴጥሮስ ልጄ እያለ ይጠራዋል። (፩፡ጴጥ ፭፥፲፪) ከጌታ የሰማውንና የተማረውን ጽፏል። ወንጌሉም ከእሱ በኋላ በእሱ ስም ተጠርቷል። ወንጌሉን የጻፈበት ዘመን ጌታ ከዐረገ አሥራ አንደኛው ተፈጽሞ አሥራ ሁለተኛው ሲጀመር ቀላውዴዎስ ቄሳር በነገሠ በአራተኛው ዓመት ሲሆን የጻፈበትም ቋንቋ ሮማይሰጥ ነው።
ለ/ ምልክቱ
ቅዱስ ማርቆስ በአንበሳ ተመስሏል። ምክንያቱም አንበሳ በቅዱስ መጽሐፍ ለእግዚአብሔር፤ ለሰዎችም ምልክት እንደሆነ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። በኦሪት ዘፍጥረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሁዳና ከንጉሥ ዳዊት ዘር እንደሚወለድ ተተንብዮአል። በነቢዩ በሆሴዕ እግዚአብሔር አንበሳ ተብሎ መጠራቱን እናያለን (፲፫፥፯) መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አሸናፊው የይሁዳ አንበሳ ተብሎ መሰየሙን በራዕየ ዮሐንስ ተጽፏል። (፭፥፭) በአሶራውያንና በዕብራውያን ዘንድ በዙፋንና በበትረ መንግሥት ላይ የአንበሳ ምልክት ይሣል ነበር። (፩፡ነገ ፯፥፳፱-፴፮፤ ፲፥፲፱-፳)። ቅዱስ ማርቆስ በአንበሳ የተመሰለበት ዐቢይ ምክንያት ደግሞ በግብጽ የነበሩትን የአንበሳ ጣኦታት በስብከቱ አጥፍቶ አንበሳ ዕጓለ አንበሳ የተባለውን ክርስቶስን በመስበኩ ነው።
፫. ሀ/ ቅዱስ ሉቃስ
ወንጌላዊው ሉቃስ አንጾኪያ ውስጥ የግሪክ ወገን ከሆኑ ቤተሰቦች ተወለደ፤ ጌታ ከዐረገ በኋላም ቆይቶ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር አብሮ ወንጌልን እንዳስተማረ ተጠቅሷል (፪፡ጢሞ ፬፥፬) ሐኪምም እንደነበረ ተጽፎአል (ቆላስይስ ፬፥፲፬)። በስሙ የሚጠራውን ወንጌልና የሐዋርያትን ሥራ የጻፈው ወንጌላዊው ሉቃስ ነው። ጌታ ከሙታን ተለይቶ ሞትን ድል አድርጎ በተነሣበት ቀን በፍኖተ ኤማሑስ (በኤማሑስ መንገድ) ጌታችን ከተገለጸላቸው ከሁለቱ ደቀመዛሙርት አንዱ ቅዱስ ሉቃስ እንደሆነ የቤተክርሰቲያን ሊቃውንት ያስተምራሉ። (ሉቃስ ፳፬፥፲፫-፴፪)። ወንጌሉንም የጻፈበት ዘመን ጌታ ከዐረገ ሃያ አንድ ዓመት ተፈጽሞ ሃያ ሁለተኛው ሲጀመር ቀላውዴዎሰ ቄሣር በነገሠ በአሥራ አራተኛው ዓመት በዮናኒ ቋንቋ ነው።
ለ/ ምልክቱ
ወንጌላዊው ሉቃስ በላህም ይመሰላል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከብቶች በረት መወለዱን፤ በዕለተ ልደቱም የከብት እረኞች ከመላእክት ጋር መዘመራቸውን ከሌሎች ወንጌላውያን ሠፋ አድርጐ ስለሚተርክ ነው። (ሉቃ ፪፥፰-፲፰) ከዚህም ሌላ ላህም በብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት እንስሳ ሲሆን ሉቃስም የክርስቶስን መስዋዕትነት በፍሪዳ ምሳሌ ጽፏል። (ሉቃ ፲፭፥፳፪-፳፬) ላም የቀንድ ከብት ነው በዚሁ መሠረት ወንጌላዊው ሉቃስ ክርሰቶስ ቀርነ መድኃኒት እንደሆነ ነቢዩ ዘካርያስ የተናገረውን ትንቢት በመግለጽ ስለጻፈ የላህም ምልክት እንደተሰጠው መተርጕማን ሊቃውንት ይናገራሉ።
፬. ሀ/ ወንጌላዊው ዮሐንስ
ጌታ ይወደው የነበረው የዘብዴዎሰ ልጅ ዮሐንስ በፍልስጥኤም ከፍልስጥኤምም ውጪ ክርስትና እንድትስፋፋ ያደረገ ጌታ በመስቀል ላይ ሳለ እመቤታችንን እንዲያገለግላት አደራ የተቀበለ የእመቤታችን የአደራ ልጅ የሆነ ነው። (ዮሐ ፲፱፥፳፮) ከዚህም ጋር ከቅዱስ ጳውሎስ ዕረፍት በኋላ ከኢየሩሳሌም ወደ ኤፌሶን ሄዶ በትንሿ እስያ ወንጌልን የሰበከ በሮማዊው ቄሣር በዶሚቴያኖስ ዘመነ መንግሥት ወደ ፍጥሞ ደሴት ተሰዶ በእስር ቤት ሳለ ራእይን የጻፈ ከዶሚቴያኖስ ሞት በኋላ ወደ ኤፌሶን ተመልሶ “ልጆቼ እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ” እያለ ያስተማረ በስሙ የሚጠሩትን ወንጌሉን እና ሦስቱን መልዕክታት እንዲሁም ራዕይን የጸፈ ነባቤ መለኮት የሚል ስም የተሰጠው ሐዋርያ ነው። ወንጌሉንም ጌታ ከዐረገ በሠላሳ (በሠላሳ አምስትም የሚሉ አሉ)። ኔሮን ቄሣር በነገሠ በስምንት ዓመት በየናኒ ቋንቋ ጻፈ። በልሳነ ጽርዕ የሚልም አብነት አለ።
ለ/ ምልክቱ
ወንጌላዊው ዮሐንስ በንሰር ተመስሏል። በሥነ አንስርት (አሞሮች) ጥናት ሊቃውንት እንደሚነገረው ንስር ከሌሎች አዕዋፍ ሁሉ ተለይቶ ወደ ላይ መጥቆ ይበራል። በላይም ሆኖ በመሬት ላይ ያሉትን ረቂቃን ነገሮችን አጣርቶ መመልከት ይችላል። ወንጌላዊው ዮሐንስም ወንጌሉን ሲጽፍ ከወንጌላውያኑ አጻጻፍ በተለየ በምሥጢረ ሥላሴ ይጀምራል፤ ስለሥጋዌም ሲጽፍ ወደላይ መጥቆ በማሰብ ቅድመ ዓለም ስለነበረው ቃል ይተርክና ያ ቀድሞ የነበረው ቃል ሥጋ ሆነ በማለት ይጽፋል (ዮሐ ፩፥፲፬)። ንስር ወደላይ እጅግ መጥቆ እንደሚበርና ወደ ምድር ሲመለከት ረቂቃን የሆኑትን ነገሮች መመልከት እንደሚችል፤ ዮሐንስም ረቂቅና ጥልቅ የሆነውን ትምህርት ያስተምር ነበር። እነዚህም እግዚአብሔር ፍቅር ነው እግዚአብሔር ብርሃን ነው ክርስቶስ ሕይወት ነው የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው።
ስለዚህ ከቀድሞ አባቶቻችን ሊቃውንት ሲወርድ ሲዋረድ ከእኛ የደረሰውን የአራቱን ወንጌሎች የአንድምታ ትርጓሜ መምህራን እንዲያስተምሩበት ደቀመዛሙርት እንዲማሩበት ምእመናን እምነታቸውን በስፋትና በጥልቀት እንዲረዱበት ሲያቀርብ መንፈሳዊ ደስታ ይሰማዋል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት።
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
28/05/2011 ዓም

Sunday, February 3, 2019

ፍኖተ ጽድቅ ዘተዋሕዶ