በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ቅዱስ
ወንጌልን ሊቃውንት መተርጉማን አባቶቻችን የተረጎሙትን ቤተክርስቲያናችን የምትጠቀምበትን አንድምታ ትርጓሜ አምላከ ቅዱሳን እንደፈቀደ
በየቀኑ ጥቂት ጥቂት በማድረግ ለማስነበብ እንሞክራለን ይህን ማድረግ በጣም አድካሚና ፈታኝ እንደሚሆን አስባለሁ ግን በእግዚአብሔር
አጋዥነት በእመ ብርሃን በወላዲተ አምላክ ምልጃ በእናንተም በወንድሞቸ እና በእህቶቼ ጸሎት በርትቼ ለፍጻሜ እንደምበቃ እተማመናለሁ፡፡
ስጽፍ
ፊደል ብገድፍ ምስጢር ባጓድል እናንተ እየተመለከታችሁ እንድታርሙኝ በእግዚአብሔር ስም ከወዲሁ አሳስባለሁ፡፡ መልካም ንባብ!
“ይኸው
ዛሬ ጀምረናል!”
ብዙዎች
እንዲመለከቱት እንዲማሩበት ማጋራትን እንዳትረሱ facebookcom/melkamubeyeneB የሚለውን ይህን ገጽም መወዳጀትዎን አይዘንጉ!
***ወንጌል
ቅዱስ ክፍል 1***
==================
አርባዕቱ
ወንጌላውያን
አበው
“በቃል ያለ ይረሳል በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል” እንዲሉ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሁለቱ፤ ከሰብዓ አርድእት ሁለቱ በመንፈስ ቅዱስ ተመርጠው
ቅዱስ ወንጌልን በመጻፋቸው አራቱ ወንጌላውያን ተብለው ተሰይመዋል። እነሱም ቅዱስ ማቴዎስ፤ ቅዱስ ማርቆስ፤ ቅዱስ ሉቃስ፤ ቅዱስ
ዮሐንስ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ይደልዎ ለዘያነብብ ቅድመ ይዝክር ሰሞ ለበዓለ መጽሐፍ ወእምዝ ይምሐር ወያንብብ” እንደ
አለው (ተግሣጽ ፰ ገጽ ፺፱) ስለ አራቱ ወንጌሎች ከመጻፋችንና ከመናገራችን አስቀድሞ ስለ አራቱ ወንጌላውያን የሕይወት ታሪከ በአጭሩ
ልንገልጽ እንወዳለን።
፩.
ሀ/ ቅዱስ ማቴዎስ
በዕብራይስጥና
በአረማይስጥ ቋንቋ ማቴዎሰ ማለት ሀብተ አምላክ ወይም የአምላክ ስጦታ ማለት እንደሆነ ይነገራል። በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የስም
ዝርዝር ውስጥ በሁለተኛውና በሦስተኛው ማለትም በማርቆስና በሉቃስ ወንጌል በተራ ቁጥር ሰባተኛ ሲሆን ስሙም ማቴዎስ በመባል ተመዝግቦአል።
(ማር ፫፥፲፮-፲፱፤ ሉቃ ፮፥፲፬-፲፮) ራሱ በጻፈው ወንጌልና በሐዋርያት ሥራ ደግሞ በተራ ቁጥር ስምንተኛ ሆኖ ማቴዎስ በመባል
ተመዝግቦአል። (ማቴ ፲፥፪-፬፤ የሐዋ ሥራ ፩፥፲፫) ሌዊ ለሐዋርያነት ከመመረጡ በፊት የተጠራበት ስሙ ሲሆን ማቴዎስ ደግሞ ለወንጌል
አገልግሎት ለሐዋርያነት ከተጠራ በኋላ የተጠራበት ስሙ ነው።
ለ/
የመጀመሪያ ሥራው
ቅዱስ
ማቴዎስ ለሐዋርያነት ከመጠራቱ በፊት ሥራው (ሊቀ መጸብሐን) ቀራጭ ነበር። በሐዲስ ኪዳን የትምህርት አገላለጽ ቀራጮች እንደ አመንዝሮች፤
ዓመፀኞች ሌቦች ይቆጠሩ ነበር። (ሉቃ ፲፰፥፲፩-፲፪) በዚህ አንጻር ማቴዎሰ ቀራጭ እንደ መሆኑ መጠን የዘመኑ የሃይማኖት ሰዎች
ይጠሉት ነበር። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማቴዎሰን በመቅረጫው ቦታ አገኘውና “ተከተለኝ በማለት ስለ ጠራው ሁሉን ትቶ
ተከተለው። (ማቴ ፱፥፱) ቀራጩ ማቴዎስ ሐዋርያና ወንጌላዊ ሆነ፤ መደቡ ከአመንዝሮችና ከአመፀኞች ጋር የነበረ ነው ሌዊ ከአሥራ
ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ። ከአራቱ ወንጌሎች የመጀመሪያውን ወንጌል ጌታ ከዐረገ ስምንተኛው ተፈጽሞ ዘጠነኛው ሲጀመር ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት በዕብራይስጥ ቋንቋ ጻፈ።
ሐ/
ምልክቱ
ጌታችንና
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በሥጋ ከአብርሃምና ከዳዊት ዘር መወለዱን ለማስረዳት ከአብርሃም እስከ ቅድስት ድንግል ማርያም ድረሰ
በሰፊው ስለጻፈ ከጥንት ጀምሮ ማቴዎስ በገጸ ሰብእ ተመስሎአል። ከሦስቱ ወንጌላውያን ይልቅ በማቴዎስ ወንጌል ክርስቶስ ወልደ እጓለ
እመሕያው (የሰው ልጅ) በመባል ብዙ ጊዜ ስለተጠራ ለማቴዎስ የገጸ ሰብእ ምልክት ከአሰጡት ምክንያቶች አንዱ ነው።
፪.
ሀ/ ቅዱስ ማርቆስ
ቅዱስ
ማርቆስ ሐዋርያና ወንጌላዊ፤ እንደዚሁም ሰማዕት ነው። ከዚህም ጋር የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን መሥራች አባት ነው። ወንጌላዊው
ቅዱስ ማርቆሰ ኢየሩሳሌም ውስጥ ክርስቲያኖች በቤቷ ለጸሎትና ለትምህርት ይሰበሰቡ የነበረችው የማርያም ልጅ ሲሆን አባቱ አርስጦሎስ፤
አጐቱ በርናባስ ነበሩ። ቅዱሳን ሐዋርያት ሁልጊዜ በእናቱ ቤት እየተሰበሰቡ ጸሎት በማድረግ ፈጣሪያቸውን ያመስግኑ ነበር። (የሐዋ
ሥራ ፲፪፥፲፪) እናቱ ማርያም እጅግ የከበረች ባለጸጋ እንደነበረችም በመጽሐፈ ስንክሳር ተጠቅሶአል። ቅዱስ ማርቆስ በመጀመሪያ ዮሐንሰ
እየተባለ ይጠራ ነበር እናቱም ልጇን ማርቆስን በዕብራይሰጥና በዮናናውያን ቋንቋ እያስተማረች እንዳሳደገችው ይታመናል። ቅዱስ ማርቆስ
በወጣትነት ዘመኑ የጌታን ትምህርት ሰምቶ ልቡ ሰለተነካ ሁሉንም ነገር ትቶ የክርስቶስን ወንጌል መንግሥተ ሰማያት ለመስበክ ቆርጦ
ተነሣ። ጌታ ከዐረገ በኋላ ቅዱስ ማርቆስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በመሆን ወንጌልን በማስተማሩ ቅዱስ ጴጥሮስ ልጄ እያለ ይጠራዋል።
(፩፡ጴጥ ፭፥፲፪) ከጌታ የሰማውንና የተማረውን ጽፏል። ወንጌሉም ከእሱ በኋላ በእሱ ስም ተጠርቷል። ወንጌሉን የጻፈበት ዘመን ጌታ
ከዐረገ አሥራ አንደኛው ተፈጽሞ አሥራ ሁለተኛው ሲጀመር ቀላውዴዎስ ቄሳር በነገሠ በአራተኛው ዓመት ሲሆን የጻፈበትም ቋንቋ ሮማይሰጥ
ነው።
ለ/
ምልክቱ
ቅዱስ
ማርቆስ በአንበሳ ተመስሏል። ምክንያቱም አንበሳ በቅዱስ መጽሐፍ ለእግዚአብሔር፤ ለሰዎችም ምልክት እንደሆነ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል።
በኦሪት ዘፍጥረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሁዳና ከንጉሥ ዳዊት ዘር እንደሚወለድ ተተንብዮአል። በነቢዩ በሆሴዕ
እግዚአብሔር አንበሳ ተብሎ መጠራቱን እናያለን (፲፫፥፯) መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አሸናፊው የይሁዳ አንበሳ ተብሎ መሰየሙን
በራዕየ ዮሐንስ ተጽፏል። (፭፥፭) በአሶራውያንና በዕብራውያን ዘንድ በዙፋንና በበትረ መንግሥት ላይ የአንበሳ ምልክት ይሣል ነበር።
(፩፡ነገ ፯፥፳፱-፴፮፤ ፲፥፲፱-፳)። ቅዱስ ማርቆስ በአንበሳ የተመሰለበት ዐቢይ ምክንያት ደግሞ በግብጽ የነበሩትን የአንበሳ ጣኦታት
በስብከቱ አጥፍቶ አንበሳ ዕጓለ አንበሳ የተባለውን ክርስቶስን በመስበኩ ነው።
፫.
ሀ/ ቅዱስ ሉቃስ
ወንጌላዊው
ሉቃስ አንጾኪያ ውስጥ የግሪክ ወገን ከሆኑ ቤተሰቦች ተወለደ፤ ጌታ ከዐረገ በኋላም ቆይቶ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር አብሮ ወንጌልን እንዳስተማረ
ተጠቅሷል (፪፡ጢሞ ፬፥፬) ሐኪምም እንደነበረ ተጽፎአል (ቆላስይስ ፬፥፲፬)። በስሙ የሚጠራውን ወንጌልና የሐዋርያትን ሥራ የጻፈው
ወንጌላዊው ሉቃስ ነው። ጌታ ከሙታን ተለይቶ ሞትን ድል አድርጎ በተነሣበት ቀን በፍኖተ ኤማሑስ (በኤማሑስ መንገድ) ጌታችን ከተገለጸላቸው
ከሁለቱ ደቀመዛሙርት አንዱ ቅዱስ ሉቃስ እንደሆነ የቤተክርሰቲያን ሊቃውንት ያስተምራሉ። (ሉቃስ ፳፬፥፲፫-፴፪)። ወንጌሉንም የጻፈበት
ዘመን ጌታ ከዐረገ ሃያ አንድ ዓመት ተፈጽሞ ሃያ ሁለተኛው ሲጀመር ቀላውዴዎሰ ቄሣር በነገሠ በአሥራ አራተኛው ዓመት በዮናኒ ቋንቋ
ነው።
ለ/
ምልክቱ
ወንጌላዊው
ሉቃስ በላህም ይመሰላል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከብቶች በረት መወለዱን፤ በዕለተ ልደቱም የከብት እረኞች ከመላእክት ጋር
መዘመራቸውን ከሌሎች ወንጌላውያን ሠፋ አድርጐ ስለሚተርክ ነው። (ሉቃ ፪፥፰-፲፰) ከዚህም ሌላ ላህም በብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት
እንስሳ ሲሆን ሉቃስም የክርስቶስን መስዋዕትነት በፍሪዳ ምሳሌ ጽፏል። (ሉቃ ፲፭፥፳፪-፳፬) ላም የቀንድ ከብት ነው በዚሁ መሠረት
ወንጌላዊው ሉቃስ ክርሰቶስ ቀርነ መድኃኒት እንደሆነ ነቢዩ ዘካርያስ የተናገረውን ትንቢት በመግለጽ ስለጻፈ የላህም ምልክት እንደተሰጠው
መተርጕማን ሊቃውንት ይናገራሉ።
፬.
ሀ/ ወንጌላዊው ዮሐንስ
ጌታ
ይወደው የነበረው የዘብዴዎሰ ልጅ ዮሐንስ በፍልስጥኤም ከፍልስጥኤምም ውጪ ክርስትና እንድትስፋፋ ያደረገ ጌታ በመስቀል ላይ ሳለ
እመቤታችንን እንዲያገለግላት አደራ የተቀበለ የእመቤታችን የአደራ ልጅ የሆነ ነው። (ዮሐ ፲፱፥፳፮) ከዚህም ጋር ከቅዱስ ጳውሎስ
ዕረፍት በኋላ ከኢየሩሳሌም ወደ ኤፌሶን ሄዶ በትንሿ እስያ ወንጌልን የሰበከ በሮማዊው ቄሣር በዶሚቴያኖስ ዘመነ መንግሥት ወደ ፍጥሞ
ደሴት ተሰዶ በእስር ቤት ሳለ ራእይን የጻፈ ከዶሚቴያኖስ ሞት በኋላ ወደ ኤፌሶን ተመልሶ “ልጆቼ እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ” እያለ
ያስተማረ በስሙ የሚጠሩትን ወንጌሉን እና ሦስቱን መልዕክታት እንዲሁም ራዕይን የጸፈ ነባቤ መለኮት የሚል ስም የተሰጠው ሐዋርያ
ነው። ወንጌሉንም ጌታ ከዐረገ በሠላሳ (በሠላሳ አምስትም የሚሉ አሉ)። ኔሮን ቄሣር በነገሠ በስምንት ዓመት በየናኒ ቋንቋ ጻፈ።
በልሳነ ጽርዕ የሚልም አብነት አለ።
ለ/
ምልክቱ
ወንጌላዊው
ዮሐንስ በንሰር ተመስሏል። በሥነ አንስርት (አሞሮች) ጥናት ሊቃውንት እንደሚነገረው ንስር ከሌሎች አዕዋፍ ሁሉ ተለይቶ ወደ ላይ
መጥቆ ይበራል። በላይም ሆኖ በመሬት ላይ ያሉትን ረቂቃን ነገሮችን አጣርቶ መመልከት ይችላል። ወንጌላዊው ዮሐንስም ወንጌሉን ሲጽፍ
ከወንጌላውያኑ አጻጻፍ በተለየ በምሥጢረ ሥላሴ ይጀምራል፤ ስለሥጋዌም ሲጽፍ ወደላይ መጥቆ በማሰብ ቅድመ ዓለም ስለነበረው ቃል ይተርክና
ያ ቀድሞ የነበረው ቃል ሥጋ ሆነ በማለት ይጽፋል (ዮሐ ፩፥፲፬)። ንስር ወደላይ እጅግ መጥቆ እንደሚበርና ወደ ምድር ሲመለከት
ረቂቃን የሆኑትን ነገሮች መመልከት እንደሚችል፤ ዮሐንስም ረቂቅና ጥልቅ የሆነውን ትምህርት ያስተምር ነበር። እነዚህም እግዚአብሔር
ፍቅር ነው እግዚአብሔር ብርሃን ነው ክርስቶስ ሕይወት ነው የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው።
ስለዚህ
ከቀድሞ አባቶቻችን ሊቃውንት ሲወርድ ሲዋረድ ከእኛ የደረሰውን የአራቱን ወንጌሎች የአንድምታ ትርጓሜ መምህራን እንዲያስተምሩበት
ደቀመዛሙርት እንዲማሩበት ምእመናን እምነታቸውን በስፋትና በጥልቀት እንዲረዱበት ሲያቀርብ መንፈሳዊ ደስታ ይሰማዋል።
ወስብሐት
ለእግዚአብሔር
ትንሣኤ
ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት።
**************
መልካሙ
በየነ
ደብረ
ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
28/05/2011
ዓም
No comments:
Post a Comment