Wednesday, February 6, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 2

=======================
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።  

ታሪክ

ይሀን መጽሐፍ አሞንዮስ አውሳብዮስ ተናግረውታል። እነዚህስ መነሣታቸው ከሠለስቱ ምእት በፊት ነውን ወይስ በኋላ ቢሉ በፊት ነው። ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ ከሠለስቱ ምእት በኋላ የተነሡ ሊቃውንት ከመዝ ይቤሉ አበዊነ ከመዝ ይቤሉ አጋእዝቲነ ከመዝ ይቤሉ መምሕራኒነ እያሉ ሠለስቱ ምእትን ያነሣሉ እሊህ ባለማንሣታቸው። ያስ ከሠለስቱ ምእት በኋላ የተነሡ ሊቃውንት እንዲህ እያሉ ሠለስቱ ምእትን ማንሣታቸው በሃይማኖት ቢከራከሩ ጉባዔ ቢያቆሙ ነው። እኒህ አለማንሣታቸው በሃይማኖት ባይከራከሩ ጉባዔ ባያቆሙ ነው። መነሣታቸውም ከሠለስቱ ምእት በኋላ ነው። ይህን ስለ ሦስት ነገር ተናገረውታል።

መጀመሪያውን ግብር ቀዳማዊ ብለውታል ግብር ቀዳማዊ ይባላል። ለኦሪት ግብር አላት። በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ ትላለች ለወንጌል ምን ግብር አላት እንዳይሉ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሰው እንደሆነ ትናገራለችና ይህን ለመንገር ወካልዑ በቁዔት ይላል ። 

፪ተኛውን በቁዔት ብለውታል በቁዔት ይባላል ለኦሪት በቁዔት አላት ፳ኤል ፪፻ ከ፲፭ ዘመን ኑረው ከግብፅ እንደወጡ ትናገራለች ለወንጌል ምን በቁዔት አላት እንዳይሉ ነፍሳት ፭ ሽህ ፭፻ ዘመን በገሃነም ኑረው እንደወጡ ትናገራለችና ይህን ለመናገር ፡፡

ወሣልሱ ሥርዓት ይላል ሦስተኛውን ሥርዓት ብለውታል ሥርዓት ይባላል ለኦሪት ሥርዓት አላት እመኒ እንዘ ትነውም ወእመኒ እንዘ ትነቅሕ እመኒ እንዘ ትነብር ወእመኒ እንዘ ትትነሣእ እመኒ እንዘ ትቀውም ወእመኒ እንዘ ተሐውር ኢትርሣእ ተዘክሮተ እግዚኣብሔር አምላክክ በኩሉ ጊዜ ወበኩሉ ሰዓት ትላለች፡ ለወንጌል ምን ሥርዓት አላት እንዳይሉ ይእቲኬ አንብቦቱ በኩሉ ጊዜ ትላለችና ይህን ለመንገር፡፡

ወራብዑ ስም ይላል ፬ተኛውን ስም ብለውታል ስም ይባላል፤ ለኦሪት ስም አላት ኦሪት ትባላለች፤ ለወንጌል ምን ስም አላት እንዳይሉ ወንጌል ትባላለችና ይሀን ለመንገር፡፡
ወኃምሱ መሠረት ይላል አምስተኛውን መሠረት ብለውታል መሠረት ይባላል፤ ለኦሪት መሠረት አላት አስገኝዋ ጌታ ጸሐፊዋ ሙሴ እንደሆነ ትናገራለች ለወንጌል ምን መሠረት አላት እንዳይሉ አሰገኝዋ ጌታ እንደሆነ አራት ጸሐፍት አንደጻፏት ትናገራለችና ይህን ለመንገር፡፡

ወሳድሱ ምስማክ ይላል ስድሰተኛውን ምስማክ ብለውታል ምሰማክ ይባላል ለኦሪት ምስማክ አላት ለአመ ዓቀብከ ኦሪተከ ትበልዕ ከራሜ ከራሚከ ወይሰፍፍ ማኅበብተ ወይንከ ወትሬኢ ውሉደ ውሉደከ እስከ ሣልስ ወራብዕ ትውልድ ትላለች፤ ለወንጌል ምን ምስማክ አላት እንዳይሉ ከአርአያ እግዚአብሔር አሰጥታ ታከብራለችና ይሀን ለመንገር፡፡

ወሳብእ አርእስተ ነገር ይላል ሰባተኛውን ክፍለ ነገር ብለውታል ክፍለ ነገር ይባላል፤ ለኦሪት ክፍል አላት አራት ወገን ሁና ተጽፋለችና ለወንጌል ምን ክፍል አላት እንዳይሉ አራት ወገን ሁና ተጽፋለችና ይህን ለመንገር፤ ይህ አንድ ወገን ነው፤ ሁለተኛ ባዳራሸ ገብቶ ወደ እልፍኝ ማለፍ እርካብ ተረግጦ ወደኮርቻ መውጣት እንዲመች መቅድሙን ተምሮ ወደወንጌል ሲገቡ ይመቻልና። ከማያውቁት አገር የሚያውቁትን ሰው ቢያገኙት ደስ እንዲያሰኝ፤መቅድሙን ተምሮ ወደ ወንጌል ሲገቡ ደስ ያሰኛልና፤ ፪ቱን አንድ ወገን አድርገህ ፪ት በል። ሦስተኛም ለመጻሕፍት መልክ ለመስጠት ዓቢዩን በቀይ ንዑሱን በጥቁር ዘሩን በነጥብ ለመለየት፤ ሐዋርያት በዘላን አሞንዮስ አውሳብዮስ በቋሚ ይመሰላሉ፤ ዘላን ላሙን ነድቶ አምጥቶ አስረክቦ ይሄዳል እንጂ ላሙን አርዶ ሥጋውን አወራርዶ ይህ ብልት ይህ ነው ብሎ አያስረክብም ቋሚ ግን ከዘላን ተቀብሎ ላሙን አርዶ ሥጋውን  አወራርዶ ይህ ብልት ይህ ነው ብሎ ሰፍሮ ቆጽሮ ያስረክባል እንዳይሠረቅ፡፡ ዘላን ላሙን ነድቶ አምጥቶ አንዲያስረክብ ሐዋርያትም አራት አድርገው ጻፉ እንጂ ይህን ያህል ዓቢይ ምዕራፍ ይህን ያህል ንዑስ ምዕራፍ ይህን ያህል ዘር ብለው አልጻፉም፡፡ ቋሚ ከዘላን ተቀብሎ ላሙን አርዶ ሥጋውን አወራርዶ ይህ ብልት ይህ ነው ብሉ ሰፍሮ ቆጽሮ እንዲያስረክብ እንዳይሠረቅ አሞንዮስ አውሳብዮስም ይህን ያህል ዓቢይ ምዕራፍ ይህን ያህል ንዑስ ምዕራፍ ይህን ያህል ዘር ብለው ይጽፋሉና ስለዚህ ሐዋርያት በዘላን አሞንዮስ አውሳብዮስ በቋሚ ይመሰላሉ።

በስመ አብ።

በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን፡፡ 

ወወልድ  

በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን።

ወመንፈስ ቅዱስ ።

በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱሰን ሠራጺ ብለን፡፡

፩ዱ አምላክ ዘለዓለም ። 

ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብንል በባሕርይ በሕልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን ንቀድም ። አንድም አብን በልብ ወልድን በቃል መንፈስ ቅዱስን በእስትንፋስ መስለን በባሕርይ በሕልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን። 

ንቀድም በረድኤተ እግዚአብሔር ። 

በእግዚአብሔር አጋዥነት እንጀምራለን፡፡

ሐተታ እግዚአብሔርን አጋዥ ካላደረጉ እማር አስተምር አነብ እተረጐም እጽፍ እደጐስ ቢሉ አይቻልምና ኩላኬ ፍድፉዴ እንተ ይገብራ ብእሲ ኢትትፌጻም ዘእንበለ በረድኤተ እግዚአብሔር በከመ ቃሉ ለእግዚእነ ወዘእንበሌየሰ አልቦ ዘትክሉ ገቢር ወኢምንትኒ እንዲል ። አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዳስ ዘለዓለም፡፡  አሐዱ ዘለዓለም አምላክ ዘለዓለም ብለህ ግጠም ። አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ዘለዓለም አለ በሦስትነታቸው ርባዔ የለባቸውምና፡፡  አሐዱ ዘለዓለም አለ ባንድነታቸው ምንታዌ የለባቸውምና ። አምላክ ዘለዓለም አለ ከዚህ ዓለም ንጉሥ ሲለይ ። የዚሀ ዓለም ንጉሥ አንዱ ሲያልፍ አንዱ ሲተርፍ ነው። ሥላሴ ግን ቅድመ ዓለም ማዕከለ ዓለም ድኀረ ዓለም ንጉሥ ናቸውና  ሎቱ ስብሐት። ክብር ይግባውና፡፡

ይትባረክ ሥሙ ።

ሥሙ ይክበር ይመስገንና ። 

ወይትለዓል ዝክሩ ።

በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና።

ወፍጽምናሁ ።

ሕልውናው አንድነቱ ከፍ ከፍ ይበልና ።

ዘእምኔሁ ሢመተ ኩሉ ኃይል ። 

የመላእክት ሹመት ከሱ የሚገኝ። ሠያምያነ መላእክት ኄራን እንዲል፡፡  አንድም የቀሳውስት ሹመት ከሱ የሚገኝ። ወውእቱ ዘይሠይሞሙ ለሰብአ ዛቲ መዓርግ እንዲል ። አንድም የነገሥታት የመኳንንት ሹመት ከሱ የሚገኝ። አእምር ከመ ልዑል ይኴንን መንግሥተ ደቂቀ እጓለ እመሕያው ወለዘፈቀደ ይሁብ እስመ ኢይሰየም መኰንን ዘእንበለ እምኀበ እግዚአብሔር እንዲል ።  

ወቦቱ ተፍጻሜተ ኩሉ ስዕለት ።

የልመና ሁሉ ፍጻሜ በሱ የሚሆን ወኢይትከሃል ያቅርቡ ወኢምንተኒ ዘእንበለ በአራቅይናሁ ለወልድ እንዲል። 

ወኀቤሁ ምብጻሐ ኩሉ አስተብቁዖት።

የምልጃ ሁሉ መዳረሻ ወደርሱ የሚሆን። ሐተታ ጻድቃን መላአክት ቢያማልዱ ፍጻሜው ወያሱ ነውና ። ስዕለት አስተብቀዖት የሚለው እንደምን ነው ቢሉ ስዕለት የሚለው በሰባቱ በዐሥራ ሁለቱ በሃያ አራቱ ጊዜያት የሚጸለየው ነው አስተብቀዖት የሚለው ሰው ሰለሚሻው ነገር ግብር ገብቶ ቀኖና ይዞ የሚያመለክተው ነው፡፡ 

በጽሒፈ መቅድመ አርባዕቱ ወንጌላት ቅዱሳት ።

ንቀድም ጽሒፈ በ በግዕዝ ቦታ የገባ ነው አንተሰ ኢቀባዕከኒ በዘይት ርእስየ ለምሑራነ ልብ በጥበብ። ቀስተ ዮናታን ኢተቀብዓት በቅብዕ ዘእንበለ በደመ ኃያላን፡፡ ኦሪት ወነቢያት ወወንጌል ሰበኩ በክርስቶስ እንዲል ። የአራቱን ወንጌል መቅድም ሰባቱን ክፍል መጻፍን እንጀምራለን ። አንድም በ ን ስለ ማውጣት በመጻፍ እንጀምራለን በቃል መጀመር አለና፡፡ አንድም ወታቀንተኒ ኃይለ በጸብዕ እንዲል በጽሒፍ ጊዜ ረድኤተ እግዚአብሔርን መጠጋትን ለነገራችን ጥግ እናደርጋለን።
****************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
29/05/2011 ዓም

No comments:

Post a Comment